አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ትምህርትን በቴክኖሎጂ የማዘመን ጉዞ

የአሁኑ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ ማዕከል እ.ኤ.አ. በ1964/65 የኦዲዮ ቪዥዋል  ማዕከል ተብሎ ሲመሠረት አጠቃላይ የአገሪቱን ትምህርት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ለመደገፍና ከኢትዮጵያም አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ እንዲያገለግልም ነበር፡፡ የትምህርት በሬዲዮው እያደገ  ከአዲስ አበባ አካባቢ ‹‹ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ›› አልፎ በየክልሎችም ተመሳሳይ የትምህርት በሬዲዮ ጣቢያዎች ተመስርተዋል፡፡ ኦሮሚያ ባሌ ሮቤ፣ ሐረር፣ ጊምቢ፣ ጎሬና በሌሎችም ትምህርት በሬዲዮ ይተላለፋል፡፡ በደቡብ ይርጋለምና ሶዶ ያለ ሲሆን፣ የመጀመርያው የትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫ የነበረውም ሶዶ ያለው ነው፡፡ የአማራ ክልል አራት ጣቢያዎች አሉት፡፡ ደቡብም እያስፋፋ ነው፡፡ የሌላቸው የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ሲሆኑ፣ በእነዚህም ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከንኑሡ ጊዜ አንስቶ ለሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ብቻ ይሰጥ የነበረው ትምህርት በቴሌቪዥን ተስፋፍቶ ፕላዝማ ላይ ደርሷል፡፡ የፕላዝማ ትምህርቱ የሚሰጠውም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ነው፡፡ ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህ ቦጋለ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በማዕከሉ ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎች ሠርተዋል፡፡ ማዕከሉ ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙርያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት በቴሌቪዥን ሲጀመር ሥርጭቱ የት ድረስ ነበር?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  ሥርጭቱ አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱና አዳማ አካባቢ ድረስ ነበር፡፡ ሰባተኛና  ስምንተኛ ክፍሎች ተጠቃሚ የነበሩ ሲሆን፣ የሚተላለፍበት ቴክኖሎጂም መሬት ለመሬት (ቴሪስቴሪያል) ነበር፡፡ በመሆኑም ተራራ ካለ ሞገዱን ያግደዋል፡፡ ተራራማ አካባቢ ካልሆነ ከእነዚህም አካባቢዎች አልፎ ይደርስ ነበር፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል አሁን ኢቢሲ በተባለው ጣቢያ እየገባ የተወሰነ ገንዘብ እየከፈልን ይሰራጭ ነበር፡፡ ቴሪስቴሪያሉ በቂ ስላልነበረና የመምህራንና የተለያዩ የትምህርት መርጃዎች እጥረት ስላለ ይህንን ለመደገፍ ሲባል ከቴሪስቴሪያሉ ወደ ሳተላይት ገብተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ መቼ መሆኑ ነው? ፕላዝማ ወደምንለው የተሸጋገረበት ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡- አዎ በ1995 ዓ.ም. ሥራው ተጀምሮ ወደ ሥርጭት የተገባው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ በቴሪስቴሪያል የነበረውን ወደ ሳተላይት ከመቀየር ባለፈም ትምህርት በቴሌቪዥን የሚሰጥባቸው ክፍሎችም ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ሆኗል፡፡ የሬዲዮውን ክልሎች እንዲይዙት ተደርጓል፡፡ የቴሌቪዥኑ በማዕከሉ ይመራል፡፡ 12 የቴሌቪዥን ማሰራጫ ቻናል ያለን ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ከማዕከሉ ለየትምህርት ቤቶቹ ይሰጣል፡፡

[ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መንግሥት በጀት እንዲጨምር ሚኒስትሩ ጠየቁ]

ሪፖርተር፡- ሥርጭቱ ለሁሉም ክልሎች ተሟልቶ ይሄዳል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- ኔትወርክ ባለበት አካባቢ በሙሉ ይደርሳል፡፡ ሥርጭቱን መደበኛው ማለትም በየቤታችን የምንጠቀምበት ዲሽ አይቀበለውም፡፡ ለፕላዝማው የተለየና ሲባንድ የተባለ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በየትምህርት ቤቶቹ ዲሽ ይተክላል፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ክፍልም በኔትወርክ ይያያዛል፡፡ ይህ የተያያዘላቸውና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባላቸው ትምህርት ቤቶች ይሠራል፡፡ ተማሪዎች ወይም መምህሩ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ካላጠፉት በስተቀር ይሠራል፡፡ እንደ ድሮው የመልክዓ ምድር አቀማመጡ ተፅዕኖ አይፈጥርበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ፕላዝማ ትምህርት ሲጀመር ከኔትወርክ፣ ከመምህር ፍላጎት፣ ከአስፈላጊነቱ ጋርም ተያያዞ ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት በፕላዝማ ቴሌቪዥን ለመስጠት ሲታቀድ የነበረው ሒደት ምን ይመስል ነበር?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  በወቅቱ የማስተዋወቅ ችግር ነበር፡፡ ጥናት ተካሂዶ መምህሩና ተማሪው እንዲሳተፍ ባላመደረጉ እጥረት እንዳለ ታውቋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ትምህርት በቴሌቪዥን ቀድሞም ነበረ፡፡ በ1995 ዓ.ም. የተደረገው የማስፋፋት፣ የማሻሻልና የማዘመን ሥራ ነው፡፡ ከቴሪስቴሪያል ወደ ሳተላይት፣ ከሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ወደ ከዘጠኝ እስከ 12 እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሆኖም ይህንን ለኅብረተሰቡ ቀድሞ የማስተዋወቅ ሥራ ይጠበቅብን ነበር፡፡ መምህራንን ይተካል ይባል የነበረውም፣ በፊት ስንጠቀምበት የነበረው ትምህርት በቴሌቪዥን ለ15 ደቂቃ ሆኖ፣ የፕላዝማው 30 ደቂቃ በመሆኑ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶች አንድ የትምህርት ክፍል ጊዜ ደግሞ 40 ደቂቃ ነው፡፡ 30 ደቂቃ የፕላዝማ ትምህርቱ ከያዘ መምህሩ 10 ደቂቃ ነው ይኖረዋል፡፡ መምህሩ በዚህ ምንም መሥራት ስለማይችል መምህር ሊተካ ነው የሚል ስሜት ተንፀባርቋል፡፡ ይህንን ቀድመን ከመምህሩና ከኅብረተሰቡ ጋር ተነጋግረን ቢሆን ኖሮ ክፍተቱ አይፈጠርም ነበር፡፡ አንዳንዴም ወዳልተፈለገ ፖለቲካ ተቀይሮ ብዙ ነገር ይራገብበት ነበር፡፡ ይህም አግባብ አልነበረም፡፡ መምህሩ በውዥንብር ውስጥ ሆኖ ቢናገርም አይፈረድበትም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላችንም አላስተዋወቀም፣ ለስንት ደቂቃ ቢሆን ይሻላል የሚለውንም ከመምህሩ ጋር አልመከርንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህስ በኋላ እንዴት ሄዳችሁበት?

ዶ/ር ገበየሁ፡-  ከአመራሩም ከኅብረተሰቡም በዚህ መልኩ መሄድ አይቻልም የሚል አስተያየት ሲመጣ፣ ከመምህራንና ከትምህርት ማኅበረሰቡ ጋር ተመካክረን የፕላዝማ ትምህርት ደቂቃውን ወደ 20 ዝቅ አደረግነው፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቱንም እንደ መጀመርያው ከሀ እስከ ፐ ሳይሆን ከመምህራን ጋር ቁጭ ብለን የትኛው በቴሌቪዥን ቢታገዝ ጥሩ ነው፣ የትኛውስ ክፍል በመምህሩ መሸፈን አለበት ብለን ከፋፈልነው፡፡ ይህንን ያደረግነው ከየክልሉ ከመጡ መምህራን ጋር ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮም ተግባራዊ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ስታደርጉ ምን ዓይነት ግብረመልስ አገኛችሁ?

ዶ/ር ገበየሁ፡- በፊት የነበረው ዓይነት ክፍተት የለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቴክኖሎጂውን እየወደዱት ነው፡፡ ሆኖም እጥረቶች አሉ፡፡ ከቴሌ ጋር የተያያዙ የኔትወርክና የሞጁሌተር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኛም ጋር የተያያዙ ቴክኒካል ችግሮች አንዳንዴ ያጋጥማሉ፡፡ መምህራንንና ርዕሰ መምህራንን በደንብ ስላላሰለጠንን አጠቃቀም ላይም ችግሮች ይታያሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለወደፊት ተጠናክረን እስካልሞላን አሁንም ችግሮቹ ይቆያሉ፡፡ እዚህ ላይ ሦስት ነገሮችን እናያለን፡፡ የአጠቃቀም ክህሎት፣ ወደ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲገባ በቀላሉ ያለመቀበልና የአመለካከት እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግሮች አሉ፡፡ የቴክኒክ ዕቃዎችን በአግባቡ አሟልቶ ከመጠቀምና የቴክኒክ ባለሙያዎችን ከማሰማራት አንፃርም ችግሮች ይታያሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  እነዚህ ችግሮች ትምህርቱ በሥርዓት እንዳይዳረስ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው በአግባቡ ካለመተግበር ጋር ተያያዞ ችግሮች ሲያጋጥሙ ክፍተቶች በምን ይሞላሉ? ኔትወርክ ሳይኖር ትምህርቱ በምን ይሸፈናል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በየ15 ቀኑ ስብሰባ አለን፡፡ ችግር ካለ ከቴሌዎች ጋር እንነጋገራለን፡፡ እነሱም ከክልሎች ጋር ተነጋግረው መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡ በየክልሉ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አሉ፡፡ ባለሙያዎቹም ማዕከላችንም የሚቻለውን ያህል ያሰለጥናሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ቴክኖሎጂ ብቻ ይዞ ሁሌ መጓዝ አይቻልም፡፡ በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ ከሬዲዮ ቴሌቪዥን ብንደርስም ቴክኖሎጂው ወደ ኮምፒውተር፣ ኢንተርኔትና ታብሌት አድጓል፡፡ በመሆኑም ክልሎች በየትምህርት ቤታቸው የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ በማቋቋም ላይ ናቸው፡፡ ማዕከሉም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ መቆራረጦችን ለማስቀረትም እየሠራን ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት የፕላዝማ ትምህርቱ ላመለጣቸው ቅዳሜ ጠዋት የሚተላለፍበት ፕሮግራም አለ፡፡

ሪፖርተር፡-  የፕላዝማ ሥርጭቱ በመላ አገሪቱ በምን ያህል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይሰራጫል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ አሁን ወደ 3,000 የሚጠጉ ሁለተኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህን በሙሉ ማዳረስ ይከብዳል፡፡ ዘንድሮ የተከፈተን ትምህርት ቤት ሁሉንም ቁሳቁስ አሟልቶ ማስጀመር ያስቸግራል፡፡ የኤሌክትሪክ፣ የቪሳት ዲሽ (ኢትዮቴሌኮም የሚተክለው) ያስፈልጋል፡፡ 1624 ትምህርት ቤቶች ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ሁሉም ፕላዝማ ይጠቀማሉ ማለት አይደለም፡፡ ወደ 1,000 የሚጠጉት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እየተጠቀሙበት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ቀሪዎቹ ከአጠቃቀምና ከመብራት ጋር ተያይዞ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ከእኔና ከፕላዝማ ማን ይሻላል የሚሉ መምህራን እንዳሉም ሰምተናል፡፡ የማስተማር አዎንታዊ ፍላጎት ያላቸው መምህራንም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የፕላዝማ ትምህርት ሥርጭት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የራሱ ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡ ከዲሹ፣ ከኔትወርኩና ከሌሎችም ጋር የተያያዙ የቴክኒክ ችግሮች ሲያጋጥሙ እዛው ሊያስተካከል የሚችል ባለሙያ በየትምህርት ቤቱ አለ?

ዶ/ር ገበየሁ፡- ከፍተኛ የሆነው ችግር ይህ ነው፡፡ ከፍተኛ ብልሽት ሲገጥም ከማዕከላችን ባለሙያዎች ይሄዳሉ፡፡ እያንዳንዱ ክልልም የቴክኒክ ባለሙያዎች አሉት፡፡ ችግር ሲኖር የሚጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም ለምሳሌ ኦሮሚያ ባሌ አካባቢ ከፍተኛ ችግር ቢያጋጥም ክልሉ ባሌ ባለሙያ እስኪልክ ሁለት ቀን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ከሚሆን ማዕከላችን እየመከረ ያለው በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት አንድ ባለሙያ ይኑር ነው፡፡ ክልሎች ደግሞ የበጀት ችግር ያነሳሉ፡፡ ሆኖም ለምሳሌ አማራ ክልል በየትምህርት ቤቶቹ ባለሙያ ቀጥሯል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ደግሞ የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡-  ዕቅዳችሁ ፕላዝማ ቴሌቪዥን ላይ ለመቆየት ሳይሆን ወደ ኮምፒውተር ቤተ ሙከራም መሄድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ባለሙያ የግድ ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡- ይህ ትክክል ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ ባለሙያ ከሌለ በስተቀር በአንድ ቤተ መኩራ 50 እና 60 ኮምፒውተር አስቀምጦ መጠቀም ከባድ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንኳን ባለሙያ ወዲያው ይጠራል፡፡ በየትምህርት ቤቱም የቴክኒክ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መደረግ እንዳለበት በከፍተኛ አመራሩም በእኛም ተነግሯል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ሰምተውናል፡፡ ቴክኖሎጂውን ከተጠቀምን ባለሙያ በየትምህርት ቤቱ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡-  ማዕከሉ ሲቋቋም የነበረውን አገልግሎት እያሰፋና የትምህርት አሳጣጡን እያዘመነ ነው፡፡ ስሙም የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ተብሏል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ምን ያህል በቴክኖሎጂው እያዘመነ ነው?

ዶ/ር ገበየሁ፡- መንግሥት ያቅሙን ያህል ቴክኖሎጂውን በየትምህርት ቤቶች ለማዳረስና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሁሉም አካባቢ ባሉ ሬድዮኖች ተማሪዎች በየቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ወደ 36 ሺሕ የሚደርሱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ለእነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እናሟላለን ብንል ከአገሪቱ አቅም በላይ ነው፡፡ በመሆኑም አንደኛ ደረጃን በሬዲዮ፣ ሁለተኛ ደረጃን በቴሌቪዥን ትምህርት እየረዳን ነው፡፡ ይህንኑ ዘመናዊ ለማድረግ ወደ ኮምፒዩተር ቤተ መኩራ ስናቀና ታብሌትም እየመጣ ነው፡፡ ቢሆንም ክልሎች የኮምፒውተር ቤተሙከራ እንዲኖር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሌሎች ክልሎች የተሻሉ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ግቢ ውስጥ የመረጃ ቋት (Data Center) አለ፡፡ በዚህ በቀጥታ በ65 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (አዳዲሶቹ አሁን ላይኖራቸው ይችላል) በኔትወርክ ተያይዘዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው መቀበያ (Server) ከመረጃ ቋቱ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ካለ ፕላዝማ ጋር ስለተያያዘ ተማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችም ከማዕከሉ ወይም ከትምህርት ቢሮው መረጃ ቋት እየተቀበሉ ያስተምራሉ፡፡ ማዕከላችንም ዓላማው ይህ ነው፡፡ በገጠር ትምህርት ቤቶችስ እንዴት ነው ለሚለው መነሻ ጥናት በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ 120 ትምህርት ቤቶችን ለእያንዳንዳቸው 40 ኮምፒውተር በኔት ወርክ አያይዘናል፡፡ ኮምፒውተሮችም ከፕላዝማው ጋር ተያይዘዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ተማሪዎች ከትምህርት ክፍለ ጊዜው ቀድመው ትምህርቱን እንዲያገኙ ያስችላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ቀድመው የትምህርት መርጃውን ማግኘትና ማጥናትም ይችላሉ፡፡ ሆኖም ቀድመን እንዳነሳነው የቴክኒክ ባለሙያ ኖሮ፣ መምህራን በደንብ ሰልጥነው ተግባራዊ ለማድረግ ካልተቻለ ኮምፒውተሩ በየቤተ ሙከራው ቢቀመጥ ዋጋ የለውም፡፡ ፕላዝማ ቴሌቪዥን አሜሪካ ሲጠቀሙ አይተናል፡፡ በኔትወርክ የተያያዘ ሲሆን፣ እያንዳንዱ መምህርም የፕላዝማውን ቴክኒክ ያውቀዋል፡፡ ይህ የሆነው መምህራን ስለሰለጠኑ ነው፡፡ የኛንም መምህራንና ርዕሰ መምህራን ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ እንዲሰለጥኑ ማድረግ አለብን፡፡ የአይሲቲ ማኔጅመንትም ያስፈልጋል፡፡ ቴክኖሎጂው ላይ ሥልጠና ካልሰጠን ዕቃውን ብናሟላ ዋጋ የለውም፡፡ እኛም ሥልጠናውን እያገዝን ቴክኖሎጂው እንዲስፋፋ ጥረት እያደርግን ነው፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል አምና ወደ 7,000 ኮምፒውተሮች ለትምህርት ቤቶች ገዝቷል፡፡ የማስፋፋትም ዕቅድ አለው፡፡ ሌሎችም ክልሎች ዕቅድ ይዘዋል፡፡ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬዳዋ እያሟሉ ነው፡፡ አሮጌውን ጥለን አዲሱን ለማድረግ ሙሉ አቅሙ ስለሌለን ያሉትን በኔትወርክ እያገናኘን ትምህርት ቤቶችን ለማዘመን ቴክኖሎጂውን እያስፋፋን ነው፡፡ ስሙን የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያልነው ሬዲዮና ቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች አማክሎ እንዲሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  እስካሁን የተነጋገርንባቸው ቴክኖሎጂዎች ከአንድ ማዕከል የሚላኩ ናቸው፡፡ የመረጃ ልውውጡ ወይም ትምህርቱ በቀጥታ ሥርጭት የሚሆንበት፣ ተማሪዎችም ከማዕከል ከሚኖሩ መምህራን ጋር በቀጥታ የሚወያዩበትን ቴክኖሎጂ ለማምጣት ምን ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- የፕላዝማ ቴሌቪዥን ሲጀመር ሁለቱንም ወገን የሚያሳትፍ ማለትም (ቱ ዌይ ኦዲዮ ዋን ዌይ ቪዲዮ) በሚል ነበር፡፡ ሁኔታዎች ስላልተመቻቹ ከሁለቱም ወገን የሚለውን በአንድ ወገን ኦዲዮና ቪዲዮ አድርገነዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጥናቱ የተሠራው ግን ይህንን ለማድረግ ነበር፡፡ እንደዚህ ግን አይቀጥልም፡፡ 120 ትምህርት ቤቶችን በኔትወርክ አያይዘናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ 65 ትምህርት ቤቶች ተያይዘዋል፡፡ ሥርጭቱ የሁለት ወገን መስተጋብር እንዲኖረው በማዕከሉ የመረጃ ቋት ለማቋቋም ታስቧል፡፡ የቻይና ኩባንያ ጨረታውን ያሸነፈ ሲሆን፣ በስምንት ወር እንዲጨርስ ተዋውሏል፡፡ በክላውድ ቴክኖሎጂ ማለትም ትምህርት ቤቶች መረጃ የሚለዋወጡበት መረብ የሚዘረጋ ይሆናል፡፡ 1064 ትምህርት ቤቶች ኢንተርኔት ገብቶላቸዋል፡፡ ዕቅዳችን የትምህርት አሰጣጡን ከአንድ ወገን ወደ ሁለት ወገን ምልልስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሚኒስትሮች በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ያለውን እንቅስቃሴ ከያሉበት ሆነው ማወቅ የሚችሉበትን ቴክኖሎጂም ማስረፅ ነው፡፡ በዚህ የትምህርቱን ይዘት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜና ሌሎች መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ወላጆችም የልጆቻቸውን መረጃ ለማግኘት መክፈቻ (Password) ተሰጥቷቸው ስለትምህርቱ ሆነ ስለልጆቻቸው የሚከታተሉበት ሥርዓት ይኖራል፡፡ ቴክኖሎጂውን እስከዚህ ለማድረስ አስበናል፡፡

ሪፖርተር፡-  ለወላጅ መክፈቻ (Password) ሊሰጥ ነው፡፡ ተማሪዎችም በኢንተርኔት ሊገናኙ ነው፡፡ በመሆኑም የኢንተርኔት ደህንነት ወሳኝ ነው፡፡ የኮምፒውተር (የሳይበር) ጥቃት እንዳይደርስ ምን ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክረናል፡፡ ይህንን ብቻችንን አንሰራም፡፡ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ቢሆንም፣ በየጊዜው እንነጋገራለን፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ከኛ ጋር ይሠራል፡፡ ይህ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ የተነሳው ሥጋት በሙሉ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ለተማሪዎችም ኢንተርኔት ዝም ተብሎ አይለቀቅላቸውም፡፡ ትምህርትና ትምህርት ነክ የሆኑ መረጃዎች ብቻ ተገድቦ ይለቀቅላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁን 120 ትምህርት ቤቶች ጋር ነው እንዲህ ዓይነቱ ሲስተም ያለው፡፡ ሌሎቹስ ትምህርት ቤቶች? ስለዚህ የሁሉም መሠረተ ልማት መሟላት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ውድ ነው፡፡ ወጪያችሁ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- በቅርቡ ለምሳሌ አንድ 20 ደቂቃ ያለው 120 ፕሮግራም (Episode) በአማርኛ ለማሠራት ጨረታውን ያሸነፈው አገር ውስጥ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነበር፡፡ 18 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ በጣም ውድ ነው፡፡ አምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍለን ከዚህ ቀደም አሠርተናል፡፡ የፕላዝማ ፕሮግራሙ ሲጀመርም ብዙ ተከፍሏል፡፡ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በሚሰጥበት ጊዜ ግን በራሳችን ባለሙያ እናሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡-  ማዕከሉ ለምን በራሱ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ኤክስፐርቶች ለማሠራት አልቻለም?

ዶ/ር ገበየሁ፡- በ1996 ዓ.ም. ሁሉንም መጽሐፍ ወደ ቴክኖሎጂው በምናስገባበት ወቅት በቂ ባለሙያና ዕቃ አልነበረንም፡፡ አሁን የሰው ኃይል አጠናክረን መግባት ይጠይቀናል፡፡ 12 ቻናል አለን፡፡ ትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዲተላለፉበት ለኅብረተሰቡም አንዱን ቻናል ማዋል እናስባለን፡፡ ያልተማረው ጭምር ግብርናውን እንዴት ማቅናት ይችላል፣ ጤናውን እንዴት ይጠብቅ? በሚል እንዲሠራበት እያሰብን ነው፡፡ አንዷን ቻናል ከናይልሳት ጋር ለማያያዝ እሥራኤል ካለው ኩባንያ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በዓመት 3መቶ ሺሕ ዶላር ትከፍላላችሁ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማስተማር ከቻልን ብሩ ብዙ አይባልም፡፡ ኢንሳም አዲስ ሳተላይት እናስጀምራለን ብሎናል፡፡ ፕሮግራሞቻችንን የሚሠሩ የራሳችን ባለሙያዎች እንዲኖሩን ከትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተናል፡፡ የትምህርቱን ይዘት የሚያዘጋጅ ባለሙያ ግድ ነው፡፡ ቀጥታ ሥርጭትና ትምህርቱ ከሁለቱም አቅጣጫ እንዲሆንም በአዲስ መልክ ተጨማሪ ባለሙያ ያስፈልገናል፡፡ ጥሩ ክፍያ መኖርም አለበት፡፡ ይህን ያሰብንበትና የከፍተኛ አመራሩን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ቴክኖሎጂው እየተገባ ባለበት ሰዓት ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ ለኮምፒውተር አጠቃቀም አዲስ መሆን የለባቸውም፡፡ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ትምህርት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል፡፡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲጀመርና ተማሪዎች ከሥር ክህሎት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግስ ታስቧል?

ዶ/ር ገበየሁ፡- እያንዳንዱ ትምህር ቤት ቴክኖሎጂው ተሟልቶለት ቢሄድ ደስ ይለናል፡፡ መንግሥትም ያስባል፡፡ በኮሪያ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ይማራል፡፡ የኛ ኮምፒውተር ነክቶ የማያውቅ ነው፡፡ በዘመነ ሉላዊነት (Globalization) እነዚህን ልጆች ማወዳደር አይቻልም፡፡ ይህ እንዳይሆን በቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ ጥረት አለ፡፡ ሆኖም አንደኛ ደረጃንም ለማዳረስ አቅም አይፈቅድም፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂው ታግዛላችሁ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑና መረጃ እንዲያገኙ ዕድሉን ትሰጣላችሁ?

ዶ/ር ገበየሁ፡- የግልም ተማሩ የመንግሥት ሁሉም የአገራችን ዜጎች ናቸው፡፡ አቅሙ ያላቸው የግል ትምህርት ቤቶች ፍላጎቱ ካላቸው ያለንን የትምህርት መርጃ ለመስጠት ማዕከላችን ክፍት ነው፡፡ ለምሳሌ የፕላዝማ ትምህርት ፋሲሊቲ አሟልቶ ሲዲ ቢጠይቅ ይሰጠዋል፡፡ መሸጥ ግን አይችልም፡፡ የቴክኒክ ምክርም መስጠት እንችላለን፡፡