አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ስምንት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚጠይቁ ተጨማሪ መንገዶች ሊገነቡ ነው

 

የቻይና ተቋራጮች አሁንም የበላይነቱን ይዘዋል                                                                                                                                                                                                                                                          የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም. እንዲገነቡለት በዕቅድ ከያዛቸው ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ7.98 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃሉ የተባሉ የሰባት መንገዶችን የግንባታ ውሎች ከስድስት ኮንትራክተሮች ጋር ተፈራርሟል፡፡ ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ጽሕፈት ቤት ስምምነት የተፈጸመባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 468 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸውና ሁሉም በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ እንደሚገነቡ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ከሰባቱ ፕሮጀክቶች አምስቱን አራት የቻይና ተቋራጮች ሲረከቡ፣ ሁለቱን ደግሞ የአገር ውስጥ ተቋራጮች አግኝተዋል፡፡ መንገዶችን ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ መሆናቸው ተገልጾ ስምምነት ያደረጉት የቻይና ኩባንያዎች፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት፣ ቻይና ኮንስትራክሽንና ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ)፣ ቻይና ውይ ኢንተርናሽናልና ሲጂሲኦሲ ግሩፕ ኩባንያ ሊሚትድ የተባሉ ተቋራጮች ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ተቋራጮች በጠቅላላው የተረከቧቸው ፕሮጀክቶች ከ4.2 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አምስት የመንገድ ግንባታዎች ናቸው፡፡ ሰንሻይንና ገምሹ በየነ የተባሉት ሁለት አገር በቀል ተቋራጮችም የ3.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሁለት መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች ፈርመዋል፡፡

የቻይና ሬልዌይ የ1.65 ቢሊዮን ብር መንገድ

ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከተፈረሙት ሰባት የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ውስጥ ሁለቱን ፕሮጀክቶች ለመገንባት የተስማማው ቻይና ሬልዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የቻይና ተቋራጭ ነው፡፡

ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት፣ በጨረታ አሸናፊ ሆኖ ግንባታቸውን ለማከናወን ከተረከባቸው ሁለት መንገዶች አንዱ የጭኮ-ይርጋ ጨፌ 60 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 58 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ መንገድ ነው፡፡ የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድን ለመገንባት የተስማማበት ዋጋ 889 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ መንገድን ለመገንባት ውለታ የፈጸመበት ዋጋም 768.6 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ ተቋራጩ ሁለቱን መንገዶች እንዲገነባ በጠቅላላው ከ1.65 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ይከፈለዋል ማለት ነው፡፡

ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ከሚገነባቸው መንገዶች አንዱ የሆነው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድ ግንባታ ሥራ በልዩ ሁኔታ እንደሚታይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

መንገዱ ከሌሎቹ ግንባታዎች የሚለይበት ዋነኛ ምክንያትም 10,288 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውንና ትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይ ኔትወርክ ተብሎ የሚጠራው ፕሮጀክት የሚያስተሳስራቸው የተለያዩ አገሮችን የሚያቋርጠው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክት አካል በመሆኑ ነው፡፡

የጭኮና ይርጋ ጨፌ ከተሞችን ከማገናኘት ባሻገር ድንበር ዘለል ጠቀሜታ እንዳለው የተገለጸው ይህ ፕሮጀክት፣ የሞምባሳ-አዲስ አበባ ኮሪደር እንደመሆኑ መጠንም ኢትዮጵያ ላሙ እየተባለ የሚጠራውንና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን የሚያገናኘውን የወደብ ፕሮጀክት በአማራጭነት ለመጠቀም እንዲያስችላት ለያዘችው ዕቅድ ተግባራዊነት፣ ዋነኛው የመሠረተ ልማት አካል ሆኖ እንደሚያገለግል የዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ይህ መንገድ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ለሚኖረው ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኬንያ ባሻገር ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን፣ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ከተማ ካይሮ ከሚዘልቀው መንገድ ጋር እንደሚያስተሳስር የሚጠበቅ ነው፡፡

ትራንስ አፍሪካ ሃይ ዌይ ኔትወርክ የተባለው የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፣ ከሰሜንያዊቷ ካይሮ በመነሳት ወደ በደቡባዊቷ ኬፕታውን ከተማ የሚዘልቅ ሲሆን፣ መንገዱ የሚያልፍባቸው አገሮች በየራሳቸው በኩል የሚኖረውን የመንገድ ድርሻ በመገንባት ግዙፉን ፕሮጀክት እውን እንደሚያደርጉት ይታሰባል፡፡ ኢትዮጵያም ከትራንስ አፍሪካ ሃይ ዌይ ኔትወርክ ጋር የሚገናኘውን የመንገድ መስመር እንድትሠራ ከሚጠበቅባት መካከል አንዱ ይኼው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድ ነው፡፡ የሰሜን፣ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ አገሮችን የንግድ ልውውጥ ለማቀላጠፍ ይረዳል የተባለው የዚህ ግዙፍ ኔትወርክ አካል የሆነው የጭኮ-ይርጋ ጨፌ የመንገድ ፕሮጀክት ግን፣ አሁን ለቻይና ኮንትራክተር ከመሰጠቱ በፊት ሃዋክ ኢንተርናሽናል በተባለ ተቋራጭ ግንባታው ሲካሄድ የቆየ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረትም የመንገዱ ግንባታ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ሃዋክ ፕሮጀክቱን አጓቷል በሚል ከኮንትራክተሩ ጋር የነበረውን ውል አቋርጦ ሥራው ቆሞ የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሃዋክ ኩባንያ ጋር የነበረው ስምምነት እስኪቋረጥ ድረስ ከ60 ኪሎ ሜትሩ ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ሥራ ግንባታ መከናወኑ እንደተገለጸ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በሦስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረውን የጭኮ-ይርጋ ጨፌ መንገድን ለመገንባት ሃዋክ የተረከበበት የግንባታ ዋጋ 700 ሚሊዮን ብር እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ይሁንና ሃዋክ ሳያጠናቅቅ የቀረውን ሥራ ለመጨረስ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት አሸናፊ የሆነበት ገንዘብ መጠን 889 ሚሊዮን ብር መሆኑ ፕሮጀክቱ ከታሰበለት በላይ በእጥፍ ወጪ ከመጠየቁም ባሻገር ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁን ያመላክታል፡፡

በሰኞው ስምምነት ወቅት እንደተገለጸው ይኸው የቻይና ተቋራጭ ቀሪውን ግንባታ በ22 ወራት ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ሆኖ ፕሮጀክቱ አሁን በተደረሰው ስምምነት መሠረት የሚጠናቀቅ ከሆነ፣ በጠቅላላው ከሰባት ዓመታት በላይ ይፈጃል ማለት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ የሚሸፈነው የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰጠው ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት እንደሆነም ታውቋል፡፡

የሲጂሲኦሲ ግሩፕ የ999.3 ሚሊዮን ብር መንገድ

ሲጂሲኦሲ ግሩፕ የተረከበው የመንገድ ሥራ ከፊንጫአ-መነቤኛ-ሻምቡ (ኮንትራት ሁለት) የተሰኘውን የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ 65.5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ይህንን መንገድ እንዲገነባ የተዋዋለበት ዋጋ 999.3 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ተቋራጭ ከዚህ የመንገድ ሥራ ባሻገር በእጁ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው  ፕሮጀክቶችም ይገኛሉ፡፡ የመነቤኛ-ሻምቡ መንገድን ለመገንባት የተረከበው ዋጋ 4.58 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

የሲሲሲሲ የ1.06 ቢሊዮን ብር መንገድ

በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመረከብ ከሚጠቀሱ የቻይና ተቋራጮች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ከመንገድ ግንባታ ባሻገር በሌሎች ግንባታ መስኮችም በቢሊዮኖች ብሮች የሚገመቱ ፕሮጀክቶችን የገነባና አሁንም በመገንባት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ተቋራጩ በይበልጥ የሚታወቅበት የመንገድ ሥራ የአዲስ አበባ የፍጥነት መንገድ ሲሆን፣ ከዚህ መንገድ ጋር የሚያያዙና ወደ አዲስ አበባ የሚዘልቁ ሁለት መንገዶችን መገንባቱም ይታወሳል፡፡ በቅርቡም ከቃሊቲ ቂሊንጦ ሁለት ኮሪደሮች ያሏቸውን መንገዶች በ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡

ኩባንያው የተረከባቸው ፕሮጀክቶች ከ23 ቢሊዮን ብር ብላይ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከኢትዮጵያ የመንገዶች ባለሥልጣን ብቻ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች በእጁ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ከጅግጅጋ ገለልሽ-ደገህመዶ-ሰገግ ያለውን 55.4 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ከትናንት በስቲያ አዲስ ውል ፈጽሟል፡፡ መንገዱንም በ1.06 ቢሊዮን ብር እንደሚገነባው ተገልጿል፡፡ ይህ ተቋራጭ በዚህ በጀት ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የተረከበው ፕሮጀክት መሆኑ ነው፡፡

የቻይና ውይ ኢንተርናሽናል የ1.68 ቢሊዮን ብር መንገድ

 ከተፈረሙት የመንገድ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት በመውሰድ ውለታ የፈጸመው ሌላኛው የቻይና ኩባንያ ቻይና ውይ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋራጭ ነው፡፡ ተቋራጩ ስምምነት የፈጸመበት የመንገድ ፕሮጀክት ከየደዬ-ጪሪ-ናንሰቦ ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት ሲሆን፣ መንገዱ 73.35 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡

ቀደም ሲል በጠጠር ደረጃ የነበረው ይህ መንገድ፣ የ10 እና የ12 ሜትር ስፋት ያለው ትከሻ ይኖረዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ይህ መንገድ ቻይና ውይ በ2009 በጀት ዓመት የፈረመው ሁለተኛው የግንባታ ስምምነት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ውስጥ መሳተፍ የጀመረውም በዚህ በጀት ዓመት እንደሆነ ታውቋል፡፡

ተቋራጮችን በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ገምሹ በየነ፣ ሰንሻይን፣ ሲሲሲሲ፣ ቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት እንዲሁም ሲጂሲኦሲ ግሩፕ ከዚህ ቀደም የተለያዩ መንገዶችን ገንብተው አስረክበዋል፡፡ ቻይና ውይ የተባለው ተቋራጭ የመጀመሪያው ቢሆንም፣ በሌሎች አገሮች ውስጥ ባከናወናቸው ሥራዎች በቂ ልምድ እንዳለው በጨረታ ግምገማ መታየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ 

የገምሹ በየነ የ1.28 ቢሊዮን ብር መንገድ

ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ የሆነውን የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችለውን ዕድል አግኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከትናንት በስቲያ ከፈረማቸው ሰባት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የዓለም ከተማ-ደጎሎ ኮንት መንገድ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን በ1.28 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ተፈራርሟል፡፡ 85 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ይህንን መንገድ ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዓለም ከተማ-ደጎሎ ኮንት የመንገድ ፕሮጀክት በ36 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፣ መንገዱ የ10፣ የ12 እና የ14 ሜትር ትከሻ ኖሮት የሚገነባ ነው፡፡ በርካታ ፉካዎችና ሰባት አነስተኛ ድልድዮችም አካቶ እንደሚገነባ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ ተቋራጩ ከአንድ ወር በፊት የወንጪ ካቺሌ-ጨለቲ መንገድን በ846.2 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

የሰንሻይን የ1.29 ቢሊዮን ብር መንገድ

ከአገር ውስጥ ተቋራጮች የመንገድ ግንባታ ውል የፈረመው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን በጨረታ የተረከበው ከደጎሎ-ከላላ ኮንት (ሁለት) መንገድን ለመገንባት ነው፡፡ ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 71 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ሲሆን፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን መንገዱን ለመገንባት ውለታ የፈረመበት ዋጋ 1.29 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በ36 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ የመንገድ ግንባታ ወጪ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

ስምምነቶቹን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኩል አቶ አርዓያ ግርማይ ናቸው፡፡ በኮንትራክተሮቹ በኩል ሚስተር ዡ ዮንግ ሸንግ የሲሲሲሲ ሥራ አስኪያጅ፣ ሚስተር ታአ ቦ የቻይና ሬል ዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ፣ በቻይና ውይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኩል የሥራ ተቋራጩ ተወካይ ሚኒስተር ካይ ሃዩሎንግ፣ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ገምሹ በየነ የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በሲጂሲኦሲ በኩል ሚስተር ጋዎ ሊ ናቸው፡፡