አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

መራመድ የተሳናት አፍዴራ

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከዓመታት በፊት ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ ችግሮችን አስከትሎ ነበር፡፡ ከቀይ ባህር ይገባ የነበረው የምግብ ጨው አቅርቦት በግጭቱ ምክንያት ተቋረጠ፡፡ አጋጣሚው አገሪቱ ያላት የጨው ማዕድን መለስ ተብሎ እንዲታይ ያደረገ ነበር፡፡

በሰሜናዊ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በአፋር ክልል በአፍዴራ ሐይቅና በዶቢ አካባቢ 292 ሚሊዮን ቶንና በዓመት 113,200 ቶን ጨው   የመስጠት አቅም ያለው የጨው ክምችት መኖሩ ታወቀ፡፡

የአገሪቱን የጨው ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለውጭ አገር ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ያለው የጨው ክምችት እዚሁ መገኘቱ ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ቢሆንም  የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማሟላት ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡ በዋናነትም መንገድ፡፡ ወደ ሐይቁ ለመድረስ ሰዓታት ይፈጅ የነበረውን ጉዞ መንገድ በመሥራት ችግሩን ለማቅለል ተሞክሯል፡፡ ይህ የአካባቢው ተወላጆችና ሌሎችም ኢንቨስተሮች በጨው ምርት ላይ እንዲሠሩ ያበረታታ ነበር፡፡

የአገሪቱ ወርኃዊ የጨው ፍጆታ ከ450,000 እስከ 500,000 ኩንታል ነው፡፡ አፍዴራ የአገሪቱን የጨው ፍጆታ ቀጥ አድርጎ የያዘ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ቦታው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት፣ ብዙ ሀብት ያለበት ቦታ እንደመሆኑ ዕድገቱ ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የተለየ ባይሆንም ቢያንስ ጥሩ የሚባል እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይሁንና ባለፈው ሳምንት በአፍዴራ ከተማ ተገኝተን የተመለከትነው ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነበር፡፡

ወደ ሐይቁ የሚወስደው ብቸኛ የአስፋልት መንገድ ግማሽ ላይ ደርሶ ያበቃል፡፡ ቀጥሎ ያለው የጠጠር መንገድ በመሆኑ እንደ ልብ መጓዝ አስቸጋሪ ነው፡፡ አቋራጭ መንገዶችን መጠቀምም የማይታሰብ ነው፡፡ ለዚያ ተብሎ የተዘጋጀ መንገድም የለም፡፡ አካባቢው አሸዋማ በመሆኑ ለመንቀሳቀስና መኪና ለመንዳት አያመችም፡፡

 ለዚህም መንገዶቹን ጠንቅቀው የሚያውቁ አሽከርካሪዎችን መከተል ግድ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ተሽከርካሪዎች በተንቀሳቀሱ ቁጥር  በአምስት ሜትር ርቀት ላይ ያለውን ሌላ መኪና ለማየት እስከሚያስቸግር ድረስ መንገዱ በአቧራ ይሞላል፡፡ አካባቢውም ሰዎች የሚኖሩበት አይመስልም፡፡

ጨው ወደሚመረትበት አፍዴራ ሐይቅ ሲቃረቡ አንድ መንደር ይገኛል፡፡ መንደሩ ጊዜያዊ በሚመስሉ ቤቶችና ዳሶች የተሞላ ነው፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች የተሠሩት ከላስቲክ፣ ከሳጠራና ከቆርቆሮ ነው፡፡ ነዋሪዎቹም የተለያዩ አልባሳትና ፈጣን ምግቦችን አብስለው የሚሸጡ ናቸው፡፡

ደንበኞች የሚስተናገዱት በየበረንዳው በተዘረጉ የጠፍር አልጋዎችና ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለው ነው፡፡ በአፍዴራ ሆቴል አልያም ደረጃውን የጠበቀ የሚባል ዓይነት ማደሪያ ማግኘት የማይታሰብም ነው፡፡ እዚያው መሰንበት ቢሹ መኝታዎ የሚሆነው ከአንደኛው በረንዳ የተዘረጋ የጠፍር አልጋ  ነው፡፡ አለዚያ ግን ፈጠን ብለው ጉዳይዎን ጨርሰው በጊዜ ወደ ሰመራ መመለስ ይኖርቦታል፡፡

 እንደዚህ እንደነገሩ ተደርገው የሚጣሉት ዳሶች በከፍተኛ ሁኔታ ለእሳት አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ የተሠሩት በሳጠራ በላስቲክና በመሳሰሉት በቀላሉ በእሳት ሊቀጣጠሉ በሚችሉ ነገሮች፤ እንዲሁም ነፋሻማ በመሆኑ እሳት ቢነሳ በቀላሉ ማጥፋት አይቻልም፡፡

አቶ መሐመድ (ስማቸው ተቀይሯል) እንደሚሉት፣ በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የእሳት አደጋ ተከስቶ ያውቃል፡፡ በአንድ ወቅት ተከስቶ በነበረ የእሳት አደጋ አንድ መንደር  ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፡፡ ብዙዎችም ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡ እስካሁን መንደሩን መልሶ ማቋቋምም አልተቻለም፡፡

‹‹ቤቶቹ ከሳጠራና ከቆርቆሮ የተሠሩ ናቸው፡፡ እሳት ከኩሽና ሲነሳ በነፋስ በአንዴ ይስፋፋል፡፡ ሰው ሲጋራ አጭሶ ፊልተሩን በሚጥልበት ጊዜ እንኳን እሳት ሊነሳ ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ ሦስት አራት ጊዜ የእሳት አደጋ ተከስቶ ብዙ ንብረትና ገንዘብ ወድሞብናል፤›› የሚሉት ሌላ የአካባቢው ተወላጅ አቶ ኑር ዓሊ ናቸው፡፡

በአካባቢው የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ ሠርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ያስቀምጡ የነበረው ቤታቸው ውስጥ ነበር፡፡ ድንገት የሚከሰተው የእሳት አደጋ ምንም ሳያስቀርላቸው ገንዘባቸውን ጭምር አመድ ያደርገዋል፡፡ ይህ የብዙዎቹ የአፍዴራ ነዋሪዎች ችግር እንደነበር ነገር ግን በቅርቡ በአካባቢው የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ በመጠኑም ቢሆን ነገሮች መሻሻላቸውን አቶ ኑር ይናገራሉ፡፡

ከፍተኛ የሆነ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርም መኖሩን የሚናገሩ አሉ፡፡ በአካባቢው በጨው ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች ፋብሪካ ለማንቀሳቀስ የሚረዳ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ በጀነሬተር እንደሚጠቀሙና ይህም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ የሚናገሩም አሉ፡፡ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወተው የጨውና የሌሎችም ማዕድናት መገኛዋ አፍዴራ በልማት ወደኋላ ቀርታለች፡፡

የወረዳዋ አስተዳዳሪ አቶ ሙሳ መሐመድ የወረዳዋን በልማት ወደ ኋላ መቅረት በተመለከተ ‹‹እስካሁን መልማት ያልቻለችው በምንም ሳይሆን በመልካም አስተዳደር ችግር ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን አንዳንድ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የወረዳዋ ነዋሪዎች የመጠጥ ውኃ የሚያገኙት 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ከምትገኘው ሎጊያ ከተማ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በ4.2 ሚሊዮን ብር ወጪ የውኃ ማጣሪያ ማሽን ተገዝቶ የነዋሪዎቹን የውኃ ችግር መቀነስ ተችሏል፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ሌሎችም የውኃ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በሌሎችም የመሠረተ ልማት አውታሮች ዙሪያም የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አቶ ሙሳ ተናግረዋል፡፡