ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ስማ አንድ ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ከወር በላይ ነው ያሰብኩበት፡፡
 • እኮ ምንድን ነው?
 • የሚገርም የቢዝነስ ሐሳብ ነው፡፡
 • በቃ ሙሉ ጊዜሽን ቢዝነስ ለመሥራት ወሰንሽ?
 • ስማ አንተ እኮ ስነግርህ ልትሰማኝ አልቻልክም፡፡
 • ምኑን?
 • አሁን የሚያዋጣው ቢዝነስ ነው፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ስለዚህ እሱን ብናጠናክር ነው የሚሻለን፡፡
 • እሺ ምን አሰብሽ?
 • አሁን አንድ ትልቅ በዓል አለ፡፡
 • ገና አለፈ አይደል እንዴ?
 • አንተ ደግሞ፡፡
 • ጥምቀትስ ቢሆን አልፏል አይደል እንዴ?
 • እኔ ስለእነሱ አይደለም የማወራው፡፡
 • ስለብሔር ብሔረሰቦች በዓል ነው የምታወሪው ታዲያ?
 • በቃ አንተ ዞረህ ዞረህ እዚያው ነህ አይደል?
 • እና የምን በዓል ነው?
 • ለስሙ ውጭ ነው የተማርኩት ትላለህ፡፡
 • የውጭ አገር በዓል ነው እንዴ?
 • እሱማ አመጣጡ ከውጭ ነው ግን እዚህም በጣም እየተከበረ ነው፡፡
 • የምን በዓል ነው?
 • ቫላንታይንስ ዴይ፡፡
 • ምን ዴይ?
 • የፍቅረኛሞች ቀን፡፡
 • አሁን ምን ዓይነት ቢዝነስ አስበሽ ነው?
 • መቼም ለፍቅረኞች በግና ፍየል እሸጣለሁ አልልህም፡፡
 • እኮ ምን ልትሸጪ ነው?
 • አበባ፡፡
 • ለመሆኑ በዓሉ መቼ ነው?
 • ነገ ነው፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • በጣም ገርመሽኝ ነዋ፡፡
 • በምንድን ነው ያስገረምኩህ?
 • በአንድ ቀን የሚበቅል አበባ የት ነው የሚገኘው ብዬ ነዋ?
 • አንተ ደግሞ?
 • ምነው?
 • አበባ ተክዬ ልሸጥ ያሰብኩ ይመስልሃል?
 • እና ከየት አምጥተሽ ልትሸጪ ነው?
 • በመጀመሪያ ያሰብኩትን ልንገርህ፡፡
 • እሺ ንገሪኝ፡፡
 • ከተማችን ውስጥ በጣም ታዋቂ አሥር ሞሎችን መርጫለሁ፡፡
 • እሺ፡፡
 • በቃ በእነዚህ ሞሎች አሥር አይሱዙ አበባ ብንሸጥ እንተኮሳለን፡፡
 • አበባውን ከየት አምጥተሽ ነው የምትሸጪው?
 • ሚኒስትር ነህ አይደል እንዴ?
 • እሱማ ነኝ፡፡
 • በርካታ የአበባ እርሻ ያላቸውን ባለሀብቶች ታውቃለህ አይደል?
 • አዎን አውቃለሁ፡፡
 • በቃ እነሱ ይሰጡሃላ፡፡
 • እንዴ እነሱ ፍቅረኛዬ አይደሉም እኮ?
 • ፍቅረኛሞች ትሆናላችኋ፡፡
 • እንዴት?
 • አንተ መሬት ትሰጣለህ፡፡
 • ከዚያስ?
 • አበባ ትቀበላለህ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው የሆኑ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቤት ወዳጄ፡፡
 • እኔ የምልዎት ስንት ጅል ባለሥልጣን ነው ያለው?
 • እንዴት ማለት?
 • አንዱ ያደረገውን ሰምቼ ተቃጠልኩ፡፡
 • ምን አድርጎ ነው?
 • እኛን ለማሳጣት ሆን ብሎ ያደረገው ይመስለኛል፡፡
 • እኛን ለማሳጣት ስትል?
 • አጉል ሀቀኛ ነኝ ሊል ፈልጎ ነዋ፡፡
 • በዚህ ዘመን ምቀኛ እንጂ ሀቀኛ መቼ አለ?
 • ለነገሩ እውነትዎን ነው፣ ምቀኛ ብለው ይቀለኛል፡፡
 • እንዴት?
 • እኛ እንዳንጠቀም ሆን ብሎ ነዋ ያደረገው፡፡
 • ምኑን?
 • መንግሥት ቦታ ሰጥቶት ትልቅ ቤት ይሠራል፡፡
 • ታዲያ ይኼ ምን ችግር አለው?
 • ቤቱን ሲያጠናቅቅ አከራየው አልኩት፡፡
 • ምን አለህ ታዲያ?
 • ይኸው አዲስ የሠራው ቤት ውስጥ ገባበት፡፡
 • የነበረበትን የኪራይ ቤት ምን አደረገው?
 • መለሰው፡፡
 • ለማን?
 • ለመንግሥት!

[የክቡር ሚኒስትሩን ቤት የሚሠራው ኢንጂነር ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ኢንጂነር?
 • ዛሬ በጣም የሚያስደስት ዜና አለኝ፡፡
 • አንተ ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው የሚያስደስት ዜና የኖረህ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንዴ ሲሚንቶ ጨመረ፣ አንዴ ብረት ተወደደ አይደል እንዴ የምትለኝ?
 • ከዚህ በኋላ እንደዚህ ማለት ቀረ፡፡
 • ለምን?
 • ቤቱ ተጠናቋል፣ ቁልፉን መረከብ ይችላሉ፡፡
 • ምን ትቀልዳለህ?
 • በእውነት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም አስደሳች ዜና ነው፡፡
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ እዚያ ደላላ ጋ ልደውል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከደላላው እኔ አልሻልም?
 • እንዴት?
 • እኔው ቤቱን የሚመጥን ፈርኒቸር ብገዛለት ጥሩ ነው፡፡
 • እየቀለድክ ነው?
 • የምሬን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምንድን ነው ፈርኒቸር የምገዛው?
 • ቤቱን አይገቡበትም እንዴ?
 • እኔ እኮ ጅል አይደለሁም፡፡
 • እና ምን ሊያደርጉት ነው?
 • አከራየዋለሁ!

[ክቡር ሚኒስትር ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]

 • በዓሉን እንዴት ነው የምታከብረው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ በዓሉን አላከብርም፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • ሚስቴ አበባ ይዤላት ብሄድ የበለጠ ትጣላኛለች፡፡
 • እ…
 • የምትበላው የላት የምትከናነበው አማራት አሉ፡፡
 • ስለምንድን ነው የምታወራው?
 • ስለፍቅረኛሞች ቀን ነው የሚያወሩኝ አይደል?
 • ኧረ እኔ ስለፆም መያዣ ነው የማወራህ?
 • የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
 • አንተ ተረት አብዝተሃል፡፡
 • ደመወዜ አልበዛ ሲለኝ ተረት ማብዛቱን ተያይዤዋለሁ፡፡
 • ፆም መያዣ እንዴት ነው የምታከብረው ነው ያልኩህ?
 • እየቀለዱብኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ፆሙን አትፆምም መሰለኝ?
 • ኧረ እኔ መፆም አቋርጬ አላውቅም፡፡
 • ማለት?
 • 365 ቀናት ነው የምፆመው?
 • ምን ዓይነት ወንጀለኛና ኃጢያተኛ ብትሆን ነው ዓመቱን ሙሉ የምትፆመው?
 • ተገድጄ ነው፡፡
 • የነፍስ አባትህ ነው ያስገደዱህ?
 • ኧረ እሳቸው ምን በወጣቸው?
 • ታዲያ ማን አስገድዶህ ነው?
 • ኑሮ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር የተናደዱ ይመስላሉ?
 • ይኼ ውኃ በጣም ነው ያማረረኝ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው ውኃ ከጠፋ ሳምንት ሆነው እኮ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ የምኖረው ኮንደሚኒየም ውስጥ ነው፡፡
 • እዚያ ውኃ አይጠፋም እንዴ?
 • ኧረ ውኃ እያለ ሦስተኛ ፎቅ ስለማይደርስ፣ ከውኃ ጋር ከተሰነባበትን ቆየን፡፡
 • ለመሆኑ ምንድን ነው ችግሩ?
 • የአዲስ አበባ የከርሰ ምድር ውኃ እያለቀ ነው መሰለኝ፡፡
 • እንዴት ያልቃል?
 • ያው ጉድጓዶቹ በጥልቀት ስላልተቆፈሩ ውኃ ማውጣት አልተቻለም መሰለኝ፡፡
 • እኔ እኮ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡
 • ምንድን ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በጥልቅ መታደስ አለብን እያሉ ይሰበሰባሉ፡፡
 • እ…
 • በጥልቀት የውኃ ጉድጓድ መቆፈር ግን አይችሉም፡፡
 • ጉድጓድ ቆፋሪዎቹ በጥልቀት አልታደሱም ማለት ነው፡፡
 • ለማንኛውም እኔ በውኃ እጦት ተማርሬያለሁ፡፡
 • ለምን ከዚህ አይወስዱም?
 • በምን?
 • በጀሪካን ነዋ፡፡
 • ሚኒስትር መሆኔን ረሳኸው እንዴ?
 • ያው ከችግሩ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
 • እኔማ ግፍ ፈርቼ ነው እንጂ ገንዳዬን ልሞላው ነበር፡፡
 • በምን?
 • በኃይላንድ ውኃ፡፡
 • ይችላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም ለብቻዬ እንዲቆፈርልኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • ምንድን ክቡር ሚኒስትር?
 • ጉድጓድ፡፡
 • ለመቀበሪያዎት ነው?