አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

እየተመናመኑ የመጡት አቦሸማኔዎች

በዓለም በፈጣን ሯጭነታቸው የሚታወቁት አቦሸማኔዎች በመመናመን ላይ መሆናቸውን ናሽናል ጂኦግራፊ አስታወቀ፡፡ በቅርቡ የተደረገው የአቦሸማኔዎች ቆጠራ በዓለም 7,100 ያህል ብቻ መቅረታቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ እነዚህም በሚቀጥሉ 15 ዓመታት በ53 በመቶ እንደሚቀንሱ ተገልጿል፡፡

የዓለም የዱር ድመቶች ጥበቃ ድርጅት (ፓንቴራ) ፕሬዚዳንት ሉክ ሃንተር፣ የአቦሸማኔዎች ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መሄድ አደጋ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ፈጣን መቀነስ ታይቷል ይህንን ችግር መድረስ አለብን፤›› ሲሉም  አክለዋል፡፡

በናሽናል አካዴሚ ኦፍ ሳይንስ ፕሮሲዲንግ የሰፈረው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ1975 በአፍሪካ ላይ በተሠራ ጥናት የአቦሸማኔዎች ቁጥር ከ21 ሺሕ በላይ ነበር፡፡ በወቅቱ በአብዛኛው የአፍሪካና የእስያ አገሮች ይገኙ የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በአፍሪካ በስድስት አገሮች ማለትም በአንጎላ፣ ናሚቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካና ሞዛምቢክ ብቻ ይገኛሉ፡፡ በእስያ ጠፍተዋል በሚያስብል ደረጃ ሲሆኑ፣ በኢራን በአንድ ከሰዎች ንክኪ በራቀ ደሴት 50 ያህል ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም አቦሸማኔዎች ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ከሚባሉ የዱር የእንስሳት ምድብ ወጥተው፣ ለመጥፋት የተቃረቡ በሚለው ዝርዝር እንዲሰፍሩ ጥናቱ ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

ሥጋ በል ለሆኑት አቦሸማኔዎች ቁጥር መመናመን ሰዎች ዋና ምክንያት ሲሆኑ፣ ለእርሻና ለቁም ከብት ግጦሽ ተብለው በየጫካው የተሰጡ ቦታዎች ለዱር እንስሳቱ መመናመንና መጥፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡