ለ40/60 ቤቶች የማያዳግም ምላሽ እንፈልጋለን!

 

የ40/60 የመኖሪያ ቤት መርሐ ግብርን በተመለከተ ባለኝ መረጃ መሠረት፣ ከ2005 ዓ.ም. አጋማሽ ወዲህ ከከፍተኛ እርከን ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም ከነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ቤት ፈላጊዎች በሚፈልጉት የመኖሪያ ቤት መጠንና የክፍያ ሁኔታ ምዝገባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

እኔም ስለፕሮግራሙ የተሰጠውን መግለጫ መሠረት በማድረግና ከመኖሪያ ቤት ችግር በአፋጣኝ ለመላቀቅ በነበረኝ ጉጉት መሠረት ሙሉ ክፍያውን በመክፈል በነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ምዝገባዬን አጠናቅቄ መጠበቅ ከጀመርኩ ይኸው አሁን ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ሆኖኛል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ተገንብተው የተጠናቀቁት የ40/60 ቤቶች በቅርቡ ይተላለፋሉ ቢሉም ይኼው እሳቸው እንኳ ይህንን ካሉ የአንድ ዓመት ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ይህንኑ የቤት ፕሮግራም ግንባታ የሚከታተሉ የቤቶች ኢንተርፕራይዝ ኃላፊም ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የሰንጋ ተራና የቃሊቲ ክራውን የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊጠናቀቅ የአንድ ወር ጊዜ ቢቀረው ነው በማለት ገልጸው ነበር፡፡ እኚሁ ኃላፊ፣ ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣም የሁለቱ ሳይቶች ቤቶች በቅርብ ቀናት ውስጥ ለዕድለኞቹ ይተላለፋሉ ብለው ነበር፡፡ ይህንኑ አባባላቸውን ከዓመት በኋላ እኚሁ ኃላፊ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቤቶቹ ስለሚተላለፉበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ፣ የከተማ ልማትና ቤቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርብ ቀን መግለጫ ይሰጡበታል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የ20/80 እና የ10/90 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ሲተላለፉ በቴሌቪዥን በተላለፈ ዘገባ የ40/60 ቤቶችም በቅርብ ቀን ውስጥ ይተላለፋሉ ተብለን ነበር፡፡ ማለቂያም ማብቂያም በሌለው ቀን በተስፋ ተንጠልጥለን ይኼው የቤት ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ተቸግረናል፡፡ ችግሩ እኔንም ሆነ ሌሎች በቤት ኪራይ ያለነውን በባሰ የኑሮ ዝቅጠት ውስጥ እንድንዳክር ስላስገደደን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይተላለፋሉ ባሉበት ቃላቸው መሠረት ተግባራዊ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን፡፡ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎችን በተስፋ ለማንጠልጠል ብቻ የታለሙ ቃላትን ማዥጎድጎድ ለምን ያስፈልጋል? እባካችሁ የማያዳግም ምላሽ አሰሙን፡፡

(የ40/60 ቤቶች ተመዝጋቢ)

* * * * * * *

ግልጽ የቅሬታ አፈታት ሥርዓት አለን!

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ጋዜጣችሁ ላይ ይድረስ ለሪፖርተር በሚለው ዓምድ ሥር “ለማን አቤት እንበል?” በሚል ርዕስ በአቶ አሰፋ ብርሃኔ የቀረበውን አስተያየት አንብቤ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው በጽሑፋቸው ውስጥ “ቤቴል አካባቢ ደረጃ ስድስትና ሰባት ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ያለው የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የቤት ካርታ በመቀየር ላይ ነው፤” ይላል፡፡ ደረጃ ስድስትና ሰባት የሚለውን እኔ ወረዳ ስድስትና ሰባት ብዬ ላስተካክልላቸው፤ ምናልባት ሲቸኩሉ ተሳስተው ወይም አላወቁትም ከሆነ ብዬ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ወረዳዎች ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 818/2006፣ ይህን አዋጅ ተከትሎ በወጣው ደንብ ቁጥር 324/2007 እና መመርያ ቁጥር 45/2007 መሠረት የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ እያከናወነ ያለው መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሳይሆን፣ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡

በመሬት አስተዳደር አካባቢ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን ለመቅረፍ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል እያንዳንዱን ቁራሽ መሬት አረጋግጦ ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት እያስገባ፤ ለዚህም አዲስ የዋስትና ሰርተፊኬት እየሰጠ ያለው ይኼው የተጠቀሰው ተቋም ነው እንጂ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አይደለም፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በተቋቋመ በጥቂት ዓመታት ውስጥም እጅግ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በርካታ ልምዶችም ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የቅሬታ አፈታት ሥርዓታችን አንዱ ነው፡፡

የይዞታ ማረጋገጡ ሥራ በጊዜ ገደብ በግልጽ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡ መዝግቦ ሰርተፊኬት ለመስጠት ግን አስተያየት ሰጪው ያሉትን ጊዜ የሚያቆይ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡

በሒደቶቹ ማንም ቅሬታ ያለው ባለይዞታ ቅሬታውን አቅርቦ የሚስተናገድበት ግልጽ የሆነ የቅሬታ አፈታት ሥርዓትም ተዘርግቷል። በአዋጁም፣ በደንብና በመመርያውም ስለቅሬታ አፈታቶች በግልጽ የተቀመጡ አሠራሮች አሉ፡፡ በመሆኑም በአስተያየት ሰጪው የቀረበልን ቅሬታ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ምክንያቱም ጠንካራ የቅሬታ አፈታት ሥርዓት ያለን ከመሆኑም ባሻገር እንደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤታችን ቅሬታ ቀርቦልን በእኛ ደረጃ መፈታት የሚችል ሆኖ ያልተፈታ ቅሬታ ስለሌለ፡፡ ቅሬታ ለማቅረብ ለሚፈልጉ ተገልጋዮቻች፣ በባለጉዳይ ቀን ብቻ ሳይሆን በሥራ ቀናት ሁሉ በራችን ሁሌም ክፍት ነው፡፡ ነበርም፡፡ “ታዲያ አቶ አሰፋ ብርሃኔ ይህን ማወቅ ምነው ተሳናቸው?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ለመገልገል ስላልመጡ ወይም የ“አሉ-አሉ” ወሬ ሰምተው በተሳሳተ መንገድ ጽፈው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይኖረኛል፡፡ የሕዝብ አገልጋይ ነንና የማንኛውንም ባለጉዳይ ቅሬታ ለመፍታት ትልቅ ስፍራ ሰጥተነው እንደምንሠራ ይወቁ እላለሁ፡፡

አቶ አሰፋ ብርሃኔ በአስተያየታቸው ከተቋም ባለፈ መንግሥታችን ያደረገውን የጥልቅ ተሃዲሶ ግምገማንም ለማንኳሰስ ሞክረዋል፡፡ ቢሆንም እንኳን በአንድ ተቋም ውስጥ ደረሰብኝ ባሉት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት መንግሥትን በጅምላ መኮነናቸው በጣሙን አስገርሞኛል፡፡ "በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ መንግሥት (ኢሕአዴግ) ታድሻለሁ፣ መልካም አስተዳደር አሰፍናለሁ በሚልበት ጊዜ ብሶበታል፤" በማለትም በድፍረት ጽፈዋል። ይኼ ከግነትም ያለፈ ጭፍን አገላለጽ እንደሆነ ማንም ሊረዳው ይችላል። የእኛ ተቋምም የተሃድሶ ግምገማውን በበቂ ሁኔታ እንደከወነ ልነግርዎት እሻለሁ፡፡ ተቋማችን እያካሄደ በነበረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ አጠቃላይ ሠራተኛውን በንቃት በማሳተፍ ሠራተኛው በቅልጥፍና፣ በጥራትና በሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ እንዲተጋ በርካታ የተሃድሶ ሥራዎች ተሠርተዋል። የተሃድሶ ውጤቱም አበረታች እንደሆነ እያየን ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለአቶ አሰፋ ብርሃኔ ለመግለጽ የምፈልገው “ለማን አቤት እንበል?” ላሉት ይጠፋዎታል ብዬ ሳይሆን ለማስታወስ ያህል በተቋማችን ውስጥ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት ተዘርግቶ ይገኛል፡፡ ከተቋም ባለሙያ ጀምሮ እስከ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ድረስ አቤት ማለት ይቻላል፡፡ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የማይፈታም ከሆነ እስከ ዋና መሥሪያ ቤቱ (ማዕከሉ) ድረስ የራሱ የሆነ የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓት በግልጽ ተዘርግቶ እያለ ምን የሚሉት አፋልጉኝ ነው?

በመሆኑም በአቶ አሰፋ ብርሃኔ የተሰጠው አስተያየት የከተማውን የመሬት መረጃ ችግር ለመፍታት እየሠራ ያለና እስካሁንም ያለውን የተቋማችንን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ካልሆነ በስተቀር፣ መሠረተ ቢስና የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትን አይገልጽም እላለሁ፡፡ የጋዜጣ አዘጋጆችና አንባቢያንም በዚሁ አግባብ እንድትረዱልን እንፈልጋለን፡፡

(የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ)