ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲል ልጃቸውን አገኙት]

 • ምን እያደረግክ ነው አንተ?
 • ምን አደረግኩ?
 • እስካሁን እንዴት አልሄድክም?
 • የት ዳዲ?
 • ሁሌ በዚህ ሰዓት የት ነበር የምትሄደው?
 • እ… ትምህርት ቤት?
 • አዎ ለምን አልሄድክም?
 • ዛሬ የለም፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • የለም ተብለን ነው፡፡
 • ታዲያ ለምን ለእኛ አላሳወቁንም?
 • እኔ እንጃ ዳዲ፡፡
 • ሌላ ጊዜ በደብዳቤ ያሳውቁን ነበር እኮ?
 • ምንም ደብዳቤ አልሰጡንም፡፡
 • ለምንድን ነው ግን የሌለው?
 • እ…
 • አንተ ልጅ እየዋሸኸኝ ነው?
 • ኧረ አይደለም ዳዲ፡፡
 • ቆይ ዳይሬክተሩ ጋ ልደውል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ዳይሬክተሩ ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ!
 • ጤና ይስጥልኝ፡፡
 • ሰላም ምን ፈለጉ?
 • ስለልጄ ጉዳይ ለማናገር ነበር፡፡
 • መተው ያናግሩኛ፡፡
 • እ…
 • ጢንንን….

[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]

 • አሁኑኑ መሄድ አለብን፡፡
 • የት ዳዲ?
 • ትምህርት ቤት ነዋ፡፡
 • እ…
 • ምንድን ተፈጥሮ ነው ንገረኝ?
 • አይ ከማሚ ጋር እሄዳለሁ፡፡
 • ለምን ከእኔ ጋር አትሄድም?
 • ወላጅ አምጣ ተብዬ ነው፡፡
 • ምን?
 • ምንም አላደረግኩም እኮ ዳዲ፡፡
 • እና ለምን ወላጅ አምጣ ተባልክ?
 • ዝም ብለው ነው እነሱ፡፡
 • ለዚህም ደርሰሃል ማለት ነው?
 • ኧረ ዳዲ አታካብድ፡፡
 • እሱን በኋላ እንነጋገራለን፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የዳይሬክተሩ ቢሮ ከልጃቸው ጋር ገቡ]

 • ሰላም አረፍ ይበሉ፡፡
 • ይቅርታ ቅድም ደውዬ ነበር፡፡
 • ማን ልበል እርስዎን? ዶክተር፣ ፕሮፌሰር…
 • ክቡር ሚኒስትር ካልክ ይበቃል፡፡
 • እኔ እኮ የት ነው የማውቅዎት ብዬ ነበር?
 • ማለት?
 • የሆነ ቦታ አይቼዎታለሁ፡፡
 • የት ነው ያየኸኝ?
 • ያው ቲቪ ላይ ነዋ፡፡
 • እሺ ስለልጄ ጉዳይ ላናግርህ ነበር፡፡
 • እሱ ልጅዎት ነው እንዴ?
 • አዎ ምነው?
 • ከየት ነው የወጣው ታዲያ ክቡር ሚኑስትር?
 • ምን አደረገ?
 • በጣም አስቸጋሪ ልጅ ነው ያለዎት?
 • ይኼን ያህል?
 • አሁን እኮ ለ15 ቀን ልንቀጣው ነው፡፡
 • ምን አድርጎ?
 • ትምህርት አይማርም፣ ሁሌ እንደፎረፈ ነው፡፡
 • እ….
 • ስለዚህ ለ15 ቀን ሰስፔንድ ልናደርገው ነው፡፡
 • እንዴ በአንድ ጥፋት እንዴት ይኼን ያህል ይቀጣል?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ እኮ አምስተኛ ጊዜ ነው፡፡
 • ምን?
 • ወላጅ ሲያመጣ እርስዎን ለአምስተኛ ጊዜ ነው፡፡
 • ከዚህ በፊት ማን ነበር የሚመጣው?
 • እናቱ ነበር የሚመጡት፡፡
 • እኔ ሳላውቅ?
 • ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው ይባላል፡፡
 • እንዴት?
 • ስንት የአገር ጉድ እያወቁ…
 • እ….
 • ለቤትዎት ጉድ ሆኑ ባዳ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

 • አንቺ ሴትዮ፡፡
 • ሄሎ፡፡
 • ምን እየሠራሽ ነው?
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • እንዴት ነው የምትደብቂኝ?
 • አትጩህ እስቲ፡፡
 • የምታወሪው አይሰማኝም፡፡
 • አሞኛል እባክህ፡፡
 • ምን ሆንሽ?
 • ቶንሲል ነው መሰለኝ፡፡
 • የት ነው ያለሽው?
 • ቤት ነው ያለሁት፡፡
 • አሁኑኑ መጣሁ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ደረሱ]

 • ምን ሆነሽ ነው?
 • ጉንፋን ነገር ነው፡፡
 • ድምፅሽ ለምን ተዘጋ?
 • ቶንሲሌም ተነስቶብኛል፡፡
 • ቀዝቃዛ ነገር ጠጣሽ እንዴ?
 • ኧረ የሰሞኑ አየር ከአቅሜ በላይ ሆኗል፡፡
 • በይ ነይ ሆስፒታል እንሂድ፡፡
 • እሺ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ሆስፒታል ሲደርሱ አንድ ባለሀብት አገኙ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አላወቅኩህም ይቅርታ፡፡
 • ባለፈው ስብሰባ ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡
 • የትኛው ስብሰባ?
 • ከግል ባለሀብቶች ጋር ያደረጋችሁት ስብሰባ ላይ፡፡
 • እሺ እንዴት ነህ?
 • ሰላም ነኝ እኔ፣ ምነው እዚህ ተገኙ?አይ ትንሽ…
 • አመመዎት እንዴ?
 • ሚስቴን ትንሽ አሟት ነው፡፡
 • ውይ ምነው በሞትኩት?
 • አንተስ ምን ትሠራለህ?
 • ሰው ልጠይቅ መጥቼ ነው፡፡
 • ለነገሩ እሷም ቶንሲሏ ተነስቶባት ነው፡፡
 • ታዲያ እዚህ እንዴት ይመጣሉ?
 • ከሆስፒታል ውጪ የት ልሂድ?
 • ማለቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምና በጣም ከባድ ነው፡፡
 • እ…..
 • ለእንቅርት ኩላሊት የሚቀዱ ሐኪሞች ባሉበት አገር፡፡
 • እሱስ እውነትህን ነው፡፡
 • እርስዎ ደግሞ እንዴት ያሳክሟቸዋል?
 • አልገባኝም?
 • እርስዎ የሕዝብ አገልጋይ ነዎት እኮ፡፡
 • ሌላ የሚያሳክምልኝ ሰው የለም፡፡
 • እኛ እያለን፡፡
 • እ….
 • ምን በወጣዎት ስልዎት?
 • ኧረ አይገባም፡፡
 • የእርስዎ ሚስት ደግሞ እዚህ መታከም የለባቸውም፡፡
 • ታዲያ የት ትታከም?
 • ባንኮክ ነዋ፡፡
 • ጉንፋን ነገር እኮ ነው፡፡
 • መሄድ አለባቸው ስልዎት፡፡
 • ለምን?
 • ለሙሉ ቼክአፕ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ጋ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር ቀጠሯችን እንደተጠበቀ ነው አይደል?
 • አይ አይመስለኝም፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • አፋጣኝ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡
 • እየቀለዱ መሆን አለበት?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • ዛሬ መገናኘታችን ግዴታ ነው፡፡
 • የቤተሰብ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው እኮ፡፡
 • ለሦስተኛ ጊዜ ቀጠሯችን ሊሰረዝ?
 • ምን ላድርግ?
 • የእኛ ጥምረት እኮ የብዙዎችን ሕይወት ነው የሚቀይረው፡፡
 • የሕዝቡን ሕይወት ይቀይራል ብለህ ነው?
 • የእኔና የእርስዎ ሕይወት ሲቀየር በዚያው የሕዝቡ ሕይወት ይቀየራል፡፡
 • እ….
 • እንዳይቀሩ ይምጡ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ደረሰ]

 • አንተ ጤነኛ ነህ?
 • ሆስፒታል ስለመጣን በዚያው ሊያስመረምሩኝ ብለው ነው?
 • እየቀለድኩ አይደለም፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከእኔ ጋር እንደዚህ ማውራት የጀመርከው ከመቼ ጀምሮ ነው?
 • ኧረ ይቅርታ ለጨዋታ ብዬ ነው፡፡
 • የት ነበርክ እስካሁን?
 • መንገድ ተዘግቶ ነው፡፡
 • እኮ ለምን?
 • ዛሬ ከተራ እኮ ነው፡፡
 • ታቦት ይሸኛል ለካ ዛሬ?
 • እርስዎም ታቦት ይሸኛሉ እንዴ?
 • ብሸኝማ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
 • በጣም ይገርማል፣ የቀድሞው ሚኒስትር እኮ የሚሸኙት ሌላ ነበር፡፡
 • ምን ነበር የሚሸኙት?
 • ኢንቨስተር፡፡
 • ዛሬ ታዲያ ማንን ቀጥረው ነው?
 • አንድ ኢንቨስተር፡፡
 • በቃ በታቦቱ ፋንታ እሱን ይሸኙታል፡፡
 • ማንን?
 • ኢንቨስተሩን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ኢንቨስተሩ ጋ በጣም አርፍደው ደረሱ]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይቅርታ በጣም፡፡
 • ተስፋ ቆርጬ ልሄድ ነበር እኮ፡፡
 • መንገድ ተዘግቶብኝ እኮ ነው፡፡
 • አንዳንዴ ይረሱታል ልበል?
 • ምኑን?
 • ሚኒስትር መሆንዎን?
 • ለታቦት እኮ ነው የተዘጋው፡፡
 • የእኔ ታቦት እርስዎ ነዎት፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም ላረፈዱበት ይቀጣሉ፡፡
 • ምንድን ነው የምቀጣው?
 • አንድ ሔክታር መሬት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ደህና ነኝ፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው?
 • ያው ተያይዘነዋል፡፡
 • ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብዎት ያውቃሉ አይደል?
 • በሚገባ፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰሙ?
 • ከየትኛው ልጀምር?
 • ማለት?
 • ከትንሹ ይሻላል ከትልቁ?
 • አልገባኝም?
 • የቲቪውን ላውራ ወይስ የቪ8ቱን?
 • እ….
 • የበጉ ይሻላል ወይስ የባንኮኩ?
 • ስጦታ እኮ ነው፡፡
 • የመንግሥት ባለሥልጣን ስጦታ መቀበል አይችልም፡፡
 • ባህላችን እኮ ነው፡፡
 • ይኼ ሙስና ነው፡፡
 • ሙስና የሚባለው እኮ እኔ በምትኩ ሌላ ነገር ስሰጥ ነው፡፡
 • እና ሙሰኛ አይደለሁም እያሉ ነው?
 • በሚገባ፡፡
 • ለነገሩ አሁን የሚባሉት ሌላ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የምባለው?
 • ዕጩ ሙሰኛ!