አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ኑሮ ሲጎድል

አቶ ብዙነህ አየው በ70ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኙ አዛውንት ናቸው፡፡ የእህል ነጋዴና ኑሯቸውም የሞላ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የተቸገሩን መርዳት ልምዳቸውም ነበር፡፡ ይህ ግን በነበር ከቀረ ቆይቷል፡፡ ንግዱ አክስሯቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚበሉት እስኪያጡ ይቸገራሉ፡፡ በችግር ምክንያት የሚኖሩበትን ቀዬ ሰላሌ ኩዩ ገብረ ጉራቻን ለቀው አዲስ አበባ ከመጡ ስምንት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ዘጠኝ ልጆቻቸውም እሳቸውን ተከትለው አዲስ አበባ ከገቡ ሰነባብተዋል፡፡

አቶ ብዙነህ አዲስ አበባ የተሻለ ኑሮ እንደሚያጋጥማቸው አስበው የመጡ ቢሆንም፣ የጠበቃቸው ፍጹም የተለየ ነበር፡፡ ማደሪያ ከማግኘት ጀምሮ ሌሎችም መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለመሙላት ይቸገራሉ፡፡ ልጆቻቸው የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ በሊስትሮነትና በተለያዩ የቀን ሥራዎች ተሰማርተዋል፡፡ የሚያገኙት ግን ከእነሱ አልፎ ለአባታቸው ለአቶ ብዙነህ የሚተርፍ አይደለም፡፡ በመሆኑም አቶ ብዙነህ በመጦሪያቸው ሰዓት የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ ወገባቸውን አስረው ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል፡፡

የሚያገኙት ግን ከምግብ አልፎ ለቤት ኪራይ የሚሆናቸው አይደለም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ይኖሩ የነበሩት በደህና ጊዜ የሚያውቃቸው አንድ ወዳጃቸው ጋር ተጠግተው ነው፡፡ እዚያ ጥቂት ጊዜ ከቆዩ በኋላ ቤቱን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡

ልባሽ ጨርቆችንና የሞባይል ካርድ ሸጠው የሚያገኙት ገንዘብ ለቤት ኪራይና ለዕለት ጉርሳቸው ስለማይሸፍን ከንግዱ ጐን ለጐን ልመናንም እንደመተዳደሪያቸው አድርገዋል፡፡

ማደሪያ አጥተው ጐዳና የሚያድሩባቸው ቀናት መኖራቸውን በመግለጽ ‹‹ጎዳና ለመውጣት ዳርዳሩን እያልኩ ነው፡፡ የሚደግፈኝ ካልተገኘም ወደዚያው ነው›› ይላሉ፡፡

እንደ ስኳርና ደም ግፊት ያሉ ክትትል የሚያስፈልጋቸው በሽታዎችም አሉባቸው፡፡ ይሁንና ማደሪያና የሚበሉት ብርቅ ለሆነባቸው አቶ ብዙነህ ሕክምና የማይታሰብ ነው፡፡

በአንድ ወቅት የሞላ ኑሮ የነበራቸው፣ ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩ እንደ አቶ ብዙነህ ያሉ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በችግር ሲቆራመዱ ይታያሉ፡፡ ቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ጦማቸውን ውለው የሚያድሩም ብዙ ናቸው፡፡ ቸገረን ብለው የሰው ፊት ላለማየት ገመናቸውን በሚስጥር ይዘው በረሃብ የሚሰቃዩትንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ምግብ ሳይመገቡ ትምህርት ቤት የሚላኩና ራሳቸውን ስተው የሚወድቁ ተማሪዎችም መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለምሳ ቆሎ ተቋጥሮላቸው የሚላኩም አሉ፡፡

ቤተልሄም (ስሟ ተቀይሯል) 13 ዓመቷ እንደሆነ ነግራናለች፡፡ እሷና ወንድሞቿ የሚኖሩት ከአባታቸው ጋር ነው፡፡ አባታቸው የሚያስተዳድራቸው የቀን ሥራ ሠርቶ ነው፡፡ የሚያገኘው ገንዘብ ከቤት ኪራይ አልፎ በበቂ የሚመግባቸው አይደለም፡፡ ሥራ ጠፍቶ ሳይሠራ የሚውልባቸው ቀናት ስለሚኖሩም፣ ገቢው አስተማማኝ አይደለም፡፡ ይህም መላው ቤተሰቡ እንዲቸገር የሚበላ ጠፍቶ እንዲራብ አድርጓል፡፡ ጾማቸውን የዋሉባቸው ቀናትም አሉ፡፡

‹‹አባታችን እየዞረ በግ ያርዳል፡፡ በሱ የተወሰነ ገንዘብ ይከፍሉታል›› የምትለው፣ ቤተልሄም፣ አንድ ቀን ረሃብ አስበው የማያውቁትን ነገር እንዲያደርጉ እንዳስገደዳቸው ትናገራለች፡፡ ምግብ በአፋቸው ሳያልፍ አንድ ቀን ሆኗል፡፡ ተርበዋልም፡፡ ቤታቸው ውስጥ የነበረው ለድመት የሚሰጥ ሳምባ ብቻ ነበር፡፡ የበግ ሳምባ የሚበላባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም፣ ልምዱ ያልነበራቸው ቤተልሄምና ወንድሞቿ ሳምባውን ጠብሰው በሉት፡፡ ሳምባ የበሉበት ቀን ሁሌም እንደማይረሳት ትናገራለች፡፡

ከትምህርት ቤት መልስ ለምነው የሚኖሩ ተማሪዎችም አሉ፡፡ የሚበሉት ጠፍቶ ከልጆቻቸው ጋር የሚቸገሩ ጎዳና ወጥቶ ለመለመን በቋፍ ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የለበሱ ሰዎች ሳይቀሩ በችግር ምክንያት እጃቸውን ለልመና እየዘረጉ ነው፡፡ የተገኘውን ሠርቶ ለማደር ፍላጐት ያላቸው እንኳ ሥራ አጥተው ይንከራተታሉ፡፡ ታክሲ ላይ ረዳት ሆኖ ለመሥራትም ችግር የሆነባቸውም አሉ፡፡ የቀን ሥራም ቢሆን ሁሌ ስለማይኖር ገቢው አስተማማኝ አይደለም፡፡

እንዲህ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞችን መንግሥት በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ ካደረገ ቆይቷል፡፡ በዚህም ጥሩ የሚባል ለውጥ መፍጠር ተችሏል፡፡ ነገር ግን ትኩረቱን በገጠር ብቻ ያደረገ በመሆኑ በከተሞች ላይ ያለው የከፋ ድህነት ተዘንግቶ ከርሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የድህነት ምጣኔ ከገጠሩ ይልቅ በከተሞች በተለይም በትልልቅ ከተሞች የከፋ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 በተደረገ ጥናት በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ የደሃው ቁጥር 29.6 በመቶ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በገጠሩ 30 በመቶ፣ በአዲስ አበባ 28.3 በመቶ እንዲሁም በድሬዳዋ 28.1 በመቶ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተሞች ያለው የድሆች ቁጥር ከገጠሩ መብለጡም ይነገራል፡፡ ከሕዝብ ዕድገት ጋር ተያይዞ እ.ኤ.አ. በ2028 በአገሪቱ ያለው የከተማ ነዋሪ መጠን 30 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ይህም ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ወደ ከተሞች እንዲዞር የሚያስገድድ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ በከተማ የሚገኙ ድሆች በአነስተኛ የሥራ መስክ አልያም በጣም ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ጠዋሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች ዋነኛ የከተሞች የድህነት ገጽታ አመላካች ናቸው፡፡ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የ10 ዓመት የምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ስትራቴጂ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አማካይነት ተቀይሶ በተግባር ለማዋል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ በፕሮግራሙ በ927 ከተሞች የሚገኙ 4.7 ሚሊዮን በድህነት የሚኖሩ ዜጐችን ለመደገፍ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ፕሮግራሙ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ከሳምንታት በፊት የከተማው አስተዳደር ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በዕለቱ በፕሮጀክቱ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማከናወን የታሰበው ዝርዝር ተብራርቷል፡፡

ለአምስት ዓመት የፕሮጀክቱ ወጪ 300 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ ሲገኝ፣ 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተመደበ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በከተሞች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙት ዜጐችን የአደጋ ተጋላጭነትና የምግብ ዋስትና ችግር መቀነስ ቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ ተግባራዊ የሚሆነውም በአገሪቱ በሚገኙ 11 ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በደሴ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በጅግጅጋ፣ በሰመራ፣ በሎጊያ፣ በጋምቤላና በአሶሳ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ በተመረጡት አሥራ አንዱ ከተሞች የሚገኙ 604,000 ዜጐችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህም ማለት ፕሮግራሙ በከተሞቹ ከድህነት ወለል በታች ከሚኖሩ 55 በመቶ የሚሆኑትን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የማኅበራዊ አገልግሎት የገንዘብ ድጋፍ ከማቅረብ ጐን ለጐን፣ የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ መስጠትና ተጠቃሚዎች ከሚገኙበት የኑሮ ሁኔታ እንዲላቀቁ፣ አቅም ያላቸው በተለያዩ የጉልበት ሥራ እንዲሰማሩ፣ አቅም ለሌላቸው ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ ንዑስ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የፕሮግራሙ መሠረታዊ መርሆች ናቸው፡፡

የገንዘብ ድጋፍ የሚደረገው ጊዜያዊ የምግብ ችግርን ለማቃለል ሲሆን የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ግን የቤተሰብ ገቢን በዘላቂነት ማስፋትና ማሻሻልን ያለመ ነው፡፡ በአካባቢ ልማት ለሚሳተፉ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ጥገኞች እንዳይሆኑና የተሻለ የገቢ ማስገኛ አማራጭ ላይ ማተኮር እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡ የተለየ ድጋፍ የሚያሻቸው ተጠቃሚዎች ደግሞ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡

የአካባቢ ልማት የሥራ ክፍሎችም ደረቅ ቆሻሻ የመሰብሰብ፣ መለየትና ኮምፓስት መሥራት፣ ለአረንጓዴ ልማትና ለከተማ ግብርና መጠቀም፣ የከተሞች አረንጓዴ ልማት ሥራ፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ሥራ፣ በተመረጡ ቀጠናዎች የሚሠራ የከተማ መሠረተ ልማት ግንባታና የከተማ ግብርና ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ቦታዎችን ማዘጋጀት ናቸው፡፡

በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ በመጀመሪያ ዓመት ለተጠቃሚዎቹ የምክር አገልግሎትና የክህሎት ሥልጠና መስጠት፣ በደመወዝ ቅጥር ፓኬጅ ለደመወዝ ተቀጣሪዎች አስፈላጊውን ምክር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥልጠና እንዲሁም በግል የሥራ ፈጠራ ፓኬጅ አስፈላጊውን ሥልጠና መስጠት ናቸው፡፡ በኑሮ ማሻሻያ የገንዘብ ድጋፍ የሥልጠና ወጪን ወይም የንግድ ሥራ ማስፋፊያ ወጪን ለመሸፈን የፌዴራል የሥራ ዕድልና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ እስከ 10,000 ብር ድረስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

84 በመቶ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች የአካባቢ ልማት ተሳታፊሆች ናቸው፡፡ 16 በመቶ የሚሆኑት ግን መሥራት የማይችሉ በቀጥታ ድጋፍ የሚካተቱ ናቸው፡፡ የአካባቢ ልማት የክፍያ አደረጃጀት ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተጠቃሚዎች በዓመት 240 ቀናት እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ የሁለተኛው ዓመት ደግሞ 160 ቀናት ይሠራሉ፡፡ የሦስተኛ ዓመት ተጠቃሚዎች ደግሞ 80 ቀናት ይሠራሉ፡፡ ተጠቃሚዎቹ የሚሠሩባቸው ቀናት ከዓመት ዓመት እየቀነሱ የሚሄዱት በሌላ ዘላቂ ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ሲሆን፣ በቀን የሚከፈላቸው 60 ብር ደግሞ የገበያውን ሁኔታ መሠረት አድርጐና ይህም በየዓመቱ የሚታይ መሆኑን የፌዴራል የሥራ ዕድልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልጸዋል፡፡

በቀጥታ ድጋፍ የሚካተቱት አረጋውያንና ሕፃናት ሲሆኑ፣ ነፃ የጤና አገልግሎት፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችና በወር 170 ብር ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በአካባቢ ልማት ከሚታቀፉት በተለየ ለቀጥታ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ፍላጐቱ እስካለ ድረስ ድጋፉ ይቀጥላል፡፡

70 በመቶ የሚሆነው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በአዲስ አበባ ላይ የሚተገበር ነው፡፡ ተጠቃሚዎች የደሃ ደሃ የሚባሉት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ናቸው፡፡ የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴተኛ አዳሪዎችና የጐዳና ተዳዳሪዎች በፕሮግራሙ ተካተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ቤት የሌላቸው የጐዳና ተዳዳሪዎች አልያም በጊዜያዊ መጠለያ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከገጠር ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ወደ ከተሞች የተሰደዱ ወጣቶችና ሕፃናትም ይገኙበታል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ለመታቀፍ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ቢያንስ ለስድስት ወራት በቀበሌው ነዋሪ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡  

ፕሮግራሙ እንደ አቶ ብዙነህና የቤተልሔም ቤተሰቦች ላሉ ዜጐች መልካም ዜና ቢሆንም፣ ምን ያህል ለችግራቸው ምላሽ ይሰጣል?

ለቀን ሥራ የተመደበው 60 ብር በአሁኑ ወቅት ለአንድ የቀን ሠራተኛ ከሚከፈለው ያነሰ መሆኑን፣ ቀጥታ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተጠቃሚዎች በወር የተመደበው 170 ብርም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ጠቅሰው ጋዜጠኞች ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ‹‹170 ብር የሚሰጠው ለአንድ ግለሰብ ብቻ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ይበቃል የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገር ግን ከምንም ይሻላል፣ ከዚህ በፊትም ያለዕርዳታው ኖረዋል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ነው›› በማለት ሌሎችም ተጨማሪ ነፃ የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዳሉና የተሻለ መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ ለቀን ሥራ የተመደበው ክፍያን በተመለከተም በገበያ ላይ እየተከፈለ ያለው አማካይ ክፍያ መሆኑንና እንደ ገበያው ሁኔታ በየጊዜው እየታየ እንደሚስተካከል ተናግረዋል፡፡

ዓምና ሰኔ ወር እንደሚጀመር የተነገረለት ፕሮግራሙ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ ተግባራዊ የተደረገው ሰሞኑን ነው፡፡ ‹‹ሥራው የሚጀመረው እንደ ከተሞቹ ዝግጅት ነው›› ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ሐዋሳ የተለያዩ ቅድመ ሥራዎችን ከሌሎቹ ከተሞች ቀድማ በማጠናቀቋ የተመለመሉት ተጠቃሚዎች ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

መቀሌ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋና ሐረር ከተሞችም ተጠቃሚዎችን የመለየት ሥራ አጠናቀዋል፡፡ የተመለመሉትን ተጠቃሚዎች ስም ዝርዝር ለሕዝብ በሚታይ ቦታ በመለጠፍ እያስተቹ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባም የተጠቃሚዎች ምዝገባ ተጠናቋል፡፡ በከተማው በሚገኙ 35 ወረዳዎች ከ600,000 በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚያደርገው 123,000 ዜጐችን ሲሆን፣ የመመልመሉ ሥራ መጀመሩን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ በልዩ ድጋፍ ሥር የተመደቡትን ጐዳና ተዳዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች የሚደገፉበት ፕሮጀክት ገና አለመጀመሩንም አክለዋል፡፡ በአገሪቱ ያለው የድህነት መጠን ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡