አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

በባብኤል መንደብ አካባቢ ያለው የወቅቱ ሁኔታ ኢትዮጵያ በጂቡቲ የጦር ሠፈር እንደሚያስፈልጋት አመልካች ነው

በተስፋዬ ታደሰ (ኮማንደር)

      የባብኤል መንደብ ስትራቴጂካዊ ምንነትና የወቅቱ የመካከለኛው የምሥራቅ የደኅንነት ሁኔታ ሲቃኝ፣ ጂቡቲ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ሆና በመገኘትዋ በዓለም ኃያላን መንግሥታትና ሌሎቹም የአካባቢው ጉዳይ ያሳስበናል ያሉ አገሮች ሁሉ፣ በዚህ ሥፍራ የጦር ሠፈር በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጂቡቲም ለሁሉም ባይሆንም ለጠየቁ አገሮች ለአብዛኛዎቹ ማለትም ለፈረንሣይ፣ ለአሜሪካ፣ ለጃፓን፣ ለሳውዲ ዓረብያና ለሌሎችም አወንታዊ መልስ እየሰጠች በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡

በአሁኑ ወቅት የጂቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ወጪና ገቢ ንግድ ማስተናገጃ ብቸኛ ወደብ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ የዚህ ወደብ የልብ ትርታ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ትልቅ አንድምታ አለው፡፡

የባብኤል መንደብ ጂኦፖለቲካል ምንነት

ባብኤል መንደብ የአፍሪካ ቀንድና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኝ የባህር ላይ አጣብቂኝ የሆነ (Check Point) መተላለፍያ መንገድ ነው፡፡ ባብኤል መንደብ ለአፍሪካ ቀንድና ለመካከለኛው ምሥራቅ፣ ለሜድትራኒያን ባህርና ለህንድ ውቅያኖስ አገናኝ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ ሥፍራ የመን፣ ጂቡቲና ኤርትራ ድንበር አካባቢ ይገኛል፡፡ የቀይ ባህርን ከኤደን ባህረ ሰላጤና ከዓረብ ባህር ያገናኛል፡፡ ከአፍሪቃ ቀንድ ከፔርሺያ ባህረ ሰላጤ በስዊዝ ካናል የሚያልፉ ገቢና ወጪ ንግዶችን በባብኤል መንደብ በኩል ያልፋሉ፡፡ 2.3 ሚሊዮን በርሜል ያልተጣራና የተጣራ ነዳጅ በዚህ የባህር መንገድ በኩል ወደ አውሮፓ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስያና አፍሪካ ቀንድ ይጓጓዛል፡፡

ባብኤል መንደብ 18 ማይልስ ስፋት ያለው ጠባብ ሥፍራ አለው፡፡ ይኼ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በሁለት ማይልስ ስፋት ብቻ ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የባህር ጥልቀት ብዙም ባለመሆኑ በዚህ ውስን ሥፍራ ብቻ መርከቦች ለመንቀሳቀስ ይገደዳሉ፡፡

የባብኤል መንደብ ቢዘጋ ከፔርሺያ ሰላጤ የሚመጡ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ደቡብ አፍሪካ ጫፍ ዞረው ለመሄድ ይገደዳሉ፡፡ ይኼ ግን ነዳጅ ወደተፈለገበት ሥፍራ ለመጓጓዝ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል፡፡

በቀድሞው ዘመን የቀደሙት መንግሥታት ቀይ ባህርን ለአፍሪቃ፣ ለእስያና ለአውሮፓ ንግድ ሥራ ይገለገሉበት ነበር፡፡ ሆኖም በነዳጅ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ተሠርተው ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ፣ አውሮፓውያን ወደ ህንድና ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ሲያደርጉ፣ ቀይ ባህርና ባብኤል መንደብ ስትራቴጂካዊ ጥቅማቸው ዋጋ ቢስ ሆኖ ነበር፡፡

በኋላ የስዊዝ ካናል በመከፈቱ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ሊመለሱ ችለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1967 በእስራኤልና በዓረቦች መካከል በተከሰተው ‹‹የስድስት ቀን ውጊያ›› እስራኤል ስዊዝ ካናልን በመዝጋትዋ ምክንያት፣ ቀይ ባህርና ባብኤል መንደብ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው እምብዛም ሆነ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ1973 በእስራኤልና በዓረብ አገሮች መካከል ሰላም ሲፈጠር፣ ይኼ የባህር መንገድ እንደገና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ሊመለስ ችሏል፡፡ ይኼ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው በቋሚነት ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 40 በመቶ የሚሆነው ነዳጅ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በዚህ የባህር መንገድ ይጓጓዛል፡፡ በገንዘብ ሲመነዘር ወደ 700 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነዳጅ በዓመት በዚህ የባህር መንገድ ላይ ይስተናገዳል፡፡

ጂቡቲ በዚህ እጅግ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ዳርቻ የምትገኝ አገር በመሆንዋ ወታደራዊ ጠቀሜታዋ ከምንጊዜውም በላይ እየጎላ በመምጣቱ፣ ታላላቅ የዓለም መንግሥታትና ሌሎችም የሚመለከታቸው አገሮች በዚህ ሥፍራ በመገኘት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እየሞከሩ ነው፡፡

የባብኤል መንደብ የባህር ትራፊክ እንቅስቃሴን ቀጥሎ በተዘረዘሩት ሁኔታዎች በቀላሉ ማወክ ይቻላል፡፡

  1. የባህር ላይ ፈንጂ (Sea Mine) በመበተን
  2. በታጠቁ እጅግ ፈጣን አጥቂ ጀልባዎች በመርከቦች ላይ ሁከት በመፍጠር
  3. በአየር ጥቃት
  4. ከምድር በሚወነጨፉ ሮኬቶች
  5. በሌሎችም መሣሪያዎች

እ.ኤ.አ. በ1980 በኢራንና በኢራቅ መካከል በተከሰተው ግጭት የዚህ ዓይነት ሁከት በሆርሙዝ ስትሬት አካባቢ ተፈጥሮ፣ በፔርሺያ የባህረ ሰላጤ ለዓለም አቀፍ ንግድና ለነፃ የባህር ጉዞ መታወክ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተመረጡ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ነፃ የመርከቦችን ጉዞ ያውኩ ነበር፡፡

አሁንም የወቅቱ የአካባቢው ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በተመሳሳይ በባብኤል መንደብ የመርከቦች መተላለፍያ ላይ ይኼ ችግር የማይከሰትበት ምክንያት የለም፡፡

በየመን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተደረገ ጥልቅ ትንተና እንደሚያመለክተው፣ የየመን ሁቲዎችና ደጋፊዎቻቸው በአካባቢው አገሮች ላይ የሚያደርጉት ትንኮሳ ብሎም ጥቃት ጦሱ ከአካባቢው አገሮች ያለፈና ሌሎችንም የሚያውክ ነው፡፡

በአካባቢ ያሉ የሁቲ ደጋፊዎች በየመን የጦር አውሮፕላኖችንና የጦር መርከቦችን በማሠለፍ ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሁኔታ የባህረ ሰላጤውንና አካባቢውን ከበባ በማድረግ ሊቆጣጠሩት ይችላሉ፡፡ ይኼ ጉዳይ ደግሞ መዘዙ ብዙ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያንዣበበ አደጋ

ከላይ የጠቃቀስኳቸው መንደርደሪያዎቼ ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ለመግባት እንዲረዱኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በባብኤል መንደብ አካባቢ እየሆነ ስላለው ጉዳይና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ የትም ቦታ ያየሁት ወይም የሰማሁት ነገር በግሌ የለም፡፡ ሆኖም አይኖርም ብዬ ድምዳሜ ላይም አልደረስኩም፡፡ ነገር ግን ጭብጡን ባለማወቄ ብቻ ነው የለም እያልኩ ያለሁት፡፡ ሆኖም ጂቡቲ ይኼን አስመልክቶ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ቢገጥማት ጉዳዩ ኢትዮጵያን እጅግ በጣም የሚያሰጋ ይሆናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኛትን ትራንስፖርት ማለትም የባቡር መስመርና ሌሎችም ለኢኮኖሚ ዕድገት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እያጣደፈች በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚህ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የትራንስፖርት ግንባታዎች፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገሮች በሁለት አንገብጋቢ ጉዳዮች በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ እነርሱም ለንግድና ለወታደራዊ ተግባራት፡፡

ስለወታደራዊ ተግባር ካነሳን አይቀሬውን ሥጋት አስመልክቶ ዛሬ ሌሎች አገሮች እያደረጉ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በሥፍራው ምንም ዓይነት የባህር ኃይልም ሆነ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ተቋምና ዘላቂ ጥቅሟን ሊያስጠብቅ የሚችል በሥፍራው ያስቀመጠችው ነገር የለም፡፡ ጠንከር ያለ ችግር በሥፍራው ቢከሰት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ተጠቂ አገር ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ለጂቡቲም ሆነ ለባብኤል መንደብ በጣም ቅርብ አገር እንደመሆንዋ መጠን በአካባቢው ችግር ሲፈጠር ብሔራዊ ጥቅሟን በከፍተኛ ደረጃ ለመጠበቅ ጠንከር ያለ ወታደራዊ ኃይል በሥፍራው ሊኖራት ይገባል፡፡

ይኼ ማለት ግን ኃያላን አገሮች ዛሬ በሥፍራው ስላሉ ከእነሱ ጋር ለመወዳደር ሳይሆን፣ የእነሱን ቀድሞ መገኘት ሐሳብ በመደገፍና ለጥረታቸውም ተጨማሪ ኃይል ለማሠለፍ ነው፡፡ ዓላማው ዓላማችንን  የደገፈ ሆኖ በመገኘቱ፡፡

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአካባቢው ማውለብለብና የኢትዮጵያ ተዋጊ መርከብም በሥፍራው መታየት፣ በአካባቢው ለሚከሰተው ወታደራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው ለተከሰተው ችግር ዘላቂ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ምን ያህል የቆረጠች መሆንዋን ያመላክታል፡፡

በተጨማሪ ደግሞ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ አገር በመሆንዋ የባህሩ ጉዳይ ከማንም በላይ ያሳስባታል፡፡ እንዲሁም ቀድሞ ካለው ልምድ በመነሳት በአካባቢው የሚከሰት ማንኛውም ሥጋት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ብሔራዊ ደኅንነት ፀር ነው፡፡

በእርግጥም ወደ መቶ የሚጠጉ ወታደሮችና አንድ ሁለት የጦር ጀልባዎች ጂቡቲ ስናስቀምጥ የውጭ ምንዛሪ ማስወጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይኼም ብቻ አይደለም በአጠቃላይ በመከላከያ በጀትም ላይ ትንሸ ጫና ሊፈጥር ይቻላል፡፡ ሆኖም የጂኦፖለቲካል ምንነቱ ሲገመገም ጥቂት ገንዘብ ለዚህ ወሳኝ ጉዳይ መመደብ ጥቅሙ እጅግ የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ በምድርም ሆነ በባህር ሥጋት አላት፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በርከት ያሉ የንግድ መርከቦች በባህር ላይ አሰማርታ ገቢና ወጪን ንግዷን እያጧጧፈች ትገኛለች፡፡ በአካባቢው ውጥረት በሚከሰትበት ወቅት እነዚህ መርከቦች በባብኤል መንደብና በባህረ ሰላጤው ሲደርሱ በኢትዮጵያ የጦር መርከቦች ታጅበው ወደ ጂቡቲ ወደብ መድረስ አለባቸው፡፡ ሌሎች አገሮች እያደረጉ እንዳሉት ሁሉ እኛም የጦር መርከቦች አሠማርተን ጥቅማችንን ማስጠበቅ አለብን፡፡ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ብቻ ከባህር ርቀን እያለን ነገር ግን በምድር ዙሪያችን የተከበብን ብቸኛ የዓለም አገር እኛ ብንሆንም፣ የወደፊት ሥጋታችንን ከአሁኑ በመገንዘብ ከማያስፈልግ ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› አባባል ርቀን ብሔራዊ ችግራችንን በአግባቡ ለመፍታት ዛሬ ብቁ ሆነን ቀድመን መገኘት አለብን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ እየሆነ ላለው ሁኔታ ቀደም ብለን ባንዘጋጅም፣ የዓለም ኅብረተሰብ እኛ ወደንና ፈቅደን ከተቀላቀልነው በኮሌክቲቭ ሴኪዩሪቲ ጉዳይ ኢትዮጵያ በማንኛቸውም መሥፈርቶች ቀደም ብላ የታወቀች ናት፡፡ ለዚህም ምስክራችን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ በኮሪያ፣ በኮንጎ አሁን ደግሞ በአፍሪካ ችግሮች ሁሉ ቀደም ብሎ በመገኘት ችግር ፈቺ አገር መሆናችን ይታወቃል፡፡ ይኼ ጉዳይ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ቢሆንም፣ ሁሉም አገሮች በሥፍራው የተገኙት ለተመሳሳይ ዓላማ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቡድኑን መቀላቀል እጅግ በጎ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ለጥረታችንም በጎ ምላሽ እንደሚያደርጉ አያጠራጥርም፡፡ በዚህ ጥረት ላይ የኢትዮጵያ መሳተፍ በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲው ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት ዳግም በግልጽ ያረጋግጣል፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ የበጀት ጉዳይ ቀደም ሲል ማንሳቴ ያለምክንያት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በተለይም የባህር ኃይል ተልዕኮ (Operation) በወጪ በኩል ከሌሎች ኃይሎች ጋር ሲወዳደር ትንሽ ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ አጽንኦት ሰጥቼ ዘርዘር አድርጌ ለመግለጽ እገደዳለሁ፡፡ ይኼን ጉዳይ ወታደራዊ ዕቅድ አውጪዎችና ስትራቴጂስቶች በይበልጥ ይገነዘቡታል፡፡ አንድ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ወስነን መርከበኞችና መርከቦችን በሥፍራው ካሠማራን፣ በተመሳሳይ ዓላማ በሥፍራው የሚገኙ ኃያላን አገሮች የመርከብ ሥምሪት የሚያስከትለውን የበጀት ጫና ይገነዘባሉ፡፡ ተልዕኮአችን ከተልዕኮአቸው ተመጋጋቢ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከዚያ በላይ ደግሞ ከአካባቢው የወጣን ኃይል በመሆናችን በወጪ መጋራትና በሌላም ሁኔታ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቀደም ካለው ልምድ በመነሳት ቅን ዕምነቴን እገልጻለሁ፡፡

ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በወርቃማ ዘመኑ በቀይ ባህር ላይ ለተሠማሩ መርከቦች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሥፍራው በመድረስ ለተቸገሩበት ጉዳይ መፍትሔ ይሰጥ ነበር፡፡ ማለትም በአካል መሰርጎድ ምክንያት መርከብ በውኃ ሲጥለቀለቅ፣ የእሳት አደጋ ሲያጋጥማቸው፣ በናቪጌሽን ስህተት መሬት ላይ ሲወጡ፣ የቴክኒክ ችግር ሲከሰት፣ ወዘተ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል በተለይ በደቡብ ቀይ ባህር ቀድሞ በመገኘት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ዓለም አቀፍ ግዴታውን በብቃት ይወጣ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ያሉ አስገራሚ መሪዎች አንድ ሌሊት ቀይ ባህር ላይ ተንሳፋፊ አደገኛ ፈንጂ  በዘሩበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በቀይ ባህር ላይ የነበሩ መርከቦችን ከአደጋው እንዲርቁ በሬዲዮ በመምከርና ፈንጂውም ሲታይ አቅጣጫውን በሬዲዮ በማሳወቅ፣ መርከቦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የበኩሉን የዓለም አቀፍ ግዴታ ሁሉ ሲወጣ የነበረ ኃይል ነው፡፡

ለዓለም ሰላምና በጎ ተግባር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታወቁት የምድር ጦርና የአየር ኃይላችን ብቻ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያ የባህር ኃይልም የተቀረፀው ከወታደራዊ ግዳጁ ባሻገር ለበጎ ተግባርም እንደነበር በጥረቱ ይታወቅ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የአካባቢውን ጂኦፖለቲክስ ጠንቅቆ መረዳት እጅግ ብልህነት መሆኑን መገንዘብ አለባት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ኃያላን አገሮች ለጉዳዩ አጽንኦት በመስጠት በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ አካባቢው እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ እየተለዋወጠ ነው፡፡ የመንም ሉዓላዊነትዋን ብዙዎች እንደሚገምቱት ቶሎ አስከብራና አስጠብቃ እንደ ነፃ አገር የምትኖርበት ጊዜ ብዙም ቅርብ አይመስልም፡፡

በተጨማሪ ከየመን ዳርቻ በባብኤል መንደብ ከአካባቢ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ከምድር በተተኮሰ ሮኬት መርከቦችን ለማሸማቀቅ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም እንደ አጋጣሚ የተተኮሰው ሮኬት በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከብ ላይ በመሆኑ ወዲያው አፀፋ መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን የተተኮሰበትን ሥፍራ በግልጽ በአካባቢው ለሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች በማሳወቅ ወንጀለኞቹ በማያዳግም ሁኔታ ተደምስሰዋል፡፡ በዚህ ንቁና ፈጣን መልስ የተነሳ አካባቢው ከወንበዴዎች ከመፅዳቱ በተጨማሪ ለጊዜው ሥጋቱ ለመቀነስ ችሏል፡፡

ይኼን ሥጋት ለጊዜው ያቆመው የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል ነው፡፡ ይኼ አጋጣሚ በቀይ ባህር ላይ የንግድ መርከቦች ተሸማቀው እንዳይንቀሳቀሱ ሥጋት ሊፈጥር ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ቅፅበታዊ ዕርምጃ በመወሰዱ ለጊዜው ሥጋቱ ሊገታ ተችሏል፡፡

ጽሑፉን ከመደምደሜ በፊት ሳልጠቅስ የማላልፈው የኢትየጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት በባህረ ሰላጤው የባህር ወንበዴዎች ጥቃት ወቅት የወሰደውን ቆፍጣና ዕርምጃ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ የዚህ ግዳጅ አፈጻጸም ዝርዝር መረጃ ባይኖረኝም፣ በጉዳዩ ታስቦና ታቅዶ በችግሩ ወቅት አንድም የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ በወንበዴዎች ታግቶ ባለመወሰዱ፣ ይኼም አስቀድሞ የተደረገ ጥንቃቄና የብዙ ዝግጅት ውጤት ስለሆነ መልካም ጅምሩን ደግሞ አደንቃለሁ፡፡ አሁንም ችግሩ ለጊዜው ተዳፈነ እንጂ ጨርሶ ባለመወገዱ ቀደም ያለው ጥረት ግለቱ ሳይቀዘቅዝ ቢቀጥል እላለሁ፡፡

ዳግም በአጽንኦት ልገልጽ የምፈልገው ስለዓለም አቀፍ ማሪታይም ውዝግብና ድንገት በአገር ኢኮኖሚና ደኅንነት ላይ ስለሚያስከትለው አደጋ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይኼን ቅስም ሰባሪ ሁኔታ እንድትቋቋም አስቀድሞ መደረግ ስላለበት ቅድመ ዝግጀት ነው የማሳስበው፡፡ ኢትዮጵያ ይኼን አይቀሬ ሥጋት በመቋቋም የግዴታ የታጠቀና በብቃት የተደራጀ ተወርዋሪ ኃይል ጂቡቲ ላይ ሊኖራት ይገባል፡፡ ይኼን ካደረግን ስትራቴጂካዊ የሆኑ ሸቀጦቻችን (Strategic Commodities) ወደ አገራችን በሰላም ይገባሉ፡፡ የአገራችንም ደኅንነት በይበልጥ የተጠበቀ ይሆናል ብዬ በአጽንኦት አምናለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ኃያል አገሮችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አገሮች በጂቡቲ መሰባሰብ፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው ያላት የፀጥታና የደኅንነት አመለካከት በሚገባ መመርመር አለባት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ ባህር ኃይል አባል፣ የቀይ ባህርና የባህረ ሰላጤው አካባቢ ወታደራዊ ጉዳዮች ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡