አካል ጉዳተኞች በፋሽን

‹‹ብዙዎች ስለ ውበት ሲያስቡ አካል ጉዳተኞችን ማሰብ ይከብዳቸዋል፡፡ ይህን አመለካከት ለመስበር አካል ጉዳተኞች በፋሽን ዘርፍ ማድረግ የሚችሉትን ማሳየት አለባቸው፤›› የምትለው ሰላማዊት ተስፋዬ 21 ዓመቷ ሲሆን፣ አማተር ሞዴል ናት፡፡ ሐዋሳ ተወልዳ ያደገችው ሰላማዊት ዓይነ ሥውራን እንዴት ሞዴል መሆን ይችላሉ? የሚለው የተዛባ አመለካከት ቢፈታተናትም ህልሟን ዕውን ለማድረግ እየተጣጣረች ነው፡፡

ዓይነ ሥውር መሆኗ ከልጅነቷ ጀምሮ የምትወደውን የፋሽን ዘርፍ እዳትቀላቀል ሊያግዳት እንደማይችል ለማሳየት አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ የፋሽን ትርዒቶች ዘወትር ታፈላልጋለች፡፡ ምኞቷን ማሳካት ግን ቀላል አልሆነም፡፡ እንኳን ፋሽን መሠረታዊ የአካል ጉዳተኞች ፍላጎቶችም በቀላሉ በማይሟሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሞዴል የመሆን ህልሟ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡

ሰላማዊት ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ብትጀምርም በመሀል ለማቋረጥ ደብዳቤ ሳታስገባ ወደ ሐዋሳ በመሄዷ ስትመለስ ትምህርቱን መቀጠል አልቻለችምና ቱጌዘር የአካል ጉዳተኞች የተራድኦ ድርጅት ውስጥ ገብታ የኮምፒውተር ሥልጠና ወሰደች፡፡ አሁን ድል በትግል ትምህርት ቤት ውስጥ ኮምፒውተር ታስተምራለች፡፡ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ የፋሽን ትርዒቶች በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ከምንም ይሻላልና ትሳተፋለች፡፡ በዓይነ ሥውራን ማኅበርና በሌሎችም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በሚሠሩ ማኅበራት በተዘጋጁ ሦስት የፋሽን ትርዒቶች ሞዴል ሆናለች፡፡

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ፋሽኑ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አይደለም፤›› የምትለው ሰላማዊት፣ ሁኔታው እንዲቀየር አካል ጉዳተኞች መወጣት ያለባቸው ኃላፊነት እንዳለ ታምናለች፡፡ አካል ጉዳተኞች እንደ ተረጂ ሳይሆኑ የሚፈልጉትን ዓይነት መድረክ በማዘጋጀት አቅማቸውን ማሳየት ይገባቸዋል ትላለች፡፡ ዓይነ ሥውራንም ይሁን ሌሎች አካል ጉዳተኞች በራሳቸው ጥረት ሁሉንም ነገሮች ማድረግ እንደሚችሉ ሲያሳዩ ለውጥ እንደሚመጣ ይሰማታል፡፡ ‹‹እንዲሁ ከሚወራው በበለጠ መድረክ ላይ በዕውን የሚታየው ነገሮችን ይለውጣል፤›› ስትልም ትገልጻለች፡፡

ነገሩ መሬት ላይ ሲወርድ የሚባለውን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ የፋሽኑ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማኅበራዊ ክንውኖችስ ዕውን አካል ጉዳተኞችን ያማክላሉ? የሚለው ያጠያይቃል፡፡ ከፋሽን ትርዒቶች አድቀድሞ ልብሶች ሲዘጋጁና ለገበያ ሲቀርቡም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ አይደለም፡፡ የልብስ ዲዛይን፣ የሞዴሊንግና ሌሎችም የፋሽን ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን የዘነጉ መሆናቸውም ይስተዋላል፡፡

ዘርፉ አካል ጉዳተኞችን ከማግለሉ ባሻገር አብዛኛው ማኅበረሰብ ውስጥ ውብ ወይም ቆንጆ የሚባል ሰው የሚገለጽበት መንገድ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ‹‹ቀጠን ረዘም ያለች ሴት ወይም ደንደን ያለ ወንድ›› የሚለው ተለምዷዊ የተዛባ የውበት አገላለጽ ቁንጅናን በአንዳች መንገድ ብቻ የሚገድብ ሲሆን፣ የሰው ልጆች ባጠቃላይ እንደየአፈጣጠራቸው ውብ መሆናቸን የዘነጋም ነው፡፡

ውበት የሚተረጎምበት መንገድ ላይ ጥያቄ የምታነሳው የ25 ዓመቷ ጽዮን ብርሃኔ ‹‹ድንኮች የፋሽን ትርዒት ማሳየት ይችላሉ እንዴ?›› ተብላ የተጠየቅባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ቢሆኑም ሞዴል የመሆን ፍላጎቷን የሚያስቆሙ አልሆኑም፡፡ ራስ መኰንን ድልድይ አካባቢ የተወለደችው የ25 ዓመቷ ጽዮን፣ ለወላጆቿ ሰባተኛ ልጅ ስትሆን የቤተሰቦቿን ድጋፍ ባታገኝ ኖሮ አሁን ያለችበት ደረጃ ለመድረስ ትቸገር እንደነበር ትናገራለች፡፡

ከምትኖርበት አካባቢ ጀምሮ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ለድንኮች ያለው አመለካከት ሕይወቷን ፈታኝ ቢያደርገውም፣ እሷ በቁመቷ ምክንያት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ትናገራለች፡፡ ‹‹አትችይም ስባል መቻሌን በተግባር አሳያለሁ፤›› ትላለች፡፡ ከዓመታት በፊት አሎሎ ውርወራ መወዳደር እፈልጋለሁ ስትል በቁመቷ ምክንያት መቻሏን የተጠራጠሩ ቢኖሩም አሰላ ላይ ከንድኮችና መደበኛ ቁመት ያላቸው ጋር በተደረገ የአሎሎ ውርወራ ውድድር ተሳትፋ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡

የምትፈልጋቸውን ነገሮች ማሳካት ደስታ የሚሰጣት ጽዮን፣ ጉዞዋን ባይገቱትም ብዙ ህሊናዋን የሚነኩ ነገሮች መባሏን ትናገራለች፡፡ ‹‹ሰው የሚለው ነገር ያማል፡፡ ፀጉር ቤት ስሄድ እንኳን የሚባለው ነገር ያሳዝናል፡፡ ነገሩ በተለይ በሴቶች ላይ ይከብዳል፡፡ ድንክዬዎች አይወልዱም፣ እርግማን ነውና ሌላም ብዙ እንባላለን፤›› ትላለች፡፡ ልብ የሚሰብሩ ነገሮች ሲባሉና ሰብዓዊ ያልሆኑ ቀልዶች ሲሰነዘሩ ከመጎዳት ይልቅ መቻሏን በማሳየት የኅብረተሰቡን አመለካከት መቀየርን መምረጧን ታክላለች፡፡

‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ መዘነጥ እወዳለሁ፤›› የምትለው ጽዮን፣ ሞዴል የመሆን ፍላጎት ያደረባት ልጅ ሳለች ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የድንክዬዎች የፋሽን ትርዒት ሲዘጋጅ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላት ተሳተፈች፡፡ ትርዒቱ ግን ከጥቂት ጊዜ በላይ መቀጠል አልቻለም፡፡ ሆኖም የቁመት መርዘም መስፈርቱ የሆነበትን የውበት አገላለጽ ለመቀየር ሌሎች አማራጮች መፈለጓን አላቆመችም፡፡

እንደ ሰላማዊትና ጽዮን የፋሽኑን ዘርፍ የመቀላቀል ህልም ቢኖራቸውም ነገሮች የከበዷቸው አሉ፡፡ በተቀረው ዓለም በዊልቸር ወይም በክራንች ድጋፍ የሚሄዱ ሞዴሎች መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ መስማት የተሳናቸው፣ ዓይነ ሥውራንና ሌሎችም አካል ጉዳተኞችም የፋሽኑን ዘርፍ ይቀላቀላሉ፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ አልባሳት የሚያዘጋጁ ዲዛይነሮችም እየተበራከቱ ነው፡፡ በቅርቡ ኒውዮርክ ታይምስ በፋሽን ኤንድ ስታይል አምድ ‹‹በአንድ ወቅት ፋሽን ገንዘብ ያላቸው፣ ተክለ ቁመናቸው ‹‹ያማረ›› የሚባሉ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ፋሽን የሁሉም መሆኑን የማሳየት አብዮቱ ተጧጡፏል፤›› በማለት ተገልጿል፡፡ ጽሑፉ በዋነኛነት ያተኮረው ለአካል ጉዳተኞች ተብለው ዲዛይን በሚደረጉ አልባሳትና በአካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ዙሪያ ነበር፡፡ 

አምና አንድ ብራዚላዊ ዲዛይነር ለአካል ጉዳተኞች ያዘጋጃቸው ልብሶችን ሲያስተዋውቅ፣ አካል ጉዳተኞች ምቹ ልብስ ለማግኘት ስለሚያዩት ውጣ ውረድ ገልጾ ነበር፡፡ አልባሳቱ በአካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ተለብሰው እንዲታዩ አድርጎም ነበር፡፡ በዓለም ዕውቅናን እያተረፉ ከመጡ አካል ጉዳተኛ ሞዴሎች አንዷ ካናዳዊቷ ዊኒ ሀርሎ በቆዳ ሕመም ትሰቃያለች፡፡ በልጅነቷ በቆዳዋ ሁኔታ ምክንያት የዕድሜ እኩዮቿ ‹‹የሜዳ አህያ›› እያሉ ይቀልዱባት ነበር፡፡ ዛሬ የፋሽን ዘርፉን አካሄድ በተለየ ሁኔታ እየቀየሩ ካሉ ወጣት ሞዴሎች አንዷ ናት፡፡

የዊኒ ተሞክሮ ባህር ተሻግሮ ኢትዮጵያዊቷ ርግበ ገብረዋህድ ጋር ደርሷል፡፡ የተወለደችው ትግራይ፣ ደግሀሙዝ ከተማ ሲሆን፣ ፖልዮ የያዛት በሁለት ዓመቷ ነበር፡፡ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ብትመጣም ባለመዳኗ አሁን በክራች ድጋፍ ትሄዳለች፡፡ ርግበ በተለያዩ አካል ጉዳተኞችን የማካተት (ኢንክሉዥን) ላይ የሚሠሩ ድርጀቶች የሠራች ሲሆን፣ አሁን ኬናዊ የተባለ የአካል ጉዳተኞች አማካሪ ድርጅት አቋቁማ እየሠራች ነው፡፡

‹‹ልጅ እያለሁ ማኅበረሰቡ ያስቀመጠውን መስፈርት ስለማላሟላ ቆንጆ አይደለሁም ብዬ አስብ ነበር፤›› ትላለች፡፡ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ልዩነት በራሱ ውበት እንጂ መለያያ ምክንያት እንዳልሆነ ስትገነዝብ ለውጥ ለማምጣት ብርታት ሆናት፡፡ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ፋሽን (ኢንክሉሲቭ ፋሽን) ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማካሄድ እንዳሰበችም ትናገራለች፡፡

ሐሳቧን ለመደገፍ ፍቃደኛ ከሆኑት የፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበርና አሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን የፋሽን ትርዒት በሸራተን አዲስ አዘጋጅታለች፡፡ በትርዒቱ በ15 ዲዛይነሮች የተሠሩ አልባሳት በ28 አካል ጉዳተኛ ሞዴሎች ይቀርባሉ፡፡ ከሞዴሎቹ መካከል ሰላማዊትና ጽዮንም ይገኙበታል፡፡ ‹‹ውበት የሚተረጎምበትን መንገድ የሚቀይሩ፣ በሁሉም ሰው ውበት እንዳለ የሚያሳዩ አካል ጉዳተኛ ሞዴሎች አሉ፤›› ትላለች፡፡ መሠረታዊ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ስለ ፋሽን ማሰብ ቢከብድም ትርዒቱን በመጠቀም በሌሎች ዘርፎችም አካል ጉዳተኞች መሳተፍ እንደሚችሉ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ልብስ በማምረትም ይሁን በዲዛይንና ሞዴሊንግ አካል ጉዳተኞችን የማሳተፍ እንቅስቃሴ ‹‹ዜሮ ነው›› የምትለው ርግበ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እንደሚኖር ተስፋ ታደርጋለች፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ፣ በማኅበራዊ መስተጋብርና ሌሎችም ሁነቶች አካል ጉተኞች እንዲካተቱ ብዙ መሠራት እንዳለበትም ትገልጻለች፡፡ ‹‹በፋሽኑ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዘርፎችም የጥቂቶች ሳይሆኑ የሁሉም መሆናቸውን በማሳየት ድንበሩ መፍረስ አለበት፤›› ስትልም ታስረዳለች፡፡

አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የፋሽን ትርዒት መዘጋጀቱ አንድ ዕርምጃ መሆኑን የምትገልጸው የፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ ናት፡፡ ‹‹ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ልብስ አዘጋጅተን ገበያ አናወጣም ነበር፡፡ አካል ጉተኞች ገበያ ሲወጡ ምቹ ልብስ እንዲያገኙ ከትርዒቱ በኋላም ሌሎች ልብሶች ዲዛይን ስናደርግ አካታች ይሆናል፤›› ትላለች፡፡ አልባሳት ዲዛይን ሲደረጉ የተጠቃሚውን ምቾችና አቅም ያገናዘቡ መሆናቸው ቅድሚያ ይሰጠዋልና አካታችነቱን እንደሚቀጥሉበት ታክላለች፡፡ ዲዛይነሮቹ ለትርዒቱ አልባሳት ሲያዘጋጁ አካል ጉዳተኞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው በመጠየቅና እርስ በርስ በመወያየትም ነበር፡፡

በትርዒቱ በዊልቸርና በክራንች ድጋፍ የሚሄዱ፣ መስማት የተሳናቸው፣ ዓይነ ሥውራን፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያላቸው፣ በሥጋ ደዌ የተጠቁና ሌላም ዓይነት የአካል ጉዳት ያላቸው የተካተቱ ሲሆን፣ ከ28 ሞዴሎች አምስቱ ወንዶች ናቸው፡፡ ትርዒቱን ዓመታዊ የማድረግ ዕቅድ እንዳለም ዲዛይነሯ ትናገራለች፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፋሽን ሲባል አካል ጉዳተኞችንም የሚያካትት መሆኑን በማሳየት ረገድ ጭላንጭል እየታየ ነው፡፡