በጥላቻ የተከፋፈለና የተነካከሰ አደገኛ የትግል ጎዳና

ገዢዎች “እኛ በሥልጣን ላይ ካልቆየን አገር ትበታተናለች፣ መፋጀት ይመጣል” እያሉ እንዲያስፈራሩና እንዲከፋፍሉ አቅም የሚሆናቸው፣ የምርጫ ክንዋኔዎችንም የአንድ ፓርቲ መፈንጫ እንዲያደርጉ ፈቃድ የሚሰጧቸው የሕዝቦችና የትግሎቻቸው ድክመቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተባዛው የማንነት ምድሮችን በመፍጠር ውስጥ መትረክረክና ብሔረሰባዊ መሥፈሪያን የንግድ ሥራ መያያዣ እስከ ማድረግ የተጣበበ ጎጆኛነት የሕዝቦችን ትኩረት በታትኗል፣ ፖለቲካዊ ዕይታቸውንና ጉልበታቸውን ከታትፏል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ስለምንገነባው አንድ የፖለቲካና፣ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ቢደነግግም፣ የማንነት ጥያቄና ተግባራዊነት በተወሰነ ምድር ላይ ባለቤትነትን የማስከበርና የመተሳሰብ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የቅርጫው ትግልም እስከ ትንንሽ ወረዳዎች ድረስ ዘልቆ የእኔ ነው ባዩ ንትርክና ግብ ግብ በዚያው ልክ ተባዝቷል፡፡ በሌላ ጎን የተወሰነች ምድር “ባለቤቷ” ታወቀ ማለት የገዢነቱ መብት የማን እንደሆነ ተለየ ማለት ነውና የባለቤትነት መብት ከፀደቀለት ማኅበረሰብ/ማኅበረሰቦች ውጪ ያሉ ወገኖች ባይተዋርነት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ይኼንን ተከትሎም ”የባለቤት”/የዋና ማኅበረሰብን መብቶችና ዕድሎች አብልጦና አስፍቶ የንዑሳኑን ወይም “የባይተዋሮች”ን የማሳነስና የማጥበብ ድርጊት ተገቢ ሆኖ ብቅ ይላል፡፡ “ያገሩ” ባለቤት ከሆኑ ማኅበረሰብ ሰዎች ይበልጥ በሀብት የከበረ “መጤ” በዚያ ካለ በዘራፊ ዓይን መታየቱ  አይቀርለትም፡፡ የእሱን ብጤዎች መድፈቅና የእኛ የሚባሉ ቱጃሮች መፍጠር ዓላማም ይሆናል፡፡ አድልኦና አበላላጭነቱ መቆሚያ የለውም፡፡ ከትምህርትና ከሥራ ዕድሎች አንስቶ እስከ ሕግ ማስከበርና እስከ ዳኝነት ሥራ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ በማስፈራራትም ሆነ በማሳበቢያ ጥፋት በ‹‹መጤ›› ላይ የማባረር ዕርምጃ መውሰድ ላያስገርምና ቀጪ ላያገኝ ይችላል፡፡ ምክንያቱም “ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናቸው” የሚል ኢሕገ መግሥታዊ አስተሳሰብ፣ እንኳን በአካባቢው ያሉትን በፌዴራል ደረጃም የተቀመጡ ሹሞችን ሳይቀር ሲያሳስት ይታያል፡፡ በመጤዎች ላይ ጥቃት የማድረስ ድርጊት እየተደጋገመ የተፈጸመው (በቅርቡ በ2008 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም. ቁጣ ጊዜም የተከሰተው) የክፍልፋይነት ርዕዮተ ዓለምና ተግባሩ ስላልታረመ፣ የትም እኩል የመኖር (ቢያጠፉም ባሉበት ሥፍራ ያለ አድልኦ በሕግ ፊት የመቆም) መብት ስላልተቋቋመ የዜግነት እኩልነት በቀፎው የቀረ ስለሆነ ነው፡፡

እናም በግልና በጅምላ ሲካሄዱ የኖሩ አድልኦዎች ያመረቷቸው የመቃቃር፣ የቂምና የጥላቻ ማጦች የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ የመተሳሰብና የመተጋገዝ አቅም እንዲዝል አድርገዋል፡፡

መቃቃርና ጥላቻ ህሊናን እየመዘመዘ ምክንያታዊ አስተሳሰብን ይከለክላል፡፡ የመበቃቀል ፍላጎትን እየቀሰቀሰ ተስማምቶ የመኖር ብርታትን ያነክታል፡፡ በደሎችን በአንድ ላይ እምቢ የማለት ኅብረትን ከማሳጣቱም በላይ፣ ለመጫወቻነት አጋልጦ ይሰጣል፡፡ ከዚያም አልፎ መቋሰልና ጥላቻ  ደርጅቶ ሲቆይ የሚያስገኘው የመጨረሻ ውጤት እርስ በርስ እየተፋጁ መጠፋፋት ነው፡፡ ይኼንን የቀመሱና በእኛ የደረሰ በእናንተ እንዳይደርስ እወቁበት የሚል ማስጠንቀቂያ የሚረጩ ልምዶች በአፍሪካም ሆነ ከአፍሪካ ውጪ በርካቶች ናቸው፡፡ ግን ቆም ብሎ ትምህርት መውሰድና አካሄድን ማረም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገና ደካማ ነው፡፡ በተለይ በመንግሥት በኩል እሳት ብልጭ ሲል ከመንከውክውና እሳት ከማጥፋት ያለፈ ዘላቂ መፍትሔ ማድረግ የዋዛ ችግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአገዛዙ ርዕዮተ ዓለምና ብሒል ከዚህ ማለፍን የሚቀናቀንና የንቁሪያ ጣጣዎችን የሚፈለፍል በመሆኑ ነው፡፡

አንድ አገር ብቻውን ተነጥሎ ዕድገቱንና ሰላሙን ማስጠበቅ የማይችልበት (የአገሮች ዕጣ እርስ በርስ በእጅጉ የመመረኳኮዙ) ዓለማዊ እውነታ የማያሳየን የለም፡፡ የአንድ አሜሪካ የምርጫ ሒደትና ውጤት ብቻውን እንኳ አኅጉራዊና አኅጉር ዘለል የፖለቲካ፣ የጦርና የንግድ ሽርክናዎችን ያላላ/ያናጋ ይሆን ብሎ እስከ ማስጨነቅ ድረስ፣ የገንዘብ ምንዛሪንና የአክሲዮን ገበያን አዝማሚያ እስማደናገር ድረስ፣ በኢትዮጵያ ብጤ አገሮች ዘንድም ዕርዳታንና ከታሪፍ ነፃ የሆነ የገበያ ዕድልን ያሳጥፍብን ይሆን የሚል ሥጋት እስከ ማሳደር ድረስ የዓለምን የተሳሰረ ዕጣ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡ የእኛ አገር ገዢዎችና ከእነሱ ጋር ዕይታቸው የገጠመ ብሔረተኞች ግን፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ህልውናና መጪ ዕድል በአገር ደረጃ ተግባብቶ በመኖር ላይ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተጣጥመው በመተሳሰራቸው ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን፣ በዴሞክራሲዊ ፌዴራላዊነት አብሮ መኖር የቢሻኝ ጉዳይ ሳይሆን፣ መባላትን አምልጦ ሰላምና ዕድገትን የመቀዳጀት ግድ መሆኑን ጨብጦ የማስጨበጥ ተግባርን ግራ እያጋቡ ይገኛሉ፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የቀጠለችው ብሔረሰቦቿ በመፈቃቀዳቸው እንደሆነ፣ ብሔረሰቦች የዕድሎቻቸው ብቸኛ ወሳኞች እንደሆኑ፣ መነጠልና አለመነጠልም የውዴታቸው ጉዳይ እንደሆነ አድርጎ ከሚደልል ቀጣፊ ግንዛቤ ጋር ይዳራሉ፡፡ ብሔረሰባዊ የፖለቲካ ቡድን ፈጥሮ “የማንነት” ቤትን ማቋቋምና በየወገን መሽቀዳደምን ማኅበራዊ “ንቃት” እያደረጉ ሕዝብን የክፍልፋይነት እስረኛ ያደርጋሉ፡፡

በተለይ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ያለው መወነባበድ በሁለት ተቃራኒ የፖለቲካ መስመሮች የሚካሄድ ነው፡፡ መንግሥታዊው “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” ፈቅደህ ኢትዮጵያዊ ሆነሃል፣ የብሔር ጥያቄህ ተመልሷል፣ ሉዓላዊነትህ ከነይዞታህ ተረጋግጧል፣ አብሮ የመኖርም ሆነ የመለየት መብትህ ተከብሯል ሲለው፣ በተቃውሞ በኩል ከኦነግ ጀምሮ ሲሰባ የኖረ መስመር ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነት/ሐበሻነት በግድ የተጫነብህ የግፍ ተገዢ ነህ ይለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካልተበታተነች የኦሮሞ ነፃነት አይገኝም የሚለው የፖለቲካ ሥሌትም በቅርቡ ለንደን ውስጥ የተገኘ አይደለም፡፡ ለመነጠል የሚጠቅም ቁጭትና በቀል ማደራጃ አድርጎ ታሪክን መተርጎም ከተጀመረ እንደቆየ ሁሉ፣ የአቢሲኒያውያን ኢምፓየር ሲፈራርስ ብሔረሰቦች ነፃ ይወጣሉ፣ ከእነሱ ውስጥ በግዙፍነት ኦሮሞን የሚያይል አይኖርምና ኦሮሞ ዳግመኛ ነፃነቱን የማጣት ሥጋት አይኖርበትም፣ እንዲያውም ኩሾችን አሰባስቦ ትልቅ የኩሽ  አገር ገንቢ ይሆናል የሚል በቀለኛ ንድፍ በፅንፈኞቹ ተነድፎ አዕምሮን ሲሰረስር የኖረው ገና ድሮ ነው፡፡ ዛሬም ይኼንኑ ንድፍ በገዳዳም ሆነ በቀጥታ የሚሰብኩ ሐሳቦች እየተበተኑ ነው፡፡

በዓለማችን ውስጥ እየታየ ያለው ማለቂያ ያጣ የቀውሶች ልምድ፣ ጨፍጫፊ መንግሥታትን በኃይል/በአመፅ ገርስሶ የዴሞክራሲ ለውጥ የማካሄድ ፍላጎትን አስደንግጧል፡፡ የአመፅ መንገድ የታሰበውን ለውጥ ያመጣ ይሆን? ወይስ የባሰ መተላለቅና ሥርዓት አልባነት ውስጥ ይከት ይሆን? ብሎ እስከ መሥጋትና ዴሞክራሲ ናፋቂ አመፀኞችን ለመደገፍ እስከ መቸገር ድረስ ግራ አጋብቷል፡፡ ከዚህ ማዕዘን አገር በትኖ የቁራሽ ምድር “ነፃነት” የማግኘት ሥሌት ሲመዘን፣ ከእብደት በላይ የገሃነም መላዕክተኛ መሆን ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ መበታተን ለማንም የማይበጅ (ኤርትራን፣ ጂቡቲን፣ ሱዳኖችን፣ የሶማሊያ ክፋልዮችንና ኬንያን ሁሉ ጠልፎ የሚያስገባ፣ ከእስላማዊ አሸባሪነትና ከተሻጋሪ የውኃ ጥቅም ጋር የተወሳሰበ የእርስ በርስ መተላለቂያ) መሆኑ የማይታየው ቢኖር ማየት ያልፈለገ ብቻ ነው፡፡

በሌላ ጎን በስተኋላ የተገለጡ የታሪክ መረጃዎችና ትንታኔዎች የ‹‹ኩሽ›› ኦሮሞ ሕዝቦች ሰሜን ኢትዮጵያ ድረስ ከጥንት ጀምሮ እንደ ነበሩ፣ “ሴም” በሚባሉ ቋንቋዎች ውስጥ የሚታዩት “ኩሻዊ፣ ኦሟዊ” የቋንቋ አሻራዎች ቢያንስ ቢያንስ የኩሽ ቋንቋዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበሩ (የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች በኩሽ የሕዝቦች ባህር ውስጥ እንደነበሩ) የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በድምሩም በሰሜኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ ውስጥ “ኩሾች”ና ጥንተ ኦሮሞዎች እንደ ነበሩበት እንድንቀበል የሚያስገድድ ነው፡፡ ዛሬ ባለንበት እውነታም፣ ባልተቋረጠ የሕዝብ ሥርጭትም ሆነ እዚያም እዚያም በተዥጎረጎረ መልክ አገሪቱን በሰፊው አሸብርቆ የሚገኝ ኦሮሞ ነው፡፡ በቀሪዎቹ ብሔረሰቦች ታሪካዊ ማኅበረሰባዊ እነፃ ውስጥም ኦሮሞ ሥጋና ደም ሆኗል፡፡ ራሱም በሞጋሳና በጉዲፈቻ ልዩ ልዩ ሕዝቦችን በተለያየ ጊዜ እየቆረሰ ኦሮሞነትን አንጿል፣ አግዝፏል፡፡ በዚህም ኦሮሞነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪካዊ ነፀብራቅ ከመሆኑ ባሻገር አገሪቱን እንደ መርፌ ሰፍቶ አያይዟታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኦሮሞነት የኢትዮጵያ ትልቅ አገርነት ዋና ዋልታ መሆኑን የሚያሳዩ ገጽታዎች “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” ባይነትንና ተነጣይነትን ከራስ ጋር እንደመጣላት ትርጉመ ቢስ ያደርጉታል፡፡

የመነጠል ፍላጎት በሻዕቢያም ሆነ በኦነግ እንዳየነው ቀዳሚ ተግባሩ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ውጪ የሚያደርግ ሸለቆ መፍጠር መሆኑ እውቅ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ የመነጠል ዝንባሌ ለረዥም ጊዜ የኦሮሞ ትግል ውስጥ መቆየት መቻሉና ኦሮሞነት የኢትዮጵያ ሕዝብች ነፃነት ዋና ሞተር የሆነበት እንቅስቃሴ አለመመዘዙ እንቆቅልሽ ነው፡፡

ኦሮሞ ላይ ግፈኛ ዘመቻ በታሪክ ውስጥ መፈጸሙ እንቆቅልሹን ይፈታዋል እንዳይባል፣ የዚያ ዓይነት የግፍ ታሪክ ከዓለም አገሮች ሁሉ ጀርባ ያለ ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያም ውስጥ የተካሄደው ዘመቻ በኦሮሞ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የአገሪቱ ገዥነት ለረዥም ዘመናት ከአማራና ከትግሬ በወጡ መሳፍንትና መኳንንት ቁጥጥር ሥር መቆየቱ፣ የ1960ዎች ጊዜም የአርነት ትግሎች የደሩበት ዘመን የነበረ መሆኑ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ትግል በደርግ ከተደመሰሰ በኋላ ሜዳውን የተቆጣጠሩት ብሔረተኛ ትግሎች መሆናቸው፣ ብሔረተኛ ጉዞን ትክክለኛ አስመስሎት ስለነበር ይሆናል የሚል ትንታኔም ብዙ አያስኬድም፡፡ ከሻዕቢያና ከሕወሓት ድል በኋላ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የተገኘው ልምድ “ዴሞክራሲ”፣ “ነፃነት” የሚሉ ቃላት እየለጠፉ የበረሃ ትግል ውስጥ መግባት ለዴሞክራሲና ለነፃነት መገኘት ዋስትና እንደማይሆን፣ ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ እንደማይደገስ፣ ዴሞክራሲ በእውነተኛ ኑሮ ውስጥ የሚለፋበት ከምርጫ የዘለለ፣ የአቋሞች ብዙነትና ጥል የለሽ ውድድር የሚኖርበትና መብቶችና ኃላፊነቶች የተግባቡበት የአዲስ ሕይወት ግንባታ እንደሆነ አስተምሯል፡፡ በመራራ ቅያሜ የተሞላ ብሔረተኛ ትግል ከፋፋይና ነጣጥሎ አስጠቂ መሆኑ የማያከራክር ጉዳይ ሆኗል፡፡

ይኼ ሁሉ ትምህርት የተገኘበት ያሁኑ የታሪክ ምዕራፍ የኦነግን አሮጌ መስመር የጣዕረኛ መፈረጋገጥ ያደረገው ቢሆንም፣ ሁለት ፀጉር ያበቀሉ ብዙ ነባር ታጋዮችም የመነጠል መንገድ በፀረ ዴሞክራሲ ውስጥ ሲማቅቁ መኖር ወይም የአገር ተያይዞ መጥፋት መሆኑንና የሚበጀው ኃይልን አስተባብሮ ነፃነትና እኩልነት የተቋቋመበት ፌዴራላዊ አገር መገንባት መሆኑን ቢገነዘቡም፣ ግንዛቤውና አብሮ የመኖር ትልሙ በብሔረተኛነት ዕይታ ውስጥ የተሰነከለ የቢቸግር መፍትሔ ከመሆን አልራቀም፡፡ በዚያው በብሔርተኛ ግቢ ውስጥ የኦሮሚያን ድርሻ መተሳሰብና እንዳይቀነስ አፍጥጦ መጠበቅ፣ ኦሮሞ ግዝፈቱን የሚመጥን የሥልጣን ወንበር ማግኘት አለማግኘቱን ማሰላሰል፣ በኦሮሚያ የተፈጥሮ ሀብት ብልጫ እየተመኩ የማጫረስ ደባ እንዳይፈጸም ወደዚያ የገባ ኦሮሞ ያልሆነን ሥራ ከፋች ሁሉ በጥያቄ ምልክት ውስጥ እያስገቡ መብከንከን ህሊናን ይረብሻል፡፡ የመንግሥት የፀጥታ ክትትልና አፈና በብሔረተኛ ተቃውሞ ላይ ሲበረታ ኦሮሞን ለይቶ የማጥቃት ዓላማ ገዢው መንግሥት ያለው አድርጎ መብገን፣ በዚያው በብሔረተኛነት ውስጥ ያለን ስህተተኛ የትግል ብቸኝነት ከማስተዋል ፋንታ ከሌላው የተለየ ተበዳይነትን የማጦዝ ሰበበኛነት ፀረ ጭቆና ትግሉን ተጭኖት ይታያል፡፡ ኦሮሞን ከሚመለከቱ የብቻ ጉዳዮች ታልፎ፣ ኦሮሞ ማለት መላ አገሪቱ የማለት ያህል መሆኑን ባጤነ ዕይታ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲና የእኩልነት የጋራ ጥያቄዎች ላይ አንደኛ ደረጃ ትኩረት ቢደረግ፣ ወዲያውኑ የኦሮሞ የብቻ ትግልና የብቻ ጥቃት ብሎ ነገር መላ አገርን የሚመለከት ወደ መሆን እንደሚቀየር፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ ያለ የመተማመን ጉድለት ባንዴ እንደሚሞላ ጥርጥር የለውም፡፡ ይኼንን አለማጤን ትልቅ ድክመት ነው፡፡

ይኼ ብቻም አይደለም፡፡ በዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ ነፃነቶች የፈኩባት የተባበረች አገር በመገንባት የትግል መስመር ውስጥ ባሉት የነባር ትውልድ ፖለቲከኞችና በአሁኑ ወጣት ትውልድ መካከል ቅርብ የፖለቲካ ተራክቦ አለመኖሩ፣ አገዛዙም ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ዳተኛ መሆኑና በተቃውሞ ላይ የሚያሳርፈው በትር የሚያስከትው የስሜት መጎሽ የመነጠል ዝንባሌ ግባዓተ መሬቱ እንዳይፈጸም እያደረገ ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ዛሬ ምን ያህል ተከታይ  እንዳለው መገመት ከባድ ቢሆንም፣ የኦሮሞን በቅኝ ውስጥ መሆን የሚያወሩ መጻሕፍት ኅትመትና ሥርጭት እያገኙ መምጣታቸው፣ እንዲሁም ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነት ውጪ አድርጎ ማየት በወጣት ኦሮሞዎች ዘንድ እየጨመረ መሆኑ ወይ የመነጠል ፍላጎት እያንሰራራ መሆኑን፣ አለዚያም ራስን ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ማድረግና ባርነት ውስጥ ነን ብሎ ማለት አገዛዙን መፃረሪያና መበቀያ መደረጉን ይጠቁማል፡፡ ሁለቱም ዝንባሌዎች አይቃረኑም፡፡ የጎሸ ስሜትን የሚገራና የሚያሰክን የፖለቲካ ሥራ እስካልተካሄደ ድረስም እነዚህ ደም ፍላት የጠነነባቸው ዝንባሌዎች የቀውስ አጋጣሚ ሲያገኙ፣ ኦሮሞንና ሌላውን ሕዝብ የሚለመጥጥ እሳት የማስነሳታቸው አስፈሪነት አፍጥጦ ይቆያል፡፡

ጥበት የለብንም ለአንድነት የቆምን ነን በሚሉ ወገኖች በኩል መፈራራትንና ጥላቻን ለማሸነፍ የማያበቁ ችግሮችን እናገኛለን፡፡ ከቀላሉ ብንጀምር ብሔረተኛነትን ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ሥውር መርዝ ወይም የአንድነት ፀር አድርጎ ማየትና ማጥላላት ለአንድነት መጠናከር አንዳችም ጥቅም አለመስጠቱ፣ ጭራሽ በተቃራኒው እልህ እያጋባ መራራቅንና መቋሰልን የሚያባብስ መሆኑ ገና በአግባቡ አልተጤነም፡፡

“የዱሮ ሥርዓት ለመመለስ የሚሻው የአማራ ትምክህት” የሚል ማብቂያ ያጣ የካድሬ ውትወታና መጤዎችን (በተለይም አማሮችን) የማፈናቀል ዶሴ እስከ ዛሬ ድረስ አለመዘጋቱ እስከዚህ ድረስ አማራ በምን ኃጢያቱ ነው የተጠመደው? ከማንም በበለጠ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ደሙን ስላፈሰሰ ነው? የሚል እንቆቅልሽ ፈጥሯል፡፡ በሕወሓትና በትግራውያን ዘንድም፣ ትግራዊን የደመኛ ያህል የሚያይ ጥላቻ የተስፋፋው ስለምን? የትግራይ ልጆች ከማንም ይበልጥ በፀረ ደርግ ትግል መስዋዕትነት ከፍለው ለሁሉም የተረፈ ለውጥ ስላመጡና አሁንም ለኢትዮጵያ ልማት በግንባር ቀደምነት እየተዋደቁ መሆናቸው ጥፋት ሆኖ? የሚል ግራ መጋባት አለ፡፡

ተራው አማራና ትግራዊ በእነዚህ እንቆቅልሾች ውስጥ ቢወዘወዝ አያስገርምም፡፡ ትምህርት የዘለቁ አማራና ትግራዊ ፖለቲከኞች እንቆቅልሹን እንደ ጋቢ ተከናንበውት (በዘረኞች እኩይነት እያመካኙ) መቆየታቸው ግን እውነቱን ለመጨበጥ ካለመቻል ይልቅ እውነቱን ከመሸሽና  በማላከኪያ ራስን ከማታለል የመጣ ነው፡፡ በየትኛውም ኅብረ ብሔራዊ አገር ውስጥ ሥልጣነ መንግሥት ከአንድ ወይም ከጥቂት ማኅበረሰቦች በመጡ ገዢዎች የበላይነት ሥር እስከ ወደቀ ድረስ ለገዢዎቹ መገኛ ማኅበረሰቦች የሚተርፍ ጥላቻ እንደሚፈጠር፣ “የእኔ ወገኖች ሥልጣን ያዙ” የሚል መመካት ብዙ ማናለብኝነት እየወለደ ጥላቻንና ብግነትን እንደሚያራባ፣ በኢትዮጵያ የትናንትናና የዛሬ ኑሮ ውስጥ ማጤን ከባድ አይደለም፡፡ የአማራና የትግራይ ብዙ ትምህርት ቀመሶች ግን ይኼን ማስተዋልና መቀበል ሲተናነቃቸው ይታያል፡፡

ለአማራ መጠመድ የሥረ መሠረት መዘዝ የነበረው የአማራ ገዢዎች የተከማቹበት ቅድመ ኢሕአዴግ አገዛዝ እንደነበር ሊካድ አይችልም፡፡ የአገዛዙን መገርሰስ ተከትሎም “ነፍጠኞች”ን የመበቀል ስሜትን፣ ግጭትንና መፈናቀልን የማይመለጥ ያደረገው ችግሩ ትክክለኛና አርቆ አስተዋይ የፖለቲካ አያያዝ አለማግኘቱ ነበር፡፡ ከዚያም ወዲያ በተለያየ ዘዴ “መጤ” መግፋትና ማባረር ብቅ ጥልቅ ሲል የቆየው ሥልጣን ላይ የወጣ ጎሰኝነት “ፀረ ትምክህት ትግል”ን የግል ዝርፊያን ለመሸፈን፣ የሕዝብ ቅዋሜን ለማደናገርና ዒላማ ለማሳት ስለሚጠቀምበት ነበር፡፡ ከመአሕድ ጀምሮ ብሔረተኝነት ጠንቄ ያለ የፖለቲካ ስብስብ መልክ እየቀያየረ መቀጠሉም ለዚህ ዓይነቱ አጭበርባሪ ቀዘፋ መገልገለያ ሆኗል፡፡ እነዚህ እውነቶች በቅጡ አልተጨበጡም፡፡ “ሰው በላ”ን ሥርዓት በሚያመጣ “የአማራ ትምክህት” የሚያስፈራራውን የዛሬ ገዢዎች ብልጣ ብልጥነትን እንደምን ማክሸፍ ይቻላል የሚለው ጥያቄም በአማራ ፖለቲከኞች ዘንድ እስካሁን መልስ አላገኘም፡፡

ለኢትዮጵያ የተከፈለውን መስዋዕትነት ከሌላው የማስበለጥ ማናህሎኝነትም ጥላቻን ለማሳፈርም ሆነ ለማስወገድ የማይጠቅም፣ እንዲያውም ትዝብት ላይ ሊጥልና ጥላቻን ሊያብስ የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ረዥም የአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ አማራነትን ዘርግቶ ለማየት ቢሞከር የሚደረሰው ራሱ በራሱ እየተዋለደ የመጣ ሕዝብ ዘንድ ሳይሆን ከብዙ ምንጮች የተዘማመደ ጥንቅር ዘንድ ነው፡፡  የጎጃሜነትን፣ የወሎዬነትን፣ የጎንደሬነትን፣ የመንዜነትን፣ የምንጃሬነትን፣ ወዘተ የቅርብ ታሪካዊ ጀርባ ጫን ብንለው ኦሮሞነት፣ አገውነትና ትግሬነት እዚያና እዚህ ፍጭጭ ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የ“አማራ” ስያሜ ነባር አጠቃቀም ከሥፍራ አመልካችነቱ ሌላ፣ ቢያንስ ክርስትናን የሚከተሉ ማኅበረሰቦችን ሁሉ የሚሸፍን እንደመሆኑ “አማራ” እያለ የሚያወሳን ትረካ ሁሉ ለአንድ ዓይነተኛ ብሔረሰብ መስጠት ስህተት ላይ መውደቅ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሰሜን እስከ ታች ድረስ በተሳተፉበት የፀረ ፋሽስት አርበኝነት ጊዜ፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረን የትግል መደብዘዝ ለአማሮች የትግል ብልጫ ማነፃፀሪያ ለማድረግ መሞከር ጅል ድንቁርና ወይም ሚዛን መሳት ነው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ላይ የፈጠረው ማስኮረፍ፣ በሰሜንና በደቡብ የነበረው የመሬት ሥሪት ልዩነት፣ ወራሪው ጣሊያን ጭሰኝነትን መሰረዙ፣ የአርበኝነት ትግሉ ደግሞ በአያሌው ከመኳንንታዊ መሪነት አለመራቁና ጭሰኝነት ዳግም የማይመለስበትን ሥርዓት የማቋቋም ዓላማን አለማንገቡ፣ በአንድ ላይ የአርበኝነት ትግሉን ፋይዳ ፋሽስቶች ያስወገዱትን ጭሰኝነት እንደገና ለማስመለስ ከመዋደቅ ጋር አመሳስሎት ነበር፡፡ እንደዚህ ያለው ‹አይውጡት አይተፉት› የሆነ ሁኔታ፣ የፋሽስት ወራሪው ከፋፋይነት ተጨምሮ፣ የተወሰነ አካባቢ ላይ ፈጥሮት የነበር መፍዘዝ በለጥኩ ብሎ ለመመፃደቅ እንደማይመች መረዳት ይበጃል፡፡

ከኢሕአዴግ ሥልጣን ወደዚህ በትግራዊ ብሔረሰብ ላይ ያረፈው “ቅያሜ” መንኮታኮትም የግድ ሕወሓትን ማንቀርን አይጠይቅም፡፡ ወይም ኢሕአዴግ ከሥልጣን እስኪወርድ ድረስ መዘግየት አይኖርበትም፡፡ የአገሪቱ ሥልጣነ መንግሥት ምሰሶዎች ከቡድን ታማኝነት ያለ ቀውስ  እንዲፀዱና ለመላው ሕዝቦች ሉዓላዊነት ብቻ እንዲያድሩ ሆነው እንዲታነፁ በፓርቲ ውስጥና ከፓርቲ ውጪ መታገል፣ እንዲሁም የግለሰቦችን ጥላቻ አበራካች እብሪቶች ያለ ጎሰኛ ሽፋን ማጋለጥ ጎልቶ ቢወጣ የሚመጣው የበጎ ስሜት ለውጥ ፈጣን ከመሆኑም በላይ፣ ጥላቻን አፍረክርኮ ሆድ ለሆድ ለመገናኘት የሚያስችል ነው፡፡ ይህንን የመሰለ መልካም ውጤት ከሚያስገኝ እንቅስቃሴ ብዙ ሰዎችን ገትተው የያዙት ችግሮች ተከታዩ ውጤት በጎ ስለመሆኑ እርግጠኛ አለመሆን (አገዘዙን ገለልተኛ አደርጋሁ ሲባል በቀል በትግራዊ ላይ ሊዘምት ቢችልስ የሚል ሥጋት)፣ እንዲሁም ይችን መሰሏን “ፍርኃት” በማናፈስ ውስጥ ተሸሽጎ የሚካሄድ ጥቅም አባራሪነት ናቸው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በእነዚህ ችግሮች ውስጥ አንቀላፍቶ መቆየትና አለመቆየት፣ ፈንጂ ቀብሮ አጋጣሚ እስኪረግጠው በመጠበቅና ከወዲሁ በብልኃት በማምከን መካከል ምርጫ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ በጥላቻዎች ተነክሶና ተከፋፍሎ መኖር ለማንም የደህንነት ዋስትናም መፍትሔም አይሆንም፡፡ የብሔረሰቦች መብቶች ተጨባጭነት የሚያገኙትና የሚዘልቁት ከሕዝቦች የጋራ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ጋር በደንብ መግባባት እስከቻሉ ድረስ ነው፡፡ የብሔረሰቤ ሰው ይግዛኝ በሚል ዕይታ ውስጥ መቅለጥ ተከፋፍሎ ለመረገጥ መመቻቸት ነው፡፡ የጋራ መብቶችን ማጣት የብቻ መብትንም ማጣት ነው፡፡ የንዑሳንና የመጤ ማኅበረሰቦች መብት እንዲረገጥ መፍቀድ የራስንም መብት ማስረገጥ ነው፡፡ የሕዝቦችን ኃይል የሚከፋፍል የበደልና የኩርፊያ ተጋሪ ሆኖ፣ ተቃራኒ ሐሳብን በውንጀላና በዱላ ከማጥቃት ድርጊት ለመውጣትና ተደማምጦ ለመወያየት ሳይጣጣሩ ዴሞክራሲንና ነፃነትን ለማግኘት መጓጓትም አፍ ገጥሞ ለመጉረስ እንደመመኘት መላ ቢስ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡