አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ልሂቅ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ (1928-2009)

 

በኢትዮጵያ በአካውንቲንግ ዘርፍ ‹‹አባት›› በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህልም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በቅድመና ድኅረ ምረቃ መምህርነትና በተመራማሪነት ላቅ ያለ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በአፀደ ሥጋ የተለዩት ፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ፡፡

ከልሂቅ ተመራማሪነታቸው የሚሠርፁ ከ54 በላይ የምርምር ውጤቶች በታዋቂ ጆርናሎች (የምርምር መጽሔቶች) ማሳተማቸውና በኮንፈረንሶች ማቅረባቸው፣ ከዕውቀት ትሩፋታቸው ተቋዳሽ ለመሆን የታደሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙትንም ተደራሽ አድርጓል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛነት ከ20 ዓመታት በላይ፣ እንዲሁም ለተጨማሪ 27 ዓመታት በአጠቃላይ ለ47 ዓመታት በመምህርነትና በተመራማሪነት ላገለገሉት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም አገልግሎት ዘመን ልዕልናቸው በ1996 ዓ.ም. ልሂቅ ፕሮፌሰር (ፕሮፌሰር ኤምሪተስ) ማዕረግን አጎናፅፏቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ ከ1963 እስከ 1966 ዓ.ም. የአዲስ አበባ የአስተዳደርና ልማት ባላደራ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ በዚሁም ጊዜ የዩኒቨርሲቲው የኅብረተሰብ ሳይንስ የአካውንቲንግ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኃላፊም ነበሩ፡፡ ከ1966 እስከ 1977 ዓ.ም. እና ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም. የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ እንዲሁም የቢዝነስ አስተዳደር ኮሌጅን በዲንነት አገልግለዋል፡፡

እንዲሁም ከ1998 እስከ 1990 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ተቋምን በዳይሬክተርነት የመሩት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀለውን የሚድሮክ ኢትዮጵያን የትምህርትና ሥልጠና ተቋምን በማቋቋም ይጠቀሳሉ፡፡

በተጓዳኝም፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰው ኃይል ልማት ላይ ሥልጠና በየጊዜው መስጠታቸው፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በሥልጠና አማካሪነት ሠርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሐንስ በሕይወት ዘመናቸው ካገኟቸው በርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶች መካከል የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሽልማት፣ የፓን አፍሪካን የኮርፖሬት ገቨርናንስ ሽልማት፣ በምርጥ የኤምሪተስ ፕሮፌሰርነት የአፍሪካ አመራር ሽልማት ይገኙባቸዋል፡፡

የአፍሪካ የትምህርት አመራር ሽልማትን በ2006 ዓ.ም. በሞሪሸስ በተካሄደው የአፍሪካ - ህንድ የአጋርነት ስብሰባ (Africa-India Partnership Summit) ላይ ያገኙት ‹‹ወርልድ ኮርፖሬት ሶሻል ሪስፖንስብሊቲ›› የተሰኘ ቀንን መታሰቢያ በማድረግ ነበር፡፡

በወቅቱ እንደተገለጸው፣ ፕሮፌሰር ዮሐንስ በአመራር ጥበባቸው፣ በትምህርታዊ ፈጠራቸው ቀጣይ መሪዎችን ለማፍራት ለተቋማት ግንባታ ያዋሉ ልሂቅ  ነበሩ፡፡

ባካበቱት የዳበረ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት መነሻነት የአሥር አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሙያ ማኅበራት አባል የነበሩት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፣ ከ1978 እስከ 1986 ዓ.ም. የፉልብራይት ስኮላርሽፕ ማዕረግ ከዳላስ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሒሳብ አያያዝ ልማት ማዕከል የተሰጣቸው ሲሆን፣ በጀርመን  ከያል ዩኒቨርሲቲ የፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን የሲኒየር ሪሰርች ፌሎሽፕም  አግኝተው ነበር፡፡

 በ1955 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አካውንቲንግን በማስተማር ፍኖተ ዕውቀትን የጀመሩት ፕሮፌሰር ዮሐንስ በ1966 ዓ.ም. የተባባሪ ፕሮፌሰርነት፣ በ1987 ዓ.ም. የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በመጨረሻም በ1996 ዓ.ም. ፕሮፌሰር ኤምሪተስነትን (ልሂቅ ፕሮፌሰርነትን) ተቀዳጅተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ከአባታቸው ከደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዋጋዬ ገብረ ሚካኤል ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. በአክሱም ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስመራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሱዳን ካርቱምና በአዲስ አበባ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ኮተቤ) ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡

በ1952 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ1955 ዓ.ም. ከአሜሪካው ኡታህ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ እንዲሁም በ1962 ዓ.ም. በዚያው ከሚገኘው ከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ከሙያቸው ጋር ከተያያዙ ድርሳኖችና መጻሕፍት ከማሳተም በተጨማሪ፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን (1928-1933) ለመመከት በተደረገው አገራዊ ተጋድሎ ተሳታፊ የነበሩት አባታቸውን የሕይወት ታሪክ አሳትመዋል፡፡ ‹‹ደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔ (1884-1964) በሚል ርዕስ ያዘጋጁትና የኅትመት ብርሃን ያየው መጽሐፋቸው፣ አባታቸው ከአንጥረኝነት እስከ ደጃዝማችነት ያሳለፉትን ሕይወት የሚገልጽ ነው፡፡

የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ባጋጠማቸው ድንገተኛ አደጋ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ መጋቢት 5 ቀን በ81 ዓመታቸው ያረፉት ፕሮፌሰር ዮሐንስ ሥርዓተ ቀብር፣ በማግሥቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጵያ በላከው የሐዘን መግለጫ፣ ለሁለት አሠርታት ለዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሰጡት አገልግሎት ለኩባንያው ብቻም ሳይሆን ለአገሪቱም ለአፍሪካም ባለውለታ የነበሩና ሁሌም ሲታወሱ የሚኖሩ ምሁር ናቸው ብሏል፡፡

ልሂቅ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ ባለትዳርና የሁለት ወንድና ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡