ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር ለማሰናሰል ሕገ መንግሥታዊው የማንነት ጥያቄዎች አፈታት ሚና

ውብሸት ሙላት

በዚህ ዓመት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ሥራቸውን ሲጀምሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ትኩረት ካደረጉባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ያልተመለሱ የማንነት ጥያቄዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ስለዚሁ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ምንም እናኳን ከዓመት በፊት የማንነት ጥያቄን መልሰናል ቢሉም፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች ግጭት እያስከተሉም ከመምጣታቸው በተጨማሪም የዕውቅና አሰጣጡ ሒደት ወጥ አለመሆን አድሏዊ ወይንም ለጊዜው እንዲጠቅም ከሚል መነሻ የመመለስ አዝማሚያን አልታደገውም፡፡ በሽግግር ዘመኑ ጊዜ ‘ብሔርነት’ ይገባናል ባይሉም መንግሥት 63 ብሔረሰቦችን ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ በኋላ ደግሞ ስልጤ፣ አርጎባና ቅማንት በጥቄያቸው መሠረት ታውቀዋል፡፡ በእርግጥ የአርጎባዎች ጥያቄም ሆነ መልስ በለሆሳስ የተከናወነ በመሆኑ ብዙ አቧራ አላስነሳም፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ከአሥር በላይ ብሔረሰቦች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ የመንጃ ማኅበረሰብ ዕውቅና ተነፍጎታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ጥያቄ ካነሱ 20 ዓመታት የሞላቸው አሉ፡፡ በመሆኑም ከማንነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ላይ እልባት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ላለፉት 26 ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት የተቸረው በደርግ ዘመን የነበረውን ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለውን ሙሉ በሙሉ በመቀየር ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ይቅደም›› የሚመስል አካሄድ በመሆኑ ‘ለኢትዮጵያዊነት’ ወይንም ‘ለኢትዮጵያዊ ማንነት’ ሥጋትነቱ እየጨመረ የመጣ ይመስላል፡፡ በዚህ ዓመት በተከበረው 11ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከወትሮው በተለየ አኳኋን ስለ ኢትዮጵያዊነት ስሜትና መንፈስ መጠናከር አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥተው መናገራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በ2008 ዓ.ም. በአገሪቱ የተከሰተው ብሔር ነክ ግጭት የሥጋቱን የአሳሳቢነት ደረጃ ያሳያል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦች ባህልና ልዩ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ላይ እንጂ አንድነታቸውን በሚመለከት የተጣለበትን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ በአግባቡ አለመወጣቱን ያሳያል፡፡

ይባስ ብሎ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን (በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያዎች) እንደምንታዘበው ‘ኢትዮጵያዊ’ የሚባል ማንነትም የሚሉ ወገኖችም እየተበራከቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ የዜግነት ጉዳይ እንጂ ማንነት ጋር ግንኙነት የለውም የሚል ክርክርም ያቀርባሉ፡፡ ዜግነት አንድ ግለሰብ ከአንድ አገር ጋር ያለው ሕጋዊ ግንኙነትን የሚያመለክት ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ደግሞ አርበኝነትን ወይንም በእንግሊዝኛ ‘Patriotism’ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የሚመለከት ነው፡፡ አርበኝነት አንድ ሰው ለአገሩ የሚኖረውን ፍቅር፣ መውደድ፣ ታማኝነት ወዘተ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ዜግነታቸው የሌላ አገር የሆነ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ፍቅርና ታማኝነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዜግነት፣ ለኢትዮጵያዊነት መሠረት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆን ኢትዮጵያዊነት አይተካውም፡፡ ጥሩ ማሳያው ባንዳ የሆኑ ዜጎች መኖራቸው ነው፡፡

 የኢትዮጵያዊነትን ፍቅር፣ ስሜት፣ ታማኝነት የሚጋሩ ሰዎች ሁሉ አንድ የሚጋሩት ማንነት ወይንም ልዩ የሚያደርጋቸው መገለጫ አላቸው ማለት ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ግን ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚመለከት ሳይሆን ብሔርን መሠረት ያደረገውን ማንነት ነው፡፡ ዋና ዓለማውም ብሔርን መሠረት ያደረገውን ማንነት እንዴት መስተናገድ እንዳለበት አንዳንድ ነጥቦችን ማቅረብ ነው፡፡ አሳሳቢ የሆኑትን ማስተካከል ስንችል የኢትዮጵያዊ ማንነትም አብሮ በትይዩ እንደሚያድግ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ብሔር ላይ የተመሠረተውን ማንነት በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻልን ውሎ አድሮ ትልቁ ማንነታችንን (ኢትዮጵያዊነትን) መፈታተኑና መሸርሸሩ አይቀሬ በመሆኑ ነው፡፡

የማንነት ጽንሰ ሐሳብ

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት በዋነኛነት የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚችሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ የዚህ መብት ተጠቃሚ ለመሆን ግን አስቀድመው ከእነዚህ ከሦስቱ አንዱን መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ የብሔርነት ወይም የብሔረሰብነት ወይንም የሕዝብነት ዕውቅና ማግኘት ማግኘት አለባቸው፡፡ ከአንቀጽ 39 በረከት ተቋዳሽ ለመሆን ዕውቅና የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው ማለት ነው፡፡

እንደ ዕውቁ የማንነት ፖለቲካ ፈላስፋ ቻርለስ ቴለር፣ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ዕውቅና ከማግኘት፣ ከአማናዊነት (Authenticity)፣ በልዩነት ከመታወቅና ከእኩል ክብር መቀዳጀት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ አማናዊነት የሚያመለክተው አንድ ማኅበረሰብ ማንንም ለመምሰል ሳይጥር እውነተኛው ራሱን መሆንን ነው፤ የራሱን አመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጠቃላይ አኗኗር ዘዬ ተከትሎ መኖር ነው፡፡ ‹‹የሠለጠነ›› ለመባል ሌላ ብሔርን መምሰል ወዘተ አማናዊ የሆነ ባሕርይ አይደለም፤ ማስመሰል ነው፡፡ በመሆኑም ማንነት አማናዊ የመሆን ግስጋሴ ነው፡፡ የሥልጤ ማኅበረሰብ የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ሲያነሳ ያደረገው አማናዊ ማንነቴ ሥልጤ እንጂ ጉራጌ አይደለም እያለ ነበር ማለት ነው፡፡

ማንነት ከዕውቅና ጋርም በቀጥታ የተዛመደ ነው፡፡ የዕውቅናን ነገር ጀርመናዊው ፈላስፋ ሔግል በአለቃና ምንዝር (ባርያ) ተምሳሌት የጻፈው የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ እንዲህ ነበር ያለው! ‹‹አንድ ሰው ራሱ ማን እንደሆነ የሚባንነውና የሚያውቀው ሌላ ሰው ያንን ማንነቱን ሲነግረው ነው፤›› ይላል፡፡ አለቃው ምንዝሩን ‹‹ምንዝር›› ሲለው ነው ምንዝርነቱን የሚያውቀው፤ ምንዝሩም አለቃውን በአለቃነት ዕውቅና ሲሰጠው ነው “አለቃ ነኝ” የሚለው ነው ሔግል ያለው፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ አወንታዊ በሆነ መልኩ አንድ ብሔር ብሔርነቱን ሌላው ዕውቅና ሲቸረው ነው ማንነቱ የሚታወቀው፡፡ ለዚያም ነው የማንነት ጥያቄ ሲቀርብ በውስጠ ታዋቂነት ያለው ፍላጎት ‹‹እኛ›› መሆናችንን ዕወቁልን የሚል መልዕክት ያለው የሚሆነው፡፡ ሌሎችም ለአማናዊው የብሔሩ ማንነት ዕውቅና መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ማንነትህን ‹‹አላውቅም›› ማለት ወደ ግጭትና ጥላቻ ከመግፋት ባለፈ አያፋቅርም፤ አያዋድድም፡፡

ጉራጌዎች ረዘም ላለ ጊዜ ‹‹ሥልጤ ጉራጌ እንጂ የተለየ አማናዊ ማንነት የለውም›› ማለታቸው በመካከላቸው ቅሬታ ከመፍጠር በዘለለ ቢያንስ በወቅቱ አላዋደዳቸውም፡፡ በተለይ ከቡታጅራው ኮንፈረንስ በኋላ የፌደሬሽን ምክር ቤት እስከሚወስን ድረስ ግንኙነታቸው የበለጠ እየሻከረ መሔዱ መነሻው ምንም ሳይሆን ‹‹በሥልጤነታችን ዕወቁን አናውቃችሁም›› የሚለው እሰጥ አገባ ነው፡፡

ከዕውቅና ማግኘት ላይ የሚመነጨው ሌላው ፀጋ ደግሞ እኩል ክብር መቀዳጀት ነው፡፡ ሌላውን መስሎ መኖሩን ትቶ፣ ራሱን ሆኖ እና እኩል የብሔርነት ክብር አግኝቶ፣ ብሔርነት ከሚያስገኛቸው ትሩፋቶች ተቋዳሽ መሆንን ያስችላል፡፡ ራስን ማስተዳደር፣ በፍትሐዊነት በየተቋማቱ መወከል ወዘተ.

ልዩ መሆንም አንድ የማኅበረሰብ አባላት እንደቡድን እኛ ራሳችን እንደምናስበው  እንጂ እናንተ እንደምትስሉን አይደለንም፤ እናንተ ለእኛ ካላችሁ አመለካከት የተለየ ማንነት ነው ያለን፤ ልዩ ነን፤ ማንነታችንን እናንተ ሳትሆኑ እኛው ራሳችን እናውቀዋለን፤ ይልቁንስ እኛ የምንለውን ተቀበሉን የሚል መልዕክት ያዘለ ነው፡፡

የማንነት ዓይነቶች

ስለወል ወይንም ቡድናዊ ማንነት ሲነሳ መታወስ ያለበት አንድ ሰው ለብዙ ዓይነት ማንነቶች ታማኝ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ኦሮሞነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሜጫነቱ፣ በቦረናነቱ፣ በቱለማነቱ፣ በገላንነቱ ሊሰባሰብ ወይንም የበለጠ ሊያስተሳስረው ይችላል፡፡ አንድ ሶማሌም ኦጋደናዊ፣ ሀውያዊ፣ ኢሳዊ ማንነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ጎሳዊ ማንነት መሆኑ ነው፡፡

አፋር የተለያዩ ጎሳዎች ቢኖሩትም አዶሔመራ ወይንም አሶሔመራ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገዳዊ ማንነት መሆኑ ነው፡፡ አንድ ወሎዮ አምባሰሌ፣ ኩታበሬ፣ የጁዬ፣ ቦረኔ፣ ወዘተ በማለት የወንዜ ልጃዊ ማንነት ሊኖረው ይችላል፡፡

ባህር ዳር ከሚኖሩ የአማራ ባለሥልጣኖች አንዱ ጎጃሜያዊ፣ ሌላው ጎንደሬያዊ ሌላው ሸዋዊ  ማንነት ሊኖረው ይቻላል፡፡ ወይንም የበለጠ ሊያሰባስበውና ሊያገናኘው ይችላል፡፡

አዲስ አበባ የሚኖረው ደግሞ በአማራ፣ በኦሮሞነት፣ በትግሬነት ወዘተ ሊሰባሰብ ይችላል፡፡ ወይንም ሰዋው ማንነትን በመከተል ብሔሩን፣ ነገዱን፣ ወንዜያዊነቱን ሊዘለው ይችላል፡፡

ውጭ አገር የሚኖረው ደግሞ በኢትዮጵያዊ ማንነት ሊሰባሰብ ይችላል፡፡ ጥቁሩ ከነጩ የተለየ፣ ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ የተለየ ለዘሩና ለሃይማኖቱ ታማኝ ሊሆን ይችላል፡፡

በመሆኑም አንድ ሰው ከላይ በተገለጹት እንኳን ስምንት ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸው የሚኖረው የታማኝነት መጠን ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ፈጽሞ ታማኝ የማይሆንበትም ሊኖር ይችላል፡፡ አማራው በወንዙ፣ በክፍለ አገሩ የበለጠ ይሰባሰባል ሲባል አማራነቱ ትዝ አይለውም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በአማራዊ ማንነቱ ያለው ትስስር ግን ዝቅተኛ ሊሆን ይቻላል፡፡

አንዳንድ ምሁራን ማንነትን ለሦስት በመክፈል የእያንዳንዱን ሰው ልዩ ባሕርያት ከግምት በማስገባት ግለሰባዊ ማንነት፤ የባህሉን፣ የብሔሩን፣ ወንዛዊነቱን፣ ሃይማኖታዊ ማንነቱን መሠረት በማድረግ ቡድናዊ ማንነትና ሰው በመሆን ብቻ ነጥረው የሚወጡ ማንነቶች ደግሞ ሰዋዊ በማለት ይከፋፍሉታል፡፡

ማንነት አንዴ ተፈጥሮ የሚጠፋ ወይንም በአንድ ወቅት ስላልነበረ ለዘላለም የማይኖር ጉዳይም አይደለም፡፡ ነገር ግን አንፃራዊ የሆነ የተረጋጋ የጊዜ ቆይታ አለው፡፡ የራስነት (Selfhood) መገለጫዎቹ በፍጥነት የሚቀያየሩ አይደሉም፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ የምዕራባውያንን ግላዊነትና ሊብራሊዝምን እየተፈታተነ የመጣው ማኅበራዊና ቡድናዊ ወግ አጥባቂነት መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታላቋ ብሪታኒያ በአለፉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ከብሪቲሻዊነት ይልቅ እንግሊዛዊነት፣ ስኮቲሽነት፣ ዌልሳዊነት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡ በመሆኑም ቀደም ብሎ ያልነበረው ማንነት አሁን እያደገ መምጣቱን እንታዘባለን፡፡ ብሪቲሻዊነት በአብዛኛው ከፖለቲካዊ ማንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቀድሞ ተፈጥሮ የነበረው የአንድ ብሔር አንድ አገርነት እየተሰነጣጠቀ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡ አዝማሚያው የሚያሳየው ብዙ አገሮች ወደ ባለብዙ ብሔር አገርነት እየተመለሱ መሆኑን ነው፡፡ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት መከበርና የመሳሰሉት ሊያቆሙት አልቻሉም፡፡

የማንነት ይታወቅልኝ መነሻውም መድረሻውም ብሔር ወይንም ብሔረሰብ መሆን ነው፡፡ የእነዚህ ትሩፋቶች ደግሞ ራስን ማስተዳደር መቻል፣ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ውስጥ መወከልና መሳተፍንም ጭምር ያስችላል፡፡ የስልጤ ማኅበረሰብ የስልጤ ብሔረሰብ ሲሆን የራሱን ልዩ ዞን ማቋቋም ቻለ፡፡

ማንነትን ማን ይወስን?

የማንነት ጥያቄ ለማን ነው የሚቀርበው? ወይንም በሌላ አገላለጽ የማንነትን ጥያቄ የመጨረሻ ወሳኙ ራሱ የማኅበረሰቡ አባላት ቢሆኑም ጥያቄው መቅረብ ያለበት የፌደሬሽን ምክር ቤት ወይንስ ለክልል ነው? የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ የሆነ መልስ ስለሌለው የፌደሬሽን ምክር ቤት የማንነት ጥያቄ ዞሮ ዞሮ ዋና ዓላማው ራስን ማስተዳደር ስለሆነ ይህን ጥያቄ የመፍታት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2)(ሀ) መሠረት የክልል ምክር ቤት ነው በማለት ወስኗል፡፡

የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደራዊ ተቋማት ከመመሥረት እንዲሁም ክልል ከማቋቋምም ይቀድማል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የመወሰን ሥልጣን የክልል ከሆነ የማንነትማ ወደ ፌደራል ተቋማት በቀጥታ ሊሔድ አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ወይንም በሚሰጣቸው ምላሾች ቅር የተሰኘ ወገን የመጨረሻ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሊሔድ ይችላል፡፡ ይህንን በስልጤ ጉዳይ ከተሰጠው ውሳኔም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(3) ማለትም ‹‹የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይወሰናል፤›› ከሚለው መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ የማይታለፍ አንድ ጥያቄ አለና እሱን እናንሳ፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ሲባል ምን ማለት ነው? ከፊት ለፊቱ ሲታይ በእርግጥ በይግባኝም ይሁን በአቤቱታ ወደሌላ አካል ሊቀርብ አይችልም ማለት ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውሳኔ ከተሰጠ አከተመ፤ የመጨረሻ ነው እንደማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ትርጉሙ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ ምክንያቱም በክልል ምክር ቤት አንድን ማኅበረሰብ ብሔር ወይንም ብሔረሰብ ለመሆን ማሟላት ያለባችሁን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) ላይ ከተዘረዘሩት አምስት መስፈርቶች የተወሰኑትን አላሟላችሁምና ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ አያስፈልግም ተባሉ እንበል፡፡ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ይዘው መጡ፡፡ በዚህ ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ሁለት የውሳኔ አማራጮች አሉት፡፡ የክልል ምክር ቤቱን ውሳኔ ሊሽረውም ሊያጸናውም ይችላል፡፡ ከሻረው ሕዝበ ውሳኔ ሊካሔድ ይችላል፡፡ አስቸጋሪው ጉዳይ የሚመጣው ሲያጸናው ነው፡፡ ማለትም ‹‹ብሔር ወይንም ብሔረሰብ መሆን አትችሉም፤›› ሲባሉ ነው፡፡

የመጀመሪያው ችግር ይህ ማኅበረሰብ ማስረጃዎቻቸውን አሰባስበውና ጥያቄያቸውን አጠናክረው በሌላ ጊዜ ማንሳት ይችላሉ ወይንስ አይችሉም? የሚለው ይሆናል፡፡ መልሱ ’አይቻልም’ ከሆነ በፍትሐ ብሔር የክርክር ሒደት ‘ፍርድ በተሰጠበት አንድ ጉዳይ ላይ  ተመሳሳይ ወገኖች በድጋሜ በፍርድ ቤት አቅርበው ዳኝነት መጠየቅ አይችሉም’ የሚለውን መርህና ድንጋጌ (res judicata) ይመስላል፡፡ ስለሆነም አድቦ ጥያቄውን እርግፍ አድርጎ ትቶ ጥያቄ አቅራቢው ማኅበረሰብ “ነኝ” የሚለውን ማንነቱን በመተው ሌሎች በሚያውቁት ማንነቱ መቀጠል ነው ማለት ነው፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ ጥያቄው በድጋሚ ሊቀርብ ይችላል፤ ድጋሜ እንዳይቀርብ የሚከለክል ሕግ የለም ቢባል እንኳን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል የሚለው ሕግ ትርጉም አይኖረውም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ሊቀርብ ይችላል የሚለውም ለመልስ የሚሆን ፍንጭ ስለሌለ ይሄም ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡

ማንነቴ ይታወቅልኝ በማለት መጠየቅ የሚችለው ራሱ ማኅበረሰቡ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ አስቸጋሪው ማኅበረሰቡ ወይንም ሕዝቡ ማለት ምን ማለት ነው? መቼም ሁሉም ሕዝብ በአንድነት ተሰባስቦ ይጠይቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም የዚያ ማኅበረሰብ ልሂቃን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለአብነት የቅማንትን የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ 120 አባላት ያሉት የኮሚቴ አባላት ናቸው ወደተለያዩ ተቋማት ያደረሱት፡፡ ዋናው ነገር ማኅበረሰቡን ይወክላሉን? የሚለው ነው፡፡ ይህ በትክክል ይወክላሉ ወይንም አይወክሉም የሚል መሥፈርት በማስቀመጥ ለማረጋገጥ የሚከብድና እንደተፈለገ ለመተርጎም የሚመች መለኪያ መስተካከል አለበት፡፡ የሕዝብን ወይንም የአንድ ቡድንን ጥያቄ ለማቅረብ ግልጽ የሆኑ መለኪያዎችን ማስቀመጥ በየትም አገር የተለመደ ነው፡፡ ማንም ሰው እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚያቀርብባቸውንና በሽብር ክስ እከሰስ ይሆን ወይንስ አልከሰስም ከሚል ሥጋት የሚያላቅቅ መሆን አለባቸው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ትኩረት ሊሰጠው ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ነው፡፡

ለራስነት የተለየ ቋንቋ አስፈላጊነት

ዓለም አቀፋዊ አዝማሚያው፣ የግሎባላይዜሽንና የቴክኖሎጂ ተፅዕኖዎች ሲደማመሩ ብሔር ለመባል የተለየ ቋንቋ መኖር ተጨማሪ እንጂ ቅድመ ሁኔታ አይመስሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተደነገገውም ሊግባቡበት የሚችሉበት ቋንቋ መኖሩን እንጂ የተለየ መሆን አለበት አይልም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ፣ የሕገ መንግሥቱ ዕሳቤ ምን ነበር የሚለውንና አሁን ያለው አዝማሚያ ምን እንደሚመስል ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

በመጀመሪያ የሕገ መንግሥቱን ዕሳቤ እንይ፡፡ ሲረቀቅ ታሳቢ ያደረገው ከአንድ በላይ የሆኑ ብሔሮች አንድ ቋንቋ ሊኖራቸው እንደሚችል ነው ወይንስ አንድ ቋንቋ ካላቸው አንድ ብሔር እንደሆኑና እንደሚሆኑ ነውን?

የሽግግር መንግሥቱ ወቅት 63 ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በአዋጅ ሲዘረዝሩ ቋንቋቸውን ብቻ መሠረት በማድረግ ነበር፡፡ የሥነ ልቦና አንድነት፣ የጋራ ማንነትና ሌሎች መሥፈርቶችን ከግምት ያስገባ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን በደርግ ጊዜ የተቋቋመውን የብሔረሰቦች ምርምር ተቋም ጥናት ውጤትን እንደግብዓት ቢወሰድም የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ማንነት የተወሰነው በሕዝቡ ሳይሆን በሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት ነበር፡፡ መለያው ደግሞ ቋንቋ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46፣ ክልል ለመመሥረት ከተቀመጡት መሥፈርቶች ውስጥ አሰፋፈር፣ ፈቃደኛነትና ማንነት ጋር አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ የተለየ ቋንቋ የሚጠይቅ ባይሆን ኖሮ መቼም ቋንቋ የሌለው ሕዝብ ስለማይኖር እንደመስፈርት አይገባም ነበር፡፡ ክልሎችም ሲመሠረቱ ወሳኙ መሥፈርት ቋንቋ ነው፡፡ የተለያየ ቋንቋ ላላቸው ብሔሮች የተለየ ክልል እንዲመሠርቱ ነው መነሻው፡፡ ቢያንስ በዛ ያለ ቁጥር ላላቸው፡፡ 

ባለፉት 20 ዓመታት የነበረውን የማንነት ፖለቲካን ደግሞ እንይ፡፡ ሥልጤ የራሱ ቋንቋ ስለነበረው ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ወይጦዎችና ትግረ ወርጂዎች በቋንቋቸው እየተጠቀሙ ስላልሆነ ወይንም የተናጋሪው ቁጥር ስለቀነሰ፣ የጉጂ ኦሮሞዎች ከሌላው ኦሮሞ ከፍተኛ የዘየ ልዩነት ያለው ቋንቋ ቢኖራቸውም ከሕዝብ ቆጠራ ሪፖርትም ወጥተዋል፡፡ የመንጃ ማኅበረሰብ ከቋንቋቸው አንፃር የካፋና የሸካ ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ ጎሳዎች እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ብሔረሰብ አይደሉም በማለት የደቡብ ክልል የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ምክር ቤት ወስኗል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ውሳኔውን አፅድቆታል፡፡ ከእነዚህ አድራጎት አንፃር አሁንም የተለየ ቋንቋ መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ምክር ቤት ስለቅማንት የሰጠውን ውሳኔ ስናይ ደግሞ ሁሉም የብሔሩ/የብሔረሰቡ አባላት በተለየ ቋንቋ መግባባት አለባቸው ሳይል ዕውቅና መስጠቱ ደግሞ አንድ ሌላ ተቃራኒ የሆነ አካሄድ መኖሩን ማሳያ ነው፡፡

ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ድምዳሜዎች ላይ አርፈናል፡፡ ከሞራልና ከፍልስፍና እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጻፈው ዓረፍተ ነገር አንፃር ቋንቋ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ታሳቢ ካደረገውና አሁን እየሆነ ካለው የማንነት ፖለቲካ አንፃር ደግሞ የተለየ ቋንቋ መኖር ግድ ነው፡፡ የትኛው ትክክል ነው ከተባለ መልሱ የፖለቲካው ንፋስ ሁለቱንም ትክክል ሊያደርጋቸው ይችላል ነው፡፡

በአንድ ወቅት ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ዳውሮ ብሔረሰቦች ቋንቋዎቹ መሠረታዊ ልዩነት የላቸውም በማለት ‹‹ወጋጎዳ›› በማለት አንድ የጽሑፍ ቋንቋ በመቅረጽ ሁሉም በዚሁ ብቻ እንዲማሩ ተጀምሮ ኋላ ላይ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች አንድ ናቸው፤ ልዩነታቸው የዘዬ ብቻ ነው ከተባለ የተለየ ቋንቋ መኖር ግድ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አራቱም የተለያዩ ብሔረሰቦች እንደሆኑ ቀጥለዋልና፡፡ የወቅቱ ፖለቲካ በአንድነታችሁ ቀጥሉ የሚያስብል አልነበረም፡፡ በ1990ቹ መጀመሪያ ላይ ለሕገ መንግሥት ጉዳይ አጣሪ ጉባኤ ጥያቄ ያቀረቡት የባህረ ወርቅ መስመስ ማኅበረሰቦችም የሚናገሩት አማርኛ በመሆኑ፣ የደንጣ ቡደም ክንቺቺላ ሕዝቦች ደግሞ ከከንባታና ሀዲያ ሕዝቦች የተለዬ ቋንቋ ስለሌላቸውም ይመስላል እስካሁን ድረስ ዕውቅና ባያገኙም በተለይ ስለ ሁለተኛው ብሔር ጥናት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፖለቲካው ለቅማንት የተሰጠው መልስ ደግሞ ከላይ ካለው የተለየ ነው፡፡ ወይንም ንፋሱ ጠንክሮ ነበር ማለት ነው፡፡ ማለትም ምንም እንኳን የራሳቸው የሚግባቡበት ቋንቋ የነበራቸው ቢሆንም የማኅበረሰቡ አባላት በሙሉ የሚግባቡት ግን አይደለም፡፡ ከአምስት በመቶ የበለጠ ሕዝብ የሚግባባበት አይደለም፡፡

መንጃ ራሱን ‘መንጃ ነኝ’ ቢልም፣ ካፋና ሸካም መንጃ ‘መንጃ’ እንጂ ካፋም ሸካም አይደለም ቢሉም፣ ውሳኔ ሰጪው አካል ግን መንጃ  ካፋ እና/ወይንም ሸካ እንጂ ሌላ የተለየ ማንነት የለውም በማለት የሰጠው ምላሽ ለቅማንት ከተሰጠው ተጻራሪ ነው፡፡ ወይ ደግሞ የተለየ የዘር ግንድ መኖርን እንደመሥፈርት ተወሰደን? ስልጤና ቅማንት ከጉራጌና ከአማራ የተለየ የዘር ግንድ ያላቸው ሲሆን መንጃ ግን ከካፋ፣ ሸካና ሺናሻ ጋር አንድ የዘር ግንድ አላቸው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አራቱም አንድ ብሔር እንጂ መከፋፈል አልነበረባቸውም፡፡ ስለሆነም ጥናት ላይ ያልተመረኮዘ ዘፈቀዳዊነትም ከፖለቲካው ላይ የተጨመረበት ይመስላል፡፡

እርግጥ ነው ገደብ በሌለው ሁኔታ የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ባሰኘው ጊዜ እየተነሳ ብሔር ነኝ የሚል ከሆነ፤ ብሔር ከመሆን የሚመነጩ የራስን ክልል፣ ዞንና ወረዳ እናቋቁም፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንወከል የሚሉ ማለቂያ የሌላቸው ውስብስብ ችግሮችን እንደሚያስከትል ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የፌደሬሽን ምክር ቤት አስማሚና አስታራቂ መፍትሔ መሻት አለበት፡፡