አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ለአትሌቲክስ ውጤታማነት አዲሱን አመራር ተስፋ እናደርጋለን

  ብዙውን ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮትም ሆነ በጋዜጦችና መጽሔቶች የሚተላለፉና የሚወጡ ትዝብቶች ወይም አስተያየቶች በአብዛኛው በታዋቂ ግለሰቦች በምሁራን አለያም በፖለቲከኞች ይጣበባሉ፡፡ እንደ እኔ ያለው ጭቁን የገጠር መምህር ግን እንዲህ ያለው ዕድል ብዙም አይገጥመውና እንዲሁ ዕድሌን ልሞክር ብዬ ነው ይህን ጽሑፍ መላኬ፡፡ ለሚዲያ ቢሆን ብዬ ስጽፍም የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፡፡

ዕድሜ ለአበበ ቢቂላ ይሁንና ከእሱ ጊዜ ጀምሮ አትሌቶቻችን በመላው ዓለም ታውቀው አሳውቀውናል፡፡ አበበ ቢቂላ በዓለም የውድድር መድረክ አሸንፎ ከመጣ በኋላ ስታዲየሙን እየዞረ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለበ ሲዞር፣ በወቅቱ በሥፍራው የነበረ አፍሪካዊ ስደተኛ ራሱን ደፍቶ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ደስ አለው፡፡

 ጀግኖች አትሌቶቻችን የታመመንም ያድናሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ መንደርደሪያዬ ሙያዊ ብቃታቸው የትየለሌ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ፌደሬሽንን ቀርቶ ዓለም አቀፍ ተቋምን መምራት እንደሚችሉ የሚያሳየን አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት እንደተመረጠ ወዲያውኑ ድጋፋቸውን በተለያዩ ድረ ገጾች፣ ዓለም አቀፍ መጽሔቶችና ጋዜጦች ሲገልጹ ማየታችን ነው፡፡ በዓለም ጋዜጦችና ታዋቂ ድረ ገጾች መነጋገሪያ መሆንና መሞካሸት ከሙያ ብቃት የመጣ ነው፡፡ አትሌት ኃይሌ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማግኘቱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ዱሮ ታዳጊ ልጆች እያለን ነፍሳቸውን ይማርና ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማም በተለያዩ የዓለም መድረኮች አገራችንን ከፍ ከፍ አድርገውን እንደነበር ይታወሰኛል፡፡ የኃይሌን መመረጥ የደገፍኩት በተለይ ሕዝቡን የማገልገል ውስጣዊ ፍላጎትና ብቃቱን ሳስብ ነው፡፡ በጀግንነት ባሸነፋቸው መድረኮች የራሱን ደስታ ብቻ አይደለም ያየነው፤ አገር ወዳድነቱን ጭምር እንጂ፡፡ ከፊቱ ከሚነበበው ስሜት፣ በቄንጠኛ ሁኔታ ባንዲራውን እያውለበለበ በርከክ ማለቱ ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመርና ባንዲራዋ ሲሰቀል እንባውን ማፍሰሱ ተቆርቋሪነቱንና ወገንተኝነቱን የሚያሳይ ነው፡፡

ወደፊት ፌዴሬሽኑን ሲመራም በሀቀኝነት ሁሉንም እያሳተፈ ውጤታማ መሪ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ያለአግባብ ለመጠቀም ብሎ እንደማይሠራ አምናለሁ፡፡ የዋህ ባህርይ የተባበሰ ሰው ነውና ቢሳሳትም ከአቅም ወይም ከአመራር ልምድ ማነስ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ሕዝብንና አብረውት የሚሠሩ ባልደረቦቹን አክባሪ፣ ምክር ጠያቂም እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞች ሙያዊ አስተያየትም ትምህርት ሰጭ እንደሆነ የሚቀበል ሰብዕና ያለው ስለመሆኑ እንዴት አወቅህ ብትሉኝ፣ በቴሌቪዥን የሚደረጉ ውይይቶችን ስለምከታተል ነው፡፡ የገጠር አካባቢ መምህር ብሆንም እንደአቅሚቲ በማገኛቸው መረጃዎች አማካይነት ነገሮችን ለመመዘን ስለሞክር፣ ወደ መጻሕፍት ጎራም ስለማዘወትር ለማገናዘብ የምችልበት ዕድል ሰጥተውኛል፡፡

ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስና ላለፉት ስድስት ወራት የስፖርት ዜና አንባቢዎች የሕዝብን ድምፅ እየተከታተሉና ከራሳቸውም ስፖርታዊና ሙያ መርኅ በመነሳት ለሚመለከታቸው የአትሌቲክስ ዘርፍ ኃላፊዎች ለምን ወደ ኋላ እየተጓዝን እንደሆነ፣ ውጤታችን ለምን ከዱሮው እንደቀነሰ ወዘተ እየጠቃቀሱ ሲያነጋግሩ፣ ሹሞቹ ሲሰጡ የነበሩትን ምላሽ ለሕዝብ ድምፅ ጆሮ አለመስጠት ይታይባቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ስፖርት እንደሆነ ወዳጅን ብቻ ሳይሆን የሚያገናኘውና የሚያፈቅረው በክፉ የሚፈላለገውንም ጭምር ነው፡፡ የእስራኤልና የፍልስጤም ሁለት ወጣቶችን የዛሬ አምስት ዓመት አፋቅሮ ለጋብቻ ያበቃቸው ስፖርታዊ ትዕይት ነበር፡፡

የፖለቲካ ታማኝነት ብቻውን የትም እንደማያደርስና እንደማያዋጣ መገንዘብ ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች በዓለም ኦሊምፒክ መድረክ አንድ ወርቅ ብቻ ማግኘታችን ውድቀትን አያሳይም ወይ? ብለው ሲጠይቋቸው፣ በተቃራኒው ውጤታማ ነን በማለት ድርቅ ማለታቸው የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሙያዊ ብቃት አስፈላጊነቱ ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ባለሥልጣኖቹም ጥፋታቸውን ማመን ይገባቸዋል፡፡ የሕዝቡን ውጤት አጣን ጥያቄ ማስተናገድ ይገባቸዋል፡፡

ጋዜጠኞች ውጤት ያጣንበትን ምክንያት በማውሳት እርምት እንዲደረግ ብዙ ታግለዋል፡፡ ሆኖም ሹሞቹ ግን ድንግጥም የሚሉ ዓይነት ሆነው አልተገኙም ነበር፡፡ እነሱ አይሰሙም እንጂ መንግሥት የምሁራንን ሚና ተረድቶ በፕሮፌሰሮችና በዶክተሮች የተሞላ ካቢኔ አቋቁሟል፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና አዲሱ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ የወደፊቱን አትሌቲክስ ስፖርት በድል ጎዳና እያራመዱ፣ የጠፋውን ውጤት እንደሚያስመልሱ በማመን መልካም የሥራ ዘመን እላለሁ፡፡

(አደፍርስ፣ ከወሎ ሐይቅ)

                        ******************

የሕንፃዎችን የፓርኪንግ ክፍያ ተመን የሚቆጣጠር አካል አለን?

ለተለያዩ ጉዳዮች መኪኖች በሕንፃዎች ማቆሚያ ቦታዎች ወይም የፓርኪንግ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ማቆም ሊያስፈልገን ይችል ይሆናል፡፡ ያስፈልጋልም፡፡

ምንም እንኳ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሕንፃዎች ተገቢውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ በመገንባት ረገድ የሚወቀሱ ቢሆኑም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ እያሉ ያሉት ሕንፃዎች እንዲህ ያለውን አገልግሎት የሚሰጡ የፓርኪንግ ቦታዎችን ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ እሰየው ያስብላል፡፡ ይሁንና ግን ችግር ያለባቸውም አሉ፡፡ አገልግሎቱን ቢሰጡም ለሚሰጡት አገልግሎት የሚጠይቁት ክፍያና የሚከተሉት የክፍያ አጠያየቅ ሥርዓት አስገራሚም፣ አሳፋሪም ሆኖ ያገኘናቸው ሕንፃዎች አሉ፡፡

ከሰሞኑ የገጠመኝም ከዚሁ ከፓርኪንግ ክፍያ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ቦሌ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የሚገኝ ዘመናዊና አዲስ ሕንፃ ነው፡፡ የተሟላ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ቢኖረውም፣ ሕንፃው የሚከተለው የክፍያ ሥርዓት ግን አግባብነት የጎደለው ይመስለኛል፡፡ ለአንድ ሰዓት ቆይታ የሚያስከፍለው ገንዘብ ስምንት ብር መሆኑ ግራ አጋብቶኛል፡፡ በየመንገዱ ለምናቆምበት የምንጠየቀው ሃምሳ ሳንቲም ሆኖ ሳለ በዚህ ሕንፃ ውስጥ ለአንድ ሰዓይ ቆይታ ስምንት ብር መጠየቅ ከምን መነሻ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የሒሳቡ መጋነን ሳያንስ ወደ ማቆሚያ ቦታ ለሚገባው አሽከርካሪ ሒሳቡ አይነገረውም፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሥነ ምግባር የሌለው ድርጊት ነው፡፡

በጥቅሉ ግን እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አሠራሮች እየተለመዱ ከሄዱ የኋላ ኋላ ነገሮችን ለማስተካከል አስቸጋሪ ያደርጋቸዋልና የሚመለከተው አካል ካለ እርምት ያድርግበት፡፡

(ቢሻው ቢልልኝ፣ ከአዲስ አበባ)