አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ኬንያን እየተገዳደረ መምጣቱ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

ከሰሞኑ ትዊተርን ጨምሮ በሌሎችም ማኅበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆነው ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ የተገኘው ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ልዕለ ኃያልነቱን ከኬንያ እየተረከበች መምጣቷን የሚያትተው ዜና ነው፡፡

በኬንያ ዋና ዋና የዜና አውታሮች ሽፋን የተሰጠው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማትና ዕቅድ ኢንስቲትዩትንም ያሳተፈ ነበር፡፡ ኢንስቲትዩቱ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ከሆነ ኢትዮጵያ ለዓመታት በኬንያ የበላይነት ተይዞ የቆየውን የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ የበላይነት ለመውሰድ ተቃርባለች፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ዓመታዊ ዕድገት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ሲነፃፀር ኬንያ ኢትዮጵያን ታስከነዳ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 የኬንያ ኢኮኖሚ የ14 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የጠቅላላ ምርት ዕድገት እንደነበረው ይገመት ነበር፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግማሽ ያህል ቀንሶ ማለትም በስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይከተል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በ72 በመቶ ገዳማ ከኬንያ ያነሰ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

እንዲህ የነበረው የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ልዩነት በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ እየጠበበ መጥቶ፣ ጭራሹንም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ኬንያን መብለጥ እንደምትጀምር የሚያሳዩ መረጃዎች ይፋ ወጥተዋል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክን ጨምሮ ሌሎች አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሚሳተፉበት፣ ዓመታዊው የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገትን የሚቃኘው ሪፖርትን መሠረት ያደረጉ ትንበያዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ዘንድሮ ኢትዮጵያ የሚኖራት የኢኮኖሚ ደረጃ በምሥራቅ አፍሪካ የበላይ እንድትሆን የሚያበቃት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህም የበላይነቱን ከኬንያ ለመረከብ ያስችላታል ተብሏል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ትኩስ አኃዛዊ መረጃዎች ዋቢ ያደረጉት ዘገባዎች እንደሚያትቱት፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋና ምንዛሪ ስሌት መሠረት፣ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ወይም የአገር ኢኮኖሚ አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚለካበት መመዘኛ መሠረት፣ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 70 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት ግዝፈት ይኖረዋል፡፡ ይህ ካቻምና ከነበረበት 62 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አኳያ ሲታይ የስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በአንፃሩ ኬንያ ካቻምና ከነበራት የ64 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኢኮኖሚ ወደ 69 ቢሊዮን ዶላር የምታሻቅብ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በስላሽ ተቀድማ አውራነቱን እንደምታስረክብ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግዝፍናው እያየለ፣ ዕድገቱም እየጨመረ መምጣቱ በመላው ዓለም ሲነገር ሰንብቷል፡፡ በያመቱ በአማካይ የአሥር በመቶ ዓመታዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበ የመጣው የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ በምሥራቅ አፍሪካ በኬንያ የተያዘውን የበላይነት ጠብቆ እንደሚዘልቅም ተነግሮለታል፡፡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ከባዱን ሚዛን የያዘው የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ መንግሥት የሚያከናውናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ዋናውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በመቀጠል ሊጠቀስ የሚችለው በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ነው፡፡

በመንግሥት የሚካሄደው ኢንቨስትመንት፣ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ የ40 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ ይህ ከስምንት ዓመት በፊት ከነበረው አኳያ በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያሳይ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና በሌሎችም አውታሮች የመንግሥት ሚና ገዝፎ የሚታይበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደፊትም በዚሁ አኳኋን እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ የኬንያ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያካሂደው ኢንቨስትመንት በ22 በመቶ እንደሚያድግ ሲጠበቅ፣ ዓመታዊው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በስድስት በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የኬንያ መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ኢትዮጵያም ባለሁለት አኃዝ ዕድገቷ ላለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ታች እየወረደ በመምጣት ከስድስት እስከ 8.5 በመቶ ባለው እርከን ውስጥ ሲዋልል ቆይቷል።

ይሁንና በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ድርቅ እንዲሁም በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያቀዛቅዙ የሚችሉ ፈተናዎች ሆነው ይቀርባሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የእነዚህ ተፅዕኖ ዝቅተኛ መሆኑን ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት የሚከተለው ፖለቲካዊ ሥርዓትም በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊሳርፍ እንደሚችል ይተችበታል፡፡ በተለይ የፖለቲካ የበላይነቱን በመያዙ ምክንያት የሚያሳድረው ጫናና የመብት ረገጣ በምዕራባውያኑ ዘንድ ሲያስኮንነው ቆይቷል፡፡ የኬንያ ጋዜጦችም መንግሥት በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰው ወከባና እንግልት በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ ነጥቦች መካከል ይመድቡታል፡፡ በዚህ መመዘኛ ኬንያ ከኢትዮጵያ የተሻለ ነፃነት የሰፈነባት ሆና እንደምትገኝ ያምናሉ፡፡

በነፍስ ወከፍ ገቢም ቢሆን ኬንያ ከኢትዮጵያ የተሻለች ሆና እንደምትገኝ አኃዞች ያረጋግጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) 686 ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 760 ዶላር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካቻምና ከነበረበት 1,434 ዶላር በዚህ ዓመት 1,522 ዶላር ገደማ እንደሚደርስ ስለሚጠበቅ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ መመዘኛ ከኢትዮጵያ የተሻለ ሆኖ ይገኛል፡፡

እርግጥ 100 ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከኬንያ አኳያ ከእጥፍ በላይ ብልጫ አለው፡፡ የኬንያ ሕዝብ ብዛት ለ50 ሚሊዮን ፈሪ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ያህል መሆኑ ትልቅ ገበያ መሆኑን በመጥቀስ በተለይ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ ትልቅ ሚና እንዳለው ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ትልቁን ማበረታቻና የኢንቨስትመንት ድጋፍ የሚሰጠው በአገር ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚመረቱ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉለት ነው፡፡

ይህም ቢባል በያመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ አገሪቱ እየመጡ እንደሆኑ የዓለም ባንክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ባደረጉት መረጃ መሠረት፣ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች መጥተዋል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ የበላይነት እንድትይዝ እያስቻሏት ከሚገኙ መገለጫዎች ውስጥ ቢመደብም፣ አገሪቱ መሳብ ከምትችለው የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥ አሁንም አነስተኛውን መጠን እያገኘች እንደምትገኝ ይገልጻል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሌሎች የኢኮኖሚ መለኪያዎች (ሒውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ) ማለትም የትምህርት፣ የጤና፣ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ፣ የኑሮ ደረጃና የመሳሰሉት መለኪያዎች ሲታከሉበት የኢኮኖሚው ዕድገት ወደ ታችኛው ሕዝብ ድረስ በመውረድ እያስገኘ ያለው ለውጥ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአገሪቱ የተንሰራፋውንና ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን የሕዝብ ቁጥር መጠን በግማሽ ለመቀነስ እንዳስቻለ የዓለም ባንክና ሌሎች ተቋማትም እማኝ ይሆኑለታል፡፡