ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተቃራኒ የሆነው የመሬት አስተዳደር ሁኔታ የጋምቤላ ክልል እንደ ማሳያ

በውብሸት ሙላት

በዚህ ሰሞን መንግሥት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ የበርካቶችን ቀልብ የገዛው በጋምቤላ ክልል ለግብርና ኢንቨስትመንት ሰፋፊ መሬት በሊዝ ወስደው ነገር ግን እጅግ በጣም ደካማ በሚባል ደረጃ ወይንም ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ያላከናወኑ ‹‹መሬት ወራሪዎች›› ይፋ ማድረጉና በቀጣይ ይወሰዳል ተብሎ የሚጠበቀው ዕርምጃ ነው፡፡ በእርግጥ እልከኛው መንግሥታችን ከራሱ ካልመጣ በስተቀር ዕርምጃ አይወስድም፤ ወይንም ጥፋቶችንና ችግሮችን ለመስማት ዝግጁ አይደለም እንጂ በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን የመሬት ቅርምቶችና ወረራዎች የአገር ውስጥም የውጭ ተመራማሪዎች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላትም በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ በተደጋጋሚ የመሬት ወረራ እንዳልሆነ ሲያስረዳ ከርሞ ነበር፡፡

ስለ መሬት ቅርምት የተጻፉ መጽሐፍትንም ይሁን መጣጥፎችን በድንገት የተመለከተ ማንም ሰው የኢትዮጵያን ስም ሳያገኝ አይቀርም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የመሬት ቅርምት የሚከናወነው  ሦስት አካባቢዎች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህም ከሰሐራ በታች ያለው አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ደቡብ ምሥራቅ እስያ ናቸው፡፡ ከሦስቱ ደግሞ ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገሮች መሬታቸውን በማስወረር ቅድሚያውን ይወስዳሉ፡፡ ምሁራንም ይህንን ድርጊት ያለ ጦርነት የሚደረግ ‘የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ’ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ‘ኒዮ ሊበራሊዝም’ በማለት ይጠሩታል፡፡

በአፍሪካ ካሉት አገሮች ደግሞ ኢትዮጵያ ዋናዋ ተጠቃሽ ናት፡፡ መሬት ወራሪዎቹ፣ የውጭም ባለሀብቶች፣ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ የአገሬው ዜጎች አሊያም ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይ የውጭ ባለሀብቶች ከራሳቸው አገር መንግሥት ከፍተኛ እገዛና ዕርዳታ እንደሚያገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬትን ለግብርና ተግባር በግዥ ወይንም በረጅም ጊዜ ሊዝ ባለሀብቶች ሲወስዱ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው፡፡ በእርግጥ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን ለመቅሰም፣ የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ማድረግን በማሰብ የውጭ ባለሀብቶችን እንደሚጋብዙ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የጋምቤላው ሪፖርት ከላይ የተገለጹት ግቦች ያላሳካ፣ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ መሬትን የሕዝብና የመንግሥት የሆነበትን ምክንያት የጣሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው ከመሬት ጋር ያለውን ግንኙነት በመፈተሽ በተለይም አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊው የመሬት ሥሪታችን የታለመለትን ግብ የማሳካቱን ጉዳይ ይጠይቃል፡፡

የመሬትና የራስን ዕድል በራስ መወሰን ግንኙነት

የራስን ዕድል በራስ መወሰን ስናነሳ መቼም ሊታለፍ ከማይችለው ቁም ነገር አንዱ የመሬት ነገር ነው፡፡ መሬት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም ጭምር ነው፡፡ ከማንነትም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ የቡድን ማንነትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ የታወቀ ድንበር ያለው ግዛት መኖር ጠቃሚ ነው፡፡ ግዛት ደግሞ ያለመሬት የለም፤ በኢትዮጵያ የመሬት ነገር ዋና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዳወሪያና ማጠንጠኛ ሆኖ መቀጠሉ አልቆመም ምናልባትም ለረጅም ጊዜ የሚቀጥልም ይመስለኛል፡፡ መሬት ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትና ሉዓላዊነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው በአጭሩ ያላቸውን ግንኙነት እንፈትሻለን፡፡ በተለይም መሬት የመንግሥትና የሕዝብ መሆኑ የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰን ያልተገደበ ሥልጣን ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ የሚኖረውን አንድምታውን ቆንጸል በማድረግ አከራካሪ የሆኑትን ጭብጦች ብቻ እናንሳ፡፡

‹‹መሬት ላራሹን የምትሹ፤

ተዋጉለት አትሽሹ፡››

በማለት ከአሥር ዓመታት በላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፊታውራሪ በመሆን ሲታገሉለት የቆየው የተዛባ የከበርቴና የጭሰኛ (ባሪያ፣ ገባር፣ አራሽ ወዘተ.) ግንኙነት ደርግ በ1967 ዓ.ም. ባወጣቸው አዋጆች መሠረት መሬት የመንግሥት ሆነ፡፡ በመሆኑም በሹመት፣ በዘር (በውርስ) ወይም በግል ጥረት ተይዘው የነበሩ ሠፋፊ የእርሻ መሬቶች ተወረሱ፡፡ ፊውዳላዊው ወይንም ካፒታሊስታዊ ጉዞ ተገታ፣ መሬት ታገረ፣ እርግጥ ነው መሬት ላራሹ ማለት መሬትን ‘የአገር ሀብት ማድረግ (ማገር) ማለት አይደለም’ የሚሉም አሉ፡፡ ‘አራሽ ጭሰኞች የሚያርሱትን መሬት ባልተቤት እንዲሆኑ ማድረግ እንጂ’ ይላሉ፡፡

መሬት ላራሹ ሲባል ባለቤትነትን ይጨምራል ወይንም አይጨምርም የሚለውን በተመለከተ ምናልባት በወቅቱ የነበረውን ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብም ከግምት ማስገባት የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ከልሂቃኑ ይልቅ የሕዝቡ ፍላጎት ምን እንደሆነ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ በዘመነ ስታሊን በ1936 የወጣውም ይሁን እ.ኤ.አ. የ1977 የሶቪየት ኅብረት ሕገ መንግሥታት መሬትንም ማዕድንንም በመንግሥት ሥር አድርጎታል፡፡ በደርግ ጊዜም ይሁን በዘመነ ኢሕአዴግ የወጡት አዋጆችም ይሁኑ ሕግጋተ መንግሥታት እንደ ሶቪየት ኅብረቱ ናቸው፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ያለው የመሬት ሥሪታችን በመሠረታዊነት አንድ ዓይነት ለዚያውም ሶሻሊስታዊ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(3) የመሬት ባልተቤትነትን በተመለከተ መንግሥት ሕዝብ እንዲሁም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው ይላል፡፡ በአንቀጽ 89(5) ደግሞ የማስተዳደርን ሥልጣን ሕዝብን በመወከል የመንግሥት ሆኗል፡፡

የአሁኑ የመሬት ሥሪት ምክንያቶች

በኢትዮጵያ የነበረው የመሬት ሥሪት በተለይ በደቡብ፣ በአፋርና በኦሮሚያ የነበረው ከብሔር ግንኙነት አንፃር ከሰሜኑ የተለየ ነበር፡፡ ለሰሜኑ የመሬት ጥያቄ በአብዛኛው የመደብ ጥያቄ ላይ የተንተራሰ ሲሆን፣ የሌሎቹ ግን የብሔርም የመደብም ጥያቄ እንደነበር ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡ የብሔር ጥያቄ የሚያሰኘው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ይዘው የነበሩት የገዥው መደብ አባላት የአብዛኛዎቹ ብሔር አማራ ስለነበር መሬታቸውን የተነጠቁትና ወደገባርነት የተቀየሩት ደግሞ የሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አባላት በመሆናቸው ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ወደ ገባርነት የተቀየሩት ከጥንት ጀምሮ በዘር ሲተላለፍ የነበረውን የብሔራቸውን መሬት ሲነጠቁ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የቋንቋ አጠቃቀማቸው ላይ ለውጥ መኖሩ ግድ ስለሆነ የብሔር ማንነት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይህንን ሁኔታ ብሔርን መሠረት ያደረጉና የተወሰኑ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶችም ይጋሩት ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ ጭቆናው በዋናነት የመደብ ስለሆነ እሱ ሲወገድ የብሔር ጥያቄም አብሮ ያከትማል የሚሉም እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በአመዛኙ ግን ከሰሜን ውጪ ያለውን የመሬት ሥሪት የብሔር ጣጣም እንደነበረበት ይስማማሉ፡፡

የመሬት ጉዳይ የብሔርም ጥያቄ ካለው ለመሬት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ይህንንም ከግምት ማስገባት አለበት ማለት ነው፡፡ የኢሕአዴግም አንደኛው አቋሙ ይሄው ነው፡፡ ምንም እንኳን የደርግና የአሁኑ የመሬት ሥሪት ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ከብዙ አገሮች ልምድ በተለየ አካሄድ መሬትን ሕገ መንግሥታዊ አድርጎታል፡፡ መሸጥና መለወጥን ፈጽሞ ከልክሏል፡፡ ባልተቤትነቱ የሕዝቡ ሆኖ አስተዳዳሪው ግን መንግሥት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ለዚያውም ስለመሬት በዋናነት የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ የማውጣት ሥልጣን ሲኖረው ክልሎች ደግሞ ያስተዳድራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ መንግሥት በተለያየ ጊዜ እንደ ሁኔታው በድጋሚ የመሬት ክፍፍል ሊያደርግ ይችላል ማለት ነው፡፡ ጥያቄው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ (ሌሎች ፓርቲዎችም ጭምር) መሬት ለምን የመንግሥትና የሕዝብ እንዲሆን መረጡ? ወይንም መሬት ለምን የግል እንዲሆን አልፈለጉም?

የመጀመሪያው መከራከሪያ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይኸውም ገበሬው ችግር ላይ ሲወድቅ መሬቱን ሽጦ መሬት አልባ በመሆን ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም መሬትን መሸጥ ገበሬው ስለማይፈልግ አሁን እንዳለው የመንግሥትና የሕዝብ ሆኖ መቀጠሉን ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ደግፏል የሚለውም አለ፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ የሚነሳው ሕዝብ የመሬት መሸጥ አለመፈለጉ መሬት የመንግሥት ይሁንልኝ ማለት አይመስልም፡፡ በተለይም በሰሜን አካባቢ የነበረው የርስትና የአጽመ ርስት ሥሪት ማንም ሰው ከመሬቱ (ከርስቱ) በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን መለየትና መነቀል አለመፈለጉን የሚያሳይ እንጂ መሬቱን መንግሥት በሞግዚት እንዲያስተዳድርለት ውክልና መስጠት ፈልጎ ነው ማለቱን ስለመሆኑ አጠያያቂ ነው፡፡ እንዲያውም ከርስቱ መለየት ለማይፈልግ ማኅበረሰብ መሬቱን ለመንግሥት ይሰጣል ማለት ፈጽሞ የዋህነት ነው፡፡ መሬት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ይሁን የሚለው ኢሕአዴግ ብቻ ነው ማለት አይደለም፤ ምሁራኖች፣ ፖለቲከኞችም ይሁኑ ፓርቲዎች የተለያየ አቋም አላቸው፡፡

ሌላው ምክንያት በቀጥታ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ሥር ሊወድቁ የሚችሉ የኢሕአዴግ ሁለት መከራከሪዎች አሉ፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡ በቀጥታ እንደ ኢሕአዴግ አተራረክና ክርክር በአገራችን ዋነኛ የሀብት ምንጭ መሬት ስለሆነ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው አንዱ ማረጋገጫ መሣሪያ በመሆኑ በተፈጠረው ልማታዊ ጎዳና ራሳቸውን እንዲለወጡ አሁን ያለው ሥሪት  ባለቤትነታቸው ዋስትና ይሰጣቸዋል ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በአገራችን ሁኔታ መሬት ከማንነት ጋር እንደተያያዘ በመግለጽ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተረጋገጠላቸውን የማንነት መብቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ግልጽ አሰፋፈር ሲኖራቸውና የመሬት ባለቤትነት ዋስትና ሲረጋገጥላቸው ነው ይላል፡፡ የማንነትን ጉዳይ በዋናነት ራስን ከማስተዳደር ስለማይለይ የማንነት ቡድኖች በተለያዩ አጋጣሚዎች ይዘውት የቆዩትና የእኔ የሚሉት ግልጽ አሰፋፈር ሲኖራቸውና ዋስትና ሲያገኙ ነው ይላል፡፡ ታሪክንና ባህልን ማሳደግ የሚቻለው ተሰባስቦ በሚኖርበት አካባቢ ነው፡፡ የራሳቸውን ልዩ ቋንቋ አለን የሚሉ የአንድ ማንነት ሰዎች ቋንቋውን መጠቀም እንዲችሉ በአንድ አካባቢ መሰባሰብ ግድ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ብሔር ብሔረሰቦች የማንነት መገለጫዎቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና ሲያገኙ እንደሆነ በተለያዩ የፓርቲው ሰነዶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር መሬት በመንግሥት መተዳደር ያለበት የጋራ ሀብት እንዲሆንና እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ የተፈለገበት ከብሔር አንፃር ምክንያቱ ማንነትን ጠብቆ ለመኖርና ባህልን ለማሳደግ በሌሎች ከመወረር የሚድኑት እንዲሁም እነዚሁ ሕዝቦች ሳይበታተኑ በአንድ አካባቢ ሲኖሩ ነው የሚል ነው፡፡ እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በመጤዎች በመወረራቸው የብሔር ማንነታቸው ላይ አደጋ ተጋርጦ ስለነበር፣ አሁንም ቢሆን መሬት መልሰው የመግዛት አቅሙ ‹‹በነፍጠኞች›› እጅ ሊሆን ስለሚችል መልሶ የብሔር ጥያቄ ማምጣቱ አይቀርም የሚል ነው፡፡

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ መሬት የሕዝብ እንዲሆን ከቀረቡት ሰባት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ከላይ የቀረበውን በማጠናከር ‹‹መሬትን መሸጥና መለወጥ መፍቀድ ውሎ አድሮ የአንዳንድ አናሳ ብሔረሰቦችን ማንነት ምልክት ማጥፋት መፍቀድ እንደሆነ፣ ለዚህም መሬትን በመሸጥና በመለወጥ ሒደት የሕዝቦችን መፈናቀል ስለሚያስከትል የአንዳንድ አናሳ ብሔረሰቦች ቀስ በቀስ መበታተንና የማንነት ምልክት የማጥፋት ችግር የሚያስከትል ስለሆነ ፖለቲካዊ ችግር ስላለው የሚያዋጣ አይደለም፤›› ይላል፡፡ ክርክሩን ለማስረገጥ የመዠንግር ብሔረሰብ ተወካይ ከሆኑት ከአቶ ወይናቶ አበራ የተናገሩትን መጥቀሱ ተገቢ ነው፤ አሁን ጋምቤላ ላይ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ‹‹መዠንግር ብሔረሰብ ከሚገኝበት አካባቢ ነፍጠኞችና ትምክህተኞች መሬትን ብቻ ሳይሆን ሰውንም ይገዙ እንደነበር፤ በዚህም ጭቆና የተነሳ ብሔረሰቡ ወደሌሎች አጎራባች አካባቢዎች እንዲሰደድ…›› አድርገውታል ብለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ከተነሱት ሰባት ምክንያቶችን አንዱ ከላይ የተገለጸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ያለበት ደረጃ በጣም ዝቅተኛነት፣ ብዙ ያልታረሰ መሬት መኖሩ፣ በአርብቶ አደሩ አካባቢ መሬትን የግል ማድረግ በተግባር ስለማይቻል፣ መሬት የማያድግ ሀብት በመሆኑ የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ለማከፋፈል እንዲቻል፣ የአነስተኛ እርሻዎች አገራዊ ፋይዳ ከትልልቆቹ የበለጠ መሆኑ፣ ለረጅም ዘመናት ተማሪው መሬት ላራሹ በማለት ሲጠይቀው ስለነበር ታሪካዊ ምክንያት ያለው በመሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ወይንም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የወል ሀብት በመሆን ሊያሳካ ከታሰበው ዓላማ ዋናው በተለይ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦች ማንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በሥራ ላይ ያለው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲም ይሁን ተግባር ከላይ የተገለጸውን ግብ የሚቃረንና የሚያፈራርስ ነው ያሰኛል፡፡ ‹‹ለምን?›› ቢሉ መከራከሪያው የሚከተለው ነው፡፡

በቀዳሚነት እነዚህ ሥጋቶች በዋናነት ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦችን የሚመለከት ነው ከተባለ የመሬት ሥሪቱን መለያየትና እንደ ብሔሩ ባህል መሠረት እንዲተዳደርና ይህንን የመደንገግም ሆነ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለፌዴራል ሳይሆን ለክልሎች መተው ነበረበት፡፡ እንደ ባህላቸው ጠብቀው ለመኖርና ማንነትን እንዳይነካ ለማድረግ ተያያዥ የሆነው ምክንያት የማንነት ቡድኖች (ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) የራሳቸውን ዕድል በመሰላችሁ መንገድ የመወሰን የማይነካ መብት ቢኖራችሁም መሬትን በተመለከተ ግን ተገንጥላችሁ የራሳችሁን ነፃ አገር ካልመሠረታችሁ በስተቀር እንዳፈታታችሁ መወሰን አትችሉም ማለት ነው፡፡

ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመገንጠል መብትን የተጎናጸፉ ብሔሮች ስለመሬታቸው ጉዳይ ግን አስተዳዳሪውንም፣ ባልተቤቱንም መንግሥት እንዲሆን ማድረግ ዞሮ ዞሮ የሚመነጨው አንድም ከብሔሮች በላይ መንግሥት ስለብሔሩ የበለጠና የተሻለ ያውቃል ከሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አገዛዝን ለማራዘም ከሚመነጭ የሥልጣን ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብትን ይጋፋልም በባህርዩም የሚጋጭ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ማንነትን ለመጠበቅ ሲባል መሬት የሕዝብና የመንግሥት መሆን አለበት የሚለው አሳማኝ አይመስልም፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መሬት ባይሸጥም ባይለወጥም እስከ 99 ዓመት ሊቆይ በሚችል ኪራይ (ሊዝ) ለባለሀብቶች የሚከራይ ከሆነ ዞሮ ዞሮ እነዚህ መሬቶች በብዛት ያሉት በአፋር፣ በኢትዮጵያ ሶማሊያ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልል በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያንና በውጭ ባለሀብቶች በጣም በዝቅተኛ የሊዝ ኪራይ እጅግ ሰፋፊ መሬቶች እየተያዙ መምጣታቸውን ስናይና የተፈቀደም በመሆኑ፣ ‹‹በነፍጠኞች›› ይሁን በሌሎች ‹‹ልማታዊ›› ባለሀብቶች መከራየቱም መገዛቱም ለውጥ የለውም፡፡ ለዚያም ነው ሰፋፊ መሬቶች በተወሰኑ ባለሀብቶች (የውጭም የውስጥም) ለልማት የሚወስዱትን በተመለከተ የመሬት ቅርምት፣ ወረራ፣ ዘረፋ ወዘተ. በማለት የሚጠሩት፡፡ ዞሮ ዞሮ ሌሎች ሰዎች መጥተው መስፈራቸው አልቀረም፡፡ መሬቱም ከብሔሩ አባላት ውጪ በሆኑ ሰዎች ይዞታነት መቆየቱን አይከለክልም፡፡ ስለሆነም የመጤዎቹ ማንነት ማንም ይሁን ማን፣ ወረራው  እስከቀጠለ ድረስ ለማንነትና ባህል ሥጋት መሆኑ አይቀርም፡፡

ይህንን ሁኔታ በተጨባጭ ማስረጃ ለማጠናከር የመንግሥትን ሪፖርት እንውሰድ፡፡ በጋምቤላ ክልል ሰፋፊ መሬት ከወሰዱ (ለመውሰድ በሒደት ላይ ካሉት) ከስምንት መቶ በላይ ባለሀብቶች ውስጥ የአካባቢው ተወላጆች 25 ብቻ ናቸው፡፡ ለባለሀብቶች የተላለፈው መሬት ደግሞ ከ630 ሺሕ ሔክታር በላይ ነው፡፡ ከዚህ መሬት ውስጥ ከ400 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በዓመት ከ20 እስከ 30 ብር ብቻ በሔክታር የሚከፈልበት ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በዝናብ የሚለማ ከሆነ 111 ብር፣ በመስኖ ከሆነ 158 ብር ይከፈልበታል፡፡ ከላይ ከተገለጹት ባለሀብቶች ውስጥ 119 የሚሆኑት ምንም ዓይነት ክፍያ ከፍለው አያውቁም፡፡ ከአካባቢው ነባር ብሔረሰቦች 500 የማይሞሉ ሲቀጠሩ፣ ከሌላ አካባቢ በመምጣት የተቀጠሩት ወደ 4,300 ይጠጋሉ፡፡ እነዚህን መረጃዎች ስንመለከት፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን አጠያያቂ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ከሁሉም የበለጠ ግን ይህንን ያክል መሬት በአዲስ ነፍጠኞች ተወስዶ፣ ከአሥር እጥፍ በላይ የሌሎች ክልል ተወላጆች መጥተው ከሰፈሩ መሬት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና የመንግሥት የጋራ ሀብት የሆነበትን ማንነትን የማስጠበቅ የሚቃረን መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ ይልቁንም ከእነዚህ ምክንያቶች ባለፈ ሌሎች ምክንያቶችን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

ሕግ አውጪው ፌዴራል፣ አስፈጻሚው ክልል

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የክልሎቹንና የማዕከላዊውን መንግሥታት ሥልጣንንና ግንኙነትን በተመለከተ የተለያዩ እንዲሁም በርካታ ደንቦችን አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ሥልጣንና ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ መሬትን ይመለከታል፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51(5) በግልጽ እንደተቀመጠው የመሬትን አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮችና የሚወክላቸው ሌሎች ተቋማት (ለምሳሌ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች) መሬትን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(1)(ሀ) ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች በምን ዓይነት ሁኔታ በክልሎች ዘንድ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ መመርያ ባያስቀምጥም፣ ስለመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ከሌላው በተለየ መልኩ እንዴት መፈጸም እንዳለባቸው የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝርበት አንቀጽ 52 ንዑስ ቁጥር 2 ፊደል ‘መ’  ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ ‹‹የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፤›› ይላል፡፡ በመሆኑም የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ ያወጣል፣ ክልሎች ይህንን ሕግ መሠረት በማድረግ ወይንም በመጠቀም መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራሉ ማለት ነው፡፡

የክልሎቹን ሕግጋተ መንግሥታት ስንቃኝም የምናገኘው ተመሳሳይ ነው፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ላይ የተገለጸውን ቃል በቃል የሁሉም ክልሎች  ላይ ተደግሟል፡፡ በመሆኑም የከተማና የገጠር መሬትን የሚመለከቱ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ የወጡት አዋጆች ለክልሎችና ለከተማ መስተዳድሮች ለአፈጻጸም ይረዷቸው ዘንድ ተጨማሪ ደንቦችና መመርያዎችን ማውጣት እንዲችሉ ውክልና ወይንም ኃላፊነት ሰጥተዋቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ ያወጧቸውን ሕጎች በወፍ በረር እንኳን የተመለከተ ሰው በርካታ ትዝብቶች ይኖሩታል፡፡ አንዱን ትዝብት፣ ክልሎች ያወጧቸው አዋጆች ከፌዴራሉ ሕግ ላይ ከተገለጹት የተለያዩ መብቶችን የሚያጎናጽፉ እንዲሁም ግዴታዎችን ዜጎች ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች ለማስፈጸም የሚረዱ ዝርዝር ሕጎች ከማውጣታቸው አስቀድመው ከፌዴራሉ ሕጎች ጋር የሚቀራረቡ አዋጆችን አውጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹም የፌዴራሉ የመሬት አዋጆች ላይ የሌሉ መብትና ግዴታዎችን አስቀምጠዋል፡፡ የተለየ መብትና ግዴታ ከመጨመራቸው ባለፈ ደግሞ አንዱ ክልል ከሌላው በተለየ ሁኔታ ደንግጓል፡፡ መሬትን ማውረስ፣ ማከራየት እንዲሁም በዋስትና ማስያዝን በተመለከተ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ ክልሎችና የፌዴራሉን የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጆች መመልከቱ በቂ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሚያወጧቸውን ሕጎች ክልሎች የሚያስፈጽሙባቸው መንገዶች በየአገሮቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ ሁለቱን ዋና ዋና መንገዶች ብቻ በአጭሩ እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው የተማከለ የፌዴራልን ሕጎች በክልል የማስፈጸም አካሄድ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎች አንድም ከክልሎች ጋር በመግባባት፣ የተለያዩ ማትጊያዎችን በመጠቀም ማስፈጸም፣ ካልሆነ ግን የራሱን ተቋማት ወይንም ቅርጫፎች በመክፈት የሚፈጸምበት አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ሞዴል ክልሎችን ማዘዝ አይቻልም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መርሁም እንበል ትዕዛዛዊ ደንብ (Anticommandeering Rule) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህንን ሞዴል ከሚከተሉ አገሮች ውስጥ አሜሪካን አብነት ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ሞዴል ደግሞ ያልተማከለ ወይንም አስፈጻሚያዊ ፌዴራሊዝም በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ዋና ተግባሩ ሕግ ማውጣት ሲሆን፣ የክልሎቹ ደግሞ ማስፈጸም ነው፡፡ የክልል መንግሥታት ድርሻ፣ ማዕከላዊው መንግሥት ያወጧቸውን ሕጎች እየተከታተሉ ማስፈጸም ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ክልሎች እንዲያቋቁሙ በማዘዝ የሚሾሙት ሰዎችም ላይ አብሮ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ ይህንን ሞዴል ከሚከተሉት ውስጥ ጀርመንና ስዊትዘርላንድን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከላይ ከተገለጹት ሞዴሎች አኳያ የኢትዮጵያን የመሬት አስተዳደር ሁኔታ ብንፈትሸው ከሁለቱም ውጪ መሆኑን መገንዝብ አያዳግትም፡፡ የፌዴራል መንግሥት የራሱን ቅርንጫፍ በመክፈት አያስፈጽምም፡፡ ክልሎችንም የሚያዝበት ተቋማትን ለማስከፈት የሚያስገድድበት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ የለም፡፡ በመሆኑም ጅምር አስፈጻሚያዊ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ያልተቋጨ፣ ያላለቀ፣ ግልጽ ሕገ መንግሥታዊ ደንብ ያልተበጀለት፣ ተጀምሮ የቀረ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ዓይነቱ አሠራር በርካታ ክፍተቶችን ስለሚፈጥር፣ በክፍተቶቹም ሕዝብ ስለሚጎዳ አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል፡፡ ከግልጽ ጉዳቶቹ ውስጥ በጋምቤላ ክልል የተፈጠረውን ችግር ዓቢይ አስረጂ ነው፡፡ በዚህ ክልል ለተፈጠሩት ችግሮች ዋና መንስዔው አስፈላጊ የሆኑ ሕጎች አለመኖር እንዲሁም የወጡትንም ቢሆን እንኳን በአግባቡ ሥራ ላይ አለማዋል ነው፡፡ ሲጀመርም ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገው የፌዴራሉ መንግሥት የመሬት ሕግ እንደሚያወጣ ነው፡፡ ለክልሎች በውክልና ተጨማሪና ዝርዝር ሕግ እንዲያወጡ ውክልና መስጠትን የሚከለክል ባይኖርም፣ ተገቢ ሕጎች ካልወጡ የፌዴራሉ መንግሥት ውክልናውን በማንሳት ሕጎቹን ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ጋምቤላ ላይ እንደተፈጠረው ዓይነት የተዝረከረከ አሠራርን ለማስተካከል ከክልሎች የበለጠ የፌዴራሉ መንግሥት ዝርዝር ሕጎችን ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ክልሎች ደግሞ በእነዚህ ሕጎች መሠረት ማስተዳደር! ምናልባትም ዝርዝር ሕግ እንዳይኖር ማድረግ ዋነኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ሊሆንም ይችላል፡፡ ሕግ ካለመኖር የሚያርፉ ሰዎች ሕግ እንዳይኖር ስፖንሰር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል ወጥ የመሬት ይዞታና ባለቤትነት ማስፈን፣ መሬትን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የፌዴራል መሆኑ ዝርዝር ሕጎችን የማውጣት አስፈላጊነት፣ አሁን ያለው መሬትን ለኢንቨስተሮች በገፍ የመስጠት አካሄድ ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አንፃር ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ 

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡