አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ልዩነት ውበት የሚሆነው አበባ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ነው

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት ገብረ ክርስቶስ

ውበትን ለመግለጽ እጅግ በርካታ መንገዶችን መሄድ ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አርዕስት ላይ እንደተጠቀሰው የአበባ መሸጫ ሱቅ ውስጥ የተለያዩ አበቦችን አንድ ላይ በማዋሀድ ዕይታን የሚማርክ ውበት መፍጠር ይቻላል፡፡

ሠዓሊያን የተለያዩ ኅብረ ቀለማትን በማድመቅና በማደብዘዝ ዓይን የሚማርኩ ውብ ሥዕሎችን ይሥላሉ፡፡ መኪና አምራቾች የሚያመርቱት መኪና መስጠት የሚገባውን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ ውበቱን ጠብቆ ተወዳጅ እንዲሆንና በገበያ ውስጥ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

በኅብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ ግን ልዩነት መጥበብ እንጂ መሥፈርቱ ለዕድገትም ለልማትም የማይጠበቅ በመሆኑ፣ ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› እያልን የተሳሳተ ፍልስፍና ማራመድ የለብንም፡፡ ልዩነት በብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ አመጋገብ፣ አለባበስ ወዘተ ያለ ቢሆንም ይህ ሒደት ማንም ከሚጠብቀው ፍጥነት በላይ እየጠበበ እየሄደ ያለበት ዘመን በመሆኑ ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› እያልን ጊዜያችንን ማባከን የለብንም፡፡ ለዕድገትና ለልማት በሚደረጉ በርካታ ተግባራት ምክንያት ሕዝቦች እየተቀራረቡ የጋራ ማንነት እየፈጠሩ በመሄዳቸው ሒደት፣ ፍጥረቱ በእጅጉ እየጨመረ የመጣበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት እየተዘዋወርን ብንመለከት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በአለባበስ፣ በአመጋገብና በሌሎችም በርካታ የዕለት ዕለት ተግባራችን ላይ በምናከናውናቸው ሥራዎች ተመሳሳይነት በእጅጉ የበላይነቱን እየያዘ ያመጣት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ደጋግሞ እያነጋገረን ያለው ልዩነትን ማስተናገድ የቻለ ሥርዓት የእኛ ብቻ ነው ይበለን እንጂ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸው በእጅጉ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የገባው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ለምሳሌ ቋንቋን ብንወስድ በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

1ኛ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ ቋንቋ

2ኛ ባለበት ሳያድግ ያለ ቋንቋ

3ኛ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ቋንቋ

እነዚህን ሦስቱን ሁኔታዎች በአግባቡ ብናያቸው ኢሕአዴግ ለሥልጣኑ ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚሠራበትን ቋንቋ ማለትም አማርኛን በሚያስገርም ሁኔታ እንዲያድግ አድርጎታል፡፡ አማርኛ ቋንቋ ባለፉት 25 ዓመታት ያሳየው ዕድገት ቋንቋው ከተፈጠረ ጀምሮ ካሳየው ዕድገት የሚበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም፡፡

በመቶኛ ደረጃ ዕድገቱን ለማየት ብንሞክር በወፍ በረር ግምት ከ1000 (አንድ ሺሕ) ፐርሰንት በላይ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ቋንቋዎች እንደ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የመሳሰሉት ቋንቋዎች ደግሞ ባሉበት ምንም ዓይነት ዕድገት ሳያስመዘግቡ የተጓዙበትን ሁኔታ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ዕድገት ሲባል በሁለት ከፍለን ብናየው መልካም ነው፡፡

 2.1 የተጠቃሚዎች ብዛት መጨመር

 2.2 ቋንቋው ራሱን ከሳይንስና ከዕድገት ጋር እያዛመደ የሚያደርገው ዕድገት

በሦስተኛ ደረጃ ልናያቸው የምንችለው ቋንቋዎች እጅግ በርካታ ሲሆኑ፣ እነዚህ ቋንቋዎች በከፍተኛ ደረጃ (በተለይ አዲሱ ትውልድ በፍላጎት ለመጠቀም ያለው ዝንባሌ እየቀነሰ በመሄዱ) የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ እነዚህን ቋንቋዎች በተለያዩ መንገዶች ሌላ ቢቀር በቅርስነት እንኳን ጠብቆ ለማቆየት በቂ ሀብት መሰብሰብ ባለመቻሉ፣ የባህል ባለቤት የሆኑትን ሕዝቦችም የማዕከላዊም ሆነ የክልላዊ መስተዳድሮች በቂ እንክብካቤ ለማድረግ አቅም መፍጠር ባለመቻላቸው፣ ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡

አለባበስ፣ አመጋገብና ባህልን በተመለከተ በብዙ ብሔር ብሔረሰቦች በእሴትነት የሚታዩ የዕለት ተዕለት መገልገያ መሆናቸው እያበቃ፣ በመጤ ቁሳቁሶችና አልባሳት እየተዋጡ መሄዳቸውን የበዓላት ቀን ብቻ ማድመቂያ መሆናቸው በስፋት ይስተዋላል፡፡

ኅዳር 29 በደረሰ ቁጥር ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› እያልን ልዩነት ግን እየተደመሰሰ የሚሄድበት ሁኔታ በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ፣ ሌላው ቢቀር በቅርስነት ደረጃ ጠብቆ የማቆየት ሥራ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ውበት የከፍተኛ ችሎታና የከፍተኛ ትጋት ውጤት በመሆኑ፣ የሚሠራበትንና የሚጠቅምበትን ቦታ ለይቶ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከልዩነታቸው ይልቅ አንድ ዓይነት አስተሳሰቦችን ወይም የተቀራረበ አስተሳሰብ ቢያራምዱ ለአገርም ለዕድገትም ጠቃሚ ነው፡፡ የተለያዩ አስተሳሰብ የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ግጭትም ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ ብሔር ብሔረሰቦችም ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰፊ አገር፣ የጋራ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም ቢኖራቸው በሁሉም መመዘኛ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡

‹‹ልዩነት ውበት ነው›› እያልን ለማጉላት መሞከር ሳይሆን፣ አንድነት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ጥቅም ለወጣቱ ትውልድ  ማስተማር በእጅጉ የሚበጅ ተግባር ነው፡፡

ልዩነት በባህል፣ በአስተሳሰብ፣ በፖለቲካና በአኗኗር በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ያለና ወደፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ልዩነትን ለማስተዋወቅ ወይም ለማጉላት መሥራት በፍፁም የለብንም፡፡

በማንኛውም ተግባር ላይ አንድ አባባል ሁሌ የሚደጋገም ከሆነ፣ በተለይ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች አብሮአቸው ስለሚያድግ የማይጠቅምን ነገር አጉልቶና ደጋግሞ ማስተጋባት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ ያለንን በጎ ነገር ነው ለማጉላት መሞከር ያለብን፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት፣ ለነፃነታችን የታገልን ሕዝቦች፣ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ የታገልን ሕዝቦች፣ ወዘተ እያልን በጎ በጎውን ብቻ እያየን መሄድ እንጂ፣ የማይጠቅም ነገር መናገሩ አስፈላጊ ስላልሆነ በዝምታ ማለፍ ተመራጭ ነው፡፡

እዚህ ላይ በኢሕአዴግ ፖለቲካ ውስጥ ስለብሔረሰብ ሲነሳ ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› ይልና ፓርላማ ውስጥ ደግሞ ልዩነት አስፈላጊ አይደለም ይለናል፡፡ ልዩነት ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሌም ያለና የሚኖር ሲሆን፣ ልዩነትን ችሎ ለመኖር ብቃትን ማዳበር እንጂ ልዩነትን ለማጉላት ተግቶ መሥራት በፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡

ሰሞኑን እያነበብነው ያለነው መጽሐፍ የሚያስገነዝበን በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ በኃይል የተፈጠረ አንድ አስተሳሰብ መኖሩን እንጂ፣ በተግባር ግን ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ አባላት ሁሉ የራሳቸው አስተሳሰብ እንዳላቸውና ደብቀው ጊዜ እየጠበቁ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ፈረንጆች አንድ አባባል አላቸው ‹‹The best friend is the worst enemy›› ይላሉ፡፡ በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ አንድ መንግሥት ተሳክቶለት አንድን አገር በአንድ አስተሳሰብ ብቻ ለመምራት ቢሞክርም፣ የሥርዓቱ አባላት በዚህ መልኩ የሥርዓቱ ገመናዎችን ማጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ማንኛውም መንግሥት ነገሮችን ደብቆ ለማስኬድ የማይቻልበት ዘመን በመሆኑ፣ ግልጽነት በምንም ሁኔታ በግንባር ቀደምነት የሚጠበቀው ከፍተኛ ኃላፊነት ከተሸከመው መንግሥት ነው፡፡

ሰዎች መደበኛ መንገድ አጥተው በተለይ በሚዲያና በፓርላማ የተለያዩ ሐሳቦችን ማንፀባረቅ ካልቻሉ ውጭ አገር ሄደው የሚያቀርቡት የልዩነት ሐሳብ የሚያስከትለው አደጋ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘበት ጊዜና የሚያራምደው አስተሳሰብ በፍፁም አብረው የማይሄዱ መሆኑን ተገንዝቦ ጊዜ ሳይጠፋ፣ በራሱ ላይ ከፍተኛ ተሃድሶ ማድረግ አለመቻሉ ለአገርም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች  አደጋው የከፋ መሆኑን መገንዘብ አለበት፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢሕአዴግ ውስጥ እየወጡ ወደ ውጭ አገር በመሄድ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እጅግ የሚያስደነግጡ መረጃዎችን የሚቀርቡበት አጋጣሚ እየተፈጠረ በመሆኑ፣ መንግሥት ዝምታን መምረጡን ትቶ በሕዝብ ውስጥ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች አደጋ ከመፍጠራቸው በፊት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ መታረም ያለበት ጉዳይም በአስቸኳይ መታረም አለበት፡፡ የድሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት እንኳን መጽሐፍ እስኪጻፍ ሳይጠብቁ ሕዝቦች ስለእኔ ምን ይላሉ እያሉ ሰዎችን በተለያዩ ቦታዎች በመላክ መረጃ ያሰባስቡ ነበር፡፡

አሁን በሠለጠነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ይህንን አለማድረግ በእጅጉ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ለከፍተኛ አደጋ የዳረጉ መንግሥታት በሕዝብ ዘንድ ስላለ አሳሳቢ ጉዳይ በቂ ትኩረት ወይም ምንም ትኩረት አለመስጠታቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን ወሳኝ ወቅት በአግባቡ ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ቀደምት የኢሕአዴግ አባላት ወይም ውስጥ አዋቂዎች የሚያቀርቡትን መረጃ መንግሥት በዝምታ ማለፉ የሚያስነሳው አቧራ አደገኛ በመሆኑ፣ በሕዝቦች ዘንድ የተለያዩ አረዳዶችን ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ አፋጣኝና ትርጉም ያለው ዕርምጃ ከኢሕአዴግ ይጠበቃል፡፡ ወይም ስህተቱን ያለ ምንም ማቅማማት ማረም ወይ ደግሞ አጥጋቢ መልስ መስጠት፡፡

 ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡