ለፀጥታው ምክር ቤት ወንበር ሁለንተናዊ ዝግጅት አለን ወይ?

በበሪሁን ተሻለ

የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል ሆና የመመረጧን ድል አዳንቀው ሲያከብሩት እየሰማን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተመድ አባልና መሥራች አገር ናት፡፡ አባል መሆን ብቻውንና በገዛ ራሱ ምክንያት የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆንን ስለማያጎናጽፍ፣ የምክር ቤቱ አባል የመሆንን ክብር፣ ኢትዮጵያ ማግኘቷን ዜና ማድረግ ማጣጣምና ማጋራት የድሉንም ትርጉምና አንደምታ ማሳወቅና ማስተማር ነውር የለበትም፡፡ ነውር የሚሆነውና የሚያስጠይቀው ይህንን ጉዳይ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ማድረግ የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባልነት የሚያስከትለውን ኃላፊነት፣ የሚጠይቀውን ምግባርና ባህርይ አሳውቆ አለመነሳት የመሳሰለው ነው፡፡

ጉዳዩን በዝርዝርና ከሥር ከመሠረቱ እንመልከተው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ማለት የተመድ ዋነኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡ ጦርነት የሚያውጀውና ማዕቀብ የሚጥለው እሱ ነው፡፡ ይህ የሥልጣን አካል አሥራ አምስት አባላት አሉት፡፡ አባላቱ ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ቋሚ አባላትና ቋሚ ያልሆኑ አባላት ይባላሉ፡፡ ቋሚ አባላት አምስት ናቸው፡፡ አሥሩ ደግሞ ቋሚ ያልሆኑ አባላት ናቸው፡፡ የአንድ ቋሚ ያልሆነ አባል የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት ነው፡፡ ቋሚ ያልሆኑ አባላት ሁሉምና አሥሩም በአንድ ጊዜ የሁለት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን ፈጽመው አንዴ ውልቅ ብለው ሄደው ደግሞ ሌላ አዲስ አሥር አባላት መምጣታቸው ስላልተፈለገ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆኑ አባላት የሚመረጡት በየዓመቱ ነው፡፡ በየዓመቱ ሁልጊዜም አምስት አምስት ቋሚ ያልሆኑ (ከዚህ በኋላ ለዚህ ጉዳይ ተራ ብለን የምንጠራቸው) አባላት ይመረጣሉ፡፡

ለፀጥታው ምክር ቤት በአባልነት የመመረጥ ጉዳይ የተመድ አባልነትን ተከትሎ የሚመጣ፣ የወር ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ አባል ያልሆነ አገር የፀጥታውን ምክር ቤት ተራ አባልነት መቀመጫ ባያገኝም አባል መሆን ብቻውን ግን ለዚህ ክብር መመረጥን አያጎናጽፍም፡፡ ተራ አባል ሆኖ የሁለት ዓመቱን የሥራ ጊዜ የፈጸመ አባል አገር ወዲያውኑና ቀጥሎም አባል ሆኖ መመረጥ ባይችልም፣ አዘውትረው አባል የሆኑ አገሮች አሉ፡፡ ብራዚልና ጃፓን የዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በታች ደግመው ደጋግመው አባል ሆነው የተመረጡ ወይም የሚመረጡ አሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት በዚህን ያህል ዘመን ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የመመረጥ ዕድል ያገኙት አልፎ አልፎ በሚባል መደብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1967‑1968 እና በ1989‑1990 የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል ሆና ሠርታለች፡፡ በዚያ መካከል እ.ኤ.አ. በ1985‑86 ለተራ አባልነት ተወዳድራ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ የተመድ 39ኛ ጉባዔ በመጀመሪያው ስብሰባው አራቱን ተራ አባላት ቢመረጥም አምስተኛውን ተራ አባል ለመምረጥ ግን ሌሎች ሁለት ስብሰባዎች አስፈልገውታል፡፡ በመጨረሻው ስብሰባ ላይ አሥር ጊዜ ድምፅ ቢሰጥም ኢትዮጵያም ሆነች የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ሆና ለምርጫ የተሳተፈችው ሶማሊያ ተገቢውን ድምፅ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በአፍሪካ አገሮች ቡድን ሊቀመንበር አግባቢነት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ተወዳዳሪነታቸውን አነሱና ማዳጋስካር ብቸኛዋ ተወዳዳሪ አገር ሆና የ1985‑1986 ተራ አባል ሆነች፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል ሆኖ ለመመረጥ ይህን ሁሉ ፉክክር ማለፍ ይጠይቃል፡፡ ድምፅ ሰጪ ወይም መራጭ አባል አገሮችም በተመድ ቻርተር አንቀጽ 29 የተመለከተውን የዕጩ ተመራጩን አገር ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጭምር ከቁጥር እንዲያስገቡ ይገደዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ የ2017‑2018 የአባልነቱን ዘመን ቦታ አግኝታ የተመረጠችው በዚሁ ስብሰባ እንደተመረጠችው እንደ ቦሊቪያ ሁሉ ተቀናቃኝ ተወዳዳሪ ሳይኖርባት ነው፡፡ ከኢትዮጵያና ከቦሊቪያ ጋር የተመረጡት ሌሎች ሁለት አገሮች ካዛኪስታንና ስዊድን ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ የተመረጡት እጅግ ሲበዛ ፍልሚያ የበዛበትን ውድድር አልፈው ነው፡፡ ካዛኪስታንና ታይላንድ ለእስያ ለተመደበ አንድ ተራ መቀመጫ ተወዳድረው ካዛኪስታን አሸነፈች፡፡ ጣሊያን ኔዘርላንድና ስዊድን ደግሞ ለሁለት መቀመጫዎች ተፋለሙና ስዊድን አንዱን አሸነፈች፡፡ ለተቀረው አንድ የአውሮፓ መቀመጫ ተወዳዳሪነት ጣሊያንና ኔዘርላንድ ተፈላጊውን የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሳያገኙ ቀርተው ጉዳዩ ለተከታታይ የድምፅ መስጠት የሙከራ ሥራ ተጋልጧል፡፡

የፀጥታ ምክር ቤት ተራ አባል ሆኖ የመመረጥ ጉዳይ አዳጋች ለመሆኑ በድርጅቱ የሰባ ዓመት ታሪክ ውስጥ አሁንም ገና 68 አገሮች ‹‹የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገር ሆነው የማያውቁ›› ስም ዝርዝር ውስጥ መገኘታቸው አንዱ ምስክር ነው፡፡ ዘንድሮ ለ2017‑2018 የአባልነት ዘመን ከታይላንድ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ ማሌዥያን የተካችው ካዛኪስታን አሁን በመመረጧ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆነው የማያውቁ አገሮች ቁጥር ወደ 67 ዝቅ ብሏል፡፡ እናም የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል ሆኖ የመመረጥ ጉዳይ በአጠቃላይ አባልነትን ተከትሎ በተራ የሚዳረስ ‹‹እኔ አባል አይደለሁም እንዴ!›› ብለው ተከራክረው የሚገኝ የዙር መብት አይደለም፡፡

ውድድር አለበት፡፡ ፉክክር አለው፡፡ ጥረትም ያሻዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ በምርጫ ለሚያዘው የአምስት የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባላት መቀመጫ መወዳደር የሚፈልጉ አገሮች መጀመሪያ ፍላጐታቸውን ብዙ ጊዜ ደግሞ ምርጫው ከሚደረግበት ወቅት ከዓመታት አስቀድሞ ያስታውቃሉ፡፡ የሚገኙበትን ቀጣና የተቋቋመ አሠራር ተከትለው የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል የመሆን ፍላጐታቸውን አስታውቀውና አስመዝግበው እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ ልዩ ልዩ ልክና መልክ ያለውን ትግላቸውንና ዘመቻቸውን ያካሂዳሉ፡፡

ከፀጥታው ምክር ቤት አሥር ተራ አባላት ውስጥ ሦስቱ ከአፍሪካ ናቸው፡፡ እነዚህን መቀመጫዎች ለማስያዝ በየዓመቱ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ሙሉ ቁጥር ባለው የካሌንደር ዓመት ከሦስቱ የአንዱ፣ ጐደሎ ቁጥር ባለው የካሌንደሩ ዓመት ከሦስቱ የሁለቱ፣ ወንበሮች ምርጫ ያካሂዳል፡፡ የዘንድሮው የ2016 (ስለዚህም ሙሉ ቁጥር ያለው የካሌንደሩ ዓመት) ምርጫ ያወዳደረው ከሦስቱ የአፍሪካ የፀጥታው ምክር ቤት የተራ አባላት መቀመጫዎች ውስጥ የአንዱንና አንጐላ በ2016 መሰንበቻ የምትለቀውን ወንበር ነው፡፡

ለአፍሪካ የተመደበውን የፀጥታውን ምክር ቤት መቀመጫ ለመያዝ በመሠረቱ ብዙ ውድድርና ፉክክር የለም፡፡ ከነጭራሹም እንደ ዘንድሮው ተፎካካሪም ተቀናቃኝም የሌለው አንድ ዕጩ ብቻ ነው የሚቀርበው፡፡ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ዓይነት ኢትዮጵያና ሶማሊያ መልሶ መላልሶ አሥር ጊዜ ድምፅ እስኪሰጥ ድረስ የተፋለሙበት ኋላም እነሱ ቀርተው ማዳጋስካር የተመረጠችበት የ1984 ምርጫ ያስመዘገበው ዓይነት ከወግና ከ‹‹ጋጥ›› የወጣ አጋጣሚ ቢኖርም፣ የአፍሪካ ምርጫ ባመዛኙና በመደቡ ብዙ ችግርና ጣጣ የሌለበት ምርጫ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ከሌሎች ቀጣናዊ ቡድኖች በተለየ ሁኔታ የተቋቋመው ‹‹የአፍሪካ ቡድን›› አሠራር ነው፡፡

የዚህን ትርጉም በአጭሩ ልግለጽ፡፡ ለፀጥታው ምክር ቤት መቀመጫ ምርጫ ሲባል መላው ዓለም ለአምስት ቀጣናዎች ተከፋፍሏል፡፡ እነዚህ ቀጣናዎች የአፍሪካ፣ የእስያ ፓስፊክ፣ የምሥራቅ አውሮፓ፣ የላቲን አሜሪካና የካሬቢያን፣ እንዲሁም የምዕራብ አውሮፓና ሌሎች ቡድኖች ቀጣናዎች ይባላሉ፡፡ ከአፍሪካ ቀጣና ቡድን በስተቀር ሌሎቹ የተጻፈና ሕግ ሆኖ የፀደቀ የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ የላቸውም፡፡ የአፍሪካ ቡድን በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የወጣና የፀደቀ በዓለማቀፋዊ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ የዕጩነት ቦታዎችን መምረጥን የሚገዛ ሕግ አለው፡፡

በዚህ ሥርዓት መሠረት በአፍሪካ ውስጥ፣ በንዑስ ቀጣናው ውስጥ ያሉ ቡድኖችና አገሮች ጭምር የሚከተሉትና የሚገዙበት ለሁሉም በዙር ወይም በተራ የሚዳረስ አሠራር አለ፡፡ ስለዚህም በንድፈ ሐሳብ ደረጃ አፍሪካ ውስጥ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ዞሮ ዞሮና በመጨረሻ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ዕጩ አባል ሆኖ መቅረብ የሚያስችለው ተራ (ወይም ወረፋ) አለው ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ የተመድ አባል አገሮች የአፍሪካን ዕጩዎች በተመለከተ ምንም ምርጫ የላቸውም ማለት ነው፡፡

እንዲህ ስለተባለ ግን የአፍሪካ ዕጩዎች መንገድ ሁሌም አልጋ ባልጋ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም. የአፍሪካ ቀጣናዊ ቡድን የመረቀውና ያፀደቀው የሱዳንን ዕጩነት ቢሆንም እፋለማሁ ብላ ፍልሚያውንም ቀጥላ መቀመጫውን ያገኘችው ግን ሞሪሽየስ ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ. 2011ም ያልተለመደ የምርጫ ዓመት ነበር፡፡ የአፍሪካ ቀጣና ቡድን የዘንድሮ ‹‹ባለተራ›› ሞሮኮና ቶጎ ናቸው ቢልም፣ ሞሪታንያ የሚጠበቅ ተራ የለም ብላ ከሞሮኮ ጋር ፍልሚያ ገጥማ ሆኖም ግን ሞሮኮና ቶጎ ያሸነፉበት ዘመን ነው፡፡

በአጠቃላይ እንደ አፍሪካ ያለ መደበኛና ሕግም ያለው የዙር ወይም ‹‹የወር ተራ›› ሥርዓት በሌለበት ቦታ ውድድሩና ፍልሚያው የታወቀ ነው፡፡ ዕጩነት ተራ ጠብቆ የሚዳረስበት ሥርዓት ግን ለወር ባለተራዎች ያደላል፡፡ ውድድርና ፉክክር ቢኖር ሲበዛ ይቸገሩ የነበሩ አገሮችን በግፊት ያስመርጣል፡፡ አባልነታቸው ለፀጥታው ምክር ቤት ትርጉም የሌላቸውን ምናልባትም ከጥቅማቸው ጉዳታቸው የሚበዙትን አገሮች ዝም ብሎ ያስመርጣል ይባላል፡፡ ለማንኛውም ግን አፍሪካ ውስጥ የተቋቋመው ተራ ጠብቆ ዕጩ የመሆን አሠራር፣ ሥርዓት ያለው ዑደት ይከተል ዘንድ የመርህ መመርያ ተደንግጎለታል፡፡ ይኸውም

  • ሰሜናዊ አፍሪካና ማዕከላዊ አፍሪካ በእያንዳንዱ ጐደሎ ቁጥር ባለው የካሌንደር ዓመት እየተፈራረቁ ለአንድ መቀመጫ ዕጩ ያቀርባሉ
  • ምዕራባዊ አፍሪካ ጎደሎ ቁጥር ባለው በእያንዳንዱ የካሌንደር ዓመት ለአንድ መቀመጫ ዕጩ ያቀርባል
  • ምሥራቃዊው አፍሪካና ደቡባዊው አፍሪካ ሙሉ ቁጥር ባለው በእያንዳንዱ ካሌንደር ዓመት እየተፈራረቁ ለአንድ መቀመጫ ዕጩ ያቀርባሉ

ይህን የመሰለው ቁልጭ ያለ አሠራር ግን (ጥርትና ቁልጭ ያለ ነው ማለት ግን የግድ ተገቢና ፍትሐዊ ነው ማለቴ አይደለም) በየጊዜው መወሳሰቡ አይቀሬ ነው፡፡ ከአንድ በላይ በሆነ ቀጣናዊ ወይም ንዑስ ቀጣናዊ ቡድን ውስጥ ተንፈራጠው የሚገኙ አገሮች ከአንዱ ወደ ሌላው ሊዘሉ፣ አሁን እዚህ ነኝ ሊሉ፣ የወር ተራውንና የወረፋውን ሕግ ሊያናጉ ይችላሉ፡፡ ከዚያም በላይ ሌሎች ተፎካካሪ ዕጩዎች ብቅ ብለው እስከ መጨረሻው ምርጫ ድረስ እንፋለማን ይላሉ፡፡ በአንድ ንዑስ ቀጣና ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አገሮችም የወር ተራና የወር ሥርዓቱ ከሚታገሰው በላይ አዘውትረው መመረጥ መወዳደር ይሻሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካና የናይጄሪያ በተለይም የናይጄሪያ አዝማሚያ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ በ2010 እስከ 2011 አባል የነበረችው ናይጄሪያ የ2014 እስከ 2015 አባልም ነበረች፡፡

ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ራሷን ለውድድር ያቀረበችውና በተቋቋመው የአፍሪካ ቀጣናዊ ቡድን አሠራር መሠረት ኬንያና ሲሸልስ ገለል ብለውላት ብቸኛዋ ተወዳዳሪ ሆና የቀረበችው ለ2017‑2018 የሥልጣን ዘመን ነው፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን (አባልነቱ ተራና ከቋሚ አባልነት የተለየ ቢሆንም) ከፍ ያለ ከሰማይ ከምድር የከበደ ሉላዊ ኃላፊነት ያሸክማል፡፡ ያንኑ ያህል የከበደ ፖለቲካዊ ዋጋ የሚያስከፍል ጣጣም አለው፡፡ በዚህ አጠቃላይ አነጋገር ሳይወሰን ለኢትዮጵያ ደግሞ ጉዳዩ ከፍ ያለና በርካታ ወሳኝና ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያካትት ኃላፊነት አለበት፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችንና አብነቶችን ለምሳሌ ያህል እናንሳ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት የሁልጊዜም አጀንዳዎች ከሆኑት መካከል አንዱ አሁን ከሶሪያ ከየመን ከሊቢያ ወዘተ ጋር የተሸራረበው የእስራኤል/ፍልስጤም ጉዳይ ነው፡፡ ዩክሬን፣ ሶሪያ፣ ኢራን የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የወሰን መስመር የምትጋራቸው የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንም ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ በፀጥታው ምክር ቤት ሥር ያሉ አባልነትን የግድ የሚያደርጉ፣ በሊቀመንበርነት መሰየምን የሚጠይቁ የታሊባን፣ የሰሜን ኮሪያ፣ የሊቢያ፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የአልቃኢዳ የማዕቀብ ኮሚቴዎች የሚባሉ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከአንድ የመንግሥታቱ አባል አገር ፍዝ ተሳትፎ በላይ ትጉ ተሳትፎን፣ ተጨማሪ የሰው ኃይልንና ጊዜን የሚሹ ‹‹የሙሉ ቀን›› ሥራዎች፣ ሥልጣንና ተግባሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ ላይ የሚወሰድ አቋም የሚተነፍሰውና የሚባለው ሁሉ እንደሌላው ወቅት የ‹‹ኮሚቴ›› ወይም የጠቅላላ ጉባዔ ሥራ ከመቀመጫ በመቅረት ወይም ድምፀ ተአቅቦ በማስመዝገብ የሚሸሹና የሚሸወዱ አይደሉም፡፡

በተለይም የምንኖርበት አካባቢ ፍትሐዊ መፍትሔ ያጣው የእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ከሃይማኖት ወገናዊነት ጋር የሚምታታበት፣ የአመለካከት ድህነትና መተነኳኮስ የበዛበት፣ የአገር ማንነትና የእምነት መብት በሃይማኖቱ ወይም በእምነቱ የአመጣጥ ዕድሜና በአማኞች ብዛት የመለካት ችግር ሥር የሰደደበት ነው፡፡ በእስራኤል፣ በነኢራንና በነአልቃይዳ ጣት የሚደነቋቆል የሶማሊያ የትርምስ እሳት የሚንቀለቀልበት የአፍሪካ ቀንድን አካባቢ ከፀረ እስራኤል ትግልና ኃይሎች ጋር ለማጠላለፍ የሚሠሩ ያሉበት አካባቢ ነው፡፡

ከዚህ አካባቢ የሚገኝ በምርጫ ውድድርም ሆነ በ‹‹ምደባ›› ዓይነት የሚገኝ የፀጥታው ምክር ቤት ወንበር ከምናውቀውና ከሚነገርለት በላይ ጠንካራ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ይሻል፡፡ በ2005 ዓ.ም. የወጣው የውጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጁ በመግቢያው እንደሚለው ‹‹ሙያዊ አቋሙ ብቃቱና ክህሎቱ የዳበረና የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በታማኝነትና በቁርጠኝነት የሚወጣ ጠንካራ የሰው ኃይል …›› ይፈልጋል፡፡ ከተለመደው የአሿሿም የውለታ መመለስ ምደባ አሮጌ ቀፎ መውጣት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ተልዕኮ ውስጥ ይህን በመሰለ ዓለማቀፋዊ መድረክ ለመግባት መወሰኗን እንደ ቀልድ የሰማነውም ለዚያውም ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የውጭውን ሰው በተለይ ባለድርሻ ባደረገ ዜና ከአራት ወር በፊት በየካቲት ወር መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር አግባብ ባለው ድረ ገጹ መልሶ የለጠፈው የኢትዮጵያ የምርጫ ዘመቻም የሚያነጣጥረው በውጭው ተደራሽ ላይ ነው፡፡

የፀጥታ ምክር ቤት ምርጫ ዘመቻ እያንዳንዱን አባል አገር እስከ ርዕሰ ብሔር ወይም ርዕሰ መስተዳደር ድረስ ያለ ተወካይ ከማግባባት፣ ከመለመንና ከማስተማመን ጀምሮ እንደየአገሩ አቅምና እንደ እጩነቱ ዓይነት (ተፎካካሪ ያለውና የሌለው መሆኑ) አነሰም በዛም የማይናቅ የጊዜና የገንዘብ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በተለመደ አሠራር ገንዘብ ይከሰከሳል፡፡ ቃል መግባትና ውለታ መተሳሰር ጀርባዬን እከክልኝ እኔም እንዲህ አድርጌ አክልሃለሁ መባባል፣ ስጦታ ይዞ በየአገሩ መናገሻ ከተማ መዞር በተመድ ውስጥ የታወቀ አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ የሰማነው ሪፖርት፣ ይገባችኋል ተብሎ የቀረበ ዘገባ የለም፡፡

ከአገር ቤት ይልቅ ለውጭው ፍጆታ ይበልጥ ያነጣጠረውና በፀጥታው ምክር ቤት የ2016 ምርጫ ድረ ገጽ ያገኘነው የኢትዮጵያ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ጽሑፍ እንደሚለው የኢትዮጵያ የምረጡኝ ማስታወቂያ በዋነኝነት ያስተጋባው የአገሪቱን የመካከለኛ ደረጃ ዲፕሎማሲ ቁርጠኝነትና የአካባቢያዊና የዓለማዊ (ግሎባል) የፖሊሲ አጀንዳዋን በትጋት የማዳበር ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቻርተሩ እንደተደነገገው የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባል ሆኖ መመረጥ ከሚለካባቸው ዋና መመዘኛዎቹ መካከል አንዱ በተለይ በአንቀጽ 23 የተወሰነው ዓለማቀፋዊ ሰላምንና ደኅንነትን ለመጠበቅ የተደረገውን አስተዋጽኦ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ‹‹ረጅምና አኩሪ ታሪክ›› እንዳላት ገልጻለች፡፡ የኮሪያን ጦርነት በመጀመሪያ ደረጃና በግንባር ቀደምትነት ጠቅሳለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ የወሰን መስመሯን ተላልፋ ደቡብ ኮሪያን ስትወር ኢትዮጵያ ጉዳዩን ወደ ነበረበት ለመመለስ የባለ አሥራ ስድስት አገሮችን የተመድ የሰላም ጥበቃ ኃይል መቀላቀሏን፣ በሦስት ዓመት ጦርነት ውስጥ 121 ወታደሮቿ መገደላቸውንና ሌሎች 536 ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጻ፣ አንድ ሰው እንኳን እንዳልተማረከባት አስታውሳ ጉዳይዋን አስረድታለች፡፡ አሁንም ከስምንት ሺሕ በላይ የመከላከያና የፖሊስ አባላቷን ከአሥር በላይ በሆኑ የሰላም ማስከበር ሚሲዮኖች ውስጥ በመላው ዓለም ማሰማራቷንም አስታውቃለች፡፡

እንኳንስ የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን ይቅርና የተመድ አባል መሆንም በራሱ የከበደ ኃላፊነትና ከፍተኛ ጠንቅ አለበት፡፡ የኮሪያ ጦርነት አንዱ ‹‹ጥሩ›› ምሳሌና ነገሩን ለማስረዳት የሚረዳ እንደ ሌሎቹ ጉዳዮች የማያሳስብና የማያስፈራ ነው፡፡ የኮሪያ ጉዳይ በተመድ መድረክነት ሲታይ በኒውዮርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ነበሩ፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በታተመ የራስ እምሩ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ በመጨረሻው ክፍል በተያያዘ እሳቸው ለንጉሠ ነገሥቱ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጻፉት ደብዳቤ እንደተገለጸው የኮሪያ ጦርነት የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ዓይነት የወራሪ ጦርነት አይደለም፡፡ ደቡብ ኮሪያን ኢትዮጵያ በ1928 ዓ.ም. ከደረሰባት ዓይነት ጥቃትና ወረራ የሚታደግ ጦርነት አይደለም፡፡ ራስ እምሩ ይህን ሁሉ ዘርዝረውና ልዩነቱን አስረድተው የኢትዮጵያ አቋም በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አስቀድመው አስታውቀው እንደነበር ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን ‹‹በኮሪያ በኮንጐ›› እየተባለ የተዘመረለትና የተዘፈነለት የኮሪያ ጦርነት ግን የሁሉንም የኢትዮጵያ ተከታታይ መንግሥታት አንድ ወጥ ድጋፍ የተጎናጸፈ አይደለም፡፡ በተለይም የ‹‹ሶሻሊስቱን›› ካምፕ ከተቀላቀልን በኋላ የአገር ቤቱን ፊውዳላዊ ሥርዓትና የመንግሥቱን የዚህ ጉዳይ አቋም ከዓለማቀፋዊው የአድህሮት ኃይል ጋር አውግዘን ሰልፍ ወጥተናል፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የመሠረቱት ፓርቲዎችም ይፋ አቋማቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆኖ መመረጥ ከዚህ የባሰ ጣጣና ጠንቅ ያለው ኃላፊነት አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ተልዕኮ እንደቀድሞው አልፎ አልፎ፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የሚያጋጥም ግዳጅ መሆኑ ቀርቶ በየጊዜው የሚመጣና የሚቀበሉት ምናልባትም እያሳደዱና እየተሽቀዳደሙ የሚሹት የፀጥታው ምክር ቤት መቀመጫ፣ ከአገር ጥቅም አኳያ ሥፍራው፣ ማለትም ወንበሩና መድረኩ የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝን ይጠይቃል፡፡ የአገር የደኅንነት ፖሊሲን በቅድሚያ የሁሉንም ቢያንስ ቢያንስ የአብዛኛውን ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጐ መቅረጽ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲም ያስፈልጋል፡፡

እንዲህ ያለ ፖሊሲና ተልዕኮ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሕዝብን ተሳትፎ፣ የሕዝብን ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ በተሳትፎና በማወቅ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ድጋፍ ደግሞ ከአንድ ወይም ከሌላ መንግሥት የሥልጣን ዘመን፣ ከአንድ የፀጥታው ምክር ቤት የተራ አባልነት መቀመጫ የቆይታ ጊዜ በላይ፣ ወረት ተሻግሮ የሚዘልቅ አቋም ያጸናል፡፡ ይህን ማድረግ እዚህ ላይ መድረስ ይቻለን ዘንድ ያለቀለትን ዕቅድና ውሳኔ በኮንፈረንስና በስብሰባ የሕዝብ ውሳኔ ከማድረግ፣ ይህንንም ለሕዝባዊ አሠራር ማረጋገጫ አድርጐ ከመጠቀም የተለመደውና አላዋጣ ብሎ መንገዱን ከዘጋብን ‹‹ጥበብ›› መውጣት አለብን፡፡

ይህ ግዳጅ፣ ከዚህ በተጨማሪ፣ የመንግሥት የማስፈጸም ብቃትን ሲበዛ ማሻሻልን፣ ከፍ ማድረግንና ማላቅን ይጠይቃል፡፡ የውጭ ግንኙነት አገልግሎቱ ከላይ እስከታችና ከአገር ቤት እስከ የውጭ አገር ድረስ በእውቀትና በብቃት ላይ የተመሠረተ መሆን ይገባዋል፡፡ የአሜሪካ የገንዘብ ሰነዶችና የገበያ ኮሚሽን በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት ጉዳይ ላይ የአሜሪካ ውስጥ የቦንድ ሽያጭን በተመለከተው ውሳኔው ያጋለጠው ችሎታችንንና ችግራችን ይበቃናል፡፡ እንዲህ ያለ በዓለም አደባባይ ያዋረደንን፣ ግልግልን በመሰለ በሌላውም ዓይነት ዓለማቀፋዊ መድረክ ያጋለጠንን ዓይነት የሰው ኃይል እየመደብንና ይህን የመሰለ ብቃት ይዘን በሰላምና በደኅንነት ጉዳይ ላይ መወሰንን ቀላል አድርጐ መቁጠር በጭራሽ አይቻልም፡፡

ባለፈው ማክሰኞ ያለተፎካካሪ ተወዳድረን ከተፈላጊ የ129 የአዎንታ ድምፅ በላይ የ185 አባል አገሮችን የድምፅ ድጋፍ አግኝተን ያሸነፍነውና ከሚቀጥለው የፈረንጆች አዲስ ዓመት መባቻ ጀምሮ የምንቀመጥበት የፀጥታው ምክር ቤት የተራ አባልነት መቀመጫም በትክክለኛው የቃሉ ወይም የሐረጉ ትርጉም ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ማድረግ የሚያስችል አደጋና ጠንቅ እንዳለውም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ማንምና የትም ቦታ ያለ መንግሥትም፣ የተመድ አካልም የማያስተባብሏቸውና ‹‹የጠላት ወሬ›› ብለው የማያጣጥሏቸው ጥናቶችና ዶክመንቶች እንደሚያስረዱት ቦታው ለባለገበታና ለማገጠበት ከፍተኛ ኪራይ መሰብሰቢያ ቦታ ነው፡፡ የውጭ እርዳታና ‹‹መቅሹሽ›› ወይም መላሾ ማሰባሰቢያ መድረክ ነው፡፡ በዚህ የሚቀመጥ መንግሥት ወትሮ ከሚያገኘው ዕርዳታ የ59 በመቶ፣ የተመድ እርዳታ ደግሞ የስምንት በመቶ ብልጫ ያለው ገበያ ይደራለታል፡፡ ለፀጥታ ምክር ቤት ተራ አባላት የሚሰጠው እርዳታ ይበልጥ የሚደራው ደግሞ በተለይ በተመድ ‹‹ቁልፍ የዲፕሎማሲ ዓመታት›› ላይ ነው፡፡ የዚህ ትርጉም እ.ኤ.አ. 1991 ያለ ምክር ቤቱ በኢራቅ ላይ ኃይል መጠቀምን የፈቀደበት ዓይነት ጊዜ ማለት ነው፡፡ የመን የአሜሪካን እርዳታ የተገፈፈችው በ1990 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት የሰጠውን የጦርነት ውሳኔ በመቃወሟ ነው፡፡ በአንፃሩ የጦርነቱን ውሳኔ ከደገፉት የፀጥታው ምክር ቤት ተራ አባላት መካከል አንዳንዶቹ የኩዌትን ልዩ ምስጋና በገንዘብ ተመንዝሮ ማግኘታቸውን የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ በወቅቱ ሰምተነዋል፡፡

እናም ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ፣ የመንግሥት የሥልጣን አካልና ባለሥልጣኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያን ‹‹ድል›› ሲያከብር እውነቱን በሙሉ፣ ሁሉንም እውነት ሊነግረን ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግሥት ሚዲያው ቅራሚ ግንዛቤን አግበስብሶ፣ ከጭራፊና ብጣሽ ነገር ላይ ተንስቶ፣ ትንሽ ጫፍ ይዞ ጋራ የሚያክል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ ማለቱን፣ ቋጥኝ የሚያክል ማጠቃለያ መስጠቱን፣ ስለዚህም እውነት እኔ ነኝ ማለቱን ቢተው አገር ከብዙ ችግር ይገላገላል፡፡

የመንግሥት ሚዲያው፣ ነገር ያሳመርኩና ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የከፍታ ደረጃ ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ የጠራ እየመሰለው የአባልነቱን ዓይነት ‹‹ተለዋጭ አባል›› ሲል እንሰማለን፡፡ ተለዋጭ ማለት በእርግጥ ተቀያሪ ማለት ነው፡፡ ተተኪ ማለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የተመረጠችው አንጐላን ‹‹ቀይራ›› ነው፡፡ አንጐላን ‹‹ተክታ›› ነው ማለት ይህን ያህል ብቻ ማስኬድ ካልቻለ በቀር ቋሚ ያልሆኑ የአሥሩ የፀጥታ ምክር ቤት አባላት ስያሜ በጭራሽ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚያም ላይ ደግሞ ዕድሜ 75 እና 50 ዓመት ለሞላው ለመንግሥት ሚዲያው እንጂ ይህ አገር ‹‹ተለዋጭ አባል›› የማለትን ትክክለኛ ትርጉም ሲያስጠናን ኖሯል፡፡ በአንድ የምርጫ ወይም የሥልጣን ዘመን ውስጥ ዋናው አባል/ሹም ቢጐድል በእሱ ምትክ ወይም ፋንታ ለጊዜው ተተክቶ የሚሠራ ማለት ነው፡፡ የፀጥታውን ምክር ቤት Non Permanent Members (በአጭር ስማቸው NPM) የሚባሉትን የሚገልጽ አይደለም፡፡ እነሱን ቋሚ ያልሆነ አባላት ማለትም አያሳፍርም፡፡ ደረጃቸውን ዝቅ አያደርግም፡፡ በጽሑፌ ውስጥ የመንግሥት ሚዲያው ‹‹ተለዋጭ አባላት›› የሚለው ስያሜ አልጥመኝ ብሎ ተራ አባላት ያልኳቸውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሚዲያው ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የገለጸ፣ ያከበረና የረዳ እየመሰለው፣ የማይሆነውና የማይሠራው ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያን ድል አጉልቶ ያሳየ እየመሰለው በዘንድሮው ምርጫ በመጀመሪያው ስብሰባ ከአምስቱ ተመራጮች መካከል የአራቱ መጠናቀቁን የአምስተኛው ተመራጭ ግን፣ የጣሊያንና የኔዘርላንድ አይሎ አሸናፊውን መለየት አቅቶ ጉዳዩ በቀጠሮ ማደሩን ይዞ ‹‹በተለይ የአውሮፓ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ሦስተኛውን ድምፅ እንኳን ማግኘት ባልቻሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው ኢትዮጵያ 185 ድምፅ አግኝታ በከፍተኛ ድምፅ የተመረጠችው፡፡ ለዚ ያበቃት ምንድነው?›› ብሎ ምሁር ማብራሪያ ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያለ አጉል ብልጠትና ጥረት የሚዲያውን ዝቅጠት ይመሰክራል እንጂ የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ሙሉ ሥዕል በጭራሽ አያሳይም፡፡ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የኢትዮጵያን የሰላም የዲሞክራሲና የዕድገት ትጋት አያግዝም፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የምንነጋገርበትን ጉዳይ የአገር አጀንዳነትና ዝርዝር ጭብጥ ይሰውራል፡፡ የተመረጥንበት ወንበር ለሚያጐናጽፈው፣ በዚያው በመንግሥታቱ ማኅበር ማዕቀፍ ውስጥ የተወሰነ፣ ነገር ግን ከፍተኛ ሥልጣን፣ ሥልጣኑን ተከትሎ ለሚወድቅብን ኃላፊነት አስፈላጊው የፖሊሲ መሣሪያና ዝግጁነት፣ የማስፈጸም አቅም ብቃትና ጥረት እንዳለንና እንደሌለን ከመነጋገር ያዘናጋል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችና ዝንባሌዎች ሊብላሉበት የሚገባውን ጉዳይ አስቀድሞ ይዘጋል፡፡

ይህን ሁሉ አልፎ ዘሎና ተራምዶ ግን በዋናው ጉዳይ ላይ መነጋገር አለብን፡፡ እንዲህ ባለ በተለይም የመንግሥት ሚዲያው ጐጂና አፍራሽ አላዋቂና ተራ ብልሀት እንኳን የሌለው መለመላውን የቆመ ውዳቂ ሥራ ሳንዘነጋ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ደኅንነት ልማትና ዕድገት በሚያግዝና ለእሱም በገበረ አቅጣጫ የምንቀመጥበትን ወንበር በምንገለገልበት መላ ብልሀትና ጥበብ ላይ ሐሳቦች ያለገደብ የሚፈልቁበት ውይይት መክፈት አለብን፡፡                   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡