አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

እህል ነጋዴዎች በቆሎና ማሽላ ላይ በተጣለው ዕገዳ ምክንያት ወደ ውጭ መላክ አልቻልንም አሉ

 

ከምሥራቅና ከደቡባዊ አፍሪካ የመጡ ገዥዎች ከኢትዮጵያ ግዥ ፈጽመዋል                                                                                                                                                                                                                       የጥራጥሬ፣ የብርዕ፣ የአገዳና የሌሎችም የግብርና ሸቀጦችን ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት በተጣለውና እስካሁንም ባልተነሳው የበቆሎና የማሽላ የወጪ ንግድ እገዳ ምክንያት መላክ እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደውና ከአሥር የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ የእህል ነጋዴዎች በተሳተፉበት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ ምንም እንኳ የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያ የበቆሎ የማሽላ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎችንም የጥራጥሬ፣ የቅመማቅመም እንዲሁም የቅባት እህሎችን የመግዛት ፍላጎት ቢያሳዩም በተለይ በቆሎና ማሽላ መላክ እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቡሩንዲ፣ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከማላዊ፣ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የተውጣጡ የእህል ነጋዴዎች በአዲስ አበባ በመገኘት የእርስ በርስ ግብይት ለመፈጸም የሚችሉበትን መድረክ አካሂደው ነበር፡፡ በመድረኩ ከፍተኛ ፍላጎት ከታየባቸው መካከል የበቆሎ ግዥ ፍላጎት ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡ ይሁንና ይህንን ምርት ከአገር ውጭ መሸጥ በመከልከሉ ምክንያት መንግሥት ይህንን ዕገዳ ያነሳ እንደሆነም ጥያቄ ሲቀርብ ተደምጧል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የእህል ነጋዴዎች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ወቅት፣ የዕገዳውን መነሳት ጥያቄ ያቀረቡት የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያን በመወከል በስብሰባው የታደሙት አቶ ይልማ አበበ ናቸው፡፡ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ መንግሥት ያስቀመጠውን ዕገዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያነሳ ስለማሰቡ ማወቅ ባይቻልም ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ግን መንግሥት ዕርምጃውን የወሰደው፣ በኤልንኖ ምክንያት በአገሪቱ ተክስቶ የነበረው ድርቅና ያስከተለውን የምግብ ዕጥረት ለመከላከል በማሰብ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃም ዕገዳው እስከመቼ ሊቆይ እንደሚችል ባይገልጽም፣ በበቆሎና በማሽላ ላይ የታጣለው ዕገዳ ግን አሁንም እንዳለ ያስረዳል፡፡

በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ በተለይ የበቆሎ ምርት እጥረት ተከስቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመጠኑም ቢሆን ከሌሎች አገሮች ይልቅ የተሻለ የበቆሎ ምርት ማስዘገብ መቻሏም ሲጠቀስ ተደምጧል፡፡ ከበቆሎ ባሻገር አኩሪ አተር፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንብራና ሌሎችም የእህል ምርቶችን ከኢትዮጵያ ለመግዛት ፍላጎት መኖሩ ታይቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የእህል ነጋዴዎች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ጄራልድ ማካው ማሲላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምክር ቤቱ በአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ትስስር እንዲጠናከር ማሳያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአገሮች መካከል የሚታየው ሕገወጥ የድንበር ዘለል ንግድ እንቅስቃሴ፣ ከዚህም ባሻገር በድንበር አካባቢ የሚታየው ሙስና፣ ተደራራቢ ታክስ፣ የመሠረተ ልማት መጓደል፣ ወደኋላ ተመልሰው የሚተገበሩ ሕጎችን መጠቀም፣ የንግድ ፍሰትን የሚገድቡና አሠራሮችና የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች በአገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን ያህል የንግድ ትስስር እንዳይኖር እያስገደደ እንደሚገኝ ምክር ቤቱ ያቀረበው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛንያ በጅምላ ያመረቱት የበቆሎ ምርት 17.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደነበር የምክር ቤቱ ሪፖርት አሳይቷል፡፡

ከበቆሎና ከማሽላ ባሻገር ለዓመታት የዘለቀ ዕገዳ በጤፍ ላይ ተጥሎ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ መንግሥት በጤፍ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ከተገደደባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በጤፍ የአዕምራዊ ንብረት ባለቤትነት ላይ እየተነሳ የሚገኘው ሙግት ይገኝበታል፡፡ ከግሉቲን ነፃ በመሆኑ እንዲሁም በብረት ማዕድን ይዘቱ በዓለም ላይ ዕውቅና እያተረፈ የመጣው ጤፍ፣ ከወደ ሆሊውድ መንደርም ተቀባይነትን ያተረፈ ተስማሚ የምግብ ዘር ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና ጤፍ ላይ የተጣለው ማዕቀፍ ቢነሳ ከቡና ይልቅ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡

በአንፃሩ እንደ አዲስ የተዋቀረውን የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርን እንዲመሩ የተሾሙት አዲሱ ሚኒስትር በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ጽኑ አቋም ያላቸው በመሆናቸው እንደ ጤፍ ያሉ አገሪቱ ሕዝብ መደበኛ የምግብ ምንጭ የሆኑ ውጤቶችን በቀላሉ ለዓለም ገበያ እንዲውሉ ይፈቅዳሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡