አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ በአዲሱ መሥሪያ ቤታቸው የመጀመሪያ የሥራ ቀን ከአማካሪያቸው ጋር እየተወያዩ ነው]

 • የእዚህን መሥሪያ ቤት መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ሳምንት ያስፈልገናል፡፡
 • ጊዜ የለኝም በአስቸኳይ አቅርብልኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በአደገኛ ኔትወርክ የተጠላለፈ ስለሆነ ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡
 • ይኼንን ኔትወርክ የሚባል ነገር ለመበጣጠስ ምን እናድርግ?
 • ክቡር ሚኒስትር ዋና ዋና የሚባሉትን ቦታዎች ማፅዳት ነው፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ለምሳሌ ፋይናንስ፣ ግዥና ጨረታ፣ የሰው ኃይል፣ ሕዝብ ግንኙነት፣ ጠቅላላ አገልግሎትና የመሳሰሉትን፡፡
 • ሌላስ?
 • የሚኒስትር ዴኤታዎች የሚመሯቸውን ዘርፎች፡፡
 • በእነዚህ ላይ ትኩረት አድርገህ የዳሰሳ ጥናትህን በአስቸኳይ አቅርብልኝ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላ ደግሞ ኔትወርክ የሚያደራጁትንና ወሬ የሚያቀባብሉትን እንዳትረሳ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በተጨማሪ የጥቅማ ጥቅም ምንጭ የሆኑትን ትኩረት አድርግባቸው፡፡
 • አደርገዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዓይንና ጆሮህን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ አድርግ፡፡
 • እሺ ጌታዬ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ካሰናበቱ በኋላ ጸሐፊያቸውን ጠሯት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አዲስ ነገር አለ?
 • ክቡር ሚኒስትር ብዙ ሰዎች እየደወሉ ነው፡፡
 • ምን ይፈልጋሉ?
 • ቀጠሮ ያዢልኝ እያሉ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ጉዳይ አለን ነው የሚሉት፡፡
 • ለምሳሌ ምን ምን ጉዳዮች አሉዋቸው?
 • አንዱ ከልጅነት ጀምሮ አውቃቸዋለሁ ካላገኘሁዋቸው እያለ ነው፡፡
 • እሺ?
 • ሌላው ስጦታ ይዤ ልምጣ እያለ ነው፡፡
 • ስጦታ?
 • የተወሰኑት ደግሞ የቆየ አቤቱታ አለን ይላሉ፡፡
 • ሌላስ?
 • አንድ ሁለት የሚሆኑት የምሣ ወይም የእራት ግብዣ ጥሪ ሊያደርጉልዎት ይፈልጋሉ፡፡
 • የተለየ አለ?
 • ክቡር ሚኒስትር ረስቼው?
 • ምኑን?
 • የውጭ ኢንቨስተሮችም ካላገኘናቸው ይላሉ፡፡
 • ምን ፈልገው ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እንኳን ደስ ያለዎት ለማለት መሰለኝ፡፡
 • ሌላ የምትነግሪኝ አለ?
 • የተወሰኑ ባለሀብቶች በጋራ የላኩት ስጦታ አለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • በትልቅ ካርቶን ታሽጎ ስለመጣ አልከፈትኩትም፡፡
 • መቼ ነው የመጣው?
 • ዛሬ ጠዋት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስልክ ደውለሽ በአስቸኳይ መጥተው እንዲወስዱ ንገሪያቸው፡፡
 • ኧረ  ጡር ይሆናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንቢ ካልሽ ራስሽን አሸክሜ ነው የማስመልሰው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ እንደ እሳቸው የተሾሙ ሌላ ሚኒስትር ዘንድ ደወሉ]

 • ክቡር ሚኒስትር ሥራ እንዴት ነው፡፡
 • አሁን ፅዳት ላይ ነው ያለሁት፡፡
 • የምን ፅዳት?
 • መሥሪያ ቤቱን እያፀዳሁ ነዋ?
 • ይኼንን ያህል ቆሽሿል?
 • አይ ክቡር ሚኒስትር በጣም፡፡
 • ምን አጋጠመህ ክቡር ሚኒስትር?
 • በረት ታውቃለህ?
 • የምን በረት?
 • ለዓመታት ያልተጠረገ በረት፡፡
 • ምንድነው የምትለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ኧረ ብዙ ጉድ አለ፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ሥራና ሠራተኛ አልተገናኙም፡፡ ዕቅድ ይታቀዳል አፈጻጸም ዜሮ፡፡ በዚያ ላይ ሌብነት፡፡
 • ምን ዓይነት ሌብነት?
 • በኔትወርክ በተደራጀ ኃይል የሚፈጸም ሌብነት፡፡
 • እህ. . .
 • ሥልቱ የረቀቀ ውንብድና፡፡
 • እህ. . .
 • አንዳንድ ሰነዶችን ስታገላብጥማ ያዞርሃል፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አንተም ቶሎ ማፅዳት ጀምር፡፡
 • ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ሥልታዊና ዘዴኛ መሆን አለብህ፡፡
 • ማለት?
 • በኔትወርክ የተደራጀው ኃይል እንደ ማፊያ ነው፡፡
 • ምን ያደርጋል?
 • ሥራ ከማበላሸት ጀምሮ ነፍሰ በላ ነው፡፡
 • እኛ ከጠነከርን ምንም ችግር የለም፡፡
 • እንዳይመስልህ፡፡
 • ምነው?
 • ጭልፊት ታውቃለህ?
 • አዎን፡፡
 • ኔትወርኩና ጭልፊት አንድ ናቸው፡፡
 • ምን ያደርጋሉ?
 • ሰላማዊ መስለው ዙሪያህን ያንዣብባሉ፡፡
 • ከዚያስ?
 • አንተንም ሰዎችህንም ያጠፋሉ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የቅርብ ዘመዳቸው ስልክ ተደውሎላቸው እየተነጋገሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንኳን ደስ ያለዎት፡፡
 • እንኳን አብሮ ደስ ያለን፡፡
 • እንግዲህ በርታ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምኑ?
 • ያው ጫናው ብዙ ነው ብዬ ነው፡፡
 • እንግዲህ ጫናውን ለመሸከም ተዘጋጅቼያለሁ፡፡
 • ግን ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡
 • አይዞህ አትፍራ፡፡
 • በብቃት እንኳን አይታሙም፡፡
 • በምን እታማለሁ?
 • አለ አይደል?
 • ተናገረው፡፡
 • እንዳይዘናጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በምን እንዳልዘናጋ?
 • ወቅቱ ከባድ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይገባኛል ግን አትፍራ፡፡
 • ዙሪያዎን በሚገባ ይቃኙ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን አለ ብለህ ነው?
 • አነካኪዎች አሉ፡፡
 • ምንድናቸው?
 • ከጉቦ ጀምሮ ብዙ የሚያቀባብሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡
 • እንዳይመስልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ያመጣሉ?
 • አስማተኞች ናቸው፡፡
 • አስማት?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ሰዎቹ ያደነዝዛሉ ተክነውበታል፡፡
 • ልክ አስገባቸዋለሁ፡፡
 • እኔ እንጃ ክቡር ሚኒስትር አይናቋቸው፡፡
 • ይኼን ያህል ያስፈራሉ?
 • ከማስፈራትም በላይ ያሸብራሉ፡፡
 • ወቸው ጉድ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ውሎአቸውን ጨርሰው ወደ ቤት እየሄዱ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • የክቡር ሚኒስትር ሾፌር መሆን ለካ አሪፍ ነው፡፡
 • ምንድነው የምትለው?
 • ክቡር ሚኒስትር ከነጋ ከ50 በላይ ስልኮች ተደወሉልኝ፡፡
 • ለአንተ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር ደስ ሲል፡፡
 • እነማን ናቸው የደወሉት?
 • እኔ የት አውቃቸዋለሁ?
 • ምን አሉህ?
 • እንኳን ደስ አለህ ሲሉኝ ነው የዋሉት፡፡
 • ምን አልካቸው?
 • ምን ይባላል በደስታ መቀበል ነው እንጂ፡፡
 • ለዚህ ነው ደስ ያለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከዚህም በተጨማሪ ስጦታ የሚልኩልኝ እንዳሉ ነግረውኛል፡፡
 • ለአንተ?
 • አዎ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ስለሆንክ?
 • የእርስዎ ሾፌር በመሆኔ ነዋ፡፡
 • ቆይ! ቆይ! ምንድነው የሚልኩልህ?
 • ምን እንደሆነ አልነገሩኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለዚህ ነዋ በደስታ የምትፈነድቀው?
 • እንዴታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ካሁን በኋላ እንዲህ ያለ ነገር መስማት አልፈልግም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምናለበት ደስታዬ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ባይቸልሱበት?
 • ዝም በል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ባለቤታቸው እየጠበቋቸው ነበር]

 • ክቡር ሚኒስትር የአዲሱ ሥራህ ውሎ እንዴት ነበር?
 • ትንሽ ግራ ያጋባል፡፡
 • ምን ገጠመህ?
 • ተርመስመስ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡
 • እስኪ ንገረኝ፡፡
 • ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡
 • አይዞህ አትሥጋ ይለመዳል፡፡
 • ምኑ ነው የሚለመደው?
 • ሥራውም ኑሮውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ትቀልጃለሽ?
 • ራስህ አትቀልድ እባክህ?
 • ምን ለማለት ነው?
 • ነቃ ማለት ያስፈልጋል፡፡
 • ሞላጫና ሌባን ለመጠንቀቅማ ነቃ ማለት ያስፈልጋል፡፡
 • ከዚያም በላይ ትኩረት ማድረግ አለብህ፡፡
 • ለምኑ?
 • አጉል ሀቀኛ ነኝ እያልክ እንዳትሸወድ፡፡
 • አንቺ ሴትዮ ካሁኑ ጀመረሽ እንግዲህ?
 • ምኑ ነው የሚጀምረኝ?
 • ስንትና ስንት ኔትወርክና ጭልፊት እያንዣበበ እኮ ነው፡፡
 • ኔትወርኩን በትልቅ መቀስ ትቆራርጠዋለህ፡፡
 • እሺ?
 • ጭልፊቱን ደግሞ በወንጭፍ ትጥለዋለህ፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያማ አካባቢህን  በብቸኝነት ትቆጣጠራለህ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • የራስህን ኢምፓየር መሠረት ታስይዛለህ፡፡
 • እንቺ እኮ አታፍሪም፡፡
 • በዓይን አውጣ ዘመን ዓይናፋርነት አይሠራም፡፡
 • ትንሽ እንኳ ይሉኝታ የለሽም?
 • ይሉኝታ የፋራ ነው፡፡
 • ምን አድርግ ነው የምትይኝ?
 • ነቃ በል!
 • ምን ለማድረግ?
 • ሰው ለመሆን!
 • የአንቺ መንገድ ሰው ሰው አይልም፡፡
 • ምን ምን እያለህ ይሆን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰይጣን! ሰይጣን!
 • የነገርኩህን ብታስብበት ይሻላል፡፡
 • አንቺም ብታስቢበት ይሻልሻል፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አለበለዚያ አውጅብሻለሁ፡፡
 • ምን?
 • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ!