አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ለማገገም የሚፍገመገመው የወጪ ንግድ

አገሪቱ የወጪ ንግድ በአማካይ በ36.3 በመቶ እንደሚያድግ የሚያመላክት ግብ ከተጣለ ሁለት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ይህ ዕቅድ በአምስት ዓመቱ የዕቅድ ዘመን ውስጥ ይሳካል ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ ከጠቅላላው የአገሪቱ የወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የተቀመጠው ትንበያ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ትንበያ በ2007 በጀት ዓመት የተገኘውን 3.01 ቢሊዮን ዶላር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በተግባር እንደታየው ግን በ2008 በጀት ዓመት የተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከተተነበየው ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዝቅ ያለ ነው፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን መጨረሻ (2007 ዓ.ም.) ወቅት፣ ከወጪ ንግድ 6.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ሲጠበቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተገኘውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር መነሻ በማድረግ የተሰላው ዕቅድ በ2007 ዓ.ም. ያስገኘው ውጤት ግን ከግማሽ በላይ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በመጀመሪያው የዕቅዱ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዓመት በአማካይ የተገኘው ገቢ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ለወጪ ንግድ ከሚቀርቡ ሸቀጦች መካከል ከቡና 783.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቅባት እህሎች 481 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጥራጥሬ 200.3 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ይታሰብ ነበር፡፡ ይሁንና ከቡና የገቢ ዕቅድ ውስጥ 61 በመቶ ብቻ ተሳክቷል፡፡ ከቅባት እህሎች 64 በመቶ፣ ከጥራጥሬ 42.4 በመቶ ብቻ ውጤት ተገኝቶ ዕቅዱ ተደምድሟል፡፡ ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ ዕቅዱ ማጠቃለያ 2012 ድረስ የተቀመጠውም የወጪ ንግድ ገቢ ትንበያ አገሪቱ በዘርፉ እመርታ የምታሳይበት ይሆናል ቢባልም ከጅምሩ ዕቅዱና ክንውኑ ሳይገናኙ ቀርተዋል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ (በ2012 ዓ.ም.) የወጪ ንግድ አጠቃላይ ገቢ 13.9 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡ እንደትንበያው ከሆነ በ2009 ዓ.ም. 6.7 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2010 ዓ.ም. 8.7 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2011 ዓ.ም. 11.03 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2012 ደግሞ 13.9 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ታሳቢ ቢደረግም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ያለውና እስከ 2009 ዓ.ም. አጋማሽ የታየው አፈጻጸም በዕቅዱ መሠረት ገቢው እያደገደ እንዳልሆነ ነው፡፡

መንፈቅ ዓመቱን ካገባደደው የ2009 በጀት ዓመት፣ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ቢጠበቅም ባለፉት አምስት ወራት የተገኘው ግን 1.57 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በአምስቱ ወራቶች ውስጥ ይገኛል የተባለው ገቢ እርግጥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ በአምስቱ ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በዕቅድ ከተያዘው ግብ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በንፅፅር ሲታይ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ የታየበት በመሆኑ፣ አሁንም የታሰበውን ያህል ገቢ ማስገኘት ያልቻለ ዘርፍ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

 በሁለቱም የዕቅድ ዘመኖች ውስጥ ዋና የወጪ ንግድ ገቢ ምህዋር የሆኑት የግብርና ምርቶች ናቸው፡፡ ከግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቀንድ ከብትና የጫት ምርቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ70 እስከ 80 በመቶ በላይ ድርሻ ይዟል፡፡

የ2009 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ መረጃ የሚጠቁመው እነዚህ ምርቶች ቀዳሚ የወጪ ንግድ ገቢ ማስገኛ ቢሆኑም፣ በአፈጻጸም ደረጃ ከዕቅድ በታች እየተመዘገበባቸው በመሆኑ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን 4.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ከባድ እንደሚያደርገው ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ ግማሹን ገቢ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ከቡና 2.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ከቅባት እህሎች 904 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጥራጥሬ 318 ሚሊዮን ዶላር፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ 69 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቀንድ ከብት 267 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከጫት 324.7 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ በዓመቱ ከተያዘላቸው ግማሽ ያህሉን ያስገኛሉ ተብሎ ነበር፡፡ መረጃዎቹ የሚጠቁሙት ግን ከጫት፣ ከጥራጥሬና ከጥቂት ምርቶች በቀር በዕቅድ ወደተቀመጠለት የገቢ መጠን የተጠጋ ሸቀጥ አለመኖሩን ነው፡፡ እንደወርቅ፣ ታንታለም፣ የቀንድ ከብት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የመሳሰሉት ከዕቅዳቸው 50 በመቶ ያልደረሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ከፍተኛ ገቢ ይገኝባቸዋል ተብለው ሲጠበቁ ነበር፡፡

በተለይ ከዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች እንደ ቅባት እህል ያሉ ምርቶች አሁንም ዝቅተኛ አፈጻጸም እያሳዩ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚጠቀሰው የቅባት እህሎች ዘርፍ በ2009 በጀት ዓመት ክዋኔው ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ፣ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ከዚህ ዘርፍ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከ110 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም በግማሽ ዓመት ውስጥ ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ከተቀመጠው ከሁለት እጥፍ ያነሰ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከቅባት እህሎች ይገኛል ተብሎ የታቀደው ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ በጠቅላላው 904.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱ አይዘነጋም፡፡ የቅባት እህል የወጪ ንግድ በ2006 ዓ.ም. 651.9 ሚሊዮን ዶላር አስመዝግቦ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. 510.1 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገኝ፣ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ 447 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቶ ነበር፡፡ ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ገቢው እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡

የአሪቱን የ2009 ዓ.ም. የአምስት ወራት የወጪ ንግድ እንቅስቀሴ የሚያሳዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ከጫት 120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ነው፡፡ ይህም በግማሽ በጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው ገቢ ጋር ተቀራራቢ ሆኗል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ከጫት ንግድ 220 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ከቡና፣ ከጥራጥሬና ከቅባት እህሎች ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በ2009 መጨረሻ ላይ ደግሞ 324 ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የወጪ ንግዱ ዘርፍ በ2006 ዓ.ም. 3.3 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2007 ዓ.ም. 3.01 ቢሊዮን ዶላር ቢያስገኝም፣ በ2008 ግን ይብሱን 2.8 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ከማደግ ይልቅ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ታይቷል፡፡ ባለፉት አምስት ወራት የታየው ገቢም ቢሆን የወጪ ንግዱ በታሰበለት ደረጃ ያለመራመዱን የሚጠቁም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ፣ የዓለም የሸቀጥ ገበያ መዋዠቅ ያስከተለው ቅናሽ እንጂ የምርት መቀነስ በአገሪቱ እንዳልተከሰተ ተናግረዋል፡፡