አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ከዚህ ካልተማርን ከምንም አንማርም

በጌታቸው አስፋው

ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመ የሪፖርተር ጋዜጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ፣ በኢትዮጵያ የተሰማራው የእንግሊዝ የማዕድን ኩባንያ የአክሲዮን ዋጋ በለንደን የአክሲዮን ገበያ ከፍ እንዳለ አስነበበን፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ ሁኔታ ባህር ማዶ ተሻግሮ የአንድን ኩባንያ የአክሲዮን ዋጋ ሊያስተምንና እንግሊዝን በሚያህል አገር ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር መቻሉ፣ በገበያ ኢኮኖሚ የዋጋ አወሳሰን አስተዳደር የዓለም ሕዝብ የት እንደደረሰ የምንመለከትበትና እኛ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረንም የምንገነዘብበት ነው፡፡ ዓለም ምን ያህል በኢኮኖሚ አስተዳደር እንደተሳሰረችም ይነግረናል፡፡

አንድና ሁለት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንግሊዛውያንና የመላው ዓለም የአክሲዮን ገበያ ተገበያዮች ናቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ፣ የኩባንያው የማደግ ተስፋ የለመለመ መሆኑን ያወቁት፡፡

ይህን መሰል መረጃ የአገር ውስጥና የውጭ አገር መረጃ ሚሊዮኖች ዘንድ ሊደርስ ባለመቻሉ ነው ትርፋማነትን መለካት ተስኖን ኢኮኖሚያችን ንግድ ላይ ብቻ ያተኮረው፡፡ ለዓለም ሕዝብ ኢኮኖሚክስ መረጃና ዕውቀት ሆኗል፡፡ ለእኛ ኢኮኖሚ መረጃና ዕውቀት ማለት የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን በጆንያና በከረጢት እየለኩ አሥር በመቶ አደገ ማለት ነው፡፡

ዓለም በገበያ ኢኮኖሚ ምርቱን እየለካ ያለው በአክሲዮን ገበያ ውስጥ በሚፈጠር የዋጋ አመልካቾች (Indices) ነው፡፡ እኛ ምርታችንን የምንለካው ጆንያና ከረጢት እየቆጠርን ነው፡፡ የሰማይና የምድር ያህል ተራርቀናል፡፡ የኤክስፖርት ምርታችንን ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ ምልክት በየቀኑና በየሰዓቱ ሊሰጠን ይችል የነበረውን በዋጋ አመልካቾች ውጣ ውረድ ሁኔታዎችን መገምገም ተስኖን፣ ዓመት ጠብቀን የአውሮፓ ገበያና የእህል ዋጋ ስለተዛባ ነው እንላለን፡፡

ቢቢሲን የመሳሰሉ ታላለቅ መገናኛ ብዙኃን በየሰዓቱ የቢዝነስ ዘገባ ብለው የሰነድ ገበያ ዋጋ አመልካቾችን መረጃ ለዓለም ሕዝብ ያስተዋውቃሉ፡፡ መሪዎች ሲለዋወጡ ወይም የኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች ሲቀያየሩ፣ ከአሸባሪዎች የፈንጂ ፍንዳታ አንስቶ ከትንሽ እስከ ትልልቅ ክስተቶች ሲከናወኑ አመልካቾቹ ከፍና ዝቅ ይላሉ፡፡ ሁኔታዎቹም በታወቁ ኢኮኖሚስቶች ይተነተናሉ፡፡

የአክሲዮኖቹ ዋጋ በራሳቸው ብቻ ትርጉም የላቸውም፡፡ ትርጉም ያላቸውና የሚያመለክቱት የድርጅትን፣ የኩባንያን፣ የክፍለ ኢኮኖሚን ወይም የዘርፍን ምርታማነትና ትርፋማነት ወይም ለወደፊት የማደግ ተስፋ ነው፡፡ ስለዚህም የምርት ኢኮኖሚው ነፀብራቅ በመሆን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የሚሰማሩበትን ዘርፍ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ኩባንያ ወይም ድርጅት ለመምረጥ ይረዳቸዋል፡፡

በእኛም አገር ኢኮኖሚክስ ምን እንደሆነ የማያውቁ የኢቢሲ ቢዝነስ ዘገባ ጋዜጠኞች ወጉ አይቅርብኝ ብለው በመሳለሚያ ገበያ የጤፍ ዋጋን በጆንያና በአትክልት ተራ ገበያ የድንች ዋጋን በከረጢት ይነግሩናል፡፡ ከጆንያና ከከረጢት መለኪያ መቼ እንወጣ ይሆን?

የመንግሥት ባለሥልጣናት መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወደ ንግዱ ነው የሚያዘነብሉት፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ አልገባ አሉ ብለው ዘወትር ያማርራሉ፡፡ ምን ይደረግ እንግዲህ? የዛሬና የነገ የገበያ ዋጋና ትርፋማነት በጆንያና በከረጢት አይለካ፡፡ የትኛው ፋብሪካ፣ ኢንዱስትሪ፣ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ዘርፍ አትራፊ እንደሆነ በምን ይወቁ?

በሀብት ማካበት የሚቀናቀናቸው እንዳይመጣ ብለው ዘመናዊ የምርት ገበያ ዋጋና የትርፋማነት መለኪያ ሥርዓት ነፀብራቅ የሆነውን የገንዘብ ገበያ ራሳቸው ባለሥልጣናቱ አገዱ፡፡ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል›› እንዲሉ ራሳቸው ምርታማነትና ትርፋማነት የሚለካበትን መንገድ ዘግተው ይዘው፣ ባለሀብቱ ወደ ኢንዱስትሪ አልገባም ብለው ይጮሀሉ፡፡

የአክሲዮን ኩባንያ ነገር ብዙ ሰዎችን እንዳቀለጠና ብዙ ሰዎችም እንደተታለሉ ከዚህ ቀደም ተጽፏል፡፡ አቤቱታው እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና መሪዎች ጽሕፈት ቤት ድረስ በር አንኳክቷል፡፡ እኔም ከዚህ ቀደም በሁለት ጽሑፎቼ ስለገንዘብ ገበያ ኢኮኖሚ የምችለውን አስተዋጽኦ ማድረጌን አስታውሳለሁ፡፡

የአክሲዮን ሕግ ተረቆ ከንግድ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንደቀረበም ተነግሮ ነበር፡፡ እንደ ሁልጊዜውም ተነግሮ ይቀራል እንጂ ፍጻሜ አያገኝም፡፡ ሕጉ ገና በመረቀቅ ላይ እያለም የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የግሉና የመንግሥት ትብብር በማለት ግዙፍ አክሲዮን ኩባንያዎችን መሥርተው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ አለመግባባት ቢፈጠር በምን ሕግ እንደሚዳኙ አይታወቅም፡፡ ኧረ እኛስ መቼ ይሆን እንደ ሌላው ዓለም ዛሬ የምንሠራው ነገ ምን እንደሚፈጥር አርቀን የምናስበው?

ከዚህ ቀደም የዳያስፖራ ዜጎች በአገር ውስጥ የገዙት የባንክና የኢንሹራንስ አክሲዮን ሕግን የጣሰ ነው በማለት ለሽያጭ ቀርቦ አንድ ሺሕ ብር የገጽታ ዋጋ ያለው አክሲዮን በሃያ ሺሕ ብር የገበያ ዋጋ መሸጡ፣ ለገዢው አላዋቂነት እንደሆነ በባለሙያዎች ትንታኔ ተሰጥቶበት ነበር፡፡ እኔም የበኩሌን አስተያየት ሰጥቼአለሁ፡፡

ሆኖም የባንክና የኢንሹራንስ የገንዘብ ክፍለ ኢኮኖሚው ተቋማት በሚከፍሉት ዓመታዊ ዲቪደንድና የድርጅቶቹ ካፒታል ከዓመት ወደ ዓመት ማደግ ምክንያት፣ ትርፋማነታቸው ከፍተኛ መሆኑን የማያውቅ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ዕድሉን ቢያገኝ መዋዕለ ንዋይ በዚያ ለማፍሰስ ዓይኑን አያሽም፡፡

የእኛ አገር ባለሥልጣናት የገንዘብ ገበያ ወይም የካፒታልና የጥሬ ገንዘብ ገበያ የካሲኖ ጨዋታ ይመስላቸዋል፡፡ የገንዘብ ገበያ የምርት ገበያውንና የአምራች ድርጅቶችን ምርታማነት ወይም ትርፋማነት በተዘዋዋሪ መንገድ መለኪያ መሣሪያ መሆኑን አይገነዘቡም፡፡    

የአክሲዮን ገበያ አንደኛ የድርጅቶችን ምርታማነትና ትርፋማነት በመለካት፣ ሁለተኛ ደሃውንም ሀብታሙንም እያንዳንዱን ሰው እንደአቅሙ ቆጣቢና ቁጠባውንም አክሲዮን ገዝቶ ራሱ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ባለሀብት ማድረጉን፣ ሦስተኛ አገሪቱ ለተጠማችው ካፒታል የገንዘብ ምንጭ በመሆን ኢኮኖሚውን እንደሚያስፋፋ ባለመገንዘብ ብዙ ዕድል አምልጦናል፡፡

በእርግጥ ዕድሉ ያመለጠው ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የገንዘብ ገበያውን በሞኖፖል ለመቆጣጠር የአክሲዮን ገበያ ፖሊሲ እንዳይወጣ በማድረግ ተጠቃሚዎች የሆኑትን አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ እንደምናውቀው ሁለተኛ የሰነድ መሸጫ ገበያ የሌለ ሲሆን፣ በአንደኛ የሰነድ ገበያ ሁለት ዓይነት ሰነዶች አሉ፡፡ አክሲዮኖች የባለቤትነት ድርሻና የትርፍ ተካፋይነትን መብት የሚያሰጡ ሰነዶች ሲሆኑ፣ ቦንዶች ግን ባለቤት የማያደርጉ ወለድ ብቻ የሚያስገኙ የብድር ሰነዶች ናቸው፡፡ በተለያዩ የዓለም አገሮች ከዚህ የሚከተሉት የተለያዩ የገንዘብ ገበያ ዓይነቶች የታወቁ ናቸው፡፡

  • የካፒታል ገበያ (የአክሲዮንና የቦንድ ገበያ)
  • የጥሬ ገንዘብ ገበያ ለምሳሌ የጋራ ጥሪት (Mutual Fund) ገበያ
  • የመድን ገበያ፣ የገንዘብ ሥጋቶችን ለማቅለል የሚገዛ ዋስትና
  • የውሎች ወይም ወደ ፊት ለመገበያየት የሚገባ ስምምነት ገበያ
  • የውጭ ምንዛሪ ገበያ ናቸው፡፡

የካፒታል ገበያ በተራው ለሁለት በመከፈል አዳዲስ ሰነዶች የሚገዙበትና የሚሸጡበት፣ አንደኛ ገበያና የነባር ሰነዶች ገበያዎች ሁለተኛ ገበያዎች ተብለው ይታወቃሉ፡፡ በሁለተኛ ገበያ የሚሸጡ ሰነዶች በፍጥነት ለመሸጥ ጥሬነታቸው ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ማለት ሰነዱ ብዙ ገዢዎችና ብዙ ሻጮች ካሉት ቶሎ ይሸጣል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወሳኙ ከሰነዱ በስተጀርባ ያለው የአክሲዮን ኩባንያው ምርት መጠን፣ ዕድገት፣ ምርታማነት፣ ወይም ትርፋማነት፣ ወይም ለወደፊት የማደግ ተስፋ ነው፡፡ 

የገንዘብ ገበያዎች ጥሪትን (Fund) ወይም ገንዘባዊ ሀብትን ከግለሰብ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወይም አበዳሪዎች ወደ ድርጅቶች ወይም ኩባንያዎች ያስተላልፋሉ፡፡ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ የመድረሻ ዕድሜ ያላቸው የጥሬ ገንዘብ ገበያዎች ድርጅቶች ለአጭር ጊዜ ሥራ ማስኬጃ ጥሪት ለመበደር የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የካፒታል ገበያዎች ግን ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ድርጅትን ለማስፋፋት ወይም አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ለመበደር የሚያገለግሉ ጥሪቶች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡