አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚንስተር

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ውስጥ ከአማካሪያቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • ምንድነው የምሰማው እባክህ?
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ ንገረኝ እንጂ?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • መሥሪያ ቤታችን በሚዲያ ስሙ እየተብጠለጠለ እኮ ነው፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አልክ?
 • እርስዎ ይኼ ለምን ያሳስብዎታል?
 • ለምድነው የማያሳስበኝ?
 • የአንድ ሰሞን ወሬ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰማህ አንተ?
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • በጀታቸውን በሕጉ መሠረት አይጠቀሙም ተባልን እኮ?
 • ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያላወራረዱት በርካታ ወጪ አለ ተብለናል እኮ?
 • እሱንም ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በሕጉ መሠረት ግዥ አይፈጽሙም ተባልን እኮ?
 • ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በዚያ ላይ በሚዲያ ሥራ ጣልቃ ይገባሉ ተብለናል፡፡
 • አዎን ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እናድርግ ታዲያ?
 • መክሰስ አለብን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማንን ነው የምንከሰው?
 • የዘገበብንን ሚዲያ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ ጭንቅላትህ አይሠራም ማለት ነው?
 • ስለሚሠራ እኮ ነው መፍትሔ ያቀረብኩት ጌታዬ?
 • ጭንቅላትህ ቢሠራ ኖሮ እንዲህ ያለ መፍትሔ አታመጣም ነበር፡፡
 • እሺ ምን ይሻላል ይላሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • በቶሎ ሌላ መፍትሔ ፈልግ፡፡
 • እንዲህ ብናደርግስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ብናደርግ?
 • ጋዜጣውን አስተባብል ብለን ወጥረን ብንይዘው?
 • እንዴት ተደርጎ እባክህ?
 • የተጻፈው በፍፁም ሐሰት ነው ብለን ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከዚያስ?
 • እያንዳንዱ የተጻፈውን እያስተባበልን በመጨረሻ ማስጠንቀቅ አለብን፡፡
 • ምን ብለን?
 • ይህንን ማስተባበያ የማታወጡ ከሆነ በሕግ እንጠይቃለን ብለን ነዋ፡፡
 • ፍርድ ቤት እንገናኝ ቢሉስ?
 • ይኼንን እንኳ የሚሉ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር?

[የንግሥት ዘውዲቱ ንግሥና ያደመቁት ሙዚቀኞች]

 • እንዴት እንዲህ አልክ?
 • የሚቀርብባቸው ክስ በወንጀል የሚያስጠይቅና የካሳ ክፍያ እንደሚኖርበት እናስጠነቅቃለና፡፡
 • የእነሱ መልስ የበለጠ ቢሆንስ?
 • እንዴት ሆኖ ክቡር ሚኒስትር?
 • በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ!
 • ከልብዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አይዞህ ተረጋጋ፡፡
 • እንዴት ልረጋጋ?
 • ሙያ በልብ ነው!
 • ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እናስበረግጋቸዋለን?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል!

 [አማካሪያቸው እንደወጣ ጸሐፊያቸው ገባች]

 • ምን ነበር?
 • ክቡር ሚኒስትር ጨንቆኛል፡፡
 • ምንድነው የጨነቀሽ?
 • የተዝረከረከ አሠራርን ማስተካከል ይሻላል ወይስ. . .
 • ምን አልሽ?
 • መሥሪያ ቤታችንን ማስተካከል ወይስ አምባጓሮ?
 • ለምን እንዲህ አልሽ?
 • አማካሪዎት ሲደነፋ ሰምቼው ነው፡፡
 • ምን አለ?
 • ‹‹ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል. . .›› ሲል ሰማሁት፡፡
 • አንቺስ ምን ትያለሽ?
 • እየተወራብን ያለው ጥሩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይሻሻል ታዲያ?
 • እኔ አተካራውን ትተን ራሳችንን እናስተካክል ነው የምለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አላሠራ ያሉንን ምን እናድርጋቸው እስከዚያ?
 • አዩ ክቡር ሚኒስትር. . .
 • እሺ?
 • ውጤታማ የሆኑት ድምፃቸውን አጥፍተው ይሠራሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ ውጤታማ አይደለንም ማለትሽ ነው?
 • ከውጤታችን ይልቅ አሉታዊ ጎናችን ብሷል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ምን አድርግ ነው የምትይኝ?
 • አሁንም ደግሜ ልናገር ችግራችንን አውቀን እንታረም፡፡
 • እኮ እንዴት አድርገን?
 • በግልጽ ስህተታችንን በማመን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ገባሽ አላደርገውም፡፡
 • ታዲያ ምን ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉንም እንደ አመጣጡ እመክተዋለሁ፡፡
 • ጥቅል ተሃድሶው ግን እንዲህ የሚል አይመስለኝም፡፡
 • ይኼ ጥልቅ ተሃድሶ ማስፈራሪያ ነው እንዴ?
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንሽ?
 • ኧረ ዝም ይበሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን?
 • ግምገማው ላይ እኮ ምን እንደተባሉ ያውቁት የለ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ እኮ. . .
 • እርስዎ ምን?
 • የሆዴን በሆዴ ይዤ ነው፡፡
 • በሆድዎ ምን ያዙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቂም ነዋ፡፡
 • የምን ቂም ክቡር ሚኒስትር?
 • ማንም እየተነሳ ባለቀሰ ቁጥር መሰደብ አለብን እንዴ?
 • ኧረ ይኼ ጉዳይ ልክ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ላፕቶፖቼ የት ነው ያሉት?
 • እዚያ መሳቢያ ውስጥ ናቸው ክቡር ሚኒስትር?
 • ቶሎ አምጪልኝ፡፡
 • የትኛውን ክቡር ሚኒስትር?
 • አነስ ያለችውን፡፡
 • ምን ያደርጉበታል ክቡር ሚኒስትር?
 • ፋይሉ ያለው እዚያ ውስጥ ነው፡፡
 • የቱ ፋይል ክቡር ሚኒስትር?
 • ግምገማ ያደረግንበት ጽሑፍ ነዋ፡፡
 • ጽሑፉን አሁን ምን ሊያደርጉት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደገና እገመግመዋለሁ፡፡
 • እርስዎ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንቺ ነሽ ታዲያ?

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቢሮ እንደወጡ አንደኛው ወጣት ሚኒስትር ቢሮ ሄዱ]

 • ክቡር ሚኒስትር ከየት ተገኙ?
 • አንድ ጉዳይ ላዋይህ መጥቼ ነው፡፡
 • ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የጥልቅ ተሃድሶውን ግምገማ ጽሑፍ አንብበኸዋል?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት አገኘኸው?
 • ከሠራንበት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
 • እንዴት ነው የምንሠራበት?
 • ባስቀመጠልን አቅጣጫ መሠረት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አልገባህ ያለኝ እኮ ይኼ ነው?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • የነበረንን ጥንካሬ የሚፈታተን ነው ጽሑፉ፡፡
 • ኧረ በተሻለ እንድሠራ ይረዳናል ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት አድርጎ?
 • መንግሥትና ሕዝብ እንዲቀራረቡና ችግሮች እንዲፈቱ ይረዳናል፡፡
 • ምን?
 • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝብና መንግሥት ድሮስ አንድ ላይ አይደሉም እንዴ?
 • ሕዝብና መንግሥት ተቀያይመው አይደል እንዴ ያ ሁሉ ችግር የደረሰው ክቡር ሚኒስትር?
 • በምን ምክንያት?
 • ሕዝብን የሚያማርሩ ችግሮች በመብዛታቸው ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
 • አይመስለኝም፡፡
 • እስቲ የእርስዎን ግምገማ ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንደኛ ጥንካሬያችንን አጥንተን በመልፈስፈሳችን . .
 • እንዴ?
 • ሁለተኛ ጠንካሮች ወጥተው ደካሞች በመብዛታቸው. . .
 • ሆሆ. . .
 • ሦስተኛ አጉል ዴሞክራት ለመሆን መፍጨርጨር ውስጥ በመገባቱ. . .
 • የባሰ አታምጣ?
 • ልጨምርልህ?
 • ምን ይሆን ክቡር ሚኒስትር?
 • አፍሪካ ውስጥ መሆናችንን በመዘንጋት. . .
 • ምን ማለት ነው እሱ ደግሞ?
 • ዴሞክራሲ ቀስ እያለ የሚመጣ እንጂ እንደ በረዶ ድንገት ዱብ ዱብ አይልም ማለት ነው፡፡
 • እርስዎ እንዲህ ነው የሚያስቡት ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎን ወጣቱ ሚኒስትር፡፡
 • እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ይዘንማ አብረን መዝለቅ አንችልም ክቡርነትዎ?
 • ጥርግ በሉ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ደርሰው ከባለቤታቸው ጋር እራት እየተመገቡ ነው]

 • ምነው የተቆጣህ ትመስላለህ?
 • በምን አወቅሽ?
 • ፊትህን ጥለኸዋል እኮ?
 • ይኼንን ያህል?
 • ምግቡን መዋጥ አቅቶህ እያየሁ?
 • ምን እባክሽ?
 • ምን ሆንክ?
 • ግማሹ በጋዜጣ ይከተክተኛል. . .
 • እ?
 • ሌላው በስመ ግምገማ ያንገበግበኛል. . .
 • አንተም እኮ አበዛኸው፡፡
 • እንዴት እባክሽ?
 • መሥሪያ ቤቱን መምራት ያቃተህ ትመስላለህ፡፡
 • እኔ?
 • አዎን አንተ!
 • እንዴት ሆኖ?
 • የተጻፈውን ሳነብ ችግሩ በሚገባ  ይታያል፡፡
 • ምን ታየሽ?
 • አንደኛ አንተን ጨምሮ ብቁ አመራሮች የሉም፡፡
 • ምን?
 • ሁለተኛ ሥራና ሠራተኛ አልተገናኙም፡፡
 • ሌላስ እባክሽ?
 • የሒሳብ መዝገቦቻችሁ ያስቃሉ ብቻ ሳይሆን ያሳፍራሉ፡፡
 • አንቺ አብደሻል ወይ?
 • ለምንድነው የማብደው?
 • የጋዜጣ ዘገባ ላይ ባየሽው እንዲህ ትፈርጃለሽ?
 • አምና ምን ተባላችሁ?
 • ማን ምን አለን?
 • ኦዲተር ጄኔራል ነዋ፡፡
 • ምን አለን?
 • የፋይናንስ አያያዛችሁና የግዢ ሥርዓታችን ብልሹ ነው አላለም?
 • እና?
 • ዘንድሮም በዚያው ባለበት መቀጠሉን እኮ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ለምን አልነገርሽኝም?
 • አንተ የገንዘብ ነገር ሲነሳብህ ያሳብድህ የለ?
 • ምን?
 • ይህንን ጉዳይ ሳነሳብህ እኮ ልታንቀኝ ነበር፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • አሁን የሚሻልህ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የበላይ አለቃህን መለማመጥ፡፡
 • ምን ለመሆን?
 • በሰላም በጡረታ ለመሸኘት፡፡
 • እኔ ጡረታ ልወጣ?
 • አትቸኩል ክቡርነትህ፡፡
 • ጡረታ ወጥቼ ምን ልሆንልሽ?
 • እሱም ከተገኘ ዕድል ነው፡፡
 • እሺ ዕድል ቀንታኝ ጡረታ ወጣሁ. . .
 • ከጡረታው ጋር ቀስ ብለህ ሌላ ውለታ ትጠይቃለህ?
 • የምን ውለታ?
 • ውጭ አገር የሚወስድህ ውለታ፡፡
 • ምን ለመሆን ነው ውጭ አገር የምሄደው?
 • ኧረ ተረጋጋ ሰውዬ፡፡
 • ከዚያስ እባክሽ?
 • ዕድል ቀንታህ ውጭ የምትሄደው እኮ. . .
 • እኔ ውጭ አገር ሄጄ ቤንዚን ቀጂነት ወይም ፓርኪንግ እንድሠራ ፈለግሽ?
 • ሰውዬ እንደምንም ብለህ አለቃሀን አሳምን እንጂ ቤንዚን ቀጂ አትሆንም አንተ፡፡
 • እሺ እንዴት ነው አለቃዬን የማሳምነው?
 • ተለማምጠህ ነዋ ጌታው፡፡
 • ምን ለመሆን ነው የምለማመጠው?
 • አንደኛ ከተጠያቂነት ለመዳን፡፡
 • ምን?
 • ሁለተኛው ደግሞ. . .
 • ንገሪኝ?
 • ኧረ ተረጋጋ እባክህ?
 • ከተጠያቂነት ድኜ ውጭ ብሄድ ምን አገኛለሁ?
 • አየህ አሁን ማሰብ እየጀመርክ ነው፡፡
 • እባክሽ ፍቅሬ ልቤ ተንጠለጠለ እኮ?
 • ዕድለኛ ሆነህ አለቃህ ከፈቀዱልህ. . .
 • ምን እሆናለሁ?
 • አምባሳደር!
 • ብራቮ የእኔ ውድ!