አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

መንግሥት ለሕብር ስኳር አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገለት ነው

በአገራችን በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሳቢያ በርካታ የአገር ውስጥና ውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን አፍሰው ለበርካታ ዜጎቻችን የሥራ ዕድል አስገኝተዋል፡፡ የአገራችን የውጭ ምንዛሪና የአገር ውስጥ ገቢም በእጅጉ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ የሚገኘውም ገቢ መንግሥት አስፈላጊ በሆኑ የላቀ ጠቀሜታ ያላቸው የልማት ዘርፎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲያካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበርም በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በመጠቀም ከ6000 በላይ ዜጎችን በማሰባሰብ መንግሥታችን የሚያደርገውን የልማት ጥረት ለማገዝና የግል ስኳር አክሲዮን ማኅበር በማቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በሕጋዊ መንገድ ተደራጅቶ በአማራ ብሔራዊ ክልል በአዊ ዞን፣ ጃዊ ወረዳና ደቡብ አቸፈር ወረዳ በበለስ ተፋሰስ ውስጥ 6183 ሔክታር መሬት ለ40 ዓመታት በሊዝ ወስዶ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለአክሲዮን ማኅበራችን ያለ አንዳች ውጣ ውረድ ለምና ድንግል መሬት በኢንቨስትመንት ከመስጠት ጀምሮ አክሲዮን ማኅበሩን በተለያዩ ጉዳዮች ለመደገፍ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት ከፍተኛ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አክሲዮን ማኅበሩን እንዲደግፍ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አስፈላጊው ድጋፎች ተደርገውለት አክሲዮን ማኅበራችን በአሁኑ ወቅት አስሮት ከያዘው ችግር ተላቆ ብሩህ ተስፋ በመሰነቅ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ከሚችልበት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላደረገልን ከፍተኛ ድጋፍ በመላ የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት ስም ላቅ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

የስኳር ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ካፒታል ስለሚጠይቅና ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ የአክሲዮን ማኅበሩም ዋነኛ ችግር የፋይናንስ አቅም ውስን መሆኑ ሲሆን፣ አሁን ያለው የአክሲዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ ይኼንኑ ችግር በመገንዘብ እጅና ጓንት ሆነው በሰከነና ብልሃት በተሞላበት አኳኋን ችግሩን ለመቅረፍና አክሲዮን ማኅበሩን ወደ ሥራ ለማስገባት ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ያለበትን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የፋብሪካ ግንባታ ውል ተዋውለን ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል ብድር ከተለያዩ የውጭ አገር አበዳሪዎች ለማፈላለግ በሜቴክ በኩል ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ብድሮች ቢገኙም፣ የውጭ አበዳሪዎች ኮሜርሻል ጋራንቲ ወይም ሶቪሪን ጋራንቲ ስለሚጠይቁ የተደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አስፈላጊውን ብድር ለመስጠት ይሁንታ ቢሰጡንም፣ ብድሩን ለመልቀቅ ግን ተቋማቱ የ25 በመቶ ኢኩቲ ወይም የአክሲዮን ማኅበሩ መዋጮን እንደቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡ ከአክሲዮን ማኅበሩ የፋይናንስ አቅም አንፃር ይህ ስለማይቻል፣ የፕሮጀክት ስፋቱን ዝቅ አድርጎ በመጀመር ወደፊት ቀስ በቀስ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመምከር በዚህ አግባብ ስትራቴጂ ተነድፎና አማራጭ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር የራሳቸውን መዋጮ በማድረግ (ኢኩቲ ሼር) የሚሠሩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ለማፈላለግ ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገው በርካታ የአገር ውስጥ ድርጅቶችና ግለሰቦች አወንታዊ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መንግሥት ሕብር ስኳርን እንዲደግፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ከአክሲዮን ማኅበሩ ለቀረበው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ አክሲዮን ማኅበሩን ባጋጠሙት ችግሮች ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱም ችግሮቹ እንዲፈቱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር በተከታታይ ውይይቶች ተካሂደው ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮችን ለማግኘት ተችሏል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የቀረቡት አማራጮች አክሲዮን ማኅበሩ አሁን ካለው የፋይናንስ አቅም ጋር ተገናዝበው ወደ መሬት ይወርዱ ዘንድ ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከአክሲዮን ማኅበሩ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በመሆኑም ጥገና በማካሄድ ለውሳኔ የሚረዳ ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ተቀባይነት በማግኘቱ ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

ስለዚህ መላው የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት እስካሁን እንደታገሳችሁት ሁሉ ጠቅላላ ጉባዔው በቅርብ ጊዜ ተጠርቶ አሁን የተጀመሩት ሥራዎች ወደ መሬት ወርደው አክሲዮን ማኅበሩ ሰንቆ የተነሳው ዓላማ እንዲሳካ የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ አብረን እንጠይቃለን፡፡

ተባብረን ከሠራን በእርግጠኝነት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ዓላማችንን በማሳካት ለአገራችን ልማት የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ አበርክተን ለወገኖቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡

(ከሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር አስተዳደር)