አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

እውን ሊሆን የተቃረበው የትውልድ ቅርስ

 

ለአገሪቱ ስፖርታዊ ዘርፎች መዳከም ምክንያት ሆኖ ይቀርብ የነበረው የማዘውተሪያ ሥፍራዎችና ደረጃቸውን የጠበቁ ብሔራዊ ስታዲየሞች በሚፈለገው መጠን አለመኖራቸው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ባይባልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ለውጦች ነገን ያስናፍቃሉ፡፡ በየክልሎች ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ብሔራዊ ስታዲየሞች መገንባታቸው፣ ግንባታቸው እየተካሄደ የሚገኙና ሊገነቡ የታሰቡ ማዘውተሪያዎች ለአገሪቱ ስፖርት ዘርፍ ጮራ መፈንጠቃቸው አልቀረም፡፡ በአዲስ አበባ ለዘመናት የቆየውና ዘመናዊነትን ያሟላ ስታዲየም አለመኖሩን ሊያስቀር የተቃረበ የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የመፀው ወራት ጥቢን በሚያበስረው አደይ አበባ ቅርፅ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ ስታዲየም፣ ለመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሒደት 2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል፡፡ አዲስ አበባ የሦስት ስታዲየሞች ባለቤት እንድትሆን የሚያበቃት ይህ ስታዲየም በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡ እንደ ፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጥበቡ ጎርፉ ከሆነ፣ የዚህ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ውል የተፈጸመው በታኅሣሥ 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው ደግሞ በ2010 ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ እንደ ፕሮጀክት አስተባባሪው በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱ ከሚወስደው 900 ቀናት 420 ቀናት አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ይህ ለመደበኛው የስታዲየም ግንባታ የሚያስፈልጉትን የቢሮ፣ የቁሳቁስና ለማሽነሪ አቅርቦቶች የዋለውን ጊዜን ያጠቃለለ ነው፡፡ ይኽም ሆኖ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ መድረሱን አቶ ጥበቡ ይናገራሉ፡፡ ሜዳውና ግንባታው ያረፈበት ቦታ 95,000 ካሬ ሜትር እንደሚሸፍን፣ ይህ ማለት ግን ከስታዲየሙ ግንባታ በተጓዳኝ የሚለውን የግንባታ መሠረተ ልማት እንደማያካትት አስተባባሪው ይገልጻሉ፡፡ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ የፕሮጀክቱ ማናጀር ሚስተር ችንዮው ግንባታው በስምምነቱ መሠረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ስምምነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የኩባንያው እምነት ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡ እስካሁን ባለው ይህ ነው ሊባል የሚችል ያጋጠማቸው ችግር እንደሌለ የሚገልጹት የፕሮጀክቱ ማናጀር፣ የነበረው ተነሳሽነት እንደሚቀጥልም ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ የዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ጎን ለጎን ከወዲሁ ሊታሰብባቸው የሚገቡ መሠረተ ልማቶች እንዳሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ለስታዲየሙ የሚመጥኑ የመንገድና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ነጥቦች ዙሪያ ከፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጥበቡ ጎርፉ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተሰጠው ጊዜ አኳያ እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ጥበቡ፡- ይህ ብሔራዊ ስታዲየም በአጠቃላይ የ900 ቀናት ፕሮጀክት ነው፡፡ እስካሁንም 420 ቀናቱ በግንባታው ሥራ ላይ ውሏል፡፡ 420 ቀናቱ ሁሉም በስታዲየሙ ግንባታ ላይ ውሏል ማለት አይደለም፡፡ የስታዲየሙ መደበኛ የግንባታ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት ለግንባታው ግብዓት የሚሆኑ የቢሮ፣ የቁሳቁስና የማሽነሪ አቅርቦት ሒደትን ያካትታል፡፡ የግንባታውን ሒደት ለይተን ስንመለከተው ደግሞ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶው ተከናውኗል፡፡ ከዚህ በመነሳት የስታዲየሙ ግንባታ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ መሆኑን ነው መረዳት ይቻላል፡፡ ፕሮጀክቱ ጊዜውን ጠብቆ ይጠናቀቃል ብለን እንጠብቃለን፤ ተቋራጩም ይህንኑ ቃል ገብቷል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ በትክክል የተጀመረበትና የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ቢገለጽልን?

አቶ ጥበቡ፡- ከተቋራጩ ጋር ውል የተገባው ታኅሣሥ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 5 ቀን 2016) ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ ሰኔ 2010 (ጁን 2018) ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ባለው የግንባታ ሒደት ምን ዓይነት ያጋጠሙ ችግሮች አሉ?

አቶ ጥበቡ፡- ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከመብራት ጋር የተያያዙ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፣ በሚመለከተው አካል ችግሩ ተወግዶ፣ በአሁኑ ወቅት ሦስት ትራንስፎርመሮች ወደ 650 ኪሎ ቮልትና ሁለትና አንድ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል መስመር ተዘርግቷል፡፡ ውኃም በተመሳሳይ ሁለት መስመሮች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ የተሟላ አገልግሎትም እየሰጠ ነው፡፡ በተጨማሪም አንድ የጉድጓድ ውኃ አለ፡፡ ስለሆነም እነዚህ በስታዲየሙ የኮንክሪት ሥራ ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ያለ አንዳች ችግር አገልግሎት እያገኘን ነው፡፡ ተባባሪ መሥሪያ ቤቶችም ለፕሮጀክቱ ሙሉ ድጋፍና እገዛ እያደረጉ ናቸው፡፡ ሆኖም በስታዲየሙ ክብር ትሪቡን በኩል ባለው ሥፍራ የነበረው የእምነት ተቋም ነበር፡፡ እሱም በአሁኑ ወቅት በሚመለከተው የመንግሥት አካል ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቶት ሥፍራው ለፕሮጀክቱ ግንባታ ክፍት እንደሚሆን ማረጋገጫ ተገኝቷል፡፡ ተያያዥ ግንባታዎችም ይቀጥላሉ፡፡ ምክንያቱም የእምነት ተቋሙ የነበረበት ቦታ የስታዲየሙ የፊኒሽንግና መሰል ሥፍራዎች የሚከናወኑበት ነው፡፡ በቅርቡ የእምነት ተቋሙ ይነሳል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙ ግንባታ በታቀደለት መርሐ ግብር መሠረት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆን ዘንድ በሚመለከተው አካል እየተሰጠ ያለው ዋስትና እንዴት ይገለጻል?

አቶ ጥበቡ፡- እስካሁን ያለአንዳች እንከን ፕሮጀክቱ በታቀደለት ፍጥነት እየሄደ ነው፡፡ ወደፊትም እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለ፡፡ ለዚህም መንግሥት እንደ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥቶ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁሞ እየተከታተለው ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ከስታዲየሙ ጋር ተያይዞ ወደፊት መታየት ያለባቸው ሁሉ ከወዲሁ ለማስተካከልና ተግባራዊም ለማድረግ ጥናትና ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ስታዲየሙ ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት ግንባታው የሚከናወነው የኦሊምፒክ ስታንዳርዱን ጠብቆ ነው፡፡ ስታንዳርድ ሲባልም ፕሮጀክቱ ትልቅ እንደመሆኑ ከመንገድ፣ ከባቡር፣ ከውኃና ከመብራት አገልግሎትና ከሌሎችም መሰል አገልግሎቶች ጋር ስለሚያያዝ ማለት ነው፡፡ በጉዳዩም መንግሥት የሚሰጠውን አቅጣጫ በየጊዜው የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ ጋር ተያይዞ ከወዲሁ ትልቅ ችግር ይሆናል ተብሎ ኅብረተሰቡን እያነጋገረ የሚገኝ ነገር አለ፡፡ ስታዲየሙ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት በሚሆንበት ወቅት ከሚያስተናግደው የተመልካች ቁጥር አኳያ የመንገድ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ረገድስ ምን የታቀደ ነገር አለ?

አቶ ጥበቡ፡- ከሁሉ በፊት ይህ ፕሮጀክት ትልቅ የትውልድ ቅርስ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ስታንዳርድን ጠብቆ የሚገነባ ነው ሲባልም አብሮ ሊታዩ የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የመንገድ መሠረተ ልማት አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የኦሊምፒክ ስታዲየም ሊያሟላ የሚገባውን ሁሉ አሟልቶ እንዲይዝ ይጠበቃል፡፡ በተለይም የምንገኝበትን ዘመን ቴክኖሎጂ የሚጠይቀውን ሁሉ እንዲያሟላ  እምነት አለን፡፡ ከዚህ አኳያ በቀጣይ የሚሠሩ በርካታ ተያያዥ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴውም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር እየመከረበት ነው፡፡ ሌላው እንደነዚህ የመሰሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ሲገነቡና አገልግሎት ላይ ሲውሉ በትንሹ ከ10,000 ያላነሱ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው የኦሊምፒክ መርህ ቢያስገድድም፣ አሁን ባለው ግን እስከ 3,000 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ለማካተት ታስቧል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሁኔታው እየታየ ከመንገዱ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ነው ያለው አጠቃላይ መንፈስ፡፡ ለዚህ ተብሎ የተመደበው አካል የድርሻውን ይሠራል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከሴኩሪቱ ጋር ተያይዞም የሚሠሩ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ስላሉ ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን ነው የሚፈለገው፡፡ በእርግጠኝነት ሁሉም የድርሻውን ስለሚሠራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱን ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ስቴት ኮንስትራክስሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በግንባታው ምን ያህል ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያንን አሳትፏል ማለት ይቻላል?

አቶ ጥበቡ፡- ቻይናውያን 193 ሲሆኑ፣ በእያንዳንዱ የግንባታ ሴክተር ክህሎቱ ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይል አላቸው፡፡ በነሱ የሚመሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 819 በድምሩ 1.012 ሠራተኞችን እያሳተፈ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ከግንባታው ጎን ለጎን ሌሎችም ሥራዎች ስለሚኖሩ እስከ 2,000 የሰው ኃይል እንደሚያካትት ይጠበቃል፡፡ ይህ ማለት አንድ እጅ ቻይናውያን፣ ሁለት እጅ ኢትዮጵያውያንን እንዲሆን የታቀደ ነው፡፡ የሚገርመው በዚህ ፕሮጀክት የታዘብኩት ቢኖር ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ሲመሩና በቻይናውያን ሲመሩ ልዩነቱ ሰፊ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ለማፍጠን አንዱ ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ክረምት ለፑቲንግ አገልግሎት የሚውሉ ጉድጓዶች ካልሆነ በስተቀር ሌላ የማይታይ ነገር አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የስታዲየሙ ግንባታ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት ተችሏል፡፡ በዚሁ ፍጥነት መቀጠል ከተቻለ እስከ ሰኔ የኮንክሪት ሥራው ይጠናቀቃል ብለን ነው የምናስበው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅቱን ጨምሮ የተለያዩ የምሕንድስና ኩባንያዎችና ባለሙያተኞች እንደተካተቱ ይታወቃል፡፡ አንዱ ከሌላው ተግባብቶ የመሥራቱ ጉዳይ እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ጥበቡ፡- በቅንጅት ነው የምንሠራው፡፡ ከራሴ ብጀምርልህ በመደበኛነት የምሠራው በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ውስጥ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እንደመሆኔ አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ፕሮጀክቱ ላይ ነው፡፡ አማካሪ መሐንዲሱ ኤምኤችም ሆነ የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ በተመሳሳይ እጅና ጓንት ሆነን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም 14 ወጣት ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ በፕሮጀክቱ እየሠሩ ናቸው፡፡ ይኼ የሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት ሽግግርም መኖሩን ነው፡፡ ለልምድም በርካታ ወጣት መሐንዲሶች እየመጡ ዕውቀት እንዲቀስሙ እየተደረገም ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የፕሮጀክቶች ባህሪያት በሆነው ከዲዛይንና መሰል ሥራዎች ጋር በተገናኘ ጥግ የደረሱ ክርክሮች የሚፈጠሩበት አጋጣሚዎች ይኖራሉ፣ ሙያዊ መፍትሔ እየተቀመጠላቸው እንዲቀሉ ሆኗል፡፡ እያንዳንዱ ውሳኔ ቀጠሮ ሳይያዝለት እዚያው እንዲያልቅ በማድረግ ግንባታው ቀጥሏል፡፡ በመንግሥት በኩልም ውሳኔ ለሚሹ ጉዳዮች ቶሎ ቶሎ መልስ የሚያገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ የተመደቡልን የኮሚቴ አባላት በሚኒስትር ደረጃ ትላልቅ ተቋማትን የሚመሩ ጭምር ናቸው፡፡ ይህ ኮሚቴ ከስታዲየሙ ግንባታ በተጓዳኝ ለሚገነቡ ግንባታዎች ትልቅ አጋዥ ኃይል እንደሚሆንም እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጀመሪያው የግንባታ ሒደት (ፌዝ ዋን) ከተያዘው በጀት ምን ያህሉ አገልግሎት ላይ እንደዋለ ይታወቃል?

አቶ ጥበቡ፡- እስካሁን ባለው ይህ ነው ተብሎ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ ምክንያት አለው፡፡ የዲዛይን ሥራው የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ በመቀመር የተጠናቀቀው በቅርቡ ነው፡፡ በዚህ የዲዛይን ሥራ ላይ እንግሊዞች፣ አውስትራሊያውያንና ደቡብ ኮሪያውያን ተሳትፈውበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ለግንባታው ደረጃ በደረጃ ምን ያህል እንደወጣ በግልጽ የሚታወቅበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም እጠብቃለሁ፡፡ አሁን ባለው እንዲህ ነው ለማለት ሕዝብና መንግሥትን ማሳሳት ነው የሚሆነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ይህ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ጥርጣሬ ነበር፡፡ ይህን የምለው ዝም ብዬ ሳይሆን ከዓመታት በፊት የብሔራዊ ስታዲየሙ ዲዛይን ወጥቶ የአሸናፊው ዲዛይን ይፋ በሆነበት ወቅት ስለግንባታው የሰዎችን አስተያየት እሰበስብ ነበር፡፡ የብዙዎቹ አስተያየት ዕውን ሆኖ እንደማያዩት የሚያመላክት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እየመጣልን ያለው አስተያየት እጅግ የሚገርም ነው፡፡ በግሌ ይህ ፕሮጀክት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በመመልከቴ ፈጣሪን የማመሰግንበት ቃል ያጥረኛል፡፡