ለውጥ አደናቃፊው የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ

በልዑል ዘሩ

የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በዓለም ላይ ከፍ ያለ ቦታ እየተሰጠው የመጣ ቢዝነስ፣ የፖለቲካና የሥራ አመራር ቀዳሚ መስክ ነው፡፡ በአገራችንም ቢሆን በተለይ ካለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ እየታወቀ ከመምጣቱ ባሻገር፣ ስሙ እየተቀያየረ (አንድ ጊዜ ፕሬስ፣ ሌላ ጊዜ ኮሙዩኒንኬሽን ወይም ቃለ አቀባይ እየተባለ በድብልቅልቅ አጠራር) እዚህ የደረሰ ሙያ ነው፡፡

ለሕዝብ ግንኙነት ሙያ አሁንም በርካታ መጠሪያ ስያሜዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተግባራቱም ያንኑ ያህል የተምታቱ ናቸው፡፡ ዘርፉ አንድ የማኅበራዊ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው አሁን እኛና መሰል አገሮች ከምንጠቀምበት አንፃር ከሚገልጹት ምሁራን መካከል ሞርና ካሉፕ አንዱ ናቸው፡፡

‹‹የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለየት ያለ አገልግሎት ያለው ሆኖ የሕዝብን አስተያየት የሚሰበስብና አመለካከት በማይጤን የተቋማትን ዓላማ፣ ፍላጎት፣ የአሠራር ሒደትና ፖሊሲ የሚያብራራ ዝርዝር የሥራ ፕሮግራሞችንና ተግባራትን እንዲሁም ክንውኖችን ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸውና እንዲረዳቸው የሚያደርግ ነው፡፡ በተቃራኒው የሕዝቡ (የደንበኞች) ፍላጎትና ጥያቄንም እያጠናና እየቀመረ ወደ ድርጅቱ የማቅረብ ሚና አለው፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ከዚህ ሳይንሳዊ ብያኔ በመነሳት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ በኩባንያ (መንግሥት) እና በደንበኛ (ሕዝብ) መካከል መስተጋብር የሚፈጥር ድልድይ ነው፡፡ ዋናው ትኩረታችን ወደ ሆነው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነት (Public Relation) ተግባር ሳናተኮርም ከዚሁ የተለየ ተግባር ሊቀመጥለት አይችልም፡፡ እውነታው ይኼ ነው፡፡ ቢሆንም በየትም አገር የሚገኙ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚዘነጉት ከሕዝቡ በኩል ያለውን ፍላጎትና ጥያቄ ነው፡፡ አንድም ፍላጎታቸው ወደ መንግሥት በማድላቱ፣ በሌላ በኩል በአቅምና ቁርጠኝነት ውስንነት ተግዳሮት ሲፈጠር ይታያል፡፡ በእኛ አገርም ቢሆን ከእነዚህ ፈተናዎች ባሻገር የሕዝብ ግንኙነት ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ላይ አይገኝም፡፡ ዘርፉ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር ወደ ጎን ማለትና ከሚጠበቀው ተግባር ባነሰ የአጫፋሪነት ሚና ላይ የመጠመዱ አደናቃፊነት፣ አገሪቱ ለጀመረችው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ሆኖበት ይገኛል፡፡ አንድ በአንድ እንመልከት፡፡

ሙያዊ ብቃትና ፍላጎት የለሽ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ (በ2004) የተዘጋጀ አንድ መድበል ላይ ‹‹የሕዝብ ግንኙነትና በዘርፉ ያሉ አመለካከቶች›› በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናት ይዟል፡፡ በጥናቱ መሠረት መጠይቅ ከቀረበላቸው ከ60 በላይ የዘርፉ ሙያተኞች 68 በመቶ ያህሉ የሕዝብ ግንኙነት ሙያና ተዛማጅ ሥልጠና የላቸውም፡፡ በሥራ መደቡ ላይ የተቀመጡትም በፖለቲካ ታማኝነት፣ በብሔር ተዋፅኦ ወይም ከሌላ ክፍል በተደረገ የሽግሽግ ምደባ ነው፡፡ በየጊዜው በሚደረጉ የቢፒአርና ሌሎች ሽግሽጎች መሠረት ተፈናጥረው ክፍሉን የሚሞሉትም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡

በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የሥነ ጽሑፍ ወይም የንግግር ችሎታ፣ አንዳንዴም ፎቶግራፍ ማንሳትና ‹‹ቅልጥፍና›› በማሳየት ብቻ እስከ ዳይሬክተርነት የደረሱ ሙያተኞችም አሉ፡፡ ጉዳቱ ይኼ ብቻ ሳይሆን መረጃ ከሰጡት መሀል 40 በመቶው ለሥራው ሙሉ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲናገሩ፣ 40 በመቶው ደግሞ በመጠኑ ደስተኛ ነኝ ያሉ ናቸው፡፡

በዚህ ጥናት ግኝትም ሆነ መሬት ላይ ባለው ሀቅ መሠረት አብዛኛው የሕዝብ ግንኙነት ሙያተኛ የዕውቀትና የፍላጎት ክፍተት ብቻ አይደለም ያለበት፡፡ ከዚያም በላይ ለሙያው ሥነ ምግባር የማይገዛ፣ እውነትም ይሁን ውሸት የአንድ ወገንን መረጃ የሚያንበለብል (ያውም መረጃውን አሟልቶ ከያዘ)፣ የሕዝቡን ጉዳይ የረሳ ሆኖ ይታያል፡፡

በቅርቡ የፌደራል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በጠራው አንድ የምክክር መድረክ ላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮም ይህንኑ ሐሳብ ተጋርተውታል፡፡ ‹‹በፌደራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ ያለው የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉ የሙያ ክፍተት ብቻ ሳይሆን ያለበት፣ ከተሰጠው ኃላፊነትም አንፃር ተግባሩን አሟልቶ የማይወጣ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህንን ኃይል ሳያስተካክሉና ሳያራግፉ የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ማስፈንና  የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከዳር ማድረስ ስለማይቻል ፈጣን የዕርምት ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ነው ያሉት፡፡

መንግሥት በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ የፌደራል የሕዝብ ግንኙነት መስኩን በክልል ካድሬዎች ሞልቶታል፡፡ እነዚህ ሙያተኞች አንዳንዶች በትምህርት ብቃት ራሳቸውን ያሳደጉና ያሻሻሉ ሲሆን፣ ብዙዎቹ እንደቆሙ የቀሩ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት መረጃ መከልከል፣ ማጓተት፣ አንዳንዶቹም ስለራሳቸው (የፕሮቶኮል ሥራ፣ የድግስና የስብሰባ ማስጀመር አልባሌ ጉዳይ ላይ) ተጠምደዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ሲባል የሕዝብ ግንኙነት ሚናን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው መረጃ ፈላጊዎች (የሚዲያ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች) በየደረጃው በሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ተገቢውን መረጃ ማግኘት ተስኖአቸዋል፡፡ በተለይ የፈለጉትን ሚዛናዊ መረጃ በፍጥነትና በጥልቀት የሚያገኙባቸው ተቋማት እጅግ ውስን እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎችም ተመሳሳይ በሆነ የፕሮፓጋንዳ ተግባር የተጠመዱ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር የአሁኑ ተሃድሶም ይባል የመንግሥት የእርምት ዕርምጃ አንዱ ሊፈትሸው የሚገባው ዘርፍ ይህንኑ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና የሕዝብ ግንኙነቶችን በድርጅታዊ አሠራር ጠፍሮ በመገምገም፣ ወይም በዓመት አንድ ጊዜ በሚካሄድ የቀናት ሥልጠና ብቻ ዘርፉን ማሻሻል አዳጋች ነው፡፡ ይልቁንም የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን በሰው ኃይል (በተለይ በሠለጠነና ብቃት ባለው)፣ በግብዓትና በሥልጠና ወደላቀ ምዕራፍ መውሰድ፣ ከጓዳ ተልኮስኳሽነት ማውጣት ይገባል፡፡ በሕዝብ የማይጠረጠር እንዲሆን ማድረግም ግድ ይላል፡፡

የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኀን አዋጁ ይፈጸም

በአገሪቱ ፓርላማ የፀደቀው አዋጅ 590/2000 የሚባለው ሕግ በፅኑ እየተተገበረ ያለው በጋዜጠኛው ወገን ብቻ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በግልም ይሁን በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች በሚያሳትሙት (ብሮድካስት በሚደያደርጉት) ዘገባ ልክ ይመሰገናሉ፣ ይጠየቃሉም፡፡ በዘገባ ሥራቸው ‹‹አጥፍተው›› የተከሰሱና የተጠየቁ (በተለይ የታሰሩ) ጋዜጠኞችም ለአባባሉ ምስክር ናቸው፡፡

በአዋጁ ክፍል ሦስት መሠረት ከመረጃ ሰጪው (ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ) በኩል ያለው አፈጻጸም ግን ዋጋ አልባ የሚባል ነው፡፡ የመንግሥት አካላት መረጃ የሕዝብ ሀብት መሆኑን ተገንዝበው በአግባቡና በጊዜው እንዲሰጡ ቢገደዱም፣ አዋጁን በመተግበር በኩል የተጠየቀ (የታረመ) የመስኩ ሰው እንደሌላ ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዱ መረጃን የግሉ (የተቋሙ) ንብረት እያሰመሰለ ሲሸሸግ፣ ሲቀሽብ ወይም ሲያዛባ ቀጪ አላገኘም፡፡ አዋጁን እንዲያስፈጽሙ ሕግ አደራ የጣለባቸው የእንባ ጠባቂ ተቋምና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን የመሰሉ ሕዝባዊ ተቋማትም እስካአሁን ከ‹‹ግንዛቤ ማስጨበጥ›› ምክክር ተላቀው፣ የማስፈጸሚያ መመርያና ደንቦችን እንኳን ሳይወጡ ከስድስት ዓመታት በላይ ተንከባልለዋል፡፡ መረጃ የመስጫ ጊዜና መጠን፣ የመረጃ አያያዝና አጠባበቅ ጉዳይ፣ የሚስጥራዊ መረጃ አያያዝ ጉዳይ ከአዋጁ ወርዶ ለትግበራ አስገዳጅነት እንኳን አለመብቃቱ የሚያስተዛዝብ ክስተት ሆኗል፡፡

ይህ በመሆኑም አሁን በተግባር እየታየ እንዳለው አብዛኛው የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት የሚያግዝ መረጃ ሰጪ ሳይሆን፣ መካችና ከልካይ ሆኖ ተጎልቷል፡፡ በየዓመቱ በየመሥሪያ ቤቱ በመቶ ሺሕዎች ብር ለኅትመት እያወጣ የመሥሪያ ቤት ዕቅድና ሪፖርትን ማተም ወይም በኃላፊዎች ፎቶ ያሸበረቀ መጽሔት ‹‹ማዘጋጀት›› የሥራ ሁሉ አልፋና ኦሜጋ መስሎም ቀርቷል፡፡ ይህ በንጉሡ ዘመን (በ1950ዎቹ) ከነበረው የሕዝብ ግንኙነት አሠራር ያልተነጠለ ጉዞ ሁለት ትውልድ ተሻግሮ፣ ዛሬ ላይ ያለውን ዜጋ ነባራዊ ሁኔታ ሊመጥን አይችልም፡፡ እጅ እጅ  የማለቱ ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡

አሁን ባለንበት ዓለም በመረጃ አንድ መንደር ሆኖ ምንም ዓይነት ኢንፎርሜሽን ከአጽናፍ አጽናፍ እየተዘናፈለ ስለክልከላ ማሰብ ኋላቀርነት ነው፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ድረ ገጽና ማኅበራዊ ሚዲያ ያውም በግል ከፍቶ የሕዝብ የመረጃ ፍላጎትን ማርካት አይቻልም፡፡ በአንድ ወገን የፕሮፓጋንዳ ቀውስ ብቻ ሕዝብ የሚያውቀውን ሀቅ ለማዳፈን መሞከርም ከንቱ ድካም ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከየተቋማቱ ሕዝብ ግንኙነትም አልፎ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ውድ የጋዜጣ ዓምዶች ‹‹በስፖንሰርሺፕ›› እየታጀበ ሲለቀቅ ደግሞ ብክነት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ በፅናት እንዳይተገበር እንቅፋት የሆኑ የመንግሥት አካላትና ራሱ የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩ ብቻ አይደለም የሚወቅሱት፡፡ ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ትልቁን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘው ሕግ አውጭው አካል (ፓርላማውም) ከታሪክ ተወቃሽነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ከአስመሳይ ‹‹ዴሞክራሲያዊነት›› ወጥቶ ሕዝብ የሚገለገልበትን ባህል ወደ መፍጠር ካልሄደ፣ ለሥርዓቱ ውድቀት ጠጠር እንዳቀበለ  የሚቆጠር ነው፡፡

በዘርፉ የሕዝብና የባለሥልጣናት ተቃራኒ አተያይ

ቀደም ሲል በተካሄደው ጥናት መሠረት በአገራችን ስላለው የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሕዝብ ያለው አተያይ ያልጠራ ነው፡፡ ከ63 በመቶ በላይ የሚሆነው የሕዝብ ግንኙነት ሙያተኛ መልስ ሰጭዎች ለሙያው የሚሰጠው ክብርና ያለው እምነት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከቀሪዎቹም 18 በመቶ ያሉ መካከለኛ ነው ማለታቸው፣ ዘርፉ እንዴት ከሕዝቡ የተነጠለ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በእርግጥ ይኸው ጥያቄ በሕዝቡ በኩልም ቢጠየቅ የተለየ መልስ አይኖረውም፡፡

   ለዚህ አተያይ የሚጠቀሱ ምክንያችም አሉ፡፡ አንደኛው መንግሥትና የመንግሥት ኃላፊዎች ለዘርፉ የሰጡት የተላላኪነትና የፕሮፓጋንዲስት አተያይ ነው፡፡ ሁለተኛው ራሱ ባለሙያና ዘርፉ ሕዝቡ የሰጠውን አደራ ወደጎን ብሎ ያልበላውን እያከከ ለዓመታት በመኖሩ ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ በሕዝብ ግንኙነት ስም የገዥው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ክንፉ ሆኖ መጠራቱ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የሚባለው ‹‹የወሬ ምንጭ›› ከላይ እስከ ታች በመዘርጋቱና ካለፉት ሥርዓቶችም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የፕሮፓጋንዳ ዘርፉ (ዋሽቶ ማሳመን ገጽታ) ተቀባይነት ማጣት ያደረ ጥላሸት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን በሚዛናዊና በትክክለኛ ትግበራ መቀየር ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡

ለዚህ ዓይነቱ ብልሽት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች (ከሚኒስቴር እስከ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ድረስ) ሕዝብ ግንኙነትን ቃለ ጉባዔ ያዥና የፕሮቶኮል ተጠሪ አድርገው ማየታቸውም ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህ በመሆኑም አመራሩ ሊፈጥርበት የሚችለውን ጉዳይ (የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ) ለሕዝብ ግንኙነቱ እየተወ ገራገሩን መድረክ ከመምረጡ ባሻገር፣ እንደ አስፈላጊነቱ የመስኩን ባለሙያ ‹‹ገመና ሸሽግ›› ሲያርገው ታይቷል፡፡ ይህ መረገም ያለበት ነውር እንደሆነ በተለይ እንደ አሁኑ ባለው የተሃድሶ ወቅት ግልጽ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በቀደመው ጥናትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተደረጉ ዳሰሳዎች የመንግሥት ሠራተኞች ራሳቸው የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን ወሬ አቀባይ (ጆሮ ጠቢ) አድርገው የመሰሉበት ጊዜም ጥቂት አይደለም፡፡ ሥራው ካለው ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ሕዝባዊ ተቀባይነት አንፃር እየተመዘነ እንደ ገለባ በመቅለሉ የዘርፉን ባለሙያም ሆነ አመራር ዝቅ ያለ ቦታ እንዲሰጠው አድርጎታል፡፡ ሕዝብ ግንኙነት የአመራር ዓብይ ተግባርነቱም ተዳፍኗል፡፡ ከዚህ አንፃር የተንሸዋረረውን ዕይታ የፈጠረው ልፍስፍሱ ተግባር ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ሲጠቃለል ምን ማለት ይቻላል?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለአምስት ዓመታት በመንግሥት የፌዴራል ተቋም ውስጥ በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት ሠርቷል፡፡ ለጽሑፉ መንደርደሪያ የሆነው ከላይ የተጠቀሰው ቆየት ያለ የጥናት ሰነድ ማግኘቱ ቢሆንም፣ ዘርፉ አሁንም ከችግር ከመውጣት ይልቅ ሲንደፋደፍ ማየቱ ቢያንስ በተወዳጁ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የግል እምነቱን ጠቅሶ ሁሉንም እንዲወያይበት ማድረግን መርጧል፡፡

አሁን አገሪቱ ከደረሰችበት የማኅበረ ኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ከሕዝቡ የንቃተ ኅሊና ደረጃ አንፃር፣ የሕዝብ ግንኙነት መንግሥታዊው መንገድ ውልክፍክፍ ነው፡፡ የስፖንጅ መዶሻ፣ የቄጤማ ምርኩዝ የሚሉት ዓይነት ለሕዝብ አይጠቅምም፡፡ ለመንግሥትም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ዓይነቱ የተዳከመ ሁኔታ ወጥቶ በእግሩ እንዲቆም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፡፡ ሕዝቡም የድርሻውን ቢወጣ መልካም ነው፡፡ ራሱ የዘርፉ ሙያተኛና አመራር ሚና ግን ተኪ የሌለው ነው ማለት እወዳለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡