አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን ቢሯቸው አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አዘጋጀህልኝ?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሪፖርቱን ነዋ፡፡
 • የትኛውን ሪፖርት ነው?
 • አንተ ሰውዬ ሥራህን ትተኸዋል እንዴ?
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የኦዲት ሪፖርቱን፡፡
 • አላዘጋጀሁትም፡፡
 • ፓርላማ የማቀርበው አይደል እንዴ?
 • ችግር የለውም አሁኑኑ አደርሰዋለሁ፡፡
 • እንዴት አድርገህ ነው የምታደርሰው?
 • ያለፈውን ዓመት ሪፖርት እኮ አፕዴት ማድረግ ነው፡፡
 • ምን?
 • ምንም አያስቡ ስልዎት?
 • ከበፊቱ ሚኒስትር ጋር እርስዎ የሚያጠፉት ተመሳሳይ ነው እያልከኝ ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ቆይ እኔና የበፊቱ ሚኒስትር ስታወዳድረን እንዴት ነን?
 • በምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በበጀት አጠቃቀማችን፡፡
 • አሁን አሁን እየተመሳሰላችሁ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በቃ ያለ ደረሰኝ በርካታ ገንዘብ እያወራረዱ ነው፡፡
 • እ…
 • በዛ ላይ በየጊዜው የተለያዩ ዕቃዎችን ያስገዛሉ፡፡
 • ለምሳሌ ምን?
 • ኮምፒዩተር ሊጠቀስ ይችላል፡፡
 • እኔ እኮ አንድ ኮምፒዩተር ነው ያለኝ፡፡
 • በስምዎት ግን የተመዘገቡ 17 ኮምፒዩተሮች አሉ፡፡
 • ምን?
 • እንዲያውም ክቡር ሚኒስትሩ ኢንተርኔት ካፌ ከፈቱ ወይ እየተባለ ይወራል፡፡
 • ስነግርህ አትሰማም እንዴ? ይኸው የምጠቀመው በአንድ ኮምፒዩተር ነው፡፡
 • ግን እንደነገርኩዎት በስምዎ የተመዘገቡት 17 ናቸው፡፡
 • ታዲያ የቻይና ኮምፒዩተር እየገዛችሁልኝ ምን ላድርግ?
 • እኮ ታዲያ 16ቱ የታሉ?
 • እኔ ሥራ አላሠራ ሲሉኝ ስለምናደድ እዚያው ነው የምሰብራቸው፡፡
 • ግን ኦዲተሮቹ ጠይቀውኛል፡፡
 • የትኞቹ ኦዲተሮች?
 • የመንግሥት ኦዲተሮች፡፡
 • ምን?
 • ምነው ደነገጡ?
 • እና ቢሮ መጥተው ነበር?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስልካቸውን ትሰጠኛለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ኃላፊዎቹ ጋ ቢደውሉ አይሻልም?
 • እሺ እዚያ ልደውል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የኦዲት ኃላፊዎቹ ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቢሮ መጥታችሁ ነበር አሉ?
 • አዎን መጥተን ነበር፡፡
 • ታዲያ ሰላም ሳትሉኝ ምነው ሄዳችሁ?
 • ያው የመጣነው ለሥራ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሁሉን ነገር እንደ ጠበቃችሁት ነው ያገኛችሁት አይደል?
 • ኧረ ከጠበቅነው በላይ ነው ያገኘነው፡፡
 • ሁሉን ነገር ነው ያሻሻልኩት፡፡
 • ሙስናውም ተሻሽሏል እያሉኝ ነው?
 • የምን ሙስና?
 • ለማንኛውም አሁን ቡድን አቋቁመናል፡፡
 • የምን ቡድን?
 • ኦዲት የሚያደርግ ነዋ፡፡
 • ኦዲት አደረጋችሁ አይደል እንዴ?
 • ሌላ ኦዲት የሚደረግ አካል አግኝተናል፡፡
 • ማን ነው?
 • ክቡር ሚኒስትሩ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • መቼም የዛሬውን ቀጠሮ አልረሱትም?
 • የምን ቀጠሮ?
 • እኔም እኮ ጠርጥሬ ነው የደወልኩት፡፡
 • ማንን ቀጥሬ ነበር?
 • ኢንቨስተሮቹን ነዋ፡፡
 • የትኞቹን ኢንቨስተሮች?
 • ክቡር ሚኒስትር መርሳት ጀመሩ ልበል?
 • እኔ በቀን ስንትና ስንት ኢንቨስተር እያገኘሁ የቱን ላስታውስ?
 • እነዚህ ግን የሚረሱ አልነበሩም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ከቻይና የመጡት፡፡
 • ሁሌስ ቢሆን ከቻይና ውጭ ሌላ ኢንቨስተር መቼ አግኝቼ አውቃለሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር እነዚኛዎቹ ቃል ገብተውልዎት ነበር፡፡
 • የምን ቃል?
 • ሼር ሊሰጥዎት፡፡
 • ትቀልዳለህ?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ልረሳው ቻልኩ ታዲያ?
 • እኔም እኮ ገርሞኛል፡፡
 • ስለዚህ ምሳ ሰዓት እንዳይቀሩ፡፡
 • በቃ ራሴ እየነዳሁ ነው የምመጣው፡፡
 • ከቻሉም በሔሊኮፕተርም ቢመጡ ጥሩ ነው፡፡
 • እሱን ማድረጌ አይቀርም፡፡
 • መቼ?
 • ድርሻዬን ስወስድ!

[የክቡር ሚኒስትሩ መኪና ነዳጅ ጨርሳ እየተገፋች ነዳጅ ማደያ ደረሰች፡፡ ቀጠሮ ቦታቸውም ስላረፈዱ ደላላው ደወለ]

 • የት ደረሱ ክቡር ሚኒስትር?
 • ነዳጅ ማደያ ተሰልፌ፡፡
 • ምን?
 • መኪናዬ ነዳጅ ጨረሰች፡፡
 • እየቀለዱ ነው?
 • ይኸው አሁን አስገፍቼ ነዳጅ ማደያ ደረስኩ፡፡
 • እርስዎ መቼም የመጀመሪያ ነዎት?
 • በምን?
 • መኪና እያስገፉ ማደያ ያስገቡ ሚኒስትር በመሆን፡፡
 • እኔ እኮ በብዙ ነገር ቀዳሚ ነኝ፡፡
 • በአንድ ነገር ቀዳሚ እንደሆኑ እኔም አውቃለሁ፡፡
 • በምን?
 • በኮሚሽን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ደላላውን የቀጠሩበት ቦታ በጣም አርፍደው ደረሱ]

 • የት አሉ ኢንቨስተሮቹ?
 • ሄዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የት?
 • ወደ አገራቸው፡፡
 • እኔን ቀጥረውኝ አልነበር እንዴ?
 • ዛሬ እንደሚበሩ ነግሬዎት ነበር እኮ?
 • ታዲያ እንዴት ሳያገኙኝ ይሄዳሉ?
 • አውሮፕላኑ ያመልጣቸዋላ፡፡
 • ከእኔ ጋር ቢስማሙ እኮ የግላቸውን አውሮፕላን መግዛት ይችሉ ነበር፡፡
 • ከሁለት ሰዓት በላይ ነው እኮ ያረፈዱት ክቡር ሚኒስትር?
 • የነዳጅ ማደያው ሠልፍ እኮ ሠልፍ እንዳይመስልህ፡፡
 • ለማንኛውም እኔ ሌላ የቢዝነስ ሐሳብ አለኝ፡፡
 • ምን ዓይነት?
 • ነዳጅ ለመግዛት ለሰዓታት ከተሠለፉ ለምን አይከፍቱም?
 • ምን?
 • ነዳጅ ማደያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • በዓሉን እንዴት ነው የምናከብረው?
 • የትኛውን በዓል ክቡር ሚኒስትር?
 • የድል በዓሉን ነዋ፡፡
 • ግንቦት 20ን ነው፡፡
 • ምን ይቀባጥራል ይኼ?
 • የብሔር ብሔረሰቦች በዓልም አልፏል እኮ፡፡
 • ስማ የጥቁሮች የድል በዓል እየተባለ የሚወራለትን ረሳኸው?
 • የዓደዋ በዓልን ነው?
 • ታዲያስ?
 • አይፍረዱብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ወድጄ አይደለም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በምን ላስታውሰው ብለው ነው?
 • ይኼ ትልቅ በዓል ነው፡፡
 • አዎ ግን ቢሆንም እኛ ብዙ የምናከብረው ግንቦት 20ን፣ ብሔር ብሔረሰቦችን፣ ምናምን ነው፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር ለእነዚህ በዓላት ሕዝብ በየአደባባዩ ወጥቶ፣ ቲሸርቱ ቢሉ ኮፍያው ኧረ ስንቱ፡፡
 • እና ለዓደዋ በዓል ቲሸርትና ኮፍያ ይዘጋጅ እያልክ ነው?
 • አይ ብቻ በዓሉ ብዙም ትኩረት አይሰጠውም፡፡
 • ስለዚህ እኛ ይህን በዓል ማክበር አለብን፡፡
 • እንዴት እናክብረው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ለሠራተኞቻችን የውይይት መድረክ ይዘጋጅ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ ለፕሮግራሙ በጀት ይመደብ፡፡
 • ፕሮግራሙ ምንድን ነው የሚሆነው?
 • ጠዋት ሁለት ከሰዓት ሁለት የጥናት ወረቀቶች ይቀርባሉ፡፡
 • ሌላስ?
 • በቃ ለጥናት አቅራቢዎች ብቻ ሃምሳ ሃምሳ ሺሕ ብር ይከፈላል፡፡
 • ኮፍያና ቲሸርት የለም፡፡
 • አዋጪው መንገድ የጥናት ወረቀት የሚለው ነው፡፡
 • ግን በዚህ አጭር ጊዜ የጥናት ወረቀት የሚያቀርቡልን አራት ሰዎች ከየት እናገኛለን?
 • ለእሱ አታስብ፡፡
 • ለምን?
 • አራቱንም የጥናት ወረቀቶች…
 • እ…
 • እኔ አቀርባቸዋለሁ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሙሰኛ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለዚህ የወጣቶች ፈንድ ላወራህ ነበር፡፡
 • ምን ፈለጉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው ዘመዶቼን በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቻቸዋለሁ፡፡
 • እሱማ እኔም አደራጅቻቸዋለሁ፡፡
 • አሁን ግን ሌላ ሐሳብ መጥቶልኝ ነበር፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • ለምን እኛም አንደራጅም?
 • በምን?
 • በአነስተኛና ጥቃቅን፡፡
 • ምን ልናደርግ?
 • ፈንዱን እንጠይቃለና?
 • ለወጣቶች ነው እኮ፡፡
 • እኛም ገና ወጣቶች አይደለን እንዴ?
 • እንዴት ሆኖ?
 • ከተሾምን ማለቴ ነው፡፡
 • እሱማ ልክ ነዎት፡፡
 • ስለዚህ በጊዜ እንደራጅ፡፡
 • በአነስተኛና ጥቃቅን?

[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሀቀኛ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼን የወጣቶች ፈንድ ለማግኘት ለምን አንደራጅም?
 • በምን?
 • በአነስተኛና ጥቃቅን፡፡
 • እርስዎ መደራጀት አይደለም የሚያስፈልግዎት፡፡
 • እና ምንድን ነው የሚያስፈልገኝ?
 • መጠየቅ፡፡
 • በምን?
 • በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት!