አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚኒስትር

 

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ተክዘው ሶፋ ላይ ተቀምጠዋል]

 • ምን ሆነሽ ነው?
 • ምን አልሆንም ብለህ ነው?
 • ተክዘሻል እኮ?
 • ሐሳብ ይዞኝ ነዋ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • አንተ ምን አለብህ?
 • ቢዝነሱ ጥሩ አይደለም እንዴ?
 • እሱ አይደል እንዴ የሚያሳስበኝ፡፡
 • አዲስ አይደል እንዴ ቢዝነሱ?
 • ታዲያ አዲስ መሆኑ አያሳስብም?
 • ማለቴ ጥሩ እየሠራ ነው ብለሽኝ ነበር?
 • እሱማ ጥሩ እየሠራ ነው፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የሚያሳስብሽ?
 • የፆሙ ነገር ነዋ የሚያሳስበኝ፡፡
 • ለዓሳ ቢዝነስ እኮ ፆም በጣም አሪፍ ነው፡፡
 • እሱማ አሪፍ ነው፡፡
 • ታዲያ ፆሙ ለምን አሳሰበሽ?
 • ሊፈታ መሆኑ ነዋ፡፡
 • ለካ እሱም አለ?
 • ፆሙ ከተፈታ ቢዝነሱ እንደዚህ ላይቀጥል ይችላል፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • ፆሙን ማስቀጠል ብትችልማ ጥሩ ነበር፡፡
 • እሱንማ እንዴት ላደርገው እችላለሁ?
 • እሱማ መላ አይጠፋም፡፡
 • ምን ዓይነት መላ?
 • አንተ ማድረግ ከቻልክ፣ እኔ መላ አለኝ፡፡
 • እኮ ንገሪኛ?
 • በቃ ሕዝቡ ላይ ኑሮ እንዲከብድ ማድረግ ነው፡፡
 • እ…
 • ከዛም ሁሌም ለሕዝቡ ፆም ይሆንበታል፡፡
 • አሁን ይኼን እንዴት ማድረግ ይቻላል?
 • እሱን አንተ ታውቅበታለህ፡፡
 • አንቺ ግን እውነትም መለኛ ነሽ፡፡
 • ወድጄ አይደለም እባክህ፡፡
 • ለጊዜው ግን መፍትሔ አለኝ፡፡
 • ምን ዓይነት መፍትሔ?
 • ፆሙ ሲፈታ ዓሳ ቤቱን እንቀይረው፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ሥጋ ቤት፡፡
 • አይ አንተ?
 • ምነው?
 • አካባቢውን በደንብ አታውቀውም ማለት ነው?
 • አካባቢው ምንድን ነው?
 • በርካታ ታዋቂ ሥጋ ቤቶች አሉ፡፡
 • ስንት ሥጋ ቤቶች ነው ያሉት?
 • አራት፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • እንዴት የለውም?
 • እነሱ ሥራ እንዲያቆሙ እናደርጋለን፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • መጀመሪያ ጤና ላይ ችግር እንዳስከተሉ መሆኑ ተገልጾ እንዲታሸጉ ይደረጋል፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያ ደግሞ ታክስ እንዳጭበረበሩ ይገለጽና ይዘጋሉ፡፡
 • አንተ ራስህ አባ መላ ነህ እኮ፡፡
 • በዛ ላይ የሚኒስትሩ ሥጋ ቤት መብላት የማይፈልግ የለም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በቃ ሌላኛው ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮ ይሆናላ፡፡
 • ምን ላድርግህ?
 • በአንቺ ወጥቼ እኮ ነው መለኛ የሆንኩት፡፡
 • ዋናው ጥያቄ ስሙ ምን ይባል የሚለው ነው?
 • ለእሱ አታስቢ፡፡
 • ማን ይባል?
 • የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥጋ ቤት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላው ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • የሚገርም ነገር ይዣለሁ፡፡
 • ምን ተገኘ ደግሞ?
 • ፀሎትዎትን እግዚአብሔር ሰምቶታል፡፡
 • ምን ነበር ፀሎቴ?
 • በቃ ሊተኮሱ ነው፡፡
 • ማን ነው የሚተኩሰው?
 • ኧረ ወዲህ ነው ነገሩ፡፡
 • አገሪቷ ውስጥ ጦርነት አለ እንዴ?
 • ከባለቤቱ ያወቀ አሉ፡፡
 • ማለት?
 • እሱንማ እርስዎ ነው የሚያውቁት፡፡
 • እኔ አገሪቱ ሰላም እንደሆነች ነው የማውቀው፡፡
 • ለእርስዎም ሰላም እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
 • በምን አወቅክ?
 • አካውንትዎት ሲጨምር ሰላምዎም አንድ ላይ ይጨምራላ፡፡
 • እ…
 • ባይሆን ደምዎም ስለሚጨምር እሱ ነው ችግሩ፡፡
 • ወሬ መቼም ማን ችሎህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ዛሬ ግን ጮማ ወሬ ነው ያለኝ፡፡
 • እኮ ምን ተገኘ?
 • አንድ ነገር አግኝቼልዎታለሁ፡፡
 • ሕንፃ አገኘህልኝ እንዴ?
 • ሕንፃውን የሚያመጣውን ነገር አግኝቼልዎታለሁ፡፡
 • ምንድን ነው እሱ?
 • ለፋብሪካ የሚሆን አምስት ሺሕ ካሬ ቦታ ተገኝቷል፡፡
 • ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ መቀላቀሉ ይሻላል ብለህ ነው?
 • የመንግሥትም አቅጣጫ እሱ ነው ብዬ ነው፡፡
 • ለነገሩ ልክ ነህ፡፡
 • አሁን ከእርስዎ አንድ ነገር የምፈልገው፡፡
 • ምን ፈለክ?
 • ውክልና፡፡
 • አንተን አምኜማ ውክልና አልሰጥህም፡፡
 • የውልና ማስረጃ ሳይሆን የቃል ውክልና ብቻ ነው የምፈልገው፡፡
 • እሱን ሰጥቼሃለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር ግን አለ፡፡
 • ምን?
 • ከቦታው ላይ የሚነሳ ገበሬ አለ፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • ያው ካሳ ያስፈልጋል፡፡
 • መክፈል ነዋ ታዲያ፡፡
 • አምስት መቶ ሺሕ ብር ይሆናል፡፡
 • ለካሳ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ገበሬ ነው ብለኸኛል አይደል?
 • አዎን ነው፡፡
 • ውሉ ላይ አምስት መቶ ሺሕ ብር ብለህ አስፈርመው፡፡
 • ሲከፈልስ?
 • አንዱን መቀነስ ነዋ፡፡
 • አንዱን ምን?
 • ዜሮ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የአጎት ልጅ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • አቤት ጎረምሳው፡፡
 • ጉድ ሆንን ጋሼ፡፡
 • ዕቃውን አላገኛችሁትም እንዴ?
 • ዕቃውንማ አግኝተነው ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ተፈጠረ?
 • ችግር ተፈጥሯል ጋሼ፡፡
 • የምን ችግር?
 • ፖሊሶች ኬላ ላይ ያዙን፡፡
 • ምን?
 • አዎን ጋሼ፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ተጠቁሞብን ነው መሰለኝ፡፡
 • ማን ነው የጠቆመው?
 • ምግብ ቤት የጠረጠሩን ሰዎች መሰሉኝ፡፡
 • ስትንከረፈፉ ነዋ የተያዛችሁት፡፡
 • አይ ሾፌሩ ትንሽ ይቀበጣጥር ነበር፡፡
 • እ…
 • በቃ ስለሚገኘው ገንዘብ ምናምን ሲያወራ የሰሙት ሰዎች ጠቆሙ፡፡
 • አሁን የት ነው ያላችሁት?
 • እስር ቤት!

[ክቡር ሚኒስትር ፖሊስ ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እናንተ ጋ የተያዙ ሰዎች አሉ፡፡
 • አሁን ኮምፒዩተርና ታብሌት በኮንትሮባንድ ሊያስገቡ የነበሩትን ነው?
 • አዎን ስለእነሱ ነው፡፡
 • በጣም ብዙ ኮምፒዩተሮችና ታብሌቶች ነው የያዙት፡፡
 • ግዳጅ ላይ ነው ያሉት፡፡
 • የምን ግዳጅ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመንግሥት የሚፈለጉ ዕቃዎች ናቸው፡፡
 • ታዲያ ለምን በኮንትሮባንድ ማስገባት አስፈለገ?
 • ሚስጥራዊነታቸው እንዲጠበቅ ስለተፈለገ ነው፡፡
 • እና ምን ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰዎቹን ልቀቃቸው፡፡
 • በማን ዋስትና ክቡር ሚኒስትር?
 • በእኔ ዋስትና፡፡
 • ለማያውቁት ሰው ዋስ መሆን አይከብድም?
 • አንዱ የወንድሜ ልጅ ነው፡፡
 • በጣም ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ችግር የለውም፡፡
 • መጀመሪያም ቢነግሩኝ አይታሰርም ነበር፡፡
 • አንተም ማጣራት ነበረብሃ?
 • አሁኑኑ እለቀዋለሁ፡፡
 • በምን ዋስ?
 • ያለ ዋስ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ገባ]

 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ችግር ገጥሞናል፡፡
 • የምን ችግር?
 • በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ላይ፡፡
 • ውይይቱ በጥሩ መጠናቀቁን ሰምቼ ነበር፡፡
 • አዩ ችግሩ ከዚህ ይጀምራል፡፡
 • ከምን?
 • እርስዎ ውይይት ይላሉ፣ እኛ ድርድር እንላለን፡፡
 • ሐሳቡ እኮ ያው ነው፡፡
 • መስማማት ያልቻልነው እንዲያውም በዚህች ቃል ነው፡፡
 • በየትኛው ቃል?
 • ሐሳብ በምትለው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • እኛ ሐሳብ የሚለው ቃል፣ በ‹‹ሀ›› መጻፍ አለባት ስንል፣ ግማሾቹ በ‹‹ሐ›› መጻፍ አለበት አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በ‹‹ኃ›› መጻፍ አለበት ብለዋል፡፡
 • ሰውዬ ጤነኛ ነህ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በየትኛውስ ቢጻፍ ምን ልዩነት ያመጣል?
 • አዩ ክቡር ሚኒስትር፣ ‹‹ሀ›› ቀዳሚነትን ነው የሚያሳየው፣ ‹‹ኃ›› ደግሞ ኃይልን ሲያሳይ፣ እናንተ ግን ሐሳብን በ‹‹ሐ›› ጽፋችሁ አመጣችሁ፡፡
 • እኛ እኮ ውይይቱን ያዘጋጀነው ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለማምጣት በማሰብ ነው፡፡
 • ቢሆንም ይኼ መስተካከል አለበት፣ ምክንያቱም በትንሹ ነገር መስማማት ካልቻልን ለሕዝቡም ጥያቄ ምላሽ ማምጣት አንችልም፡፡
 • እሺ ይስተካከላል፡፡
 • ሌላ ደግሞ ስብሰባ የሚለው ቃል የተጻፈው በእሳቱ ‹‹ሰ›› ነው፡፡
 • ምን ዓይነት አሿፊ ሰው ነህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ እኮ ትርጉም ስላለው ነው፡፡
 • የምን ትርጉም?
 • እናንተ ተቃዋሚዎች እሳት ናቸው ልትሉ ፈልጋችሁ ነው በ‹‹ሰ›› የጻፋችሁት፡፡
 • ስለዚህ እንዴት ይጻፍ?
 • በንጉሡ ‹‹ሠ››
 • ለምን?
 • ስለምንፈልግ፡፡
 • ምን መሆን?
 • መንገሥ!