አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ሚዲያ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ዓብይ ጉድለት

በገነት ዓለሙ

ያለፉት 25 ዓመታት የአገራችን መሠረታዊ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጉዳያችን ዋነኛ ጥያቄና ጭብጥ ከቀድሞው መንግሥት ከደርግ ሥርዓት ‹‹የበለጠ››፣ ‹‹የተሻለ›› ሠርቻለሁ ከማለትና ቁጥር ከማስላት ከፍ ያለ፣ ከዚህ አሮጌ ቀፎ የወጣ መሆኑንና መሆን እንዳለብን ዛሬም ገና በቅጡ አልገባንም፡፡ በኢትዮጵያ ለዘመናት፣ በንጉሡ ዘመንም ከንጉሡ በኋላም የተካሄዱት ትግሎች ዓላማና ግብ ትግልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋትና ማስወገድ ሳይሆን፣ ለትግል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ‹‹የጨዋታ ሕግ›› ማቋቋም ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ አየር ጠርቶና ፈክቶ፣ ትግሉ ወደሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ‹‹ግብግብ›› እንዲለወጥና እንዲሸጋገር ማድረግ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄያችንም ይህንን አድርገናል ወይ? የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ናት፡፡ ልዩነታችንና ወይም ዥንጉርጉርነታችን ወይም ብዝኋንነታችን ግን በዚህ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥም፣ ከዚህ ውጪም የሆኑ በአመዛኙ በኑሮ ጥቅም (መደብ) በመገናኘታቸውና በመለያየታቸው ልክ የሚወሰኑ የአመለካከትና የፍላጎት ልዩ ልዩነቶች አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ሰፊና መሠረታዊ ተመሳሳይ ውስጥም ልዩነት ይኖራል፡፡ ይህ ልዩነት የሚመነጨው በጋራ መደባቸው ውስጥ ባሉ የጥቅም ሰፊ ልዩነቶች ነው፡፡ ጥሩና ወቅታዊው ምሳሌ በአሜሪካ የሪፐብሊካንና የዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በአመለካከትም በፖሊሲም መሠረታዊ ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ተመሳሳይነታቸው ሁለቱም አንድ ሰፊ የኑሮ ጥቅምን ወይም መደብን የሚወክሉ ከመሆናቸው ይመነጫል፡፡ ሁለቱም የከበርቴ መደብ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሠረታዊ ተመሳሳይነት ውስጥ ያላቸው ልዩነት ደግሞ በጋራ መደባቸው ውስጥ ያሉ የጥቅም ሠፈር ልዩነቶች ነፀብራቅ ነው፡፡

ሰዎች እነዚህን ልዩነቶች በተለይም የኑሮ ጥቅም ልዩነቶችን መነሻ አድርገው፣ በኑሮ ጥቅማቸው ላይ በመገናኘታቸው ልክ የሚወሰን መሰባሰብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ለፍላጎቶቻቸውና ለዓላማዎቻቸው ዓርማ አበጅተው፣ የፖለቲካ ቀለም ቀብተውና ስም አውጥተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና ስብስቦሽ እየሰፋና እየፋፋ በሚሄድበት አገር ንጠቱና በየፈርጁ መዘርዘሩ፣ መሰል ከመሰል የመፈላለጉ ሒደት እየቀጠለ እየሰላ እየተባ ይሄዳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለ25 ዓመት አሁንም ከ25 ዓመት በኋላ የሚነሳው ጥያቄና የጎደለን ችግር ይኼኛው ነው፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ስብስቦሽና መስተንግዶ መፍቀድ አለመቻላችን ነው፡፡ የትኛውም ዓይነት ጥያቄ፣ ብሶት፣ ቅሬታ፣ ጠብ በውይይት በክርክር በድርድር ወይም በሌላ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ይፈታል ብለን ሥርዓቱን አለመገንባታችን ነው፡፡ የፖለቲካ ጠብም ሆነ የሕዝብ ቅሬት ወደ ጠብመንጃ የሚሄድበትን ዕድል ማጥበብና መዝጋት አለመቻላችን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ከስም ጌጡ ይልቅ እስትንፋሱ ያደረገ የሥርዓት ግንባታ ውስጥ አለመግባታችን ነው፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት ብዙ ተሠርቷል፣ ብዙ ተደክሟል፡፡ ድካሞችና ሥራዎች ሁሉ ግን የምሬትና የቅሬታ መፍለቂያ የሆኑ የፖለቲካ ብልሽቶችን ከማስወገድ ጋር አልተግባቡም፣ አብረው አልተጓዙም፡፡ ያለፉትን ሃያ አምስት ዓመታት ልፋትና ሥራ መና ያስቀረው ደግሞ ከሁሉም በላይ ሕዝብ ፍላጎቱንና ብሶቱን በይፋ ለመናገር፣ በደልን ለመጋተርና መብቱን ለማስከበር የማይፈራበት የነፃነት አየርን ሳያካትት መቅረቱ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃንን አሁን ላሉበት አሳዛኝ ፍረጃ የዳረገው ይኼው ጎዶሏችን ነው፡፡

ለኢሕአዴግ መንግሥት የሚዲያውን ሚና መናገር ባልተካሄደ ጉዳይ ላይ ማስረጃ መቁጠርና መደርደር ይሆናል፡፡ የኢሕአዴግን መንግሥት ለክርክር የማይመች ተሟጋችና ‹‹ባላጋራ›› የሚያደርገውም ይኸው ባህሪው ነው፡፡ ኢሕአዴግ በአደባባይ ‹‹ክቡር አቶ እሺ›› ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ የመሠረታዊ መብቶችን ነፃነቶች ድንጋጌዎች ሐሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነፃነትን አካትተዋል፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የሚተረጎሙት ከዓለም አቀፋዊ የመሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ዓለም አቀፋዊ ስምምነታችን ድንጋጌዎች ፈራሚ ናት፡፡ ድኅረ 2015 የአዛላቂ ልማት ስምምነት ዋነኛ መለያና ከሚሊኒየሙ የልማት ግቡ የተለየና የላቀ የሚያደርገው አንዱ ባህሪይ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የልማት እንቅስቃሴ አካልና ቅድመ ሁኔት ማድረጉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢሕአዴግ መንግሥት ሠልፍ ያማረ ነው፡፡ ኢሕአዴግን ‹‹እሺ›› ያደረገውም ይኸው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ተግባራዊና የጓዳ ፖሊሲ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የሚዲያውን ሚና አያውቅም፣ አያከብርም፡፡ ለነፃ ፕሬስቱ ሚዲያ አይታመንም፡፡ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ብሶት መዝጋቢና አስተጋቢ፣ የእውነት ማጣሪያና የጭብጦች ማብላያ የመሆናቸውን ሚና በተግባር አይቀበልም፡፡ የመንግሥትን ሚዲያ በጌታው ፊት የሚፎክርና የሚዘምር፣ እሸለም ባይ፣ ጌታውን ሰማይ እያወጣ ‹‹ውዳሴና ምሥጋና ጌትነትና ክብር›› የአንተ ነው እያለ የሚሰግድ፣ የጌታውን ተቀናቃኝ ትንኝ አሳክሎ ኩስ የነካው እንጨት አድርጎ የሚያዋርደው ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በአንድ ፓርቲና በመስመሩ የማመንና የመመራት ጉዳይ ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ አልሠራ ያለው በዚህ የኢሕአዴግ የጓዳ ባህሪይው ምክንያት ነው፡፡ እምቢ ባይነቱ ነው፡፡

ለአንደበት ወግ ያህል ስለሚዲያው ሚና ብዙ ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ የሐሳብ ነፃነት ያለ የማስመሰያ ዘዴ የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት አልጠቀመውም፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታንም አላሻሻለውም፡፡ የሐሳብ ነፃነትን የጥቂቶችና ‹‹የፈሪዎች›› የአጥር ውስጥ ጨዋታ ከመሆን አላወጣውም፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ የተደለቀለት የሚዲያ ነፃነት ሌላው ቀርቶ ካረጀ ካፈጀው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ወይም ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቁጥጥርና አስተዳደር ውጪ (ለይስሙላ እንኳን) አለመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ በተለይም የመንግሥት ሚዲያ ከነአካቴው አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው በይፋ መቆጠራቸው ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ በዝርዝርና በስፋት ለማስረዳት መጀመሪያ ለዚህ ጉዳይ አሁን በቅርቡ መነሻ የሆነኝን ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በነበረው የፓርላማ ውሎ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀረበውን ጥያቄና እሳቸው የሰጡትን መልስና ማብራሪያ አቀርባለሁ፡፡

ጉዳዩን በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሲተላለፍ ጭምር የተከታተሉት እንደሚያስታውሱት የጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የፓርላማው ውሎ በጠዋቱ የካቢኔ አባላት ሹመትና፣ ከቀትር በኋላው የጥያቄና መልስ ‹‹ክፍለ ጊዜ›› የተለያየ ነበር፡፡ በጠዋቱ ውሎ በአምስተኛው ፓርላማ ሁለተኛው ዓመት የሥራ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሁለተኛው የካቢኔ አባላት ‹‹ሹም ሽር›› ቀርቦ ፀደቀ፡፡ በከቀትር በኋላው ፕሮግራም የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት መስከረም 30 ቀን 2009 ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች የቀረቡበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መልስ የሰጡበት፣ በጠቅላላው በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የመንግሥት አቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸበት ነበር፡፡ ለምንነጋገርበት ጉዳይ መነሻ የሆነኝን ጥያቄና መልስ የሰማሁት በዚሁ የከሰዓት በኋላ የፓርላማው ውሎ ሒደት ውስጥ ነበር፡፡

ጠያቂዋ የምክር ቤት አባል ያቀረቡት ጥያቄ ሚዲያውን የሚመለከት ነበር፡፡ ክብርት እንደራሴዋ፣ ‹‹በአንድ አገር አስተዳደር ውስጥ ሚዲያ ካለው ሚና በመነሳት አራተኛው አካል ተብሎ›› እንደሚጠራ/እንደሚወሰድ ገልጸው፣

‹‹ሚዲያው በአሁኑ ወቅት መረጃ ለሕዝቡ በመስጠትና ለልማትና ለዴሞክራሲ ከማነሳሳት በላይ ችግሮችም እንዲፈቱ ፈልፍሎ በመውጣት ጥንካሬዎቹ እንዲቀጥሉ በማድረግ በኩልና በአጠቃላይ የአገራችን የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጉዞ ደጋፊ አካል ሆኖ እንዲገኝ በማድረግ በኩል ሊከናወኑ የተያዙ ጉዳዮች ቢብራሩ?›› ብለው ጠየቁ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያምም መልስ ሰጡ መልሱን እንዳለ ላቅርበው፡፡

‹‹በአገራችን የሚፈለገው ደረጃ አልተሳኩም ከምንላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትና ለሕዝብ መረጃ የሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ሚዲያ ነው፡፡ የሚዲያ ዘርፍ የሚፈለገው አቅምና ደረጃ እንዳልደረሰ በተደጋጋሚ የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ትኩረታችን በሚዲያ ዘርፉ የምናደርገው ሪፎርም፣ የሚዲያውን አቋም ግንባታ የማጠናከር፣ ከዚህ አኳያ የአገራችንን የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ የመቅረፅ፣ ይህን ስትራቴጂ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ትልቅ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡ በተለይ ደግሞ የሚዲያ ፕሮፌሽናሊዝም በተመለከተ ትልቅ ጉድለት ያለበት እንደመሆኑ መጠን የተከበረው ምክር ቤት ባቀረብኳቸው ሹመቶች ውስጥ አንዱ የዚህ ሹመት ጉዳይ ሪፎርምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፕሮፌሽናሊዝም ላይ የተመሠረተ የሚዲያ ሁኔታ ሊኖረን ይገባል፡፡

‹‹ከዚህ አኳያ የመልዕክቶች ቀረፃና መልዕክቶች በአግባቡ ለሕዝቡ እንደደረሱ የማድረግ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚዲያ ሙያዊና ከሙያው ጋር የተያያዙ ነገሮች ሁሉ ማስተካከል፣ የወጣት ጋዜጠኞቻችንና ሌሎች በሚዲያ ዙሪያ፣ በኮሙዩኒኬሽን ዙሪያ የሚሳተፉ አካላትን አቅም የማጎልበት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

‹‹የማሠልጠኛ ተቋሞቻችንም ቅድም እንደገለጽኩትም አካዳሚዎቻችንም ትኩረት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም ትኩረት ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ይሆናል ተብሎ የተወሰደ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች እንዲስፋፉ የማድረግ፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን መረጃ እንዲያገኝ የማድረግና ተሳትፎው የበለጠ እንዲጎለብት ለማድረግ የሚጫወቱትን ሚና አጠናክረን መቀጠል እንድንችል የምንሠራ ይሆናል፡፡ የተከበረው ምክር ቤት አባል የጠየቁትም በተመሳሳይ መንገድ መንግሥት ስትራቴጂያዊ ሥራዎችን በመሥራት ለውጥ ለማምጣት ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ በዚህ ዘርፍ እንደሆነ ለማብራራት ነው፡፡››

      በመከረኞቹ የመገናኛ ብዙኃን ዜና ውስጥ (በስፖርትም በቢዝነስ ዘገባም) ‹‹ዘገባው የ….. ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ነው››፣ ‹‹የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ያደረሰንን መረጃ ደረሰ ያለው ያቀርበዋል››፣ ‹‹… ሲል የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሙዩኒኬሽን ዘግቧል›› እየተባለ የሚወራውና የሚሠራው ተመልካች ያጣ አሠራር አገራችን ውስጥ የገነተረ ወግ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ዘመቻም የማይገላገሉት ክፉ አመልና ባህል መሆኑን እናውቃለን፡፡ በዚህ ምክንያት ድሮ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበረውና አሁን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሆነው የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የክልል አቻ ቢሮዎችና የየመሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነቶች ‹‹ሚዲያ›› የመባል ክብር ተቀዳጅተዋል፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ሕግ ጭምር የቀድሞው የማስታወቂያ ማኒስቴርም ሆነ፣ የአሁኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚዲያ አይደሉም እንላለን፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ቦታ የወሰደው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም የመንግሥትን የሚዲያ የቁጥጥር ሥራ የሚሠራ አካል ሆኖ አልተሰየመም፡፡ ይህንን ሁሉ የሚለው ጽሕፈት ቤቱን ያቋቋመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 158/2001 ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ራሱ ተናጋሪ ነው፡፡ የመንግሥት አፈቀላጤ ነው፡፡ የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ምንጭ ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያውን ጨምሮ በየትኛውም ሚዲያና በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም በሕዝብ ግንኙነት የግልም ሆነ የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል ያለው ግንኙነት የአቻ የሚዲያ ባለሙያዎች ግንኙነት አይደለም፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም ሆነ ሌሎች የሕዝብ ግንኙነቶች ሥራ የጋዜጠኝት ሥራ አይደለም፡፡ የቅጥር መደቡን ወይም የሥራ ቦታውን ቀይሮ አንዱ ሌላውን ማለትም ጋዜጠኛው የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ተልዕኳቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ ጋዜጠኛው አጋላጭ ነው፣ ይኸኛው ገመና ሸፋኝ ነው፡፡

ይህን እስካሁን ያልነውን ልዩ ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ነገሮች አወሳስበውታል፡፡ መጀመሪያ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሠሪ ሆነዋል፡፡ ሁለተኛ የመንግሥቱን ሥራ የሚሠሩት የማስታወቂያ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎች የመንግሥት ሚዲያዎች አመራር የቦርድ አባላት ናቸው፡፡ ሦስተኛ በዘመነ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የቀረ የተቆጣጠሪነት ሥልጣን (ሬጉላቶሪ አውቶሪቲ) አለን ባዮች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት የመንግሥት ሚዲያና የመንግሥት የአፈቀላጤነት ሥራ፣ በማናቸውም ሚዲያ ላይ ሊኖር የሚገባው በሕግ የተወሰነና የተገደበ የተቆጣጣሪነት ሥራ ባለቤትነት ድብልቅልቁ የወጣ እጅና እግር የሌለው ውሉ የጠፋበት ልቃቂት መስሏል፡፡

በሚዲያው ዘርፍ የሚደረገው ሪፎርም አቅም ግንባታን፣ ፕሮፌሽናሊዝምን፣ ወዘተ ያካትታል ሲባል አሁን በምንገኝበት የኢትዮጵያ ሁኔታ ይህ ጉዳይ የመንግሥትንና የግል ሚዲያውን መለየት አለበት፡፡ የመንግሥት ሚዲያው የአቅም ግንባታና የፕሮፌሽናሊዝም ጉዳይም ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለመንግሥት አፈቀላጤው በአደራ የሚሰጥ ሥልጣን አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መልስ፣ ‹‹ባቀረብኳቸው ሹመቶች ውስጥ አንዱ የዚህ ሹመት ጉዳይ ሪፎርምን ታሳቢ ያደረገ ነው፤›› ማለታቸው የሚያስገርመውና የሚያስደነግጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የአገራችንን የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ የመቅረፅ ይህንንም ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ የመልዕክቶች ቀረፃና በአግባቡ ለሕዝብ እንዲደርሱ የማድረግ የተባለው የሪፎርም ሥራ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ሚዲያም ሆነ የግል ሚዲያው ከሚገባው ‹‹አራተኛው አካል›› መሆን ካለበት የተቋምና የአሠራር ነፃነት ከተጎናፀፈው (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29/4) ከነፃ ፕሬስ ነፃ ሚዲያ የተለየ ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መንግሥት በመንግሥትነቱ የሚሰጠው የአገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ የግንኙነት አገልግሎት ነው፡፡ የመገናኛ አገልግሎት ነው፡፡ የመንግሥት ኢንፎርሜሽንን የማቀበል፣ የቅብብሎሹ ‹‹ማዞሪያ›› ሆኖ የማገልገል፣ ለጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የመስጠት፣ መንግሥትን የማስተዋወቅና ‹‹የመሸጥ›› አገልግሎት ነው፡፡ እንደማናቸውም መንግሥት በመንግሥትነቱ እንደሚሰጣቸው አገልግሎቶች ለሌላ ሰው በኮንትራት በ‹‹ውክልና›› አሳልፎ የማይሰጠው የባህሪ ሥራው ነው፡፡ እንደማንኛውም አገልግሎት ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት›› እና ‹‹የመልካም አስተዳደር›› ችግር የሚጠናወተው አገልግሎት ነው፡፡

መንግሥት ሙያዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የመስጠት ግዴታም ችግርም ስላለበት በዚህ ረገድ ማሻሻያ አደርጋለሁ፣ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ እቀርፃለሁ፣ ይህንንም ተግባራዊ አደርጋለሁ፣ በአዲሱ ሹመት ውስጥ አንደኛው ይህን ሪፎርም ታሳቢ ያደረገ ነው ቢል ችግርም ነውርም የለበትም፡፡ ይህ ሪፎርም በተዘዋዋሪ ለሚዲያው መልካም አጋጣሚና ደግ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን፣ ቋሚና አዛላቂ የመንግሥት ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ‹‹ማዞሪያ›› እና ገበያው ነው፡፡

ይህንን የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሥልጣንና ተግባር ግን ከመንግሥት የሬጉላቶሪ ሥልጣንና ተግባር (ለምሳሌ ብሮድካስት ባለሥልጣን) ጋር አቀላቅሎ ማየት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርና ሙያ ምንጭና ትምህርት ቤት አድርጎ መነሳት፣ የፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የጥበብ መጀመሪያ አይደለም፡፡ የመንግሥት ሚዲያም ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ›› በመሆኑ ምክንያት የመንግሥት አፈቀላጤ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ተቋም አይሆንም፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አስፈላጊነት ሲበዛ ይገባናል፡፡ መንግሥት መናገር አለበት፡፡ መንግሥትም አንድ ተናጋሪ ነው፡፡ የቸገረን፣ የጎዳንና ያሰለቸን መንግሥት አልናገርም ማለቱ፣ ሲናገርም ፕሮፓጋንዳውና ሆይ ሆይታው መብዛቱ ነው፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በነባሩና በመደበኛው የመንግሥት አፈቀላጤ ላይ (በማስታወቂያ ሚኒስቴር ላይ) ሌላ የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያቋቋምነው ሥራዎችና ተቋማት የግብር ይውጣና የይስሙላ ሆነውብን ነው፡፡ ስለዚህም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን ሥራ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መሥራት በዘርፉ ከሚደረግ ሪፎርም ወይም ‹‹በጥልቀት መታደስ›› በላይ ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ዘርፍ ፈርሶ መሠራትም ያስፈልገናል፡፡

መንግሥት መናገር አለበት፡፡ ውጤታማ መልካም አስተዳደር ማለት ራሱ ከሕዝብ ጋር ውጤታማ ንግግር፣ ግንኙነት ማድረግ ማለት ነው፡፡ የመንግሥትን ንግግር ከሌላው ንግግር የሚለየው ሌላው ሰው ሐሳብን በመግለጽ፣ በንግግርና በፕሬስ ነፃነቱ ውስጥ ያለመናገር ነፃነት ጭምር ስላለው ነው፡፡ መንግሥት ግን (ከጥቂት በሕግ የተወሰኑና ለዳኝነትም ሥልጣን አቤት ሊባሉ ከሚችሉ ጉዳዮች በስተቀር) አልናገርም ማለት አይቻልም፡፡ አልናገርም ብሎ መልካም አስተዳደር የለም፡፡

ያንኑ ያህል የመንግሥት ንግግር ብቸኛው ንግግር ሆኖ እንዳይቀር፣ የመንግሥት ንግግር መነጋገሪያና አነጋጋሪ እንጂ አላናግርም እንዳይል በሕግ ብዙ መላዎችና ሥልቶች ይበጁለታል፡፡ ቪኦኤ አሜሪካ ውስጥ የማይሰማው፣ በፓርላማ  ከተመደበው ውጪ በላይ ከሌላ የወጪ አርዕስት ወይም በጀት ላይ ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ወይም የሕዝብ ግንኙነት ወጪ የበጀት ዝውውር የማይፈቀደው፣ መንግሥት ንግግር ብቻ አፍ፣ የተቀረው ግን ጆሮ ብቻ እንዳይሆን ነው፡፡

ሁሉምና እያንዳንዱ ሰው የግድ መናገር ባይኖርበትም ሳይነገር የሚቀር ነገር ግን መኖር የለበትም፡፡ አገራችን ውስጥ እንኳን ፅድቁ በወጉ መኮነኑም ቢቀርብንም የዩኒቨርሲቲዎች የጥናት ተቋማት በየዘርፉ ያሉ ዓብይ ችግሮችንና መፍትሔዎችን ማጥናት፣ ማስጠናት፣ የተጠኑትን እያቀናበሩ ማተም፣ ትኩረትን በሚያስገኙ ዘዴዎች ለሚጠቀሙበት የማድረስ ሚና አላቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት በሚቋቋሙበት ሕግ የማሳተም ሥልጣን የሚሰጣቸውም ለዚሁ ነው፡፡ በእኛ አገር ይህ ጉዳይ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ገና ያልተነካ ነው፡፡ ዋና ዋና የአገር፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚመለከቱ መረጃዎችንና ጥናቶችን ቀምሮ የሚያቀርብ፣ የሚያወያይና የሚያከራክር ሚዲያ ዛሬም ገና ነው ማለት ይቻላል፡፡

የመንግሥት ሚዲያ አሁንም የገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ነው፡፡ የመንግሥትን አቋም ወይም ፕሮፓጋንዳ ለሚመለከቱ ዝግጅቶች የተወሰነ የአየር ጊዜ ወይም ዓምድ ተቆንጥሮላቸው ከዚያ ውጪ ያለው ሁሉ ለሕዝብ ጉዳዮች ዋለ የሚያስብል ጥርት ያለ የሥራ መፈላቀቅ እንኳ ጠፍቶ ዛሬ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ሚኒስቴሮች የሳምንት ተራ ገብተው ፕሮግራም ‹‹አሠርተው›› ሲያቀርቡ እናያለን፡፡ ይህ ሁሉ ‹‹የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› ሥራና የመንግሥት ሚዲያ መደብ  በሕግ አምላክ ሊባል ይገባዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን››ም ከእንዲህ ዓይነት በአንድ አፍ መናገርን ከሚያሰናክልና በሥልጣን ያላግባብ መገልገልን ሊያስከትል ከሚችል አደጋ ሊፀዳ ይገባዋል፡፡ ገንዘብ የሚከፈልበት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የአየር ሰዓት፣ የጋዜጣ ዓምድና የማስታወቂያ ሥራዎች ሁሉ በመንግሥት የግዢ ሥርዓት ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚተዳደሩ መሆኑን ማወቅም የዘርፉ ሀሁ መሆን አለበት፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የሥልጣን አካላት (የማዕከልና የክልል) የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአየር ሰዓት፣ የጋዜጣ ዓምድ ሲገዙም ሆነ ማስታወቂያ ሲያወጡ ግዢ መፈጸማቸው ነው፡፡ ግዢ ሲፈጽሙ ደግሞ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለው ከፍተኛ ጥቅም ላይ መድረሳቸውን ይህም ማለት ቁጠባን፣ የአፈጻጸም ብቃትንና ውጤታማነትን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በሚዲያዎች መካከል ከግዢው መወዳደሪያ መሥፈርቶች ጋር ባልተያያዙ ሌሎች ምክንያቶች አድልኦ ማድረግ የለባቸውም፡፡

መንግሥትም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንም ማወቅ ያለባቸው የሕዝብ የማወቅ መብት፣ የመንግሥት የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ግዴታ ሚዲያ ሊኖረው የሚገባው፣ የተቋምና የአሠራር ነፃነት መብት ብቸኛ የመንግሥት ተናጋሪነትን ይከላከላል፡፡ ከመንግሥት የመናገር መብት ይልቅ የመንግሥት የመናገር ግዴታን ያቋቁማል፡፡ የመንግሥት የመናገር ግዴታም የሌሎችን የዜጎችን የማንኛውንም ሰው የመናገር ነፃነት አይተካም፣ አይከላከልም፡፡ ይልቁንም ሕገ መንግሥቱ የተለያዩ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል በማለት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ድምፅ ብዝኃነት ያውጃል፡፡

በአገራችን ‹‹በሚፈለገው ደረጃ አልተሳኩም›› ከሚባሉት መካከል ሚዲያውና ራሱ የመነግሥት ኮሙዩኒኬሽን መሆኑ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ይህን ‹‹የሪፖርት ካርዳችንን›› ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገው ግን አሁንም ሚዲያና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን ለይቶ ማስተናገድ ያልቻለ አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጎ ያቀረበ ‹‹የመንግሥት አቋም›› መስማታችን ነው፡፡

መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚዲያው ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 በደነገገው ልክ መልክና ይዘት፣ ኢትዮጵያ የአገር ሕግ አድርጋ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች መሠረት ነፃ እንዲሆን ፈቃዳቸው ከሆነ ከሁሉ አስቀድሞ የመንግሥትን የክልከላ ግዴታ ይወጡ፡፡ የተከለከሉትን አያድርጉ፡፡ ጣልቃ እየገቡ ነፃነቱን አይቅጡት፡፡ በአገራችን ሁኔታ የመንግሥት አዎንታዊና የማመቻቸት ግዴታ ከጫናውና ከችግሩ ስፋትና ክፋት የተነሳ የ‹‹እዬዬም ሲደላ ነው›› ጉዳይ ነው፡፡ ቀጥሎ ቢመጣ ይደርሳል፡፡

አገራችን ውስጥ መንግሥት ከሚዲያ የሞኖፖል የባለቤትነት መብት ገና ጨርሶ አልተላቀቀም፡፡ የብሮድካስት ሚዲያን የባለቤትነት መብት ከግል ጋር ለመጋራት ሕግ ለማውጣት እንኳን እስከ 90ዎቹ ጉዳዩን በቀጠሮ ሲያጉላላው ቆይቷል፡፡ የሬዲዮ የግል ባለቤትነት በተግባር ዕውን የሆነው በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ላይ ነው፡፡ ቴሌቪዥን ዛሬም ከመንግሥት እጅ አልወጣም፡፡ ዛሬም ለመንግሥትና ለመንግሥት ‹‹አጋሮች›› ብቻ የተከለከለ፣ ለግል የተከለከለ የሥራ መስክ ነው፡፡

ለግል በተለቀቁት የኅትመት ሚዲያና የሬዲዮ የሥራ መስኮችም ጣጣው፣ ውጣ ውረዱ፣ ጠንቁ፣ አደጋው ብዙ ነው፡፡ አያደፋፍርም፣ አያበረታታም፡፡ አያበረታታም ማለት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ቦታ የለውም ማለት ብቻ አይደለም፡፡ አሳታሚነት ወይም የሚዲያ ተቋም ባለቤትነትና ጋዜጠኝነት ከሌሎች መካከል ፍርኃትን እስራትን የመሰለ ‹‹የሙያ ሥራ አደጋ›› ያለበት የኢንቨስትመት መስክ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የፕሬስ ሥራ መሥራት ከሞላ ጎደል በብቸኝነት ጤናማ በሆነባት አዲስ አበባ ውስጥ ከትርፍ ጥቅም ጋር ንግዳዊ ያልሆኑ ኃላፊነቶችን ተሸክሞና አቻችሎ መሥራት ይቻላል ብለው የተነሱ፣ ከዚያም አልፈው ከሌላ የበለጠ ትርፍ ካለበት የሥራ መስክ ይልቅ በዚህ ‹‹አደገኛ›› ሙያ ላይ የተሰማሩ፣ በዚህም በሕዝብ ዘንድ የመታመን ክብርና ሞገስ በማግኘት ዘላቂ የሚዲያ ገበያ ለመፍጠር የሚጥሩ በጭራሽ አልጠፉም ነበር፡፡ እነዚህን ሰዎች በመላ ኢትዮጵያ ብዙ ተባዙ የሚላቸውና ብዙ የሚያደርጋቸው ድባብና የአየር ሁኔታ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ግንባታ ትግል የጎደለው ይኸው ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) ውስጥ፣ በተለይም በሕገ መንግሥቱ የእንግሊዝኛ ቅጂ በግልጽና በስሙ የተጠቀሰው የዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ኦፍ ሂውማን ራይትስ አንቀጽ 19ን ድንጋጌ ከሞላ ጎደል ቃል በቃል የአንቀጽ 29 ይዘትና አካል ያደረገው የኢትዮጽያ ሕገ መንግሥት፣ ሕገ መንግሥትን በመሰለ ቋሚና ለማሻሻልም ጥብቅና ብርቱ ሥርዓት መከተል ባለበት ሰነድ ውስጥ፣ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን›› ብለን ጽፈናል፡፡ ፍላጎቱና ሐሳቡ ክፉ አልነበረም፡፡ እንዲህ ያለ የመንግሥት ሚዲያም ቢሆን ‹‹የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችላቸው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል›› ብለን ነበር፡፡ የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 29 በተለይም የተጠቀሰው ንዑስ አንቀጽ (5) ይዘት የተወቀሰውና ዛሬም ድረስ የሚወቀሰው የመንግሥትን የሚዲያ ባለቤትነት ይመርቃል፣ ያፀድቃል ተብሎ ነው፡፡

‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን›› ህልውና ዛሬም አላበቃም፡፡ የአመራር ነፃነትም አላገኘም፡፡ ነፃ የሚባሉት የቁጥጥር አካላትና የቦርድ አመራራቸው እንኳንስ ከመንግሥት ከቡድን ይዞታነትና ተቀጥላነት ያልተላቀቁ ናቸው፡፡ በዚህና በሌሎችም በተጠቀሱት ምክንያቶች የመንግሥት ሚዲያ የመንግሥት አፈቀላጤ፣ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ነው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ብቻ ነው፡፡

በተለያዩ ምከንያቶች እንዲህ ሆኖ በተሰነገው የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ የአዳዲስ ሐሳቦች መፍለቂያና የአገሪቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች መነጋገሪያ መሆን የሚሻ ሚዲያ ገለልተኛ የመሆን የየትኛውም የፖለቲካ ወገን የፕሮፓጋንዳ ከበሮ ያለመሆን፣ ከየትኛውም ወገን የሚመጡ ሥራዎችን ለሕዝብ ባላቸው የቁም ነገር ዋጋ የመመዘን፣ የሕዝብን የፖለቲካና የሃይማኖት ሰላም የሚያበለፅግ፣ ውዥንብርና ደመኛነትን የመግፈፍ ምክንያታዊና እውነተኛ ግንዛቤን የማስፋፋት ኃላፊነትን ግልጽ የተግባር ፖሊሲው አድርጎ መነሳት ግዴታ ነው፡፡ አገራችን የዚህ ዓይነት ማዲያ ደሃ ናት፡፡

የዚህ ምክንያት የመንግሥት አቅም ግንባታ ንፍገት አይደለም፡፡ የመንግሥት የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርና የሙያ ሥልጠና ችላ ባይነት አይደለም፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ሙያውና ተቋሙ በገዛ ራሱ አዛዥ እንዳይሆን ዘርፈ ብዙ ሥጋትና ጠንቅ እንዲጋረጥበት መደረጉ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡.