አገሪቱን ለቀውስ የዳረጋት መሠረታዊ ምክንያት የዴሞክራሲ ግንባታው ሒደት ወደ ኋላ መጓተት ነው

በበርሄ መኮንን (ዶ/ር)

   ኢሕአዴግ የደርግን መንግሥት በጉልበት ጥሎ ሥልጣን ከያዘ 25 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ 25 ዓመታት አገሪቱና ገዢው ፓርቲ ከገጠሟቸው ፈተናዎችም ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተደረጉትን ተቃዋሚዎች ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ በግንባር ቀደም የሚጠቀስ ነው፡፡ ቀውሱ የብዙ ሰዎች ሕይወት ከጠፋና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረት ከወደመ በኋላም ሊቆም ስላልቻለ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ደርሷል፡፡ ሁኔታዎች ለጊዜው የተረጋ ቢመስሉም ችግሩ ከመሠረቱ ተፈቷል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በተከሰተው ቀውስ ምክንያትና መፍትሔ ዙርያ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ሐሳባቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ ላይ ያለኝን ሐሳብ በዚህ ጽሑፍ አቀርባለሁ፡፡ በተቻለኝ መጠንም ካሁን በፊት በሌሎች ሰዎች ባልተነሱ ወይም በሚገባ ባልተነሱ ነጥቦች ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ፡፡

   በእኔ እምነት አሁን ላለንበት ሁኔታ የዳረጉን ብዙ ተዛማጅ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ምክንያት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በበቂ ፍጥነት ባለመጓዙ፣ ይልቁንም በብዙ መልኩ ወደ ኋላ መጎተቱ ነው፡፡ የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠቃሚ አለመሆንና የመሳሰሉ ችግሮች እንደ ምክንያት ሲጠቀሱ ይሰማል፡፡ እነዚህን ችግሮች እንደ የቅርብ ጊዜ መነሻዎች (Immediate Causes) እንጂ እንደ መሠረታዊ ምክንያት አላያቸውም፡፡ ይህን የምለው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የኋልዮሽ ባይሄድ (በሌላ አባባል የፖለቲካ ምኅዳሩ አሁን ባለበት ደረጃ ባይጠብ) ኖሮ ከፍ ብለው የተጠቀሱት ችግሮች ወይም አይፈጠሩም፣ ቢፈጠሩም ደግሞ አሁን ካሉበት ደረጃ አይደርሱም ነበር፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ችግሮቹ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የፖለቲካ ምኅዳሩ በመጥበቡ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ማለትም የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ አካል ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየሰፋ ቢሄድ ኖሮ የዴሞክራሲ ሒደቱ ራሱ ችግሮች አሁን ካሉበት ደረጃ እንዳይደርሱ ያደርግ ነበር፡፡ ሁለተኛ፣ አንዳንዶቹ ችግሮች የፖለቲካ ምኅዳሩ እየሰፋ ቢሄድም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እንደ ድህነትና ሥራ አጥነት ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮች በቅርብ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ሆኖም በእነዚህ ዓይነት ችግሮች ሳይቀር ሕዝብ ቅሬታ ቢኖረው የፖለቲካው ምህዳሩ አሁን ባለበት ደረጃ ባይጠብና እየሰፋ ቢሄድ ኖሮ ቅሬታው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይገለጽ ነበር፡፡ በሌላ አባባል ምንም እንኳን እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም፣ ሕዝቡ ችግሩን የሚገልጽበትና የመፍትሔ አካል የሚሆንበት የተወሰነች ክፍተት አለች ብሎ ቢያምን ያቺኑ ክፍተት ለመጠቀም ይሞክር ነበር፡፡ ችግሩም ከቁጥጥር ሥርዓት ውጪ አይሆንም ነበር፡፡

    የሕዝብ ብሶት በተባባሰበትና ብሶቱንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ በቂ ክፍተት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ፣ የሚቀሰቅስ ነገር በተገኘ ጊዜ የሚፈነዳና በቀላሉ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን የሚችል የሕዝብ ተቃውሞ ይፈጠራል፡፡ የተፈጠረውም ይኸው ነው፡፡ በመንግሥት ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበረው የሕዝቡን ቅሬታ ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ሲሉ አመፅ እንዲቀሰቀስ የሚሠሩ የውስጥም የውጭም ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም እነዚህ ኃይሎች ኖሩም አልኖሩም መሠረታዊ ችግሩ እስካልተፈታ ድረስ አመፅ መፈጠሩ እንደማይቀር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔውም በጣም እየጠበበ የመጣውን የፖለቲካ ምኅዳር ማስፋትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን በበቂ ፍጥነት ማስኬድ ነው፡፡ ለዚህም ገዢው ፓርቲ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ቢኖርበትም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም የራሳቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡

     ቀሪው የጽሑፍ ክፍል በአራት ክፍሎች ይቀርባል፡፡ በመጀመሪያ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደትና ጥቅሞቹ ለሚቀጥሉት ክፍሎች መንደርደሪያ በሚሆን መልኩ አጠር ያለ ገለጻ እሰጣለሁ፡፡ በመቀጠልም የ25 ዓመቱን የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞና አሁን ላለንበት ደረጃ እንዴት እንደደረስን በአጭሩ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ ከዚያም የጽሑፉ ዋና ክፍል ወደ ሆነውና የመፍትሔ ሐሳቦች ወደሚቀርብበት ክፍል እንገባለን፡፡ በዚህ ክፍል በገዢው ፓርቲናና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊወሰዱ ስለሚገቡ ዕርምጃዎች አብራራና ከዚያም ባለፈው ዓመት ከተካሄዱት ተቃውሞዎችና አመፆች መወሰድ ስለሚገባቸው ትምህርቶች አንዳንድ ሐሳቦችን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም ማጠቃለያ ሐሳብ ይኖራል፡፡

   

ዴሞክራሲ እንዴት ይገነባል? ጥቅሞቹስ ምንድን ናቸው?

    ዴሞክራሲ በብዙ መልኩ ሊተረጎም ቢችልም በመሠረታዊ ደረጃ በሕዝብ የተመረጠ አካል ለተወሰነ ጊዜ የመንግሥት ሥልጣን የማይዝበትና የሥልጣን ጊዜው ሲያልቅ ደግሞ ለተረኛ ተመራጭ የሚያስረክብበት ሒደት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ከኢዴሞክራሲያዊ (አምባገነን) መንግሥት የሚለይበት ዋናው ምክንያት እንደ ኋለኛው የሥልጣን መሠረቱ ጉልበት ሳይሆን የሕዝብ ይሁንታ መሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ትንሽ ሰፋ አድርገን እንየው ካልን ደግሞ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ከመኖሩ በተጨማሪ መሠረታዊ የሚባሉ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩበት የአስተዳደር ሥርዓት ልንለው እንችላለን፡፡

የዘርፉ ምሁራን እንደሚያስረዱት አንዲት አገር ከኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትሸጋገረው በመሪዎች (ሊህቃን) በጎ ፈቃድ ሳይሆን፣ በመሪዎችና በተራው ሕዝብ (ተመሪዎች) መካከል በሚኖረው የፍላጎት ተቃርኖ (Conflict of Interest) የተነሳ ተራው ሕዝብ በመሪዎች ላይ በሚያደርገው ግፊት ነው፡፡ ከሰዎች ተፈጥሯዊ ራስ ወዳድነት የተነሳ መሪዎች ሥልጣናቸውን በዋናነት ለራሳቸው ጥቅም ማዋል ይፈልጋሉ፡፡ ኢዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓት ደግሞ ተራውን ሕዝብ በመጨቆን የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ የሚከለክላቸው ነገር አይኖርም፡፡ ተራው ሕዝብ በዚህ ደስተኛ ስለማይሆን ሁኔታዎች ሲመቹለት ተቃውሞ ያነሳል፡፡ የሕዝቡ ተቃውሞ የማንሳት ዕድልና የተቃውሞው ጥንካሬ በውስጡ ባለው የትብብርና የመደራጀት አቅም ይወሰናል፡፡ ለዚህ ነው የከተሞችና የትምህርት መስፋፋት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደ መልካም ነገር የሚታዩት፡፡ መሪዎች ደግሞ የሕዝቡን ተቃውሞ በጉልበት ወይም መለስተኛ ለውጥ በማድረግ ለመቀልበስ ይሞክራሉ፡፡ ተቃውሞው እየጠነከረ የሄደ እንደሆነና መሪዎችም በጉልበት ወይም መለስተኛ ለውጥ በማድረግ እንደማይመለስና ይልቁንም በቂ መልስ ካልሰጡ ወደ አብዮት ተቀይሮ ከሥልጣናቸው ሊያወርዳቸው  (ከዚያ የባሰም ሊገጥማቸው ይችላል) እንደሚችል ከተረዱ ሕዝቡ የጠየቃቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ይገባሉ፡፡ለቃላቸው ማረጋገጫም የእነሱን ሥልጣን የሚቀንሱ (የሕዝቡን ሥልጣን የሚጨምሩ) እና የሕዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሕጎችንና አሠራሮችን ያወጣሉ፡፡ ይህንን የሚተገብሩና የሚከታተሉ ተቋማትን መገንባትም ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም በቀረቡት ማሻሻያዎችና በተቋቋሙት ተቋማት ጥንካሬ በተማመነ መጠንም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ ባጭሩ ይህን ቢመስልም በተግባር የተወሳሰበና ብዙ ውጣ ውረዶች የበዛበት ነው፡፡ ወደ ኋላ የመመለስ አደጋውም ሰፊ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማቱ በጣም ካልዳበሩና የሕዝቡ ተቃውሞ ከተቀዛቀዘ መሪዎች ተቋማቱን በማጥፋት ወይም በመቆጣጠር የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሒደት ሊቀለብሱት ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መሪዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ከምር ቢጀምሩም ሕዝቡ በግንባታው ፍጥነት ካልረካ አመፅ ቀስቅሶ ሊጥላቸውና የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል፡፡

   በማንኛውም አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባበት ሒደት በመሠረታዊ ደረጃ ከላይ እንደተገለጸው ቢሆንም ዝርዝር ሒደቱ አገሮች ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ የሚለያይና የሚወሰን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀድመው ዴሞክራሲን በገነቡ አገሮች (በተለይ ምዕራባዊያን አገሮች) እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በቅርቡ በጀመሩ ወይም ገና ባልጀመሩ አገሮች መካከል አንድ ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ይኸውም በቀደሙት አገሮች የነበረው ሒደት ምንም እንኳን የራሱ ውጣ ውረዶችና መስዋዕትነቶች የነበሩት ቢሆንም፣ በአመዛኙ በአገሮች ነባራዊ ሁኔታ የተነሳሳና ተፈጥሯዊ ሊባል የሚችል አካሄድ የነበረው ነው፡፡ በኋለኞቹ ላይ ግን ከውስጣቸው ነባራዊ ሁኔታ በተጨማሪ የውጪ ተፅዕኖውም ቀላል አይደለም፡፡ የውጭ ተፅዕኖው በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው በቀጥታ ከምዕራባዊያን መንግሥታት የሚመጣ ነው፡፡ ይኼ ተፅዕኖ በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ እየጨመረ መጥቷል (ምንም እንኳን አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብር ትግሉ ምክንያት እየቀነሰ ነው ቢባልም)፡፡ ከምዕራባዊያን የሚመጣው ግፊት ከጊዜ ወደ ጊዜና ከአገር ወደ አገር ቢለያይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሁሉም አገር ሊከተለው የሚገባ ሥርዓት ስለመሆኑ ከመንግሥታቱ አልፎ በዋናነት በእነሱና በሕዝባቸው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋሚ ስለሚሰበክ ገና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባልገነቡ አገሮች ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ለዚያም ይመስላል በአሁኑ ጊዜ ወቅቱን እየጠበቀ የሚመጣ ምርጫ የማያካሂዱና በግልፅ ዴሞክራሲያዊ አይደለም የሚሉ መንግሥታት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ የሆኑት ፡፡

   ሁለተኛው ተፅዕኖ ዓለም ከቀድሞው በበለጠ በመተሳሰሯ ገና ዴሞክራሲ ባልዳበረባቸው አገሮች ያሉ ዜጎች በተለይ ደግሞ የተማሩትና ከተሜዎች ዴሞክራሲ በዳበረባቸው አገሮች ያለውን ነፃነትና መብት እነሱ አገርም እንዲኖር በመፈለግ ከሚያደርጉት ግፊት የሚመጣ ነው፡፡ የዳያስፖራው ተፅዕኖም ከዚህ ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ ከማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ እየፈጠረም ነው፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በፍጥነት እንዲጀመር የማድረግ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ቢችልም፣ ከአገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ካልተቀናጁ ለወትሮው አስቸጋሪ የሆነውን ሒደት የበለጠ ውስብስብና ውጣ ውረዶች የበዙበት ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በተለይ ከምዕራባውያን የሚመጡ ቀጥተኛ ተፅዕኖዎች መንግሥታት ከእነዚሁ አገሮች የሚያገኙትን ዕርዳታ እንዳይቀርባቸው ሲሉ ብቻ የውሸት ዴሞክራሲ እንዲጀምሩ ስለሚያደርጉ፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ይታመናል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጣም ከባድና ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት ቢሆንም፣ ጥቅሞቹም የዚያን ያህል ብዙ ናቸው፡፡ ዜጎች የሚያስተዳድሯቸውን መሪዎች መምረጥ መቻላቸው በራሱ ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ ከዚ ያለፈ ተግባራዊ (Practical) ጥቅሞችም አሉት፡፡

   ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር ሲነፃፀር ለሕዝብ ጥቅም የቆመ፣ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብርና በአጠቃላይም የተሻለ የማኅበራዊ ፍትሕ እንዲኖር የሚጥር ጥሩ መንግሥት እንዲኖር የማድረግ ዕድሉ በእጅጉ የሰፋ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም በሁለቱ ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ ፓርቲዎች የሕዝቡን ይሁንታ አግኝተው ሥልጣን ላይ ለመውጣት (እንዲሁም ወጥቶ ለመቆየት) ሲሉ ሕዝብ የሚወደውን ፖሊሲ ለመቅረፅና ለመተግበር ይታትራሉ፡፡ ሁለተኛ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖሩ እንደ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ገለልተኛ ሚዲያ፣ ጠንካራ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወዘተ ያሉ ተቋማት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ እንደ ምሰሶ ከማገልገል በተጨማሪ፣ መንግሥት በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት እንዳይፈጽምና ቃል የገባቸውን ፖሊሲዎች እንዲተገብር ጫና ያደርጉበታል፡፡ እነዚህ ጥቅሞች ታድያ ዴሞክራሲ የሚፈጥራቸው ዕድሎች (Permissive Advantages) እንጂ ዴሞክራሲ ስላለ ብቻ በእርግጠኝነት የሚከሰቱ አይደሉም፡፡ አንዲት ዴሞክራሲያዊት አገር ምን ያህል በእነዚህ ዕድሎች ተጠቃሚ እንደምትሆን በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎችና ዴሞክራሲው ራሱ በተገነባበት መንገድ ሊወሰን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደ ግንባር ቀደም አርዓያ ተደርጋ የምትጠቀሰውና ራሷን ነፃው ዓለም (The Free World) እያለች የምትጠራው አሜሪካ፣ ከማኅበራዊ ፍትሕ አንፃር በጥሩ እንደማትነሳና እጅግ ብዙ የሚቀሯት ሥራዎች እንዳሏት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

    የዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ሌላኛውና እርግጠኛ ጥቅሙ የተረጋ (Stable) ሥርዓት መሆኑ ነው፡፡ የዳበረ ዴሞክራሲ ባለበት አገር የተገነባ ሥርዓት ብዙ ያልተጠበቁ ፈተናዎች (ለምሳሌ ድርቅ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ጦርነት፣ ወዘተ) ቢገጥሙትም የመበታተን ዕድሉ ወደ ዜሮ የተጠጋ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቢወርድ እንኳን (የተመረጠበት ጊዜ ሳያልቅም ቢሆን) ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት የመቀጠል ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ አንድነቷንና ሰላሟን ጠብቃ እንድትቀጥል በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በአንፃሩ ኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለበት አገር ከባድ ፈተና በገጠመ ጊዜ መንግሥት ቢፈርስ ሥርዓቱም አብሮ ስለሚፈርስ፣ አገሪቱ የመበታተን አደጋን ጨምሮ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የመግባት ዕድሏ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ጥቅም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ከፍተኛ ብዝኋነትና ገና ያልሻሩ ብዙ ብሶቶችና ቁርሾዎች ላላት ትልቅ አገር የበለጠ ነው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ የሚሰሙት፡፡ ይህን ታዲያ በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

 ያለፉት 25 ዓመታት በዴሞክራሲ ግንባታ ዓይን

    ኢሕአዴግ የደርግን መንግሥት ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ያለው ሥርዓት እንዲመሠርት የሚገፋፋ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አንደኛ በወቅቱ የቀዝቃዛው ጦርነት ማለቅና ከምዕራባውያን አሸናፊ ሆኖ መውጣት ጋር ተያይዞ ዴሞክራሲ እንደ መልካምና ሁሉም ሊተገብረው እንደሚገባ ነገር ይታይ ነበር፡፡ እንዲሁም ኢሕአዴግን በረሃ እያለ ይደግፉ የነበሩ (መንግሥት ከመሠረተም በኋላም ድጋፋቸውን የቀጠሉ) ምዕራባውያን አገሮች ኢትዮጵያዊ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ግፊት ያደርጉ ነበር፡፡ ሁለተኛ እንደ ኢትዮጵያ ባለች የብሔር፣ የሃይማኖትና ሌሎችም ብዝኋነቶች ባሏት አገር ለዚያውም ከረዥም የእርስ በእርስ ጦርነት በወጣች ማግሥትና ብዙ ሽምቅ ተዋጊዎች በተለያዩ የአገሪቱ ማዕዘናት በነበሩበት ወቅት አምባገነናዊ ሥርዓት መመሥረት ከባድ ነበር፡፡ ሦስተኛ ኢሕአዴግ ከስልሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደተወለደ ማርክሲስት ድርጅት (ከነችግሮቹ) በሽምቅ ተዋግተው ሥልጣን ከያዙ ብዙ ኃይሎች አንፃር የተሻለ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት የመጀመር ዕድል ነበረው፡፡ ከሕዝባዊ ወገንተኝነትና ከዴሞክራሲ እሴቶች ጋር የሚስማሙ አመለካቶች ነበሩት (ለምሳሌ የራስን ዕድል በራስ መወሰንና የብሔር፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ እኩልነትን መጥቀስ ይቻላል)፡፡ ይህም ዴሞክራሲን (ሙሉ በሙሉ ባያምንበትም) እንደ አማራጭ እንዲያየው ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ሌላው ኢሕአዴግ ይከተለው የነበረው (አሁንም እንደሚከተለው የሚናገርለት) የጋራ አመራር መርህ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረት የኢሕአዴግ የበላይ መሪዎች ውሳኔዎችን በጋራ ስለሚያሳልፉና ስለሚያስፈጽሙ እያንዳንዳቸው (ሊቀመንበራቸውን ጨምሮ) ውስን ሥልጣን ነው የነበራቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመጀመር በአንድ መሪ ከሚመራ ሽምቅ ተዋጊ አንፃር ለኢሕአዴግ የቀለለ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱቶች ምክንያት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲጀመር አስተዋፅኦ ቢያደርጉም፣ የግንባታው ሒደት የሰመረ በማድረጉ በኩልም አዎንታዊ ሚና ነበራቸው ማለት አይደለም፡፡ በአንፃሩ ሒደቱን ከባድ የሚያደርጉ ምክንያቶችም ነበሩ፡፡

   በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ በድህነት፣ በጦርነትና በኋላ ቀርነት የኖረች አገር ስለሆነች ለዴሞክራሲ የተመቻቹ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡ በንጉሡ ጊዜ የነበሩ ለዴሞክራሲ ግንባታ እንደ ግብዓት ሊያገለግሉ የሚችሉ አንዳንድ ባህሎችና አሠራሮች በአብዮቱ ጊዜ ጠፍተዋል፡፡ በስፋት ይታዩ የነበሩ ባህላዊና አክራሪ (Conservative) አመለካከቶችን በመገዳደር ለዴሞክራሲ ግንባታ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ የታዩ ተራማጅ (Progressive) አመለካከቶችም፣ የደርግን ወደ ሥልጣን መውጣት ተከትሎ በነበረው መተላለቅ እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በደርግ የማያባራ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ቀላል የማይባል ከተሜ (በተለይ የተማረው ክፍል) ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ እንደመጣ ከፋፋይና ዘረኛ ኃይል ያይ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ያቀነቅናቸው የነበሩ ተራማጅ አመለካከቶችም በመሠረታዊ ደረጃ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ይራመዱ ከነበሩ አመለካከቶች ጋር አንድ ዓይነት ቢሆኑም (ምንም እንኳን በአንዳንዶቹ ላይ ኢሕአዴግ ወደ ጫፍ የወጣ አመለካከት ቢኖረውም) እሱ እንደፈጠራቸውና ምንም መልካም ነገር እንደሌላቸው ተደርገው ይታዩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ከተሜ የደርግን ውድቀት እንደ ራሱ ውድቀት አድርጎ የማየት አዝማሚያ ነበረው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ተፅዕኖ እስካሁን ቀጥሎ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞች፣ በምሁራን፣ እንዲሁም ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተወለዱ ወጣቶች ሳይቀር ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአንፃሩ ኢሕአዴግ ማርክሲስት አስተሳሰቡ ደርግን የሚያህል ግዙፍ ኃይል በጉልበት ከማሸነፉ ጋር ተደምሮ ከእሱ የተለየ ሐሳብ ያራመዱትን ሁሉ የመናቅና የማጣጣል አዝማሚያ ነበረው፡፡ የተቃወሙትን ሁሉ የተለያዩ ስሞችን በመስጠት (ለምሳሌ ትምክህተኞች፣ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች፣ ወዘተ) ከመምጣቱ ጠላት ማፍራቱን ተያይዞት ነበር፡፡ አሁን ከዚህ በሽታው የተላቀቀ አይመስለኝም፡፡ ይህ አመለካከቱ በራሱ ለዴሞክራሲ ግንባታ የማይመች ሆኖ ሳለ፣ በተለይ በተቃራኒው ደግሞ የዴሞክራሲን ባህል ያላዳበረና በቀላሉ የሚገፋ ከተሜ ብዙ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ለዴሞክራሲ ግንባታ ጠንቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

   በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት የነበረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት እዚህም እዚያም ችግር ቢኖሩትም፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ነባራዊ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገብተው ካዩት በአመዛኙ መልካም የሚባል ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንፃራዊ ነፃነት ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት ኢሕአዴጎችና አጋሮቹ ቢሆኑም የተወሰኑ ተቃዋሚዎችም የሚመረጡበት ዕድል ነበር፡፡ ብዙ የግል ጋዜጦች ነበሩ፣ፍርድ ቤቶች ቀላል የማይባል ነፃነት ነበራቸው፡፡ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ግንኙነትም እንደ አሁኑ ሙሉ በሙሉ አልተደበላለቀም ነበር፡፡ ወዘተ፡፡

  በ1993 ዓ.ም. የኤርትራ ጦርነት ካለቀ በኋላ በሕወሓት ውስጥ ጀምሮ ከዚያ በሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የተሰራጨው የመከፋፈል ችግርና የተፈታበት መንገድ ገና በማደግ ላይ በነበሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ምክር ቤቶች የራሳቸውን አባላት መብት እንኳን ማስከበር የማይችሉ ጥርስ አልባ አንበሶች መሆናቸው በግልጽ ታየ፡፡ በማደግ ላይ የነበረው የፍርድ ቤቶች ነፃነትም ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡ ቢሆንም በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት የተመዘገቡት ድሎች ሙሉ በሙሉ አልተቀለበሱም ነበር፡፡ ይልቁንም ኢሕአዴግ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቴን ወደ ኋላ ይጎትቱ የነበሩ አባሎቼን በማስወገድ “ተሃድሶ አድርጌያለሁ” አለ፡፡ ብዙዎችም ከተሃድሶው መልካም ነገር ይወጣል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ከተሃድሶው ቀጥሎ በነበሩት ጥቂት ዓመታት የተወሰኑ የሚታዩ ለውጦችን ለማምጣት ይጥር የነበረው ኢሕአዴግ፣ በ1997 ምርጫ ዋዜማ ተሃድሶውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የቆረጠ በሚመስል መልኩ ነፃና ፉክክር የሞላበት ምርጫ ለማሄድ ቁርጠኝነቱን አሳየ፡፡ ኢትዮጵያም ያልጠበቀችውንና የማታውቀውን ሰላማዊ የሥልጣን ትንቅንቅ ለማየት በቃች፡፡ ዳሩ ምርጫው በጠንካራ ገለልተኛ ተቋማት ያልታጀበና በገዢው ፓርቲ ሕዝብ ይወደኛል ስለዚህ በምርጫም ማሸነፍ እችላለሁ ከሚል ግብዝነት የመነጨ “በጎ” ፈቃድ የተደረገ ስለነበረ የኋለ ኋላ መጨረሻው ሳያምር ቀርቷል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ብዙዎች ተስፋ እንዳደረጉት ዴሞክራሲ የዳበረበት ዓመት መሆኑ ቀርቶ፣ ከዚያ በፊት የነበሩትም መልካም ለውጦች ወደ ኋላ መሄድ የጀመሩበት ዓመት ሆነ፡፡

  የዴሞክራሲ ተቋማት ባልጠነከሩበትና ትንሽም ብትሆን ሥልጣን ለተቃዋሚዎች ማካፈል ፈቃደኛና ዝግጁ ባልሆነበት ሁኔታ እንደዚያ ዓይነት ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጉ በኢሕአዴግ በኩል ታሪካዊ ስህተት ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች (በተለይ ቅንጅት) ሥልጣን “ወይ ዘንድሮ ወይ መቼም (Now or Never)” የሚል የከረረ አቋም መያዛቸውና በውስጣቸው የነበረው ኢዴሞክራሲያዊነት ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል የነበረው ጥላቻና መናናቅም እንዲሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ኢሕአዴግ ለዘለቄታው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ለጊዜው ደግሞ ፖለቲካውን በመቆጣጠር ሥልጣን ላይ ለመቆየት መወሰኑን በግልጽ በሚያሳይ ሁኔታ ዕርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ፡፡ ገና በማደግ ላይ የነበሩትን ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት ጭምር ማዳከሙን ተያያዘው፡፡ አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች ተዘጉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ገለልተኝነታቸው እጅግ ቀነሰ፣ ገና ያልዳበሩ የነበሩ የሲቪክ ተቋማት ይበልጥኑ ተዳከሙ፣ ወዘተ፡፡ መንግሥትና ገዢው ፓርቲም ከልክ በላይ ተደበላልቀው የመንግሥት ሥራና ጥቅማ ጥቅም የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ መሣሪያ ሆኑ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተካሄደው የ2002 ምርጫ የፌደራል ምክር ቤቱን ከሁለት ወንበሮች ውጪ በኢሕአዴግ ቁጥጥር እንዲሆን አደረገ፡፡ ኢሕአዴግም የምርጫውን ውጤት ያልጠበቀው ይመስል (ምናልባትም አልጠበቀው ይሆናል) ኢትዮጵያ ለጊዜው የሚያስፈልጋት አንድ አውራ ፓርቲ ነው የሚል መላምታዊ ክርክር መደጋገም ጀመረ፡፡ ምክር ቤቱን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መቆጣጠሩ ለእሱም ለአገሪቱም መልካም እንዳልሆነ ተረድቶ በ2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ የፖለቲካ ምኅዳሩን በተወሰነ ደረጃ ከፈት ያደርዋል ተብሎ ቢጠበቅም ያ ሳይሆን ቀረ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የባሰ እየጠበበ ሄደ፡፡ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ግንኙነትም የባሰውን ቅጥ አጣ፣ ሙስናና የአስተዳደር በደሎችም ተባባሱ፡፡ በምርጫውም ኢሕአዴግ 100% አሸናፊ ሆነ፡፡ አሁንም ውጤቱን ያልጠበቀው ወይም ያልተቀበለው ይመስል በ100% ያሸነፈው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለደከሙና ስለበዙ ነው የሚሉ ምክንያችን መደርደር ጀመረ፡፡ ዳሩ ውጤቱ በመጠኑም ቢሆን ነፃና ፍትሐዊ ፉክክር ተደርጎበት ሕዝቡም በነፃነት መርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ማስተባበያ አያስፈልግም ነበር፡፡

    ፖለቲካውን ለመቆጣጠር ብሎ የወሰዳቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ዕርምጃዎች የኋላ ኋላ እሱ ራሱ መቆጣጠር ወደማይችለው ባሕልና መረብ እየተቀየሩ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር ችግር ሥር እየሰደዱ ሄደው ሕዝቡን ክፉኛ ወደ ማማረር ብሎም የኢኮኖሚው ዕድገት ላይም ጥላቻውን ወደ ማጥላት ደረሱ፡፡ በመጨረሻም ለብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፍና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረት መውደም ምክንያት ወደ ሆነውና የአገሪቱንም ህልውና ወደ ተፈታተነው ቀውስ አስገቡን፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

በኢሕአዴግ መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች

   ኢሕአዴግ አስቀድሞ ማድረግ ያለበት ነገር የችግሩ መሠረታዊ መንስዔ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከሚገባ በላይ መጥበቡ መሆኑን መቀበል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ችግር መሆኑን በተወሰነ ደረጃ የተቀበለ ቢመስልም እስካሁን ዋናው ትኩረቱ የመልም አስተዳደር ችግሮቸን መቅረፍ፣ ሙስናን መዋጋት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሻሻልና የመሳሰሉ ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ እነዚህን የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮችን መፍታት ጥሩ ቢሆንም በበሳል የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ዕቅድና ተግባር ካልታገዙ መሠረታዊ ችግሩን ይፈታሉ ብዬ አላምንም፡፡ እነሱ ራሳቸው የመፈታት ዕድላቸው ጠባብ ነው የሚሆነው፡፡ ለሁሉም ችግር እንደ መንስዔ እየተጠቀሰ ያለው ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ባህልም እንዲሁ የመጣ ሳይሆን፣ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው እሱ ራሱ ፖለቲካውን ለመቆጣጠር ሲል በወሰዳቸው ኢዴሞክራሲያዊ ዕርምጃዎች የመጣ መሆኑን መቀበል አለበት፡፡

   ይህን ተቀብሎ ለዴሞክራሲ ግንባታ የራሱን ተራ መወጣት አለበት፡፡ እንዲያውም በሁለት ምክንያቶች የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ አንደኛ ገዢ ፓርቲ በመሆኑና የመንግሥትን ሥልጣን በመቆጣጠሩ በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ተወዳዳሪ የሌለው አቅም ስላለው ነው፡፡ ሁለተኛ ዴሞክራሲ ቢዳብር እሱ ራሱ ተጠቃሚ ስለሚሆን ነው፡፡ እሱ በማይቆጣጠረውና ሊተነብየው በማይችል  የሕዝብ አመፅ ከሥልጣኑ ከሚወርድ፣ እሱ በመራው የዴሞክራሲ ሒደት ሥልጣኑን ቢያስረክብ ይሻለዋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሥልጣን ቢወርድ ተመልሶ ወደ ሥልጣን የመመለስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ በጉልበት ከወረደ ግን እንኳን እሱ አገሪቱ ራሷ ምን እንደሚገጥማት አይታወቅም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት 25 ዓመታት ያስመዘገበችው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችም የበለጠ እንዲዳብሩ እንጂ እንዲቀለበሱ አይፈለግም ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ታዲያ አሁን ባለበት ሁኔታ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የውስጥ ትግል አድርጎ የምር “በጥልቀት” መታደስና የዴሞክራሲ ባህሉንም ማዳበር አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም እንደ ጠላትና አፍራሽ ኃይሎች ማየቱን አቁሞ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሒደት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አካላት ማየት አለበት፡፡ ከእሱ የተለየ አመለካከት ላላቸው ወገኖች የተለያዩ ስሞችን በመስጠት የሐሳብ የበላይነት እንደማይገኝ አውቆ ሐሳብን በሐሳብና በሰለጠነ መንገድ የመሞገት ልምድም ማዳበር አለበት፡፡

   የችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ዴሞክራሲ ግንባታውን ማፋጠን መሆኑንና ለዚህም የመሪውን ሚና መጫወት እንዳለበት ከተቀበለ የሚቀጥለው ዕርምጃ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመነጋገርና በመመካከር፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋበትን መንገድ መፈላለግ ይሆናል፡፡ ለዚህ ታድያ የተለመደውን ሁሉን አውቃለሁ ዓይነት አስተሳሰቡን መተው አለበት፡፡ ለዴሞክራሲ ግንባታ ምሰሶ የሆኑት ተቋማት ላይም የሚታይ በቂ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ ለምሳሌ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን እንደ አዲስ እንዳዋቀረው ሁሉ የምርጫ ቦርዱንም ተዓማኒነቱንና ገለልተኝነቱን በሚያሻሽል ደረጃ እንደገና ቢያዋቅር፣ የፍርድ ቤቶችን ገለልተኝነትና አቅም የሚጨምሩ ዕርምጃዎችን ቢወስድ፣ የመንግሥት ሚዲያ ከተራ ፕሮፓጋንዳ ተቋምነት ተላቆ የተለያዩ ሐሳቦች የሚቀርቡበትና የተሻለ ተአማኒ እንዲሆን የሚያደርጉ ዕርምጃዎችን ቢወስድ፣ ወዘተ ጥሩ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ተቋማት ላይ በቂ ለውጥ ማምጣት አለበት ሲባልም በአንዴ የዳበረ ዴሞክራሲ ባላቸው አገሮች ያሉት ተቋማት የደረሱበት ደረጃ ላይ ይድረሱ ማለት ሳይሆን፣ አሁን ካሉበት በጣም መሻልና ሕዝቡ መንግሥት የዴሞክራሲ ግንባታውን ሒደት ከምር ወደ ፊት ለማስኬድ እንደወሰነ የሚያሳምኑ መሆን አለባቸው ለማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ተቋማቱ ላይ በበቂ መሥራት ከጀመረ የተራዘመ የተረጋ ሁኔታ የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ ይሆንና የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮቹን ለመፍታት የተመቻቸ ሁኔታ ይኖራል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮቹ እየተቃለሉ በሄዱ ቁጥር ደግሞ ለረጅም ጊዜ በፍትሕ ዕጦት እየተሰቃየ የኖረው ሕዝብ ትዕግሥት ማጣቱ ይቀንስና የዴሞክራሲ ግንባታው ላይ የበለጠ ለመሥራት ጊዜ ይኖራል፡፡

በተቃዋሚ ፓርቲዎች መውሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች

    ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍንና ሕዝቡን በማስተባበር መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር የዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ይህንኑ ሚናቸውን መቀበልና ለዚያ በሚመጥን ደረጃ ራሳቸውን መቀየርና ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በዴሞክራሲ ግንባታው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ በመጀመሪያ እነሱ ራሳቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ባህል በውስጣቸው ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዴሞክራሲም በገዢው ፓርቲ በጎ ፈቃድ ወይም በኃያላን መንግሥታት ጫና ሳይሆን፣ በተቀናጀ የሕዝብ ትግል ብቻ እንደሚገነባም ከምር መቀበል አለባቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን (ዳያስፖራ) ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ ለዴሞክራሲ ግድ የሌላቸውና ኢሕአዴግ እንዲወርድላቸው ካላቸው ፅኑ ፍላጎት ብቻ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ ፅንፈኛ የዳያስፖራ አካላት በተቻለ መጠን ራሳቸውን ማግለል አለባቸው፡፡ ሁኔታዎች በፈቀዱት መንገድ በምርጫ ተወዳድሮ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ለዴሞክራሲ ግንባታው አስፈላጊና ተገቢ ነገር ቢሆንም፣ የእነሱ ዓላማ ግን ከዚያ የላቀና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በማጎልበት ረገድ አዎንታዊ ሚና መጫወት መሆን አለበት፡፡ ለዚህም በየአምስት ዓመቱ ለሚካሄደው ምርጫ ከሚያደርጉት የበለጠ የረዥም ጊዜ ዕቅድና ቁርጠኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በምርጫ ተወዳድረው ሥልጣን መያዝ ባይችሉ እንደ ሽንፈት ማየት የለባቸውም፡፡ ለወደፊት ፓርቲዎች በነፃነትና በእኩልነት ተወዳድረው ሥልጣን የሚይዙበት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማድረግ ከቻሉ ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ለሚቀጥሉት ትውልድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ለአገሪቱ በአጠቃላይ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አለበለዚያ በዴሞክራሲ ግንባታው ሒደት የሚኖራቸው አስተዋፅኦ አዎንታዊ መሆኑ ቀርቶ አፍራሽ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይህን እንደሚቀበሉና ወደ ፖለቲካው የገቡበት ምክንያትም የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ታዲያ በተግባር መታየት አለበት፡፡

   ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን ደግሞ በባህሪው መጥሮ እንደሆነና አፍራሽ ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ኃይል አድርጎ ማየቱን ማቆም አለባቸው፡፡ ጥንካሬውና ስኬቶቹን ደግሞ ከቻሉ ዕውቅና መስጠት ካልቻሉ ደግሞ አለማጣጣል መልመድ አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ኢሕአዴግን ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ተራ ሊኖረው እንደሚችል አካል ቆጥረው በቅንነት ከእሱ ጋር ለመሥራት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ብዙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው (ምሁራንን ጨምሮ) ኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ግንባታው ሒደት አካል ሊሆን እንደማይችልና የዴሞክራሲ ግንባታውን ለመጀመር መጀመሪያ እሱ ከሥልጣን መውረድ እንዳለበት በእርግጠኝነት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ይህን የተሳሳተ አመለካከት የሚያራምዱት በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፡፡ አንድም ዴሞክራሲ የሚገነባው በመሪዎች በጎ ፈቃድ ሳይሆን በሕዝብ ትግል መሆኑን ከልብ ካለማመን የተነሳ ነው፡፡ አልያም ኢሕአዴግ ላይ ካላቸው ጥልቅ ጥላቻ የተነሳ በምንም ምክንያት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ስለማይፈልጉ ነው፡፡ አንድ ትግል ዴሞክራሲን በመገንባት ረገድ ስኬታማ ለመሆን ዋና ዓላማው የሕዝቡን መብትና ጥቅም ማስከበርና ለዚያም ዋስትና የሚሆኑትን ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መገንባት መሆን አለበት፡፡ ይህን መርህ መሠረት ያደረገ ትግል ደግሞ በቂ የሕዝብ ድጋፍና ብቃት ያለው አመራር እስካገኘ ድረስ ስኬታማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ እያለ ነው ወይስ ከወረደ በኋላ ነው የሚለው ጥያቄ፣ በሁኔታዎች የሚወሰንና በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢሕአዴግ የለውጡ አካል ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ባጠረ ጊዜና ባነሰ ኪሳራ ሊመሠረት ይችላል፡፡ ከወዲሁ ኢሕአዴግ የለውጡ ሒደት አካል ሊሆን ስለማይችል፣ የትግሉ የመጀመሪያ ዓላማ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማውረድ መሆን አለበት ከተባለ ግን ትግሉ ኢሕአዴግን ከሥልጣን በማውረዱ በኩል ስኬታማ ቢሆን እንኳን ዴሞክራሲ ሊገነባ አይችልም፡፡ እንደገና ሌላ ትግል መጀመር ሊኖርብን ነው ማለት ነው፡፡ አንድን ቡድን ከሥልጣን ለማውረድ (ወይም ወደ ሥልጣን ለማውጣት) የሚደረግ ትግል ከበጎ ፍላጎት ቢነሳ እንኳን በባህሪው ኢዴሞክራሲያዊ ስለሚሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ አይችልም፡፡

ባለፈው ዓመት ከተካሄዱት ተቃውሞዎች መወሰድ ያለባቸው ትምህርቶች

   ባለፈው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ተቃውሞዎች የተለያዩ መነሻዎች ቢኖሯቸውም በመሠረታዊ ደረጃ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁሉም ተቃውሞዎች የተከሰቱት በሕዝቡ መሀል ሥር የሰደዱ ቅሬታዎች በመኖራቸውና ቅሬታዎቹንም በመደበኛ መንገድ ለማቅረብ በሩ በጣም ስለጠበበ ነው፡፡ ተቃውሞዎቹ ለዴሞክራሲ ግንባታ መሠረት የመሆን ዕድል የነበራቸው ቢሆኑም፣ የኋላ ኋላ ወደ ብጥብጥና ሥርዓት አልበኝነት እያመዘኑ ሄደው ለብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለብዙ ንብረት መውደም ምክንያት ከመሆን አልፈው፣ የአገሪቱን ህልውና ወደ መፈታተን ደርሰው ነበር፡፡ ተቃውሞዎቹ ሙሉ በሙሉ ከሽፈዋል ባይባልም በዴሞክራሲ ግንባታ ዙሪያ ሊያመጡ ይችሉ ከነበሩት ውጤትና ካስከተሉት ኪሳራ አንፃር ስኬታማ ነበሩ ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞዎች እንዴትና መቼ እንደሚነሱ መገመት አስቸጋሪ የሆነውን ያህል፣ እንዴት እንደሚያልቁም ማወቅ ወይም መቆጣጠር ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም የነበሩ ስህተቶችን ለይቶ አውጥቶ መነጋገርና ትምህርት መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ተቃውሞዎቹ በጥንቃቄና በጥበብ የሚመራቸው የተደራጀ አካል ስላልነበረና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቶሎ ብለው ዕርምጃ መውሰድ ስላልቻሉ ፅንፈኛና ነውጠኛ የሆኑት የዳያስፖራ ኃይሎች ሰለባ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ተቃውሞዎቹ ጥሩ መሪ በማጣታቸውና በአገሪቱ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ባህል ባለመኖሩ መጨረሻቸው እንዳያምር ያደረጉ ኢዴሞክራሲያዊ የሆኑ አካሄዶች ታይቶባቸው ነበር፡፡ የተወሰኑትን እንይ፡፡

  1. በተለያዩ አካባቢዎች ከታዩት የተቃውሞ መንገዶች መካከል የቤት ውስጥ መቀመጥና የንግድ ቤቶችን መዝጋት አድማዎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የተቃውሞ መንገዶች በራሳቸው ችግር ባይኖራቸውም የተቃውሞውን ጥሪ ባልተቀበሉ (ማለትም ቤት ባለመቀመጡ ወይም የንግድ ቤታቸውን ባልዘጉ) ሰዎች ላይ ይወስድ የነበረው የማሸማቀቅና የድብደባ ድርጊት ተገቢ አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲ ቁልፍ የሆነውን የግለሰብ ነፃነት የሚፃረር አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተቃውሞ ጥሪ ሲደረግ በተለያዩ ምክንያቶች የማይሳተፉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የተቃውሞው አስተባባሪዎች ወይም ተሳታፊዎች በቂ ሰው በአድማው አልተሳተፈም ብለው ካመኑ ደግሞ ያልተሳተፉ ሰዎችን በሐሳብ አሳምነው የአድማው አካል እንዲሆኑ መጣር እንጂ፣ ጉልበት መጠቀም ትክክል አይደለም ለስኬትም አያበቃም፡፡ እንዲያውም የተቃውሞውን ትክክለኝነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ሊያዳክመው ይችላል፡፡
  2. ተቃውሞ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ፋብሪካዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረት ወድሟል፡፡ እንደዚህ ባለ ተቃውሞ አልፎ አልፎ የንብረት መውደም ማጋጠሙ የተጠበቀ ቢሆንም፣ የውድመቱ መጠንና አኳኋን ባጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን እንደ ተቃውሞ ስትራቴጂ የተወሰደ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ንብረት የማውደሙ ተግባርም ተቃውሞውን ስኬታማ በማድረግ በኩል በሁለት መንገድ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ በማኅበራዊ ሚዲያ በሰፊው ይነገር ነበር፡፡ አንደኛ የልማት ተቋማት ሲቃጠሉ ሥራ አጥነት ይጨምራል፣አጠቃላይ ኢኮኖሚውም ይዳከማል፣ ከዚህ የተነሳም ሕዝቡ የባሰ ይማረርና ተቃውሞውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ሁለተኛ ኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚው ይዳከማል፣ መንግሥት ከመሬት ሽያጭና ከቀረጥ የሚያገኘውም ገቢም ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሕዝቡን ተቃውሞ የመቀልበስ አቅሙ ይዳከማል፡፡ ሁለቱም መላ ምቶች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የዳበረ ዴሞክራሲ እስከሌለ ድረስ ለሕዝብ ተቃውሞ የሚሆን ምክንያት እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሥር የሰደደ ድህነት ባለባት አገርና በተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ በሚገኙ አገሮችም ይኖራል፡፡ የተቃውሞው ጥንካሬ የሚለካውም በዋናነት በሕዝቡ የመደራጀት አቅምና በመሪዎቹ ብቃት ነው፡፡ በአንፃሩ ከልክ ያለፈ ድህነት ለዴሞክራሲ ግንባታ እንደማይጠቅም ይታመናል፡፡ መንግሥት ገቢው ሲቀንስ ተቃውሞዎቹን የመቀልበስ አቅሙም አብሮ ይቀንሳል የሚለውም ብዙ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ሀብታም መንግሥት ሳይሆኑ ጨቋኝ ሆነው ለረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚቻል ለመረዳት ሩቅ ሳንሄድ የአገራችንን ቅርብ ጊዜ ታሪክ ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ይልቁንም እንደዚህ ዓይነት ተግባር ተቃውሞውን ወደ ለየለት ሥርዓተ አልበኝነትና የእርስ በእርስ ግጭት በመቀየር የአገሪቱን ህልውና ሊፈታተን እንደሚችል በተግባር ታይቷል፡፡ የአደጋው ጊዜ አዋጁን ተከትሎ አገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረው የህልውና አደጋ (ለጊዜውም ቢሆን) ቢወገድም ተቃውሞዎቹ በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድ ሊኖራቸው ይችል የነበረው አስተዋፅኦ እንደቀነሰ ግልጽ ነው፡፡ ለወደፊት በሚደረጉ የዴሞክራሲ ግንባታ ትግሎች ላይም መጥፎ ጠባሳ ማሳረፉ አይቀርም፡፡
  3. በአንዳንድ አካባቢዎች የተደረጉ ተቃውሞዎች የዘረኝነት አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ ይህ ችግር በተለይ በአማራ ክልል በተደረጉ ተቃውሞዎች የታየ ሲሆን፣ ዘረኝነቱ ያነጣጠረውም በትግራይ ሕዝብ ላይ ነበር፡፡ በትግሬዎች ላይ ያለው ጥላቻ በተቃውሞው ጊዜ ጎልቶ ይውጣ እንጂ ከዚያ በፊትም በስፋት ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ጥላቻውም የተፈጠረው በሁለት ተያያዥ ምክንያቶች ነው (የለየለት ዘረኝነትን ትተን ማለት ነው)፡፡ አንደኛው ትግሬዎች የመንግሥትን ሥልጣን ተቆጣጥረዋል የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዚህ መንግሥት ትግሬዎች ከሌሎች ብሔሮች አባላት የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው የሚለው ነው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እውነተኛ መሠረት አላቸው ቢባል እንኳን፣ አንድን ሕዝብ ለመጥላትና ዒላማ ለማድረግ በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መታገል ያለብንም ኢፍትሕዊነቱን እንጂ ግለሰቦቹን ወይም ሕዝቡን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ከመጠን በላይ ተጋነው የአመፅ መቀስቀሻ መሣሪያ ሆነው ነበር፡፡ በዚህም ሥልጣኑም ጥቅሙም ላይ የሌሉበት ብዙ ትግሬዎች ሰለባ ሆነዋል፡፡

    አገሪቱ በፌደራልም በክልልም ደረጃ ሙሉ በሙሉ በትግሬዎች የምትተዳደር ለማስመሰል ብዙ ፕሮፓጋንዳ ተካሂዷል፡፡ መንግሥት ተቃውሞዎቹን ለመቆጣጠር ያሰማራቸው የፀጥታ ኃይሎችም ሁሉም ትግሬዎች እንደሆኑ ለማሳመን ብዙ ተጥሯል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎች ላይ ላደረሱት ጉዳትም በብዛት ተጠያቂ ሲደረግ የነበረው በትግሬዎቹ ብቻ እንደተዋቀረ የሚነገርለት መከረኛው የአግአዚ ክፍለ ጦር ነው፡፡ የትግሬዎች በሥርዓቱ ተጠቃሚ መሆንም ከምንም ጊዜ በላይ ተራግቧል፡፡ ለወትሮው በደፈናው ይወራ የነበረው በ “መረጃ" ተደግፎ መቅረበ ጀመረ፣ ትግሬ በመሆናቸው ብቻ “የከበሩ” ስም ዝርዝር ወጣ፣ የመንግሥት ንብረትም ወደ ትግራይ እየተወሰደ እንደሆነ ተነገረ፡፡ የዚህ ሁሉ ፕሮፓጋንዳ ዓላማ በመንግሥት ስም ሌሎች ብሔሮች ላይ በደል እየፈጸሙ ያሉት ትግሬዎች ሲሆኑ፣ ምክንያቱም በዚህ መንግሥት ያላቸውን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ነው የሚለውን መልዕክት ማስረፅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ማንነትን መሠረት ያደረገ ቅስቀሳ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ በአደገኛ ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ተበድያለሁ ብሎ ያሰበው አካል ለጊዜውም ቢሆን ለቅስቀሳው በተመረጠው ማንነቱ (ማለትም ብሔር) ብቻ እንዲያስብና ሌሎች ማንነቶችን (ኢትዮጵያዊነት፣ ሰብዓዊነት፣ ሃይማኖት፣ የአገር ልጅነት፣ ጓደኝነት፣ ወዘተ) እንዲረሳ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙ በመንግሥት አካላት በደል የደረሰበት ኢትዮጵያዊ በደል የደረሰብኝ በብሔሬ (አማራ በመሆኔ፣ ኦሮሞ በመሆኔ፣ ወዘተ) ነው፡፡ በደል ያደረሰብኝም ትግሬ ነው ብሎ ሊያስብና ለበቀልም ሊነሳሳ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቅስቀሳ አገሪቱን ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ግጭትና ደም መፋሰስ ሊከት የሚችል አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ከዚያ በመለስም ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም አገር ወዳድና በዴሞክራሲ አምናለሁ የሚል ወገን ሊቃወመው ይገባል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ በአመዛኙ ዝምታን መምረጣቸው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

     ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጊቱን ወደ ማስተባበል የተጠጉ አንዳንድ ንግግሮች ይሰሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ ይህ ችግር የተከሰተው ኢሕአዴግ ለ25 ዓመታት ሲከተለው በነበረው ከፋይ ፖሊሲ ምክንያት መሆኑ በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ብዙ ፖለቲከኞችና ተንታኞችም “ኢሕአዴግ የዘራውን ማጨድ ጀመረ” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነው፡፡ እርግጥ ነው የኢሕአዴግ ፖሊሲ ለችግሩ አስተዋፅኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲከሰት መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር ድርጊቱን ማውገዝ ነው፡፡ ነገሩ እንዴት ሊከሰት ቻለ የሚለው ጉዳይ ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ የሚነሳ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ወገኖች በተቃውሞዎቹ የታዩትን መጥፎ አዝማሚያዎች መኮነን ኢሕአዴግን እንደ መደገፍ ስለሚቆጥሩት ወይም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እንዳያስመስላቸው በመፍራት ዝምታን ይመርጣሉ፡፡ ድርጊቱን ባይደግፉትም አመፁ እንዲጠናከር አድርጎ የሥርዓት ለውጥ ሊያመጣ እስከቻለ ድረስ ምን ቸገረኝ ብለው ዝም ያሉም አይጠፉም፡፡ ሌላው በስፋት ይነገር የነበረው ዒላማ የተደረጉት ግለሰቦች ትግሬዎች በመሆናቸው ሳይሆን፣ ከመንግሥት ጋር ንክኪ ስላላቸው ነው የሚለው ነው፡፡ ይህ አባባል በመርህ ደረጃ ትክክል ነው ቢባል እንኳን ሊተገበር እንደማይችልና ዞሮ ዞሮ ማንኛውንም ትግሬ ዒላማ ከማድረግ ብዙም እንደማይለይ ግልጽ ነው፡፡ ዳሩ በመርህ ደረጃም ትክክል አይደለም፡፡ በማንኛውም ግለሰብ በምንም ምክንያት የሚወሰድ የጥቃት ዕርምጃ የዴሞክራሲ ትግሉን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፡፡    

   ማጠቃለያ

    ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሕዝብ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው ነበር፡፡ ተቃውሞዎቹ የተነሱት በቂ ምክንያት ስለ ነበራቸው ነው፡፡ በመጀመሪያም ሰላማዊ ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ ግን ወደ አመፅና ሥርዓት አልበኝነት እየተቀየሩ ሄዱ፡፡ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረትም ወድሟል፡፡ በመጨረሻም የአገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ መንግሥት ያወጀውን ጊዜያዊ አስቸኳይ አዋጅ ተከትሎ ነገሮች የተረጋጉ ቢመስሉም ችግሩ ከመሠረቱ ተፈቷል ማለት አይደለም፡፡ አገሪቱን ለዚህ ቀውስ የዳረጋት ዋናው ምክንያት የዴሞክራሲ ግንባታው ወደ ፊት በመሄድ ፈንታ የኋልዮሽ መሄዱ ነው፡፡ መንግሥት ይህን በተወሰነ ደረጃ የተረዳ ቢመስልም፣ ዋናው የመፍትሔ ትኩረቱ ግን የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮች ላይ ይመስላል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መሞከር መጥፎ ባይሆንም ችግሩ ከመሠረቱ እንዲፈታ ከፈለገ ግን መፍትሔው የዴሞክራሲ ግንባታውን በበቂ ፍጥነት ማስኬድ መሆኑን መቀበልና የበኩሉን መወጣት አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከእነሱ የሚጠበቀውን ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከተደረጉት ተቃውሞዎች እንደ ሕዝብ ብዙ ትምህርት መውሰድ አለብን፡፡ በተለይ የታዩት አንዳንድ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አዝማሚያዎች ዳግም እንዳይታዩ ሁሉም የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡