አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ የ11 አገሮች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፋይናንስ ድጋፍ አደረገ

 

 ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በአፍሪካ 11 አገሮች ውስጥ ለሚገኙ 1.1 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የምርታማነት ማሻሻያና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ ፕሮግራሞችን በሚያራምዱ ተቋማት በኩል ድጋፍ ማደረጉን አስታወቀ፡፡

ፋውንዴሽኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ በአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎችን ለመደገፍ ከሚንቀሳቀሱ፣ የፋይናንስ እንዲሁም የአግሪ ቢዝነስ አገልግሎቶችን ለገበሬዎች ለማዳረስ ከሚጥሩ ሦስት ድርጅቶች ጋር ፋውንዴሽኑ ባደረገው ስምምነት መሠረት የ38.3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ዛምቢያን የሚያካትተው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ፣ ለአነስተኛ ገበሬዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርታማነታቸው እንዲጨምር በማገዝ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን አሠራራቸውን ለመቀየር እንዲቻል ለማድረግ ያለመ መሆኑን፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፋይናንሺያል ኢንክሉዥን ዳይሬክተሯ አን ማይልስ አስታውቀዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ገበሬዎች የፋይናንስና ሌሎችም ድጋፎችን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ በአፍሪካ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ሦስት ኩባንያዎች ጋር በመዋዋል 38 ሚሊዮን ዶላሩን እንዲያንቀሳቅሱ የተመረጡት ‹‹አፍሪካ አግሪካልቸር ዲቨሎፕመንት ካምፓኒ››፣ ‹‹ሩት ካፒታል›› እንዲሁም ‹‹አይሲሲሲኦ ኮኦፕሬሽን›› የተባሉ ሦስት ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በ11ዱም አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ገበሬዎች የሥልጠናና ጥራት ያላቸው የግብርና ግብዓቶችን ማቅረብ፣ የሞባይል ቴክኖሎጂዎችን መተግበር፣ ከ150 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ዶላር ካፒታል የሚጠይቁ ነገር ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ለሚታመንባቸው የግብርና ነክ ቢዝነሶችን ከመደገፍ በተጨማሪ ሌሎችም ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን እስካሁን በአፍሪካ ለሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች ከ300 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለው ገንዘብ መመደቡን አስታውቆ፣ ከዚህ ውስጥ 175 ሚሊዮን ዳላሩ በገጠር አካባቢዎች እንዲሁም በግብርና መስክ ፋይናንስ የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚውል ድጋፍ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ከአሥር ዓመት በፊት በካናዳ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ተቋም ሲሆን፣ የፋይናንስ ተካታችነትን፣ የትህምርትና ሥልጠናን፣ የወጣቶች ኑሮ መሻሻልን መሠረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡

ይኸው ተቋም ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ከ12 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች በንብ ማነብ እንዲሁም በሐር የፈተል ክር የምርት ሥራ ላይ መሳተፍ የሚችሉበትን የሥልጠናና የቢዝነስ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ መስጠቱ ይታወሳል፡፡