አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

በ70 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይድነቃቸው ተሰማ የወጣቶች እግር ኳስ አካዴሚ ተመረቀ

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራችና መሪ በነበሩት በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም የተመሠረተው አካዴሚ በቢሾፍቱ ከተማ ተመረቀ፡፡

‹‹ይድነቃቸው ተሰማ የወጣቶች እግር ኳስ አካዴሚ›› በሚል የሚታወቀውና በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው አካዴሚ መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የመረቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ኢሳ ሐያቱ ናቸው፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የተገነባው በ24 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው አካዴሚው ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎችና ጂምናዚየምን አካቷል፡፡ 100 ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን የእንግዳ መቀበያ፣ የመመገቢያ አዳራሽና የጤና ማዕከላት ተገንብቶለታል፡፡

አዲስ አበባ በምታስተናገደው 39ኛው የካፍ ጉባኤ ለመገኘት የመጡት ፕሬዚዳንቱ ኢሳ ሃያቱ፣ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በአፍሪካ ስኬታማ ለመሆን የበቁት በስፖርቱ ያለፉ ተጨዋች፣ አሠልጣኝና የአስተዳደር ሰው ስለነበሩ ነው ብለዋል፡፡ የአካዴሚ መገንባት የአገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስታዲየሞች በመንግሥት እየተገነቡ መሆኑን አውስተው የግል ተቋማትም በስፖርቱ ዘርፍ አብረው መሥራት ከፈለጉ በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አካዴሚው አቅም እስከሚፈጥር ድረስም ሞሐ፣ ደርባና ሆራይዘን ፕላንቴሽን በጋራ 50 በመቶውን እንዲሁም ቢጂአይ ኢትዮጵያ 50 በመቶ ወጭውን እንደሚሸፍኑለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ንዋይ በየነ ተናግረዋል፡፡

ለመገንባት አሥር ዓመት የወሰደው አካዴሚው ሥራውን ሲጀምርም በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ታውቋል፡፡