በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለ2.8 ሚሊዮን ሕፃናት የትምህርት መሣሪያ ድጋፍ ተደረገ

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ድጋፍ ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በድርቅ በተጎዱት አፋር፣ አማራ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ በኢትዮጵያ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ባሉ ወረዳዎች ለሚገኙ 2.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች 8.2 ሚሊዮን ደብተሮችንና 5.5 ሚሊዮን እስክርቢቶና እርሳሶችን መስጠቱን የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የድጋፉ ዓላማ በአገሪቱ ከባድ በተባለው ድርቅ ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናት የመማር መብት እንዳይጓደል መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ እነዚህን የትምህርት ቁሳቁሶች አገር በቀሉ የኅትመት ድርጅት የካቲት ወረቀቶች እንዲሁም በአሜሪካ የሚገኙ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት እንዲያቀርቡ መደረጉም ተገልጿል፡፡ የደብተር፣ የእስክርቢቶና እርሳስ ድጋፍ የተደረገላቸው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ሲሆኑ ዕርዳታዎቹ ለተማሪዎቹ ይደርሱ ዘንድ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልል ትምህርት ቢሮዎች ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ተጠቁሟል፡፡

የተደረገው የትምህርት መሣሪያ ድጋፍ በድርቅ ተፅዕኖ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት እንዲቀጥል ሕፃናቱም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማስቻሉን የዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሌዝሊ ሪድ ተናግረዋል፡፡