አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የወንድማቸው ልጅ ደወለላቸው]

 • ሰላም ጋሼ፡፡
 • አቤት ጎረምሳው፡፡
 • እንዴት ነህ ጋሼ?
 • ደህና ነኝ፡፡
 • በጣም ጠፋህ እኮ፡፡
 • ሥራዬን እያወቅከው?
 • እሱማ ልክ ነህ፡፡
 • እንዴት ናችሁ እናንተ?
 • በጣም ሰላም ነን ጋሼ፡፡
 • አባትህ እንዴት ነው?
 • በጣም ደህና ነው፡፡
 • እናትህስ?
 • እሷም ሰላም ነች፡፡
 • ቤተሰብ ሁሉ ደህና ነው?
 • ከአንተ መጥፋት በስተቀር ሁላችንም ሰላም ነን፡፡
 • ሥራው በጣም ቢዚ ያደርጋል፡፡
 • አውቃለሁ ጋሼ፡፡
 • ከየት ተገኘህ ዛሬ?
 • ላገኝህ ፈልጌ ነበር፡፡
 • በሰላም ነው?
 • ኧረ በሰላም ነው፡፡
 • ምን ነበር ታዲያ?
 • በስልክ ይሻላል ብለህ ነው?
 • ምን ችግር አለው?
 • ያው እናንተ ብዙ በስልክ አታወሩም ብዬ ነው፡፡
 • እሱ እኔን አይመለከተኝም፡፡
 • ማንን ነው የሚመለከተው?
 • ሙሰኞቹን፡፡
 • አይ ጋሼ፡፡
 • ምነው?
 • አሁን አንተ የለሁበትም እያልከኝ ነው?
 • እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አይነካካኝም፡፡
 • አልጀመርኩም እያልከኝ ነው?
 • መቼም አልጀምርም፡፡
 • አይ ጋሼ፡፡
 • ምነው?
 • ብዙ እያዋጣም ብዬ ነው፡፡
 • አንተ ግን ምን ፈልገህ ነው?
 • እኔማ ለሥራ ነው የደወልኩት፡፡
 • እኮ የምን ሥራ?
 • ሰሞኑን የሰማሁት ዜና አስደስቶኛል፡፡
 • የቱ ዜና?
 • መንግሥት ወጣቱን አደራጅቶ ገንዘብ ሊሰጥ ነው የሚለውን ዜና ሰምቼ ነዋ፡፡
 • ቆርጠን ነው የተነሳነው፡፡
 • በጣም ደስ የሚል ነገር ነው ጋሼ፡፡
 • አየህ እንደ አንተ ዓይነቶቹ ወጣቶች ውጤታማ መሆን አለባቸው፡፡
 • እኔም የደወልኩት ለዚህ ነው፡፡
 • በቃ ለሦስት ሆነህ ተደራጅተህ በሚሰጥህ ገንዘብ ሥራ መጀመር ነው፡፡
 • እንዴ ጋሼ?
 • ምነው?
 • የእኔ አጎት እኮ ሚኒስትር ነው፡፡
 • ቢሆንስ?
 • እኔ እንደሌላው ወጣት ልደራጅ?
 • እናስ?
 • እኔማ አደራጅ ነው መሆን ያለብኝ፡፡
 • ማለት?
 • ጋሼ ገጠር ያሉ ዘመዶቻችን ራሱ ፈንድቀዋል፡፡
 • ለምን?
 • ልነግርህ እኮ ነው፡፡
 • እኮ ንገረኛ?
 • እኔ ዘመዶቻችንን በጠቅላላ ሦስት ሦስት እያደረግኩ አደራጃለሁ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዛ በቃ እኔ ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኛለሁ፡፡
 • እ…
 • ለአንተም አስብልሃለሁ፡፡
 • ምን?
 • ኮሚሽን!

[የክቡር ሚኒስትሩ የአክስታቸው ልጅ ደወለችላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • ማን ልበል?
 • ማን ልበል!
 • አዎን፡፡
 • ስልኬን አጠፋኸው እንዴ?
 • አዲስ የስልክ ቀፎ ነው የያዝኩት፡፡
 • አይፎን ገዙልህ አይደል?
 • ማን ልበል?
 • የእህትህ ልጅ ነኝ፡፡
 • አንቺ ዱርዬ እንዴት ነሽ?
 • ዱርዬ ነኝ እንዴ ጋሼ?
 • አይ ለጨዋታው ብዬ ነው፡፡
 • የተናደድክ ትመስላለህ?
 • ምን የሚያናድድ ነገር ይጠፋል ብለሽ ነው?
 • ለነገሩ ሥራችሁ ከባድ ነው፡፡
 • ከባድ ብቻ?
 • አየህ ራስህን መጠበቅ አለብህ፡፡
 • እንዴት አድርጌ?
 • ለራስህ ማሰብ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ይኼ ሥራ እንደሆነ ከጥቅም ውጪ ነው የሚያደርግህ፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ በጊዜ ለራስህ ማሰብ አለብህ፡፡
 • እንዴት አድርጌ?
 • ስለእሱ አታስብ፡፡
 • ማለት?
 • እኛ አለንልህ፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • ዛሬ አንድ ነገር ላማክርህ ነው፡፡
 • ምንድን?
 • ሰሞኑን አንድ አዲስ ፕሮግራም ልትጀምሩ ነው፡፡
 • እ…
 • ወጣቶችን አደራጅታችሁ ብር ልታድሉ ነው አሉ፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡
 • ጋሼ እኛ እኮ ስትሾም ድግስ ነው የደገስነው፡፡
 • ለምን?
 • በቃ እንደሚያልፍልን ገባን፡፡
 • እ…
 • እንደውም ስምህን ቀይረነዋል፡፡
 • ማን አላችሁኝ?
 • ተሾመ፡፡
 • ቀልደኞች ናችሁ፡፡
 • ጋሼ አሁን የቀልድ ሰዓት አይደለም፡፡
 • እኮ ቀልድሽን አቁሚያ፡፡
 • ጋሼ በዚህ ዕድል መቀጠም አለብን፡፡
 • ይኼ ዕድል እኮ ለሥራ አጥ ወጣቶች ነው፡፡
 • ሥራ እኮ ለቀቅኩ፡፡
 • ለምን?
 • ተቀጥሮ መታሸት ሰለቸኝ፡፡
 • እና ምን ልትሆኚ ነው?
 • አንተ ትረዳኝና ከዚህ ፈንድ የተወሰነች ሚሊዮን ብዘግን …
 • እ…
 • በአቋራጭ መሆኔ አይቀርም፡፡
 • ምን?
 • ቀጣሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • በጣም የተናደዱ ይመስላሉ፡፡
 • ምን ላድርግ?
 • ምን አናደድዎት?
 • ምን የማያናድድ ነገር አለ ብለህ ነው?
 • ሚኒስትር ያናድዳል እንጂ መቼ ይናደዳል?
 • ምን ማለት ነው?
 • ያው የቀድሞው ሚኒስትር ስንቱን ያናዱዱት ነበር፡፡
 • በምንድን ነው የሚያናድዱት?
 • ያልገቡበት የቢዝነስ ዘርፍ የለም፡፡
 • እ…
 • ከእሳቸው አልፎ ዘመድ አዝማዶቻቸው በጣም ሀብታሞች ሆነዋል፡፡
 • እኔ እንደ እሳቸው አይደለሁም፡፡
 • ገና ነዋ ጊዜው፡፡
 • ማለት?
 • መጀመሪያማ እሳቸውም አይበሉም ነበር፡፡
 • እ…
 • ሲቆዩ ነው የጣማቸው፡፡
 • ፈጽሞ አላደርገውም፡፡
 • አይሞኙ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • በጊዜ ይጀምሩ፡፡
 • ሁላችሁም ከአንድ ወንዝ ነው እንዴ የተቀዳችሁት?
 • እነማን ናቸው ሌሎቹ?
 • ዘመዶቼ ደውለውልኝ አስበላን እያሉኝ ነበር፡፡
 • ምን አሏቸው?
 • ከአጠገቤ ጥፉ፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ዘመዶችዎን ባያስቀይሟቸው ጥሩ ነው፡፡
 • ይብሉ እያልከኝ ነው?
 • በኋላ እርስዎ መብላት ሲጀምሩ ጥሩ ሽፋን ይሰጡዎታል፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ምን እንደሰማሁ ያውቃሉ?
 • ምን ሰማህ?
 • ዛሬ አዲስ ከተሾሙት ሚኒስትሮች መካከል የአንዱን አማካሪ አግኝቼ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • በቃ ሰውዬው ዘንጣይ ናቸው አሉ፡፡
 • እ…
 • በሹመታቸው ሰበብ ያልተቀበሉት ስጦታ የለም፡፡
 • ልክስክስ በላቸው፡፡
 • ኧረ እርስዎም በጊዜ ይጀምሩ፡፡
 • ምኑን?
 • መላሱን፡፡
 • ምንድን ነው የምልሰው?
 • ስኳር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ተናደው ስጦታ ተቀበሉ የተባሉት ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቃል ገብተህ አልነበር እንዴ?
 • ምን ብዬ?
 • ሕዝብን በቅንነት አገለግላለሁ ብለህ?
 • ታዲያ እያገለገልኩ አይደል?
 • ስማ ስጦታ መቀበል እኮ አይቻልም፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • እ…
 • ጉቦ እኮ አይደለም የተቀበልኩት፡፡
 • በጣም ታሳፍራለህ፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ትቀበላለህ?
 • ቀንተው ነው?
 • ማን እኔ?
 • ሰው ከወደደኝ ምን ላድርግ?
 • ሙሰኛውማ ሊወድህ ይችላል፡፡
 • እ…
 • ሕዝብ ግን ይጠላሃል፡፡
 • ችግር የለውም፡፡
 • በጣም ደፋር ነህ፡፡
 • ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም ሲባል አልሰሙም፡፡
 • በጣም ነው ያዘንኩብህ፡፡
 • ይልቁኑ ልምከርዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድን ነው የምትመክረኝ?
 • እርስዎም በጊዜ ይግቡበት፡፡
 • ምኑን?
 • ቢዝነሱን!