አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፓርላማ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታዘዘ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እግር ኳሱን ለመምራትና ለማስፋፋት እያከናወነ ያለውን የአሠራር ሥርዓት በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው የክዋኔ ሪፖርት ላይ በፓርላማ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታዘዘ፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የእግር ኳሱ መታወቅና የክለቦች መቋቋምን ተከትሎ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራ አካል የስፖርት ጽሕፈት ቤት በሚል ስያሜ በ1936 ዓ.ም. በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራ መቋቋሙ መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው ጽሕፈት ቤት በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይልና በፋይናንስ የተጠናከረ ባለመሆኑ ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ በፌዴሬሽን ደረጃ እንዲቋም በተደረሰው ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ1941 ዓ.ም. ሊመሠረት መቻሉ ጭምር ይነገራል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከተመሠረተ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለትን ብሔራዊ ፌዴሬሽን፣ በ2008 የውድድር ዓመት ያከናወነውን የዕቅድ ክዋኔ ኦዲት አድርጎ ለፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበው ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ማብራሪያ እንዲሰጥ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዓርብ ታኅሣሥ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥሪ ተደርጎለታል፡፡ ይህንኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡  

የኦዲት ሪፖርቱ በክፍተትነት ከተመለከታቸው አሠራሮች መካከል፣ ፌዴሬሽኑ በወቅቱ ለነበረው ስፖርት ኮሚሽን ዓመታዊ ዕቅድና ክንውን ሪፖርት መላኩን በተመለከተ ስለሁኔታው የተቋሙ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለኮሚሽኑ ለመላክ አደረጃጀቱ የማይፈቀድለት እንደሆነ በመግለጽ፣ መላክ እንደሌለበት በሰጠው አስተያየት የገለጸ ቢሆንም፣ ማስረጃው እንዳልቀረበለት ነው ያስረዳው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለፌዴሬሽኑ በተላከለት ረቂቅ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ ደግሞ በአዲሱ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት የክለሳ ጥናት፣ ተፈላጊ የሥራ መደቦችን ከኦዲት ጋር በማከል ተዘጋጅቶ የመጨረሻው የአፈጻጸም ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስተዳደራዊ መዋቅሩንና የሥራ መደቦችን ማሻሻያ ዝርዝር ሰነድ አያይዞ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ዝርዝር ሁኔታው ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ስለመጽደቁ መረጃው ባለመቅረቡና የተከለከለ መዋቅር ስለመሆኑ መቀበል እንደሚያዳግት የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡ ግዴታዎችና ደንቦች በራሱ በፌዴሬሽኑ መተግበር አለመተግበራቸውን በተመለከተ፣ ረቂቅ ሪፖርቱ በጽሑፍ ከሰጠው ምላሽ ጋር ጥናት ተጠንቷል በማለት አያይዞ ያቀረበው ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ለ2008 ዓ.ም. የቡድኖች አደረጃጀት መነሻ የቀረበ ሐሳብ እንጂ የተጠና ጥናት ባለመሆኑ ፌዴሬሽኑ የሰጠውን መልስ ለመቀበል እንደማይችልም ኦዲት ሪፖርቱ ያትታል፡፡

የፌዴሬሽኑን የገቢ አሰባሰብ ሥልቶችን በተመለከተ ስለሁኔታው አሁን ያለው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በነባራዊ ሁኔታ መግለጫው ላይ በሰጠው ምላሽ፣ ይህ ጉዳይ ቀድሞ በነበሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተፈጸመ በመሆኑ በዚሁ ዙሪያ በቂ መረጃ እንደሌለው መግለጹን ያስረዳል፡፡ ሆኖም በኦዲት ክዋኔ ሪፖርቱ ኃላፊዎቹ ይህን ይበሉ እንጂ፣ የተጠየቀው የተቋሙን አሠራር እንጂ የግለሰቦች ባለመሆኑ የተወሰኑ መረጃዎች በፌዴሬሽኑ ይኖራሉ ተብሎ ስለሚያምን የተሰጠው መልስ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ያሳያል፡፡

በፌዴሬሽኑ የሚሰጡ ሥልጠናዎች የክልሎችን የሥልጠና ፍላጎት ያገናዘበ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተጠይቆ፣ ክልሎች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ በመሆኑ የሥልጠና ፍላጎታቸውን የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባቸው በተላከላቸው ነባራዊ ሁኔታ መግለጫ ላይ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይህን ይበል እንጂ ከፌዴሬሽኑ ሥልጣንና ተግባር መካከል አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በክልልም ሆነ በፌዴራል ስፖርቱ እንዲስፋፋና እንዲያድግ ድጋፍ ማድረግ በመሆኑ የተሰጠው መልስ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያመለከተው፡፡

ለአሠልጣኞችና ለዳኞች መሥፈርት ተዘጋጅቶ ደረጃ መስጠትን በተመለከተ፣ ስለጉዳዩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በነባራዊ ሁኔታ መግለጫ ላይ በሰጠው ምላሽ በአገር አቀፍ ደረጃ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ አሠልጣኝነት ሥልጠና ምዘና በማከናወን ሰርተፊኬት በመስጠት ማረረጋገጫ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጿዋል፡፡ ለረቂቅ ሪፖርቱ በጽሑፍ በተሰጠ ምላሽ ደግሞ፣ የአሠልጣኞች ደረጃ የተለያዩ አምስት መሆናቸው የተገለጸና ማስረጃም የተያያዘ ነው፡፡ የሚሰጠው ደረጃ ግን ከዓለም አቀፉ የደረጃ አሰጣጥ ጋር ለምን እንዳልተጣጣመ ምላሽና ማብራሪያ እንዳልተሰጠም ያሳያል፡፡

የብሔራዊ አሠልጣኞች መመልመያ መሥፈርትን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ለሪፖርቱ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ የፌዴሬሽኑ የአሠልጣኞች የመመልመያ መስፈርት ተዘጋጅቷል በማለት አያይዞ በቀረበው ማስረጃ ይገልጻል፡፡ ሆኖም በወቅቱ በነበረው ስፖርት ኮሚሽን ለሁሉም ፌዴሬሽኖች በ2006 ዓ.ም. የተዘጋጀ ረቂቅ ሰነድ እንጂ በየደረጃው ለሚገኙ ለሁለቱም ጾታዎች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች የሚቀጠሩ አሠልጣኞች መምረጫ መሥፈርት ተለይቶ አልቀረበም፡፡ በመሆኑም የብሔራዊ ቡድኖች አሠልጣኝ የመምረጫ መሥፈርት እንደየደረጃቸው አለመዘጋጀቱና በየጊዜው በቴክኒክ ኮሚቴው መመረጡ ፌዴሬሽኑ የሚያከናውነው ምርጫ ሁሉም በግልጽ ሊረዳው በሚችል መልኩ አለመሆኑ ምርጫውም አድሎአዊ ለሆኑ አሠራሮች የተጋለጠ ነው፡፡

ፌዴሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ደረጃ ጋር መጣጣም አለመጣጣማቸውን በተመለከተ፣ ፌዴሬሽኑ ለረቂቅ ሪፖርቱ በጽሑፍ ከሰጠው ምላሽ ጋር የውድድር ፕሮግራሞችን አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ በኦዲት ወቅት በናሙና ጥያቄ ያቀረበላቸው ክለቦች፣ አሠልጣኞችና ተጨዋቾች በሰሌዳው መሠረት እንደማይካሄድ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በወጣው ፕሮግራም መሠረት ውድድር ውድድሮቹ ተከናውነዋል በተባለላቸው ጊዜ እንኳን በትክክል ስለመጠናቀቃቸው ማስረጃ መቅረብ ባለመቻሉ የፌዴሬሽኑ መልስ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑም ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት በክፍትነት ከጠቀሳቸው ከብዙ በጥቂቱ እንደተጠቀሰው ሆኖ፣ በተለይም ከዓለምና ከአህጉር አቀፍ ተቋማት ለቴክኒካል ዕርዳታ ለተቋሙ የሚላክለትን የቁሳቁስና የገንዘብ ዕርዳታ አስመልክቶ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል አለመዋሉ መረዳት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ፣ የራሱን የገቢ ምንጭ ለማጎልበት መንቀሳቀስ እንዳለበትና ሌሎችም በርካታ በክፍተትነት የተመለከታቸውን በማመላከት ፌዴሬሽኑም ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው አስተያየቱን በመስጠት የ2008 ዓ.ም. የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን አጠናቅሯል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያለፈው ዓመት የፌዴሬሽኑን ዕቅድ ክንውን ኦዲት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ዓርብ ታኅሣሥ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በፓርላማ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ቀርበው በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሚሰጠቡት መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡