በንግድ ሚኒስቴር የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ስብሰባ ምክንያት ሥራ ለሳምንት በመቋረጡ ተገልጋዮች እያማረሩ ነው

 

- የንግድ ፈቃድ ዕድሳትና ሌሎች አገልግሎቶች ተቋርጠዋል

ንግድ ሚኒስቴር ድንገት በጠራውና ለሳምንት በሚቆየው ‹‹የጥልቅ ተሃድሶ›› ስብሰባ ምክንያት ተገልጋዮች አማረሩ፡፡ በርካታ አገልግሎት ፈላጊ ባለጉዳዮች በስብሰባ ምክንያት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ ሳቢያ ከጥበቃ ሠራተኞችና ከበታች ኃላፊዎች ጋር አተካራ ሲገጥሙና ችግሮቻቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል፡፡

‹‹ለክቡራን ደንበኞቻችን ከዛሬ ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኞ ጥር 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በጥልቅ ተሃድሶ ውይይት ምክንያት በንግድ ሚኒስቴር ስብሰባ የምናደርግ ስለሆነ ማንኛውንም አገልግሎት የማንሰጥ መሆኑን እንገልጻለን!!›› ተብሎ የተጻፈውና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ ቅርንጫፍ ቁጥር 1 ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ ፊርማ ወጥቶ የተለጠፈው ማስታወቂያ፣ ምንም ዓይነት አገልግሎት አንሰጥም ማለቱ በርካቶች የሚኒስቴሩን አገልግሎት ፈላጊዎች አስቆጥቷል፡፡ አገልግሎት ፈልገው ወደ ሚኒስቴሩ የሄዱ ተገልጋዮችና ጥቂት ሠራተኞች ሲነታረኩም ታይተዋል፡፡

ይህ ማስታወቂያ ተግባራዊ መሆን በጀመረበት ዕለት በርካታ ባለጉዳዮች፣ ሒልተን ሆቴል ጀርባ፣ ካዛንቺስ ሱፐርማርኬት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደሚገኘው የንግድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቅንተዋል፡፡ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት አገልግሎት አታገኙም በመባላቸው ከጥበቃ ሠራተኞችና ከበታች ኃላፊዎች ጋር ክርክር ሲገጥሙ ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ ባለጉዳዮቹ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማስረጃዎችን፣ የክሊራንስ ማረጋገጫ ሰነዶችንና ሌሎችም አገልግሎቶችን ለማግኘት እንዳልቻሉ፣ በዚህም ሳቢያ በየቀኑ ለቅጣት እየተደረጉ እንደሚገኙ ከወዲሁ ቢገልጹም አጥጋሚ ምላሽ ማግኘት ሳይችሉ ለመመለስ ሲገደዱ ታይተዋል፡፡

ቅሬታ ሲያቀርቡ ከተደመጡ ባጉዳዮች መካከል አራት ሚሊዮን ብር የሚያወጡና በቻርተር አውሮፕላን እንዲጫኑ የታዘዙ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ የተዘጋጁ ባለሀብት አንዱ ነበሩ፡፡ ሚኒስቴሩ ለሚላከው ምርት የንግድ ፈቃድ ማረጋገጫ መስጠት ይጠበቅ በነበረበት ወቅት ስብሰባ ተብሎ አገልግሎት በመቋረጡ፣ ኪሳራቸውን ማን እንደሚሸፍንና ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ባለሀብቱ ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡

አገልግሎት በሚሰጥበት የሥራ ሰዓትን በመሻማት ሚኒስቴሩ ስብሰባ ጠቅልሎ መግባቱ ሕዝብን ለማገለግል የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን መተው ነው የሚሉ ትችቶችን ያሰሙ ተገልጋዮች፣ የሕዝብ ተቋማት እንታደሳለን በማለት የስብሰባ ክተት ማወጃቸውን እንደማይቀበሉት ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶቹም እንዲህ ያሉ ሥራን በመዝጋት ስብሰባ የሚጠራባቸው ሁኔታዎች ከሕግ አኳያ መጠየቅ እንደሚያስልጋቸውም ሲሞግቱ ተደምጠዋል፡፡

ለሚኒስቴሩ አዲስ የተሾሙት ዶ/ር በቀለ ቡላዶን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የበታች ሹማንምንትን ጨምሮ ተራ ሠራተኞች ሳይቀሩ ክተት በጠሩበት ‹‹የጥልቅ ተሃድሶ›› ስብሰባ ወቅት፣ በርካታ ባለጉዳዮች የሚያስተናግዳቸው አጥተው ላይ ታች ሲሉ ተስተውሏል፡፡ አልፎ አልፎም የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ከስብሰባው እየወጡ አጣዳፊና አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮች ብቻ መፍትሔ እየሰጡ ወደ ስብሰባው ተመልሰው ይገባሉ፡፡ ይሁንና ይህም ቢሆንም ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ባሉት ደቂቃዎችና በምሳ ሰዓት ወቅት ባለው የዕረፍት ጊዜ ላይ መሆኑም፣ ስብሰባው ምን ዓይነት ተዓምር እንደሚያመጣ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡

ተገልጋዮች ግን ለሕዝብ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ በስብሰባ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በር ዘግቶ በመሰንበት ለውጥ መምጣት ስለመቻሉ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ተገልጋዮቹም ማግኘት ባልቻሉት አገልግሎት ምክንያት እየደረሰባቸው ያለውን መጉላላት ሲያሰሙ ቢታዩም፣ ከሚኒስቴሩ ይህ ነው የሚባል ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ሲገልጹ ታይተዋል፡፡

 ስለዚህ ጉዳይ ሪፖርተር የሚኒስቴሩን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ከአዲሱ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ምደባ ቀደም ብሎ በተደረገ ሽግሽግ ምክንያት ከሚኒስቴሩ የተነሱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችን የተኩ ሰዎችን ማግኘትና መረጃ እንዲሰጡ ማድረግ ያልተቻለ ሲሆን፣ ስለተሃድሶው ስብሰባና ስለሚኖረው ውጤት፣ ስለሚያስከትለው ለውጥ መረጃ የሚሰጥ አካል ማግኘት አልተቻለም፡፡

በአገሪቱ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ እንዲነሳና በየመሥሪያ ቤቶቹም ስብሰባ እንዲያካሂድ አስገድዶታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት የ2007 አገር አቀፍ ምርጫን መቶ በመቶ ባሸነፈ በሁተኛው ዓመቱ ሹም ሽር በማካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ ካቢኔ እንዲያዋቅር የተገደደበት ፖለቲካዊ ውጥረት በአሁኑ ወቅት እየረገበ መጥቷል፡፡ ይሁንና በሕዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በማለት የሚካሄዱ ስብሰባዎች ግን እንደ ንግድ ሚኒስቴሩ ያሉት አካሄዶች ከወዲሁ አገልግሎት እያቋረጡ መካሄዳቸው ቅሬታ ማስነሳታቸው አልቀረም፡፡ ይህም ቢባል ግን ሚኒስቴሩ ያቋረጣቸውን አገልግሎቶች እንደሚካክስ ይጠበቃል፡፡