አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

በበርበራ ወደብ የኤምሬትስ የጦር ሠፈር ለምን?

የመን ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛት የመሬትም ሆነ የባህር ድንበር የለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመን አካባቢ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ግን፣ ለኢትዮጵያ ከመቼም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ ይመስላል፡፡

ቱኒዚያ ላይ ተጀምሮ ግብፅንና ሊብያን ያጥለቀለቀውና እንደ ሰደድ እሳት የዓረቡ ዓለም የአገዛዝ ሥርዓቶችን ያነቃነቀው ሕዝባዊ ዓመፅ ብዙ መላምት እየተሰጠበት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት በቅርቡም ሆነ በታሪክ በዓረቡ ዓለም ካለው ንጉሣዊ ሥርዓት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ቢሆንም፣ የዓረቡ ዓለም ተፅዕኖ ባለባቸው አገሮች በተከበበችው ኢትዮጵያ ላይ ሊያሳድረው የሚችል የፖለቲካ ጫና ቀላል አይደለም የሚል ነው፡፡

በ2002 ዓ.ም. ለንባብ የበቃው የኢሕአዴግ ንድፈ ሐሳብ መጽሔት አዲስ ራዕይ፣ ‹‹ቆሞ ቀሮች›› በሚል ርዕስ ያቀረበውና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደተጻፈ የሚገመተው ጽሑፍ፣ ይህንን የመካከለኛው ምሥራቅ ዓለም ‹‹ዘገምተኛ›› ፖለቲካ የሚገመግም ነበር፡፡ የእነዚህ አገር ዜጎችና ወጣቶቸች ንቃተ ኅሊና ከፍ እያለ ሲመጣ፣ ንጉሣዊ አገዛዞችን መቃወማቸው አይቀርም የሚል ድምዳሜ የያዘ ነበር፡፡ የተተነበየው አልቀረም፡፡ ጽሑፉ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ‹‹የዓረብ ስፕሪንግ›› እየተባለ የሚጠራው ዓመፅ የተቀጣጠለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ዓመፅ ይካሄዳል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ግን ይህንን ትንታኔ አልተቀበሉትም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት የሚያገኛኝ ሁኔታ እንደሌለ ነበር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩት፡፡ በአንድ ነገር ግን ሥጋታቸው ገልጸው ነበር፡፡ ተመሳሳይ ሁከት በየመን የሚቀሰቀስና ምናልባት የሥልጣን ክፍተት የሚፈጠር ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ የደኅንነት ሥጋት ያስከትላል ነበር ያሉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት እያሉ የተጀመረው የየመን ዓመፅ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚስተዋለው የኃይል አሠላለፍ ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የመን ከኢትዮጵያን ጋር የምትዋሰነው ግዛትና ድንበር ባይኖርም፣ በኢትዮጵያ መሪዎች ‹‹የግመል መጠጫ›› ይሆናል ተብሎ የተናቀውና፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ የማይዋጥላቸው የአሰብ ወደብ፣ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ኃይሎች የየመን ቀውስን አሳበው እያንዣበቡበት ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል ሥልጣን ላይ የነበረውን የየመን መንግሥት በመቃወም በኃይል ለማውረድ ነፍጥ አንስተው የሚታገሉትን ሲደግፍ የቆየው የኤርትራ መንግሥት፣ በአንድ ጀምበር እጥፍ በማለት የኢራን ተቃራኒ የሆነውና በሳዑዲ ዓረብያ የሚመራው 28 የዓረብ አገሮች ያቀፈው እስላማዊ ኅብረት በመቀላቀል የቀይ ባህርን ዞን ለኅብረቱ የምድርና የአየር የጦር እንቅስቃሴ ፈቅዷል፡፡ ተባብሯል፡፡

ለዚህም ከፍ ያለ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል እየተባለ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስካሁን ከአሥራ አንድ ሺሕ በላይ የመናውያን ሕይወት በኅብረቱ ጥቃት ተቀጥፏል፡፡ ከስምንት ሺሕ በላይ ዜጎች አካለ ጎዶሎ ሆነዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ተሰደዋል፡፡

የሁቲ አማፅያን ባለፈው ዓመት የአገሪቱ ዋና ከተማን ሰንዓ በቁጥጥር አውለው ወደ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ኤደን በማምራት ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ እንቅስቃሴያቸው በኅብረቱ እየተገታ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ዋናው አሥጊው ጉዳይ የመን ውስጥ እየሆነ ያለው አይደለም፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢትዮጵያን ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢጎበኙም፣ አገራቸው እንዴት ትብብር ልታደርግ እንደምትችል ብዙ የፖለቲካ ተንታኞችን ግራ ያጋባ ነው፡፡ ዋና ወዳጇ የኅብረቱ ግንባር ቀደም አባል ከሆነችው ከሳዑዲ ዓረቢያ እጅና ጓንት ነችና፡፡

ኤምሬትስና የበርበራ የጦር ሠፈር

በየመን አካባቢ ያለውን ቀውስ ተከትሎ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የአሰብ ወደብን ለ30 ዓመታት መከራየቷ የተነገረ ሲሆን፣ በአካባቢውም የጦር ሠፈር መገንባቷ ይፋ ሆኗል፡፡ ‹‹የአሰብን የባህር ወደብ ማጣት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤›› ይላሉ የደኅንነት ተመራማሪውና በጉዳዩ ላይ ጥናት የሠሩት ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት፡፡ እንደሳቸው እምነት፣ የአሰብ ጉዳይ በዋናነት የባህር የደኅንነት ጉዳይ ነው፡፡ አሰብን መያዝ የአካባቢውን ደኅንነት መቆጣጠር ሲሆን፣ አለመያዝ ደግሞ ለተለያዩ የደኅንነት ጥቃቶች የሚያጋልጥ ሁኔታን መጠበቅ ነው፡፡

በጅቡቲ ወደብ በየቀኑ በሚከለስ ዋጋና የማያረካ አገልግሎት እምብዛም ደስተኛ ያልሆነችው ኢትዮጵያ ራሷን ከታላቋ ሶማሊያ ካገለለች 25 ዓመታት ወደ ሞላት ሶማሊላንድ ፊቷን አዙራ ነበር፡፡ የበርበራ ወደብ አዲስ ማስፋፊያ ተደርጎለት ለኢትዮጵያ ጥቅም ዝግጁ ሆኖ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት በወደቡ አጠቃቀም የቅድመ ትግበራ ስምምነት ተደርጎም ነበር፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ዲፒ ወርልድ (DP World) የተባለው የዱባይ የወደብ አስተዳደር ድርጅት በ442 ሚሊዮን ዶላር የወደቡን የማስፋፊያ ሥራ ያከናወነ ሲሆን፣ ባለፈው ታኅሳስ ወር ላይ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ነበር የአገልግሎት ስምምነቱ የተፈጸመው፡፡ በስምምነቱ መሠረትም የወደቡ አገልግሎት በ16 ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ነበር፡፡ እጅግ የተጨናነቀውና በአሁኑ ወቅት 98 በመቶ የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ዕቃ ለሚስተናገድበት የጅቡቲ ወደብ አማራጭ ይሆናል ተብሎ የተገመተው የበርበራ ወደብ፣ ከአዲስ አበባ በ937 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስፈላጊው የመንገድ መሠረተ ልማትም ተሟልቷል፡፡ ከወደቡ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ግንባታ ከተጠናቀቀ እነሆ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

በቅርቡ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ግን መደናገጥን ፈጥሯል፡፡ የአሰብ ወደብን ለ30 ዓመታት የተከራየችና ለኤርትራ ከፍ ያለ ገንዘብ መስጠቷ የሚነገርላት ኤምሬትስ፣ በበርበራ ወደብ ዙሪያ ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን የጦር ሠፈር ለመገንባት ፈቃድ አግኝታለች፡፡ ይህንን በተመለከተ በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በርሀ ተስፋይ ለአንድ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዳልሆነና በሶማሊላንድ የውስጥ ጉዳይ ኢትዮጵያ ጣልቃ አትገባበትም ቢሉም፣ አነጋጋሪነቱ ግን ቀጥሏል፡፡

ሶማሊላንድ ኒውስ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ግን የአገሪቱ አንዳንድ ኃላፊዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የሃይማኖት መሪዎችን በማነጋገር፣ ውሳኔው አገሪቱ ከኢትጵያና ከጂቡቲ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሻክርና ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ አትቷል፡፡

ዘገባው፣ ‹‹ሶማሊላንድ ከሌሎች አገሮች የሚኖራትን ግንኙነት መወሰን የምትችለው ዋና አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፤›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ዕውቅና እንድታገኝ የምትፈልግ፣ ሰላሟንና ፀጥታዋ እንዲጠበቅ የምትሠራ ታማኝና ዋና ወዳጅ ጎረቤት መሆኗን በመጥቀስ በተለይ ዋዳኒ የተባለውን ቁጥር አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ያነጋገረ ሲሆን፣ ‹‹ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር ይህንን ወታደራዊ ስምምነት መፈጸም በሶማሊላንድ መረጋጋት ላይ የሚያከትለው ጉዳት ከባድ ነው፤›› ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

ኦል ኢስት አፍሪካ የተባለውን ድረ ገጽ ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው የሚገልጸው ዘገባው ደግሞ ሼክ አደን ሲራ የተባሉ በአገሪቱ የተከበሩ የሃይማኖት መሪም፣ ‹‹ይህ ውሳኔ በአካባቢያችን ካሉት ኃያላን አገሮች ጦርነት ከመክፈት አይተናነስም፤›› ማለታቸውን አክሏል፡፡

የኢትዮጵያና የጂቡቲ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ መግለጻቸውን የአገሪቱ ድረ ገጾች ያስነበቡ ሲሆን፣ ስምምነቱ እንዳይፈረም ማሳሰቢያ መስጠታቸውም ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላት ግንኙነት በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተና ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፣ ከዋናዋ ሶማሊያ ጋር ላለመጋጨት አገሪቱ ዕውቅና እንድታገኝ በቂ እንቅስቃሴ አለማድረጓ ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት የሶማሊንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሚጠብቀውን ያህል ድጋፍ ያገኘ እንደማይመስለውም የሚናገሩ አሉ፡፡

አብዲራሺድ ጅኒ የተባሉ ሶማሊላንዳዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ምሁር፣ “Why Somaliland shouldn’t accept UAE bid for Berbera Base” (ሶማሊላንድ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በበርበራ ዙሪያ የቀረበለትን የጦር ሠፈር ግንባታ ለምን መቀበል እንደሌለባት) በሚለው ጽሑፋቸው፣ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን በመተንተን ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀው ነበር፡፡

የመጀመሪያው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ገንዘብ ያላት ሀብታም አገር ትሁን እንጂ፣ ምንም ዓይነት የወታደራዊ ኃይል የበላይነት የሌላትና የውጊያ ልምድ የሌለው ጦር ባለቤት በመሆኗ፣ ከየመን አማጽያን (ሁቲ) ተዋጊዎችና ከኢራን ሊመጣ የሚችልን ጥቃት ሶማሊላንድ ልትገላግል የማትችል ደካማ አገር መሆኗን ነው፡፡

በታሪክ የሶማሊላንድ የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆነችውን ኢትዮጵያን የሚያስቀይም መሆኑ ደግሞ ምሁሩ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ከግብፅ ጋር ያላት ታሪካዊ ግንኙነት፣ በተለይ እ.ኤ.አ. የ2013 የመንግሥት ለውጥን የደገፈችና በፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በኢትዮጵያ ላይ ታስቦ በነበረ ወታደራዊ ዕርምጃም እሷ ከጀርባ እንደነበረችበት የኢንተለጀንስ መረጃዎችን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ከግብፅ ጋር በተጓዳኝ ለምትሠራ አገርና ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት በታሰበው ወደብ ዙሪያ የጠላት አገር የጦር ሠፈር ለመገንባት መፍቀድ ምን የሚሉት እብደት ነው?›› ሲሉ ምሁሩ ይቃወማሉ፣ ሆፒን ዲፕሎማት በሚባል ድረ ገጽ በታተመው ጽሑፋቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን የመሰለ ወዳጅ በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ማጣት፣ የሶማሊላንድ ሕዝብ ጥቅምን ያላገናዘበ ቅሌት›› በማለት፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ከዓለም አቀፍ ዕውቅና ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አገሪቱ ዕውቅና እንዳታገኝ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በዋናነት አባል የሆነችበት የዓረብ ሊግ አቋም መሆኑ፣ ይኼ አቋምም በቅርብ ጊዜ ይቀየራል ብሎ የሚገመት አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ለአንድ የጠላት ወዳጅ ለሆነ አገር የጦር ሠፈር መፍቀድ ለጠላት እጅ እንደ መስጠት ይቆጠራል፤›› በማለት ምሁሩ ይደመድማሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሶማሊያ መንግሥት ጉዳዩን በመቃወም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ምን አቋም እንዳላት ጥያቄ የቀረበላቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡