መሬት ካልነኩ መሬት ነክ መብቶች በጥቂቱ

በውብሸት ሙላት

በበርካታ አገሮች፣ ለበርካታ ሕዝቦች ለምግብ ዋስትና፣ መጠለያ የማግኘት፣ በአጠቃላይ የልማትና የብልፅግና መሠረቱ  ሆነ መደላድሉ የመሬት መብትና የይዞታ ዋስትና  ናቸው፡፡ መሬት የማግኘት ዕድል በተነፈገበት ወይም በጠበበት ሁኔታ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ዋስትናቸው ይሳሳል፡፡ ሥጋት ይመጣባቸዋል፡፡

ከግጭት ወይም ከአብዮት ማግሥትም የመሬት ጉዳይ በብዙ አገሮች የፖለቲካ ማጠንጠኛ ነው፡፡ መሬት ማግኘት፣ ማከፋፈል እንዲሁም መሬት ጋር የተገናኙ መብቶች ዋስትና ማስከበር ለግጭቱ ወይም ለአብዮቱ መነሻ ለሆነው ጥያቄ እልባትና መፍትሔ በመሆን ያገለግላል፡፡ በኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም. እንደሆነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አካታችና ፍትሐዊ የመሬት መብት ማስፈን ለኢኮኖሚያዊ ብልፅግና፣ ዕድገትና ችጋርን ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

የመሬት ነገር፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህል ነክ የሆኑ መብቶችን ዕውን ለማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ኮሚቴ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ውስጥ ከመጠለያ፣ በግዳጅ ከመፈናቀል፣ ከምግብና ውኃ፣ ከጤና እንዲሁም ከባህል ነክ መብቶች ጋር በተያያዘ በርካታ መግለጫዎችን አውጥቷል፤ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፤ አስተያቶችን ሰጥቷል፡፡ ብዙዎቹ  ስለ ግለሰብ  ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ ነባር ሕዝቦችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም መሬትን የሚመለከቱ የግለሰብና የቡድን መብቶች እንዲሁም መንግሥት ስለብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው የእንደራሴነት ሥልጣን መሠረት ሲያስተዳድር እየተስተዋሉ ካሉት ችግሮች ውስጥ የተወሰኑትን ለመጠቆምና መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ማመላከት ነው፡፡

ዜጎችና መሬት ነክ መብቶቻቸው

አሁን ባለው የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት፣ ዜጎች የመሬት ባለቤትነት መብት የላቸውም፡፡ ባለቤትነት ወይም ባለንብረትነት ወይንም ባለሀብትነት ሦስት የመብት አላባውያኖችን ይይዛል፡፡ እነዚህም መሬቱን ራሱን በተለያየ መልኩ መጠቀም፣ ለአብነት መሬትን ለእርሻነት፣ ለከብት እርባታና ቤት ለመሥሪያ ወዘተ. ማድረግ ያካትታል፡፡ ሁለተኛው መሬት በተጨማሪነት ሊያስገኝ የሚችላቸውን ማናቸውንም ፍሬ (ለምሳሌ መሬትን በማከራየት፣ በወለድ አገድ በማስያዝ ገቢውን መጠቀም) የማገኘት፤ እንዲሁም በማናቸውም የማስተላለፊያ ሥልት ለሌላ ሰው ማሸጋገር ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት አላባውያን ካልተሟሉ ባለቤትነት የለም፡፡ ባለቤት እንዳይሆን የሚያደርገው ለሌላ ሰው፣ እንደሌላ ንብረት፣ ማስተላለፍ አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይም በሕገ መንግሥቱ ክልከላ የተደረገው በሽያጭም ይሁን በልዋጭ ማስተላለፍን ነው፡፡ እንደ ሕገ መንግሥቱ ከሆነ የገጠርም ይሁን የከተማ መሬት ቀጥታ በጥሬ ገንዘብም ይሁን የተወሰነ ቁራጭ መሬትን (ማሳ) በሌላ ንብረት (ለምሳሌ በቤት) መለወጥ አልተፈቀደም፡፡ ለነገሩየመሬት ባለቤትነት ሕዝብና መንግሥት ስለሆነ መሸጥና መለወጥ የሚችለው ባለቤቱ እንጂ፣ ግለሰቦች የሌላቸውን ንብረት የመሸጥ መብት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ማንም ሰው ባለቤት ያልሆነበትን ንብረት ሊሸጥ አይችልም፡፡ በሌላ አገላለጽ የሌለውን መብት ማስተላለፍ አይችልም፡፡ በመሆኑም መሬትን በተመለከተ የመሸጥና የመለወጥ መብት ያለው ባለቤቱ ማለትም መንግሥት ብቻ ነው ማለት ነው፡

ይሁን እንጂ በተለይም የከተማ ቦታን ግለሰቦች እንደ ግል ንብረታቸው ባለቤት እንደሆኑበት ሁሉ፣ እንደሚሸጡትና እንደሚለውጡት ማንም ሰው ያውቃል፡፡ ልዩነት ያለው የሚሸጥበት ሁኔታ ነው፡፡ ሌሎች ንብረቶች በግልጽ በአደባባይ ለገበያ ሲቀርቡ፣ ሕንፃ የሌለው ባዶ መሬት ግን ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ ሒደቶች ወይንም ውሎች ይኖሩታል፣ ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህም የብድር ውልና ውክልና ናቸው፡፡ ባዶ መሬት ወይንም በሽያጭ ለመተላለፍ የማይችል ቤት ያለው ሰው አስቀድሞ የሚያደርገው ከመሬቱ ዋጋ ከፍ ያለ ገንዘብ ከገዥው እንደተበደረ በማድረግ የብድር ውል መፈራረም ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተሸጠው ቦታ ላይ ገዥው  ሕንፃ እንዲገነባበት፣ እንዲያስተደዳድረው፣ እንዲሸጠውና በማናቸውም መልኩ እንዲለውጠው ውክልና ይሰጠዋል፡፡ ገዥው መሬቱ ላይ ሕንፃ ከገነባ በኋላ፣ ሻጩ የተበደረውን መክፈል እንዳልቻለ ይወሰድና ለብድሩ ማቻቻያ ሕንፃውን ያስተላልፋል፡፡ ብድሩ ይሰረዛል፡፡ ውክልናው ይወርዳል፡፡ በዚህ መሠረት መሬት ይሸጣል፡፡

ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ መሬትን ግለሰቦች መሸጥ እንደማይችሉ ቢገልጽም ፍቃድ ማውጣት የማይጠበቅባቸው የመሬት ነጋዴዎች ወይም ደላሎች ንግዱን እንደሚያጧጡፉት አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ሰፋ ያለ የከተማ ቦታ የነበራቸውና ያላቸው ግለሰቦችም እንዲሁ ተጠቅመውበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥቱ ምንም ይደንግግ ምን፣ መሬትን ከሸቀጥነት አልታደገውም፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ የዝሆን ጆሮ እንደሰጠው ነው፡፡

ከመሬት ንግድ ጋር የተያያዘው ሌላው ጉዳይ፣ የመንግሥት የመሬት ከበርቴነት ጉዳይ ነው፡፡ መሬትን በባለቤትነት የማስተዳደር ሥልጣን ያለው መንግሥት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መሬትን በአነስተኛ ዋጋ ለባለሀብት በማቅረብ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የሕዝብን ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ አሁን ላለው የመሬት ሥሪት ምክንያት ስለመሆኑ መንግሥት በተደጋጋሚ መናገሩ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የከተማ መሬት የሊዝ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናሩ ከታሰበለት ዓላማ በተፃራሪነት መቆሙ ግልጽ ነው፡፡ እንደውም ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ የነበሩት፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ይህንኑ ጉዳይ በቴሌቪዥን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት በገፍ ባለቤት የሆነበትን መሬት ለገበያ በማቅረብ ከበርቴነቱን እየተጠቀመበት ነው፡፡ አንድ የመሬት ከበርቴ ከሚያደርገው ነገር ያልተናነሰ ወይንም ተመሳሳይ ድርጊት መንግሥትም  እያደረገ ነው፡፡ ከፍተኛ ገቢም እየሰበሰበ ነው፡፡ ዓላማው ግን መሬትን በዝቅተኛ ዋጋ ለባለሀብቱ በማቅረብ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

እዚህ ላይ አንድ መታወስ ያለበት ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም በሕዝብ የመሬት ባለቤትነት (Public Ownership) እና መንግሥት ባለቤትነት (State Ownership) መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ ሕዝብ ባለቤት የሆነባቸው ንብረቶች በባህሪያቸው የጋራ ናቸው፡፡ ማንም ሰው ይጠቀምባቸዋል፡፡ የሚሸጡ ወይንም የሚለወጡ አይደሉም፡፡ በአስረጅነት መንገዶችን፣ ፓርኮችን፣ የገበያ ቦታዎችን፣ ስቴድየሞችን መውሰድ ይቻላል፡፡ ባለቤትነቱ የመንግሥት ከሆነ ግን በብዙ መልኩ ከግል ንብረት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ግለሰብ በንብረቱ ላይ የሚኖረው መብት ይኖረዋል፡፡ መሬት የመንግሥት ነው ሲባል ሌሎች ንብረቶች ላይ ከሚኖረው የባለቤትነት መብት ብዙም አይለይም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ያለው የመሬት ባለቤትነት የመንግሥት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው የመሬት ሕግ አንዱ ግቡ ዜጎች በመሬቱ ላይ የይዞታ ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በከተማ ቦታ ላይ የመንግሥት ሚናና ጣልቃ ገብነት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎች ሊጠይቁ የሚችሉት ተመጣጣኝ ካሳና ምትክ መሬት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ስለዋስትና ማንሳት ብዙም አይጠቅምም፡፡ የገጠር መሬትም ቢሆን ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ ከከተማው የሚለየው፣ የገጠርን መሬት ባለይዞታዎቹ ማውረስ የሚችሉት ቋሚ መተዳደሪያ (ብዙዎቹ ክልሎች) ለሌላቸው ወራሾች በመሆኑ ቋሚ ንብረቶች፣ የተሻሉ ቤቶችን ለመገንባት አያበረታታም፡፡

የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትም ቢሆን የሚጠቅመው ገበሬው ያለውን መሬት ለይቶ ከማመልከት ባሻገር መንግሥት ለሌላ ዓላማ እንዳይወስድ የሚከለክል አይደለም፡፡ የምስክር ወረቀት ለገበሬ ማደሉ የዛሬ 120 ዓመታት ገደማ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ የጎጃምን ሕዝብ ታሪክ ከጻፉበት አመክንዮ ብዙ ፎቀቅ አላለም፡፡ እሳቸው በወቅቱ የነበረው የመሬት ክርክር እጅግ ስላሳሰባቸው ማን የማን ልጅ (ትውልድ) እንደሆነ ሰፊ ጥናት አደረጉ፡፡ መሬት የግል ስለነበርና በውርስ ስለሚተላለፍ ዝርያቸውን በትክክል ለዳኛ ማስረዳት ያልቻሉ ወይም ማስረጃ ማቅረብ ያልቻሉት ሁሉ  ከእርስት መነቀላቸው ስላሳሰባቸው የጎጃምን ትውልድ ዘረዘሩ፡፡ መነሻቸው፣ ክርክር ሲነሳ ግለሰቦች በማስረጃ እጦት፣ በሐሰተኛ ምስክር አላግባብ እርስት አልባ እንዳይሆኑ ነው፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ፣ ለገበሬው የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ዕደላ ዋና ዓላማው የትኛው ማሳ የማን እንደሆነ ለመለየት ነው፡፡ ይኼም ቢሆን፣ የግለሰቦችን ማሳ ለመለየት እንደ ጥንቱ የቦታዎችንና የአዋሳኝ ባለይዞታዎችን ስም እንጂ በዘመናዊ መልኩ በጂፒኤስ የተዘጋጀ ስላልሆነ የይዞታ መደራረብን ብሎም ጭቅጭቅን በታሰበው መጠን መቅረፍ እንዳልቻለ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት ለባለይዞታዎች ከማስረጃነት በዘለለ ዋስትና የሚሰጥ ባለመሆኑ፣ በተለይም ፖለቲካዊ አመኔታን ከገበሬው መሸመቻ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም የሚሉም አሉ፡፡

ለአሁኑ የመሬት ሥሪት ከፍተኛ ተግዳሮት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የመሬት ክርክር ጉዳይ ነው ብለናል፡፡ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለፌደሬሽን ምክር ቤት በርካታ ጉዳዮች መቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ላይ በቅርብ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ ሌሎቹ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የላቸውም ተብለው ውድቅ ተደርገዋል፡፡ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከቀረቡት አጠቃላይ አቤቱታዎች ውስጥ እጅግ በጣም በርካታዎቹ መሬትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ውድቅ ቢደረጉም፡፡ በገጠር አካባቢ ያሉ ፍርድ ቤቶችም ከሁሉም ጉዳይ በሚበልጥ መልኩ እያስተናገዱ ያሉት የመሬት ክርክሮችን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የመሬት ሥሪቱም ይሁን አስተዳደሩ ወይም ሌላ ምክንያትም ካለው ድጋሜ ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ቀድሞ ስለመሬት ከነበረው የፍርድ ቤት ክርክሮች ብዛት አንፃር መብዛቱ ጤናማ ነው የሚባል አይደለም፡፡

መሬት ለኢንቨስትመንት መዋሉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን ሥራ ላይ በማዋል ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ብሎም ልማትን በማፋጠን የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማሻሻል ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን መብች ለማሟላት እንዲችል ግብዓት ሊሆኑት እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ክልሎች ከተሰጡት ሰፋፊ የእርሻ መሬት ሁኔታ ስኬቱን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ጥርጣሬውን ከሚያጠናክሩ ማስረጃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ሰፋፊ መሬት የወሰዱት ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን ወይም ቃል በገቡት መጠን የሥራ ዕድል አለመፍጠራቸው፣ የውጭ ምንዛሪ አለማስገኘታቸው፣ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ደካማነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የብድር ምንጫው ከአገር ውስጥ መሆኑ ሳያንስ ያገኙትንም ብድር ለሌላ ተግባር እያዋሉት መሆኑን መንግሥት ራሱ እማኝነቱን፣ ቢያንስ ጋምቤላን በተመለከተ በጥናት አስደግፎ ሰጥቷል፡፡

መሬት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ንብረት

ታሪካችን እንደሚያሳየን የመሬት ነገር ከግለሰብ መብትም ያለፈ አንድምታ አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሬትን በተመለከተ በአንቀጽ 40(3)  ላይ የሚከተለው ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፤” ይላል፡፡ በአንቀጽ 51(5) ደግሞ የፌዴራል መንግሥት “የመሬት የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤” ይላል፡፡ በአንቀጽ 89(5)  ደግሞ “መንግሥት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን በሕዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና ዕድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፤” ይላል፡፡ በመሆኑም የመሬትና የብሔሮች ግንኙነት ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ  እንግዲህ ማንነትን ከሚመለከተው ጉዳይ ውጭ ነው፡፡

የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብትም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ዘርፍም አለው፡፡ ፖለቲካዊው ብቻውን ዳቦ አይሆንም፡፡ ፖለቲካዊ ነፃነት በኢኮኖሚያዊ ነፃነት መታገዝ አለበት፡፡ ለዚያም ነው በአንድ ወቅት የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጁሌስ ኔሬሬ፣ አሩሻ ላይ የካቲት እ.ኤ.አ. 1979 “አፍሪካውያን መጻኢ ዕድላችንን የመወሰን ነፃነት እንደሌለን፣ በኢኮኖሚ ገና ከጥገኝነት እንዳልወጣን፣ በከፊልም ገና ከቅኝ ግዛት ያልተላቀቅንና ሉዓላዊ ነን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም፤” በማለት ምሬት በተሞላበት አኳኋን የገለጹት፡፡

ከላይ የቀረበው ሐሳብ ለክልሎችም በትክክል ይሠራል፡፡ በኢኮኖሚ ራሳቸውን የማይችሉ ክልሎች ከሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ውኃ እንደሚበላው ሃቅ ነው፡፡ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕቅዶችን ለማቀድም ሆነ ለማከናወንም በኢኮኖሚ ራስን መቻል ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በፌደራሉ መንግሥት ላይ ጥገኛ ሆኖ በሙሉ ነፃነት ራስን ማስተዳደር የሚቻልም አይደለም፤ የሚታሰብም አይሆንም፡፡

የራስን ዕድል በራስ መወሰን ኢኮኖሚያዊ ገጽታው የመልማት መብትና የተፈጥሮ ሀብትን በነፃነት ለሚፈልጉት አገልግሎት ማዋልን ይይዛል፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲሆንም በተገዥዎች ላይ ተፈጽሞ የነበረው አንዱ ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጥሮ ሀብትን መበዝበዝ ስለነበር፤ ይህ የብዝበዛ አድራጎት በድጋሜ እንዳይከሰት፣ ይልቁንም በተፈጥሮ ሀብታቸው የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ ነበር፡፡

በኢኮኖሚ የመበልፀግና የመልማት መብትና የተፈጥሮ ሀብትን ያላንዳች ጫናና ጣልቃ ገብነት መጠቀምን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ጀምሮ፣ በየአኅጉራቱና በየአገሮቹ ብዙ ሕጎች አሉ፡፡ የሁሉም ይዘት ተመሳሳይና ተቀራራቢ ነው፡፡ በቅኝ ግዛትና በወረራ የሌሎች ሕዝቦችን የተፈጥሮ ሀብት መበዝበዝን ዓለማቀፍ ሕጉ ይከለክላል፡፡ የማይዳፈሩት፣ የማይናወጥና የማይቀየር አንዱ የሉዓላዊነት መገለጫም  ጭምር ነው፡፡ ልማት፣ የሰብዓዊ መብት አንዱ አካል መሆኑም እርግጥ ሆኗል፡፡ ለልማት ደግሞ ወሳኝ ከሆኑት ግብዓቶች አንዱ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለሕዝቡ እንዲጠቅም ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ የሕዝቡን የመልማት መብት ዕውን ለማድረግ ወይንም በራሱ መወሰኑን ለማረጋገጥ ምቹ ሕግና ፖሊሲ ማውጣት፣ እነዚህም ሲወጡ ሕዝቡን የማሳተፍና ለውሳኔ የሚሆን ሐሳብ የማበርከት መብትንም ያካትታል፡፡ ሕገ መንግሥታችንም የሰጠው ጥበቃና ዕውቅና ብዙም (ከመሬት የባለቤትነት በስተቀር) እንከን ወይም አጨቃጫቂ የሆነ ጉዳይ ባይኖርበትም ፖሊሲዎቹና አፈጻጸማቸው ላይ ግን ብዙ አጠያያቂ ጉዳዮች በመኖራቸው ከውጭና ከአገር ውስጥ ምሁራን የሰሉ ትችቶች በተጨማሪም የሕዝብም ቅሬታ መኖሩ ይስተዋላል፡፡ ትችቶቹ በዋናነት የሚያጠነጥኑት የመሬት ባልተቤትንና የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተና በልማት ጉዳዮች ላይ ቀድሞ ሕዝብን ያለማማከርና ያለማወያየት ላይ ነው፡፡

የተሳትፎ መብት ሲባል. . .

          የዚህን መብት ይዘት ስናይ ደግሞ ዜጎች በመንግሥታዊ ጉዳዮች ማለትም የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ፣ ሕግና ፖሊሲዎችን በማውጣት ረገድ፣ በሕዝባዊ ውይይትና ክርክር በጽሑፍም ይሁን በቃል፣ በራሳቸውም ወይም በወኪላቸው በኩል መሳተፍን ይይዛል፡፡ መንግሥትም እነዚህን ሁኔታዎች የሚያሳልጥ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣትና ሌሎች ሥልቶችን የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡ የማሳተፊያ ሥልቱን በተመለከተ አንድ ወጥ መንገድ ባለመኖሩና የአገሮች ቴክኖሎጂያዊ አቅም ጋር ስለሚያያዝ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ የሚሄድ እንጂ በአንድ ቅጽበት የሚሟላ አይደለም፤ በሌላ አገላለጽ “ፕሮግራማቲክ” ነው፡፡

በንጉሣዊውና በደርግ ዘመን እጅግ የተማከለ አስተዳደር ስለነበርና አሁን ደግሞ ኢሕአዴግ እጅግ በተማከለ የፓርቲ ሥርዓትና ዲስፕሊን ስለሚመራ (ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በፓርቲ ደረጃ ስላሰፈነ)፣ የሕግም ይሁን የፖሊሲ ውሳኔዎች በመጀመሪያ በፓርቲ ደረጃ ተወሥነው ከዚያ ወደ መንግሥት ስለሚዞሩ ያው በተግባር የተማከለ አስተዳደር ነው ያለው፡፡ ከሥር ወደ ላይ እንዳይመጣ ፓርቲያዊ አሠራሩ አይፈቅድም፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ ቅርፅ የሚፈቅደው የፓርቲውን አሠራር የተገላቢጦሹን ነው፡፡ በተግባር ግን የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን አካላት በእኩልነት ማሳተፍ አዳጋች በመሆኑ፣ የተሳታፊው ቁጥር በዛ ብሎ ወደ አንዱ ካጋደለ የሚፈጠረውም ተፅዕኖ ስለሚለያይ፣ ቁጥሩ ወደበዛበት አቅጣጫ ማጋደሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር የሌላውን ጥቅም መደፍጠጡ አይቀሬ ነው፡፡

ሉዓላዊዎቹ የሥልጣን ባለቤቶች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመሆናቸው የፓርቲው ማዕከላዊነት ቅርቃር ባይሆንባቸው ኖሮ ሕገ መንግሥቱ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ያሻቸውን የመወሰን፤ የፌዴራሉም መንግሥት ቢሆን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የሚመለከታቸውን ማናቸውንም ጉዳይ በጥልቅ የመወያየትና የመወሰን የማይነካ፣ ከሉዓላዊነታቸው የሚመነጭ፣ ሥልጣንም መብትም አላቸው፡፡ እንኳንስ ያልተሳተፉበትና እነሱ ላይ ተፅዕኖ የሚኖረው ሕግና ፖሊሲ ወጥቶ አስቀይሟቸው ቀርቶ፣ ባሻቸው ጊዜና ምንም ምክንያት ሳያስፈልጋቸው፣ ኢትዮጵያን “ቻው” ብለው የመሄድ መብት እንዳላቸው ሕገ መንግሥታዊ ደንብ ሆኗል፡፡

ምናልባት ከኢሕአዴግ ውጪ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ አንድ ክልልን በማሸነፍ ማስተዳደር ቢጀምር የፌዴራሉ መንግሥት በዚያ ክልል ላይ ተፅዕኖ የሚኖራቸውን ፖሊሲዎችና ሕጎች ሲወጡ ያኔ የምር ማወያየቱንና ማሳተፉን እንታዘብ ይሆናል፡፡  ካልሆነ ግን ጥሩ ሕገ መንግሥታዊ ማስፈራሪያ (መገንጠል) አለና! ወይም ቆስቋሽ ምክንያት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው አለማሳተፍ ባይታወርነትን ያመጣል፤ ማዕከላዊ መንግሥቱ አንድን ክልል ወይም ብሔር ባይታወር የሚያደርገው ከሆነ ክልሉ ወይንም ብሔሩ “ለጥሬ ጥሬ ምናለኝ ዱሬ” እንዳለው ገበሬ “ለባይታወርነት ለባይታወርነትማ ለምን ብቻዬን አልኖርም፤” በማለት መገንጠልን ሊመርጥ ይችላል፡፡

ሌላው ስለተሳትፎ ሲነሳ ፈጽሞ መታለፍ የሌለበት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ  50(4) እንዲህ ይነበባል፡፡ “ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኟቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ፡፡ ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቀተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ “ይህ አስገዳጅ መሥፈርት ነው፡፡ በታችኞቹ እርከኖች ላይ በውክልና ሳይሆን በቀጥታ ማሳተፍና ለእነዚህ እርከኖች በቂ ሥልጣን መስጠት ግድ ነው፡፡ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሥልጣን ምንጩ ከላይ የሚመጣ ትዕዛዝ አይደለም፡፡ ከሕዝቡ ከራሱ የሚመነጭ እንጂ! ከሌላ አካል በአስገዳጅነት የሚመጣ ከሆነ ሥልጣን አይሆንም፡፡

ሕዝቡ በወኪሎቹ በኩል መሳተፍን በተመለከተ፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉት ሁሉ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተወካዮች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በእርግጥ ይህን ያህል ወኪል ሕዝብን ከማሳተፍ አንፃር ጥሩ ነው፡፡ ችግሩ ይህ ሁሉ (ወደ መቶ በመቶ በተጠጋ መልኩ) የአንድ ፓርቲ አባል በመሆናቸውና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ ከላይ የሚወርድን አጀንዳና ትዕዛዝ ብቻ አንፀባራቂ መሆናቸው ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ተሳትፎ ውስጥ የሐሳብ ብዝኃነት ድርቅ መኖሩ ዕሙን ነው፡፡

በየክልሉ የሚገኑ ሰፋፊ መሬቶች ለባለሀብቶች የተሰጠበት ሒደት በእርግጥ ሕዝቡ ተሳትፎ በማድረግ፣ ጥቅምና ጉዳቱን አስቀድሞ ተረድቶት ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ በመሆኑም ትኩረት የሚፈለግ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በተሻለ ነፃነት ለማስተዳደር የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተፈጥሮ ሀብትና በመሬት ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከላይ የተገለጹት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ማለትም አንቀጽ 40 (3)፣ 51 (5) እና 89 (5) የምንረዳው ግን እነዚህ ሀብቶች የመንግሥት፣ የሕዝብና የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት መሆናቸውን፣ ሕግ የሚያወጣው ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት መሆኑን፣ አስተዳዳሪውም ያው መንግሥት (እንደነገሩ ሁኔታ የፌዴራልም የክልልንም መንግሥት ይጨምራል) መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የብሔረሰቦችን መብት ማጫጫታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገሩን እንደሚከተለው በምሳሌ እንየው፡፡

መሬትና የተፈጥሮ ሀብትና የመላው ሕዝብ የጋራ ንብረት ከሆነ አንድ ብሔር እንዳሻው ሊያዝበት አይችልም ማለት ነው፡፡ በአፋር ያለውን ሁኔታ እንውሰድ፡፡ መሬት የመንግሥት እንደሆነ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በአፋር የባህል ሕግ ግን መሬት የጎሳ ነው፡፡ ባለቤቱም አስተዳዳሪውም ጎሳው ነው፡፡ አፋር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን የማይገደብ መብት ካለው፣ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ይችላል ከተባለ ከመሬቱ ተነጥሎ፣ የመሬት ሥሪቱን አብዮታዊ በሆነ መልኩ ቀይሮ ለፌዴራል መንግሥት አስረክቦ፣ የፌዴራል መንግሥቱ በሚያወጣው ሕግ መሠረት ብቻ እያስተዳደረ ከባለቤትነት ወደ ባለይዞታነት ዝቅ ብሎ እንደ ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት አለው ማለት ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ ከተፈጥሮ ሀብትና መሬት አጠቃቀም አንፃር ከፌዴራሉ ይልቅ የክልሎች ሥልጣን (የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት) መብለጥ ቢኖርበትም የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ በመሆኑም ከጥንቱ ግለሰባዊ የባላባትና የጭሰኝነት ሥርዓት ወደ መንግሥታዊ (ፓርቲ) ጭሰኝነት የተቀየረ ይመስላል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ወይም ምጣኔ ሀብታዊ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሲነሳ በቀጥታ የሚቆራኘው የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠቀም ጋር በመሆኑና የተፈጥሮ ሀብት ደግሞ ከመሬት ተለያይቶ ስለማይሆን የመሬት ባለቤትንና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ከብሔር ጋር በማያያዝ የሚኖረውን አንድምታ፤ በተለይም ደግሞ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውን መንከባከብና ማሳደግ ከልማት ጋር ያለውን ግንኙነትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን በሌላ ጊዜ እንመለስባቸዋለን፡፡

 

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡