ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጣም አርፍዶ ቤታቸው ደረሰ]

 • አንተ?
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጤነኛ ነህ ግን?
 • በዚህ ዘመን ጤነኛ አለ ብለው ነው?
 • ቀጠሮ እንዳለኝ ነግሬህ አልነበር እንዴ?
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ምን ላድርግ ትለኛለህ?
 • የለማ፡፡
 • ምንድን ነው የሌለው?
 • ነዳጅ፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ይኸው የትኛውም ማደያ ማግኘት አልቻልኩም፡፡
 • እንዴ ነዳጅ ልናወጣ ነው እያልን ባልንበት ወቅት ጭራሽ ጠፍቷል ትለኛለህ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር አያስቁኝ?
 • እንዴት ማለት?
 • ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ነዳጅ ይወጣል ያለው ማን ነው?
 • ምን አልክ?
 • በጥልቅ ታድሰናል ስትሉ በጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረን ነዳጅ እናወጣለን እያላችሁ ነው ማለት ነው?
 • ወሬውን ትተህ ሥራውን በሠራህ?
 • ምን ላድርግ አላሠራ ብለውኝ ነው፡፡
 • ማን ነው አላሠራ ያለህ?
 • ባለማደያዎቹ ናቸዋ፡፡
 • አሁን ለመሆኑ ቀዳህ?
 • ከየት አግኝቼ ክቡር ሚኒስትር?
 • እና በምን ልሄድ ነው?
 • ትንሽማ አለኝ፡፡
 • መንገድ ላይ ቢቆምስ?
 • ያው በሜትር ታክሲ እልክዎታለሁዋ፡፡
 • በጣም ተደፋፍረናል ማለት ነው?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚኒስትር ሆኜ በታክሲ ልሄድ?
 • ምን አለበት?
 • እውነትም አንተ ደፍረኸኛል፡፡
 • የሕዝቡን ሕይወት በዚያው ቢያዩት ብዬ ነው እኮ?
 • አላደርገውም፡፡
 • በቃ እሺ እንሠለፋለና፡፡
 • የምን ሠልፍ ነው?
 • አይ ሰላማዊ ሠልፍ አይደለም፡፡
 • ታዲያ የምን ሠልፍ ነው?
 • የነዳጅ፡፡
 • ምን ዓይነት ጣጣ ነው?
 • ችግር የለውም፣ ያው ሠልፉ የእንትኑ መገለጫ ነው ይላሉ፡፡
 • የምኑ?
 • የልማቱ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለነዳጅ ተሠልፈው መኪናቸው ውስጥ ጋዜጣ እያነበቡ ነው፡፡ ባነበቡት ዜናም ተደናግጠው አንድ ወዳጃቸው የሆነ ዳያስፖራ ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ፡፡
 • እንዴት ነህ ባክህ?
 • ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፣ ስልኬን አልያዝከውም እንዴ?
 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፣ አዲስ ስልክ ይዘው ነው መሰለኝ፡፡
 • ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ጋዜጣ ላይ ዜና አንብቤ ደንግጬ ነው የደወልኩልህ፡፡
 • ስለምን አንብበው ነው?
 • ስለሃኪንግ፡፡
 • ስለራሺያ ሃኪንግ አንብበው ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ታዲያ ስለትራምፕ አንብበው ነው?
 • ስለባንክ ነው ያነበብኩት፡፡
 • የምን ባንክ ነው?
 • የባንክ አካውንት ሃክ ተደርጎ፡፡
 • እዚህ እኛ ጋ ነው?
 • እሱማ የኢትዮጵያ ባንክ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን አስደነገጠዎት?
 • አይ የባንኩ የውጭ አካውንት ሃክ ተደርጎ ነው ገንዘብ የተወሰደው፡፡
 • ምን ያህል ገንዘብ?
 • ኧረ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡
 • በጣም ይገርማል፡፡
 • ቀልቤ እኮ ነው ግፍፍ ያለው፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • የእኔንም መጦሪያ ሃክ እንዳያደርጓት ብዬ ነዋ፡፡
 • እ…
 • የስንት ሰው ፊት አይቼ ያመጣኋትን ዶላር ላፍ እንዳያደርጉኝ?
 • እሱ እንኳን ያሳስባል፡፡
 • እኔ እኮ ከዚህ ሥራዬ ሳበቃ በእሷ እጦራለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡
 • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሷን ሃክ አድርገውብኝ ራሴን ሃንግ እንዳላደርግ፡፡
 • ኧረ የሰይጣን ጆሮ አይስማው፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • እስቲ ላስብበታ፡፡
 • እኔ ግን አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • የባንኩን ሴኩዩሪቲ ለምን አናጠናክረውም?
 • ምን አድርገን?
 • እኔ ከዚህ መላክ እችላለሁ፡፡
 • ምን?
 • ዘበኛ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ወዳጅ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
 • እኔም ዊኬንዴ ተበጥብጦ ነው ያሳለፍኩት፡፡
 • ምን ይሆን መጨረሻው?
 • ያው ቼልሲ ዋንጫ መብላቱ አይቀርም፡፡
 • ኧረ እኔ ስለኳስ አይደለም የማወራው፡፡
 • ስለተሠራው ብልግና ነው የምታወራው?
 • የትኛው ብልግና?
 • ቁማር ተበልቶ አልመድብም ስላለው ወዳጃችን?
 • ኧረ እኔ ሊቀር ነው እያልኩዎት ነው፡፡
 • ምን ዕቁባችን?
 • ለነገሩ ዕቁባችን መቅረቱ አይቀርም፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • አልሰሙም ማለት ነው?
 • ምኑን?
 • ለመሆኑ ክቡር ሚኒስትር ስንት ቦታ ቦርድ ነዎት?
 • ስድስት ቦታ መሰለኝ፡፡
 • አዲሱን መመርያ አልሰሙም?
 • የምን መመርያ?
 • ከዚህ በኋላ ዕድለኛ ከሆኑ የአንድ መሥሪያ ቤት ብቻ ቦርድ አባል መሆን ነው የሚችሉት፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ቦርድ የሆንባቸው ድርጅቶች ትርፋማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡
 • እኛ ግን ትርፋማ ነን፡፡
 • እንግዲህ ከቦርድ አባልነትዎ በቅርቡ ይነሳሉ፡፡
 • ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡
 • መመርያ ወጥቷል ስልዎት፡፡
 • እኔማ ሄጄም ቢሆን እለምናቸዋለሁ፡፡
 • ምን ብለው?
 • እኔ እስክበላ መመርያው እንዳይተገበር፡፡
 • ምን እስኪበሉ ድረስ?
 • ዕቁቡን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

 • ጉድ ሆንን ባክሽ?
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ዕቁቡ ሊቆም ነው፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ከአቅም በላይ ችግር መጥቷል፡፡
 • እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ ዕቁቡ ሊቆም የሚችለው?
 • ዕቁቡማ አልቆመም፡፡
 • ታዲያ ምን ተፈጠረ?
 • እኛ ልናቆም ነው እያልኩሽ ነው?
 • ለምን ሲባል?
 • ከየት አምጥተን እንከፍላለን?
 • እስከ ዛሬ ከቦርድ አባልነትህ የምታገኘውን ነበር እኮ የምትጥለው?
 • እኮ አሁን ሊቆም ነው፡፡
 • እኛ ዕቁቡን ሳንበላ?
 • መመርያ ወጥቷል፡፡
 • መንግሥት የለም እንዴ በአገሪቷ?
 • እኔም እንደዚያ ነው ያልኩት፡፡
 • ይኼ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡
 • ምን ላድርግ ጨነቀኝ?
 • ይኼን ጉዳይ መላ ልትለው ይገባል፡፡
 • እኮ ምን ይሻላል?
 • በግልጽም ቢሆን ተናገራ፡፡
 • ምን ብዬ?
 • ዕቁቡ እስኪወጣ እንዳያነሱህ፡፡
 • እንደዚያማ ካደረግኩ ከኃላፊነቴም ልነሳ እችላለሁ፡፡
 • ስማ በዚህ ዕቁብ ድርድር የለም፡፡
 • ይኸው መሀል ላይ ደርሰን አጉል አደረጉን፡፡
 • ሰውዬ በዚህ ዕቁብ ብዙ ነገር ነው ፕላን ያደረግኩት፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • ካልሆነ የሥራ ድርሻህን መቀየር ነዋ፡፡
 • ምን ልሁን?
 • ደላላ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ምሳ ለመብላት ቤት ሲገቡ ልጃቸውን አገኙት]

 • አንተ ትምህርት የለም እንዴ?
 • አለ ግን አልሄድኩም ዳዲ፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ምን ያደርግልኛል ብለህ ነው?
 • ምን ማለት ነው?
 • የተማሩት የት ደረሱ?
 • ምን?
 • ይህቺ አገር ለነጋዴ ነው የምታዋጣው፡፡
 • እልም ያለ ኪራይ ሰብሳቢ ሆነሃል ልበል?
 • ዳዲ ዝም ብዬ ቢዝነስ ብሠራ ነው የሚያዋጣኝ፡፡
 • ካልተማርክ እንዴት ቢዝነስ ትሠራለህ?
 • ዳዲ ደግሞ ጅል ነህ ልበል?
 • እንዴት?
 • ስንት ያልተማረ ኮንትራክተር ባለበት አገር ውስጥ ቢዝነስ ለመሥራት መማር አለብህ ትለኛለህ?
 • ጤነኛ አልመሰልከኝም አንተ ልጅ?
 • ባይሆን ቢዝነስ ለመጀመር አንድ ሐሳብ አለኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ይኸው ሰሞኑን ከባለሀብቶች ላይ እየተቀማ ለወጣቶች እየተሰጠ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
 • እሺ?
 • በቃ ለእኔም ከአንዱ ባለሀብት ላይ ቀማልኛ፡፡
 • ምን
 • ሕንፃ!