አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

በጥልቀት የመታደስ ‹የጥበብ መጀመርያ› ሕገ መንግሥቱን ማክበር ነው

በገነት ዓለሙ

የኢሕአዴግን ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ውሳኔ ከሰማንና የአዲሱን ህዳሴ አጀማመር፣ አያያዝና አንዳንድ አፈጻጸሞችም ጭምር መታዘብ ከጀመርን እነሆ ሦስተኛው ወር ውስጥ ነን፡፡ ሦስት ወር በጣም አጭር ጊዜ ቢሆንም አያያዙን አይተን እንቀማው የምንለውና የምንልበት አቅም ባይኖረንም የተሃድሶውን ሪፖርት ወሬና ዘገባ የሚቀርብበትና የሚሰማበት አሠራር ግን፣ አሁንም እንደ ቅድመ ተሃድሶው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት መሆኑ አጠራጣሪ አልሆነም፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት ሚኒስትርነት መታደል አይደለም፣ ኢሕአዴግነት የሥልጣን መቆናጠጫ መሣሪያ አይደለም ብሎ የከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ሹም ሽር ቢያደርግም ከሥልጣን የወረደውም ሥልጣን ላይ የወጣውም ጥፋትና ብቃት ዛሬም ጉም እንደለበሰ ነው፡፡ የሕዝብ ዓይንና ተሳትፎ ያላገኘው ሹም ሽር በብዙ አሉባልታ ሲታመስ ቆይቶ ደግሞ በአሥራ አምስት ቀኑ አካባቢ የተሰማው የአምባሳደር ሹመት ዜና በአሿሿም ሥርዓታችንና አሠራር ‹‹ተሃድሶ›› ላይ መልሶ ሌላ ጥያቄ፣ ጥርጣሬና ሥጋት አቀጣጥሎ አልፏል፡፡ የተሾሙት አዳዲሶቹ አምባሳደሮቻችን የተመደቡበት አገርም ዛሬም ‹‹የመንግሥት ሚስጥር ነው››፡፡

ለማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች (ሚኒስትሮች) የሹም ሽር ዕርምጃ መነሻ ወይም የዝግጁነት መነሻ ሆኖ ያገለገለው በኢሕአዴግ ውስጥ በተለይም በእያንዳንዱ አባል ድርጀት ውስጥ የተካሄደው ግምገማ ነው ብሎ መገመት እንዳይችል እንኳን፣ በአንፃራዊነት ቶሎ ግዳጁን ጣለ ሒሳቡን አወራረደ ከተባለው ከኦሮሚያው ገዢ ፓርቲ በስተቀር የሌሎቹ የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብ ክልል ገዢ ፓርቲዎች ግምገማ ውጤት ወሬ ዛሬም ድራሹ እንደጠፋ ነው፡፡

ኢሕአዴግ እውነትም በጥልቀት መታደስ ከፈለገ ያለቀላቸውን ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየዳፉ፣ እያጋለጡ ለእዚህ ያበቁትን ችግሮችና ክስረቶችን ሁሉ መቀበሉንና እነሱንም ለማስወገድ ቆርጦ መነሳቱንና ትክክለኛውን የአፈጻጸም መንገድ መከተሉን፣ ከራሱ ውጪ ሌሎችን ወገኖች የማድመጥ ለውጥ ማድረጉን፣ የኢትዮጵያን ዕድገት ከራሱ መስመሮችና ዕድል ጋር አንድ አድርጎ ከማየት ጉድጓድ መውጣቱን ማሳየትና ማረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህ ሰፊና አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ግልጽነት አንዱ ግን ከፍተኛ ጉዳይ ያለው ገጽታና ግዴታ ነው፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ኢሕአዴግ ምን ታደስኩ ቢል፣ ምን በጥልቀት ቢታደስ፣ የራሱን ሥልጣንና ተቀባይነት በዋነኛነት ሲገዘግዝ የኖረውና ጠላት ያበዛው፣ እንዲያ እያለም ለ2008 ዓ.ም. ሁከትና ለ2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ራሱ መሆኑን ከማወቅና ከመረዳት ህዳሴውን መጀመር አለበት፡፡

የኢሕአዴግ የመጀመርያው ችግር ‹‹እኔ ብቻ ልክ›› ማለቱ ነው፡፡ ይኼ እኔ ልክ ነኝ ከማለት ይለያል፡፡ ትክክለኛነትና እውነተኛነት የእኔ ብቻ ነው ይላል፡፡ ደርግን የመሰለ ወታደራዊ ኃይል ማሸነፉንና ድል አድርጎ አዲስ አበባ መግባቱን፣ የውጭ አገር መንግሥታትንና ተቋማትን ብድርና ዕርዳታ እንዲሁም ዕውቅና ማግኘቱን ሁሉ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የትክክለኛነቱ ማስረጃ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉና ዛሬም የብቸኛ ትክክለኛነቱ ማስረጃ አደርጎ የሚያቀርበው ዛሬም ድረስ ያለ ጠንካራ ተቃዋሚ መገኘቱን ጭምር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሰላማዊ ተቃውሞን መጥላቱንና በጭራሽ የማይፈልግ መሆኑን ለኢትዮጵያም እንደማያስፈልጋት ‹‹ያወጀው›› ገና አዲስ አበባ እንደገባና ጊዜያዊ መንግሥት እንዳቋቋመ፣ ያለ ተቃዋሚ የመንግሥት ሥራውን ማካሄድ አለመቻሉን እንደ ልዩ ሴራና ተንኮል ቆጥሮ መጋፋትና መምታት ሲጀምር ነው፡፡ ሌላው ሌላው ነገር የመጣው ይኼንን ሕመም ተከትሎ ከእሱ በኃላና በእሱ ምክንያት ነው፡፡

በ1993 ዓ.ም. ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመብት ጥያቄ ጋር የተሳሳበ ዘረፋ የቀላቀለ ቁጣ ያስነሳበት፣ ከኦሮሚያ ዋና ከተማ ወደ አዳማ መዞር ጋር የተያያዘ ቁጣን ያመጣበት፣ ‹‹የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ልማት›› ማለት ኦሮሚያን ያንቀጠቀጠ፣ መላ አገሪቱን ያዳረሰ፣ ‹‹በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይችል›› አደጋ ጋር ያጋፈጠውም የራሱ ኢዴሞክራሲያዊነት መሆኑን ዛሬም ኢሕአዴግ መረዳት የተሳነው ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ ይኼንን ኢዴሞክራሲያዊነቱን ከማንም ጠላት በላይ ፈርቶና ጠልቶ በተግባር ማራገፍ ካልቻለ ጥልቅ ተሃድሶውን ትርጉም የለሽ ያደርግበታል፡፡

የዴሞክራሲ መጀማመሪያው ዴሞክራሲያዊነትና ዴሞክራሲን ለማስገኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ደርግ ከተሸነፈ በኋለ የሦስት ዓመት የሽግግር ዘመን ያስፈለገው የኢሕአዴግን ጨምሮ የሌሎችን የፖለቲካ ኃይሎች ሐሳቦችና ራዕዮች በሰላማዊና በሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የሚብላሉበት መነሻ የዴሞክራሲ ሁኔታዎችን ለማቋቋም ነው፡ በዚያውም በሐሳቡና በዕምነቱ ለኢትዮጵያ በደገሰላት ራዕይ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ወይም ፖርቲዎች ሥልጣን የሚይዙበትን፣ ከሥልጣንም የሚወርዱበትን ቅድመ ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡ አሁን ኢሕአዴግን የፈለገውን ቢል ስለምርጫ ያሰኘውን ቢናገር የሆነውና የተለየው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የሽግግሩ መንግሥት አድራጊ ፈጣሪ ከዚህ በኃላም በአምስት ምርጫዎች ከሥልጣን የማይወርድ ወይ ሥልጣን በጭራሽ የማያጋራ ፓርቲ ያደረገው፣ ሐሳቦቹ አሸናፊ ሆነው ማለትም በኅብረተሰቡ በአብዛኛው ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው አለመሆኑ ዛሬ እነ ሱዛን ራይስ እንኳን በሳቅ እየፈረሱ የሚመሰክሩት ሀቅ ለመሆን በቅቷል፡፡

ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተቋቁሟል ባይ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋሚያው እውነተኛው መሠረት የሕዝብ ድምፅ ነው፡፡ በድምፅ ማጭበርበርንና ሌሎች በምርጫ ሒደት ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጉዳይ ትተን፣ አገራችን የምርጫ ድምፅና የሕዝብ ድጋፍ የተግባቡባት አገር አይደለችም፡፡ ሌላ አመለካከት እንዳይወስድብኝ ችግር እንዳይገጥመኝ ተብሎ ወደ ምርጫ መውጣትና ያልወደዱትንና ያልፈቀዱትን፣ ጨርሶ የማያውቁትን መምረጥ በአዲስ አበባ ጭምር የታየና የሚታወቅ ነገር ነው፡፡

ኢትዮጵያም ሆነ ሌላም አገር ውስጥ የምርጫ ድምፅና የሕዝብ ድጋፍ ተግባብተው በእውነተኛ የሕዝብ ድምፅ የተቋቋመ መንግሥት መኖር ራሱም ቢሆን ግን ለዴሞክራሲ መኖር ዋስትና አይሆንም፡፡ ለዴሞክራሲ መቋቋም ዋስትናው መራጩ ሕዝብ መብቶቹን አለማስነካቱና ሥርዓቱ ቀጣይነት ማግኘቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያሰናከለውና የገዛ ራሱን አምሳያ የማይገኝለት ሐውልት ምሥረታ ያጨናገፈው እዚህ ላይ ነው፡፡

ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መረጋገጥ የሚካሄደው ትግል በስብሰባና በሠልፍ፣ በመጮህም ሆነ በምርጫ ውድድር በመሳተፍ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ እዚህችም ስብሰባና ንግግር ውስጥም ኢሕአዴግ ጣልቃ ይገባብናል፡፡ የሚፈቀደውን፣ የሚከለከለውን ይወስንልናል፡፡ የምንናገረውን ይሰፍርልናል፡፡ የትግሉ ግንባርና መልክ ግን ከስብሰባ ከሠልፍ፣ ከምርጫና ከውድድር ተሳትፎ በላይ ነው፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ሰጪና ተቀባይ የማይኖርባቸው፣ በተፈጥሮ የተቀዳጀናቸው ናቸው ሲባል እኛ አገርም በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ እኛ የምንገኘው ግን ሥልጣን ላይ የወጣ አካል ሲያሻው ሊነጥቀን በማይችልበትና በማናስችልበት ማኅበራዊ ልማት ውስጥ አይደለም፡፡ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን በየዕለቱ በምንኖረው ሕይወት ውስጥ ሥር የያዙ መሆናቸው አጠያያቂ ነው፡፡ ከፖለቲካ በመለስ ባሉ ጉዳዮች እንኳን ከራሳችን የተለዩ ሐሳቦችን ለመስማት ቻይ የሆንን ሐሳባችን ሲተች የኩርፍያና የሐሜት ቀስት የማናስፈጥር ምን ያህሎች ነን? ይኼ ለኢሕአዴግ አባላት በተለይም ለከፍተኛ አመራሮች ጭምር በግለሰብ ደረጃ የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡

ለዴሞክራሲ ስንታገል ኖረናል፣ ዛሬም እንዲሟላ እንታገላለን እንላለን፣ ይሉናልም፡፡ ትግሉ ግን የታጋዮችን መታደስም ይመለከታል፡፡ ዴሞክራሲን እየዘመሩ በኢዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አሠራር በፓርቲ ደረጃ ጭምር መጠመድ አንድ ጥኑ ችግራችን መሆኑ በጭራሽ አይካድም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ እያለ በመረጃና በዕውቀት መከራከርን፣ አለመግባባትን በውይይት መፍታትን ለመለማመድ አለመጣር ይጋጫሉ፡፡ አመራርና ሥልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ ብዙ ሰዎችና ቡድኖች በዚህ ግጭት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የተፈቀደልንን ያህል በዓይናችን የምናየው ይኼንኑ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ነን በሚሉ ማኅበራትና ድርጅቶች ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሠራርንና አወሳሰንን አክብሮ መምረጥ፣ ተመራጭን በተወሰነ ዘመን ውስጥ እያደሱ፣ ወሳኝነት በአንድ ግለሰብ እንዳይሰባሰብ አድርጎ፣ ከአመራሩ መርሐ ግብርና ፍላጎት ውጪ ስብሰባ የማስጠራት ወይም የመጥራት መብትን አስከብሮና የአመራሩን ሥራ በየጊዜው ማወቅ (ቃለ ጉባዔ ባስፈለገ ጊዜ እስከማየት ድረስ) መከታተልና መመርመር የሚቻልበት ሥርዓት ዘርግቶ መንቀሳቀስና እዚህ አገር ገና የለም፡፡

የፓርቲ አመራር ላይ እኔ ካልተቀመጥኩ ወይም እከሌ ካልተቀመጠ ፓርቲው እንዳይሆን ይሆናል ባይነት ከኢዴሞክራሲያዊነት ወይም ከፓርቲ የውስጥ ዴሞክራሲ የለሽነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ በልዩ ልዩ መድረኮች ሐሳብን ማንሸራሸርና ሐሳብን በሐሳብ መርታት ይቻላልና ፓርቲን ለመምራት ግድ ወንበር ላይ መተናነቅ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ይኼ በእኛ አገር ገና ነው፡፡ የዴሞክራሲ ደንቦች እንደ ወግ ዕቃ፣ በሕገ ደንብ ውስጥ ከመስፈር ባለፈ እውነተኛ ‹‹መተዳደሪያ›› ሲሆኑ አይተን አናውቅም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን፣ ሥልጣን ላይ የወጡትን አገር የሚገዙትን ጨምሮ፣ በዴሞክራሲያዊ ባህርያቸው አርዓያ ሊሆኑ ቀርቶ ከመንታ አቋም የተላቀቁ አልሆኑም፡፡ በይፋ ፕሮግራምና በመድረክ ላይ የሚንፀባረቅ አፋዊ አቋም፣ በድብቅ ደግሞ የሚራመድ እውነተኛ አቋምና ባህርይ በብዙዎቹ ላይ ይታያል፡፡ በዴሞክራሲያዊነት ለውጥ እንዳይቀጥሉ አንድ ትልቅ ችግር የሚሆንባቸውም ይኼ መንታ ባህርያቸው ነው፡፡

ይህ ምን እንደሚመስል ምሳሌ ለመስጠት በቅርቡ ጥቅምት መጀመርያ ሳምንት ላይ አዲስ አበባ በሸራተን አዲስ በተካሄደው ‹‹የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ›› ስብሰባ ውይይት ላይ አንድ ወጣት ልጃገረድ ያቀረበችውንና መልስም አስተያየትም ሳይሰጥበት በዝምታ (ምናልባትም በዝምታ ሴራ) የታለፈውን ጥያቄና ሐሳብ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጠያቂዋ (ቆይቶ ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የበኩር ልጅ ሰምሃል መለስ መሆኗን ያወቅኩት) በውይይቱ ሒደት ውስጥ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የተወካዮች ምክር ቤት የበላይነትና በአስፈጻማው አካል ላይ ያለው የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ትክክልና ዕውን መሆን እንዳለበት አውስታ፣ በተመሳሳይም የፓርቲ የሥልጣን አካላት ተዋረድም መክበር ያለበት መሆኑን ገልጻ፣ ከፓርቲው ጉባዔ፣ ከፓርቲው ምክር ቤት፣ የፓርቲው ምክር ቤት፣ ከፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ በላይ መሆኑን ጨምራ አስታውቃ በፓርቲው የላይኛው የሥልጣን አካል የተሰናበቱ አመራሮች ከእሱ በታች በሆነ አካል ለምን ተመለሱ ብላ ጠይቃለች፡፡

ኢሕአዴግ ዛሬም ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ፣ ከ2008 ዓ.ም. ተቋውሞና ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ በኋላ ሰፊ ድጋፍ አለን ብሎ የመንቀባረር ወጉን ባይተወውም፣ በአመዛኙ ራሱና ‹‹አጋሮቹ›› ሲዋኙበት የነበረውን ምርጫ ለደጋፊ ምስክር አድርጎ መጥቀሱና መከራከሩ ባይቀርም፣ ድጋፍ ኪሳራውን ግን መደበቅ አልቻለም፡፡ በየጊዜው እየከፋ የሄደው ተቃውሞና ቁጣ ያሳጣው፣ መቶ በመቶ ያሸነፈው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት የሆነው የአምስተኛው ፓርላማ አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ ወር መጀመርያ ላይ ነው፡፡ እንዴት ዴሞክራሲ ውስጥ ያለ አገር የአንድ ፓርቲን መቶ በመቶ አሸናፊነት በምርጫ አረጋገጠ ይባላል? ተብሎ ሲጠየቅ፣ ባለሁለት ዲጂት ዕድገት የማስመዝገብ የአሥራዎች ዓመታት ሪከርድ ያለው መንግሥት መመረጡ ምን ያስደንቃል? የሚል መልስ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ኅዳር በኋላ ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱ ኢሕአዴግን ያልመረጡትን ሕዝቦች እንዳገለለ ማሳበቢያ ሆኖ ቀረበ፡፡ ኢሕአዴግ አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ተቋውሞ መስማት እንደተሳነው ነው፡፡ ከተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎችና ጥቅሞች ጋር ቋንቋ ለቋንቋ መግባባት እንዳቃተው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሌላው መሠረታዊ ችግር የኢትዮጵያን ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም እንዲሁም ዕድገት ከራሱ መስመርና ዕድል ጋር አንድ አድርጎ ከማየት ጉድጓዱ ገና አልወጣም ማለቱ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢሕአዴግ ይኼንን አቋም ‹‹ብሔራዊ መግባቢያ›› ሊያደርገው መፈለጉ ነው፡፡

አንድ አቋም ወይም መስመር የሁሉ ሰውና የሁልጊዜ መስማሚያ ሊሆን አይችልም፡፡ በሕገ መንግሥት መተዳደርና ሥልጣን መቀባበል፣ በሕገ መንግሥት መንግሥትን ግልበጣ አለመቀበል እነዚህ አቋሞች በዛሬው ዓለማችን ሰፊ ተቀባይነትና ትግግዝ ማግኘት ችለዋል፡፡ ከሶሲዮ ኢኮኖሚ ሕይወት ትርታነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው፣ እኔ በሥልጣን ላይ ካልዘለቅሁ ልማቱ ያቋርጣል፣ ይቀለበሳል፣ እኔ የጀመርኩትን ልማት ሌላው ሊቀጥለው አይችልም ባይነት ግን፣ የኅብረተሰብ የጋራ መስማሚያ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ለምንድነው ኢሕአዴግ የጀመረውን ሌላው ሊያስቀጥለው የማይችለው? ሌላውን ሌባ ኢሕአዴግን ብቻ ግን እጀ ንፁህ የሚያደርገው ምን ተዓምር ነው? ለዚህ ሁሉ የኢሕአዴግ ሰዎች ‹‹ኪራይ ሲሰበስቡ›› (ትርጉም ሲሰርቁ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ያየበትን ዓይን ጋርዶ ኢሕአዴግን በእግዜር የተመረጠ መሆኑን ከሚያሳምነን ዓይነት መልስ በስተቀር መርቻ አይኖርም፡፡

ኢሕአዴግ በዚህ አቋሙ ተፈጻሚነት ምክንያት ብቻ የምርጫ ሥርዓቱና የእሱም ቅድመ ሁኔታዎችና አጃቢ ልዩ ልዩ መብቶች እንዳይሠሩ ከልክሎና አሰናክሎ ኖሯል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስከዛሬ ድረስ የባለብዙ ፓርቲዎች ዴሞክራሲ ታወጀ ከተባለ በኋላም በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ ያለመኖሩ ትርጉም የኢሕአዴግ ካለ እኔ በስተቀር ባይነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫና በአማራጭ ፓርቲዎች መንግሥት የሚቀያየር ስለመሆኑ ተስፋም ዕምነትም የሚያሳድር ምንም ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የለም፡፡

ኢሕአዴግን በአማራጭነት በምርጫ የሚፈታተን ብርቱ ፓርቲ ያለመኖር ችግር አንዱ የኢትዮጵያ የጎን ውጋት ነው፡፡ ዋናው ባለጉዳዮች ተቋዋሚዎች ቢሆኑም ኢሕአዴግም ከደሙ ንፁህ ነኝ የማይልበት የአገር ሕመም ነው፡፡ አሉ የሚባሉ ተቃዋሚዎች ተባብረውና ተጠናክረው ቢመጡ እንኳን ከ‹‹አብዮታዊ ወገናዊነት›› ነፃ የሆነ የምርጫ ውድድር ሜዳ የማግኘቱ ጉዳይ ራሱ ብርቱና ክፉ ፈተና ነው፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ቢሳካም ያለትርምስና እንደገና አፍርሶ መገንባት ሳይኖር፣ የአገርና የሕዝብን የተረጋጋ ጉዞ ሳያደናቅፍና አለመረጋጋት ሳይኖር ሥልጣን መረካከብ የሚቻልበት ፍጥርጥር ኢትዮጵያ ውስጥ ገና የለም፡፡ ኢሕአዴግ እንደምንም ወርዶ ተቃዋሚ ፓርቲ ሥልጣን ቢጨብጥ እንኳን አዲሱ ገዢ የነባሩን ገዢ ቡድናዊ አሻራና ቁጥጥር ለማፅዳት ሲል መንግሥታዊ አውታራትን እንደገና አፍርሼ ልሥራ፣ ላጠናከር፣ ላድስ፣ ወዘተ ማለቱ አይቀርም፡፡ ገዢው ፓርቲ ራሱ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ አማራጭ ሆኖ መጥቶ አሸንፎ ሥልጣን ላይ እንዲወጣና ገዢው ፓርቲ በተራው ተቃዋሚ ሆኖ በሰላማዊ ትግል ውስጥ እገባለሁ ብሎ አይደፍርም፣ አይተማመንም፡፡ ከሥልጣን ወርዶ ተቃዋሚ ሆኖ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የመቆየት ነፃነት መብትም ሆነ ዕድል በጭራሽ አይታየውም፡፡ ይኼን ሁሉ ያመጣው ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታራትን አለመገንባታችን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲም ለራሱም የነፈገው ገዢ ፓርቲ ከሥልጣን ወርዶ ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃዋሚ ሆኖ የመዝለቅ ነፃነቱን ጭምር ነው፡፡

ትግሉ ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታራትን አልገነባንም ብቻ ሳይሆን፣ የገነባነው የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀናበሩ መንግሥታዊ አውታራትን በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ታምነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምርጫ አሸንፎ መንግሥት የሚያቋቁመውንና በአንፃሩም ከሥልጣን የሚወርደውን በሰላም ሊቀበሉና ሊሸኙ አይችሉም፡፡ አምባገነንነትንም ሆነ የፓርቲ ወገናዊነትን ያገለግሉ ዘንድ ተጠፍጥፈው የተሠሩ መንግሥታዊ አውታራት ከዚህ በተጨማሪ ሁነኛ ብልሽታችን ናቸውና የመልካም አስተዳደር መፍለቂያም በጭራሽ አይደሉም፡፡

ኢሕአዴግ እውነትም በጥልቀት መታደስ ካለበት በመላው ቢሮክራሲ ውስጥ እስከ መጨረሻው የከተማና የገጠር ቀበሌ መዋቅር ድረስ ሥጋና ደም ሆኖ የተንሰራፋበትን፣ ፓርቲውንና መንግሥትን አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጎ አገር ያመሰቃቀለውን አሠራሩንና ሥርዓቱን መጀመርያ በማነወርና በማውገዝ ህዳሴውን መለኮስና ማቀጣጠል አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየተቋማቱና በሲቪክ ማኅበራቱ (በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በመምህራን፣ በሠራተኞች ማኅበራት) እንደ ሰርዶ ውስጥ ለውስጥ ተሰረጫጭቶ ሥርና ጅማት ሆኖ የመኖር አሠራር ከዴሞክራሲ ጋር እንደሚጣላ አውጆና አውግዞ ለህዳሴው መተማመኛ መስጠት አለበት፡፡ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ እየገቡ ተይቶ የማይታወቅ ‹‹የቤተሰብ ፖሊስ›› አቋቁማለሁ እስከከማለት ድረስ ከልካይ ያጣውን የሕዝብ ስነጋ አቋርጦ፣ ሕዝብ በሥራ ቦታውም ሆነ በመኖሪያ አካባቢው በፈለገው ዓይነት በነፃ የመደራጀትና ነባር ማኅበራቱን የማደስ መብቱን ያለሥጋት በተግባር እንዲያውል በሩ ወለል ተደርጎ መከፈት ይገባዋል፡፡

አሁን በዘረዘርናቸው መለወጥ አለባቸው ባልናቸው ሁኔታ ውስጥ መኖራችንን ግዴታ ወይም ተገቢ የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም፡፡ ልማታችንም ሆነ አንድነታችን ከአምባገነንነት ይልቅ ዴሞክራሲን ከአንድ ቡድን ጠቅላይነት ይልቅ የፖለቲካ ቡድኖችን መተባበር ይጠይቀናል፡፡ ኢሕአዴግን በጥልቀት ታድሶ የማየት ዴሞክራሲንና ልማትን በማጎዳኘት ከአምባገነንነት በተቃራኒ የመቆም ጉዳይ ከዴሞክራሲ ጎን ቆሞ  የመታገል ጉዳይ፣ ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሕይወት እንዲያገኙ ማድረግ ለሕገ መንግሥቱ መቆም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡