ከአጀማመሩስ አጨራረሱ!

እነሆ ጉዞ! ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ። ማልዶ የጀመረው ግርግር ጨለማ በዋጠው ጎዳና ሊጠናቀቅ የጥቂት ሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ካፊያውና ብርዱ ከታክሲ አለመገኘት ጋር ሲደመር ሆድን ባር ባር ይላል። ብሶት ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ስለታመነ ይመስላል፣ በዚያ ግርግር የሚሰማው ጨዋታና ስላቅ ብሎም የትዕይንቱ መብዛት አንዳች አስደሳች ስሜት ያጭራል። ጃንጥላ ዘርግተው ካፊያውን ያመለጡ የመሰላቸው ቆነጃጅት ንፋስን ከነመፈጠሩ በዘነጋ አለባበሳቸው በቅዝቃዜ እያርገፈገፉ ይንቀጠቀጣሉ። ታክሲ እስኪመጣ የፍቅር አጋር ማደን የጀመሩ ወንዶች ‹‹መጠለል ይቻላል? የሰው ልጅ መቼም ልብስ፣ ምግብና መጠለያ ግድ ይለዋል ብለሽ እንደምታምኚ አልጠራጠርም። ተሳሳትኩ?›› እያሉ ይጠጋጋሉ። ድፍረት ከልባቸው ሞልቶ በዓይናቸው የፈሰሰ ዓይን አውጣዎችን እያየ ጎልማሳው ይስቃል፣ ፈሪው ትምህርት ይወስዳል። ‹‹አልተሳሳትክም!›› ትለዋለች አንዷ ስለሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች የተጠና አባባሉን እንዳነበነበ። ‹‹የክረምት ጎርፍ ያሻው ቆንጆ ልብ ላይ ይጣለኝ ብሎ አጋጣሚ ፍለጋ የሚባዝነው በርካታ ነው፤›› የሚል ሐሜት ከወዲያ ማዶ ይሰማል። የመንገድ ጨዋታና ሐሜት መቼ ያልቅና!

‹‹ይኼውልሽ እዚህ አገር የአርባ ቀን ዕድል ሆነና የምትጠለይው በቁጠባና በልመና ነው። ቁጠባውም ገንዘብ ሲኖር፣ ልመናውም ሰው ከተገኘ ማለቴ ነው፤›› እያለ የጨዋታውን ዳር ለማስፋት ይታገላል። ከሁለቱ ማዶ በጨቀየው አስፋልት መንገድ ላይ ለሳር ቤት ታክሲ ሰው ይሻማል። ተራ አስከባሪዎች የቤት መኪና ጭምር እንዲተባበር ይለምናሉ። ዝናብና ግርግር ለፕሮፓጋንዳ ያመቻል ይመስላል። አጠገቤ አንድ ወጣት በብርድ እየተንዘፈዘፈ፣ ‹‹እኔን የማይገባኝ እኮ ቆዳቸው ከምን የተሠራ ቢሆን ነው እንዲህ የሚለብሱት በዚህ ብርድ?›› እያለ ሲጠይቅ ይሰማኛል። ወደሚያይበት ስመለከት ሦስት ልጃገረዶች በጣም በአጭር ቀሚስ ለብሰው ይታዩኛል። ትችትና ማጉረምረም፣ ሳቅና ነቆራ፣ ብሶትና ትዕግሥት ማጣት ጥንድ ጥንድ ሆነው የገነኑበት ምሽት!

ቅዝቃዜውና ካፊያው ያማረረው ታክሲ ጠባቂ መንገደኛ ድንገት በተከሰተችው ጃጓር ታክሲ ለመሳፈር የሚያመነታ ዓይነት አልነበረም። አንዱ ባንዱ ተነባብሮ፣ ግብግብ የዳኘው ተሳፋሪነታችን ሲፀና ከታየነው ውስጥ በአንድ ጃንጥላ ተጠልለው የነበሩት ወንድና ሴት፣ ሦስቱ ልጃገረዶችና ያ ብቻውን ሲያወራ የነበረው ወጣት ይገኙበታል። ጢም ብላ ሞልታ በታጨቀችው ታክሲያችን ትንፋሻችን መስታውቶቹ ላይ ጉም ይገነባል። ‹‹ኧረ መስኮት! ቢያንስ መስኮት ይከፈት!›› ይላል ከወደኋላ። ‹‹አቦ አትጩህብና! ገና ለገና ተቃዋሚ ይነሳብኛል ብለህ በጩኸት ታደነቁረናለህ እንዴ?›› ይመልሳል መሀል መቀመጫ ቡዝዝ ባሉ ዓይኖቹ በመጠጥ መዳከሙ የሚታወቅበት ሽበታም። መጠጥ የሚያኮላትፈው ልሳኑ ከአዕምሮው ሆኖ እንደማይናገር የተገነዘበው ሁሉም ተሳፋሪ ስለነበር መልስ የሚያቀነባብርለት አልነበረም።

እሱ ግን ቀጥሏል። ‹‹ጩኸት አይበቃም እንዴ? አገርን ማልማት ውለታ አድርጎ የተቃዋሚ ነገር ባስበረገገው ቁጥር የሚጮህብን አይበቃንም ወይ? መስኮት አይከፈትም ብሎ የሚቃወመኝ ሰው ይኖራል ብለህ ፈርተህ ገና ለገና ምንድነው እንዲህ ሰው ማደንቆር?›› እያለ ሲናገር አባባሉ ከማበሰጫት ይልቅ ፈገግ ያሰኛል። ‹‹አዲስ ነገር ፈርተን፣ አዲስ ተሿሚ ፈርተን፣ አዲስ ሐሳብ ፈርተን መጨረሻችን ምን እንደሚሆን የሚነግረን ቢገኝ እንዲያው?›› ቀጥሏል ሽበታሙ በሞቅታ። ‘ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል’ ሆነና መስኮት ይከፈት ማለት ሰበብ ሆኖ ተገኝቶ ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ታክሲያችን የተቃዋሚና የገዢውን ፖለቲካ ማዳመጥ ግድ አላት!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላችን ጫቱን ቀነጣጥሶ እየጎረሰ ሒሳብ አዘጋጁ ካለን ቆይቷል። ‹‹ረሳው እንዴ? ኧረ ባደረገው…›› ይላል አንድ ጎልማሳ። ተሳፋሪው ዓይን ዓይኑን እያየ ይጠባበቃል። ወያላው ሌላ ዓለም ውስጥ እየገባ ነው። ሁላችንም እጅ ላይ ብር መቀመጡን ያየች አንድ ወጣት፣ ‹‹አይገርምም ብለን ብለን የታክሲ ለመክፈልም ወረፋ ያዝን እኮ። ለዳቦ፣ ለነዳጅ፣ ለትራንስፖርት መሰለፋችን አንሶ ጭራሽ ለወያላም እንሰለፍ?›› አለች። ‹‹ቻይው! ሌላ ምን ይባላል? ወያላችን ቶሎ ከመረቀነ ፈጣሪያችን እንደረሳን ሁሉ ሒሳብ መቀበሉን እሱም ይረሳው ይሆናል፤›› ይላል አንድ ችኩል ልጅ እግር። ‹‹አየህ ሙስና ከየት እንደሚጀምር? በፈጣጣ በሰው እጀ ጠባብ ዕጣ ስንጣጣል እያየህ ነው?›› ትለኛለች ቆንጂት። መልኳ ብቻ ሳይሆን አዕምሮዋም ጭምር እንዴት ንፁህና ቆንጆ እንደሆነ ማስመስከር ሳትፈልግ አልቀረችም። ከኋላችን የተቀመጡት ወጣቶች የሚጫወቱት ደግሞ እንዲህ ነው።

 ‹‹አንድ ዳቦ ለማትገዛ ገንዘብ እንደዚህ ከሆንን የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወት የሚለውጥ በጀት ስንጭበረበር ምን እንደሚያነጫንጨን እንጃ። አንገርምም?›› ብሎ አንደኛው ራሱን ይነቀንቃል። ወዲያው ወዳጁ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹እንዲህ አይደል ታዲያ የብዙኃን ስህተት ሳይፈተሽና ሳይመረመር ወግ፣ ሥርዓት፣ እምነት ሆኖ ትውልድ እየመጣ ትውልድ የሚሸኘው። በተናጠል ከምንወድቀው በመተባበር የምንከስረው ከየት ጀምሮ የት እንደሚደርስ ታያለህ?›› ይለዋል። ጨዋታቸው ጭልጥ ብሎ የሞራል ዋጋን መገምገም ሆኖ ሲከርብን ‘የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ’ ለማለት አንድ ተሳፋሪ የሚከተለውን ቀልድ ጀባ አለን። ብሶትና ብስጭቱን በቀልድ ካላበረድነው ከእዚችም ዕድሜያችን ላይ መቀነሱ ይቀራል? እሱን ነው መፍራት አትሉም!

ታክሲዋ ጉዞዋን ቀጥላለች። በብዛት ከተደረደሩ ጥቅሶች መሀል አንዷን አስተውሎ ያነበበ ወጣት መናገር ጀመረ። ‘ፍጥነት ዕድሜን ያሳጥራል እንጂ ጊዜን አይቆጥብም’ ትላለች። ገርሞት ፈገግ እንዳለ፣ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ አሁን ይኼ ጥቅስ ለእኛ ነው መለጠፍ ያለበት? ወይስ ለሾፌሩ?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹ኧረ ተወኝ ወንድሜ!›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሰለቸ ድምፀት። ወያላው በግልምጫ እያየው በምርቃናው የምናብ ሜዳ ላይ ወጣቱን የተናነቀው መስሏል። ‹‹ወይ ይኼ ምርቃና? ስንቱን ጀግና አደረገው?›› ይላል ይኼን የሚያስተውል። የሚስቀው ይስቃል። ወዲያው የዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጨዋታ ተመልሶ ተነሳ። ወጣቱ፣ ‹‹በጣም እኮ ነው የሚገርመው። ‘ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ጠንካራ የልማት ሠራዊት እንፍጠር’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። ‘ለሙስና እጅ አንሰጥም’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። መቼ ይሆን ሁሉም የራሱን ጉድፍ ማጥራት የሚጀምረው?›› ይላል።

አሁንም አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹ህም ድረቅ ቢልህ! ልፋ ቢልህ! ሰሚ ያለ መስሎሃል፤›› ይለዋል፡፡ ‹‹ወሬ! ወሬ! ኧረ ወሬ ጠላሁ!›› ሲል ወያላው እንደ መወናጨፍ ይቃጣዋል። ‹‹የመጣ የሄደው ዝም ብሎ ሲቀደድ. .  . . አንተ ምን አለብህ የምቀዳው እኔ…›› ብሎ ሾፌሩን ይተነኩሰዋል።  ሾፌሩ ግራ እንደ መጋባት እያለ፣ ‹‹ታዲያ መሥራት ካልቻልን፣ መብላት ካልቻልን፣ ቢያንስ ማውራት መቻል የለብንም?›› ይለዋል በስፖኪዮ እያየው። ‹‹እውነት ነው! ስናወራ ነው የሚያምርብን፤›› ቀጥሏል ወጣቱ። በዚህ መሀል ነበር፣ ‹‹መንግሥት ይኼን እየሰማ እንቅልፍ ይወስደዋል?›› ብሎ የጠየቀውን ፍለጋ ጥቂት ደቂቃ ዝምታ ሰፍኖ የቆየው።

‹‹ተመልከት እንዲህም አልሆን ብሎን ሰው ይወልደዋል፤›› ይለዋል ከኋላችን ከተቀመጡት ባልሰማ ያሳለፈው። ‹‹እና አንተ ምን አገባህ? ውለድ አልተባልክ። ምናለበት ሰው ዓይኑን በዓይኑ አይቶ ቢያልፍ? እዚህ አገር አንድ የእርካታ ምንጭ ልጅ ብቻ መሆኑን አጥተኸው ነው?›› እያለ መዓት ወረደበት። ‹‹ወይ የዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ? አሁን አንተ በድህነት በምትማቅቅ አገር የሕዝብ ቁጥር መጨመር ስለሚያስከትለው ጉዳት ሳታውቅ ነው አምና ዲግሪ ያዝኩ ብለህ የደገስከው?›› ብሎ ሊያሳፍረው ሲሞክር፣ ‹‹ዲግሪ ሌላ ኑሮ ሌላ። እዚህ አገር አንተስ ከመቼ ወዲህ ነው ሰዎች እንደተማሩት ሲያስቡ፣ ሲኖሩና ሲሠሩ  ያየኸው?›› ቢለው ዝም ዝም ሆነ። ይህንን ከእኔና አጠገቤ ከተቀመጠችው ቆንጆ በቀር ማንም አልሰማም። መውለድን የኮነነው ወጣት ዝም እንዳለ ጓደኛው የሚያነበንበውን ያዳምጣል። ‹‹ወልደን በዚህ ኑሮ ላይ ቅመም ካልጨመርንበት እያዛጋን እስከ መቼ? እንዴ! አስተውለሃል ለመሆኑ? ለዛ ያለው ነገር እኮ እልም ብሎ ጠፋ። ጣዕም የሚባል ነገር . . . ተወው ሌላውን ከዘፈን አቅም እንኳ የድሮ እየጎረጎርን ስናደምጥ አይደል እንዴ የምንውለው? አብዛኞቹ የዘመኑ ‘አርቲስት ነን’ ባዮች ግን አልገባቸው ብሎ በድግግሞሽ ያጠነዙናል። ራሳቸው ለራሳቸው በፈጠሩት የዝና አዙሪት ሰክረዋል…›› እያለ መውለድን ያበረታታል።  

አጠገቤ ደግሞ፣ ‹‹አይ እናንተ? አጨራረሱን እያያችሁ በአጀማማሩ ትሟገታላችሁ? ውልደት ውልደት ነው። ከደሃ ተወለደን ከሀብታም፣ ከንጉሥ ተወለድን ከአገልጋይ፣ በበረት ተወለድን በቤተ መቅደስ ለውጥ የለውም። ዋናው አጨራረሱ ነው። ይኼው አሰስ ገሰሱ ቆሻሻ ተንዶ ሕዝብ ይጨርሳል። በቁምም በእንቅልፍም ቆሻሻ እንደማገ፣ ቆሻሻ እንዳገሳ የሚሸኝ አለ። አንዳንዱን ደግሞ ሥራውና ልፋቱ ይገለዋል። ለቤተሰቡ ለወገኑ እንደ ዋተተ ፍሬ ሳያይ ይጠራል። ኧረ ተውኝ እስኪ። ደግሞ ብዬ ብዬ ሞት ልቁጠር። ብቻ የሚገርመኝና የማይገባኝ በስንፍና፣ በሙስና፣ በቸልተኝነት ደብር እግራቸውን ሰቅለው ከቤት እስከ አደባባይ ሸክም የሆኑብንን ለምን ሥራቸው እንደማያስጠይቃቸውና እንደማያስገኛቸው ብቻ ነው?›› ስትል ወያላው መጨረሻ ብሎ በሩን ከፈተው። ዝናቡ ታግሷል። እኛም ኮራ ብለን በየፊናችን ተበታተንን። ከአጀማመሩ አጨራረሱ ሲያምር ደስ አይልም? መልካም ጉዞ!