አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚንስተር

 

[የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ከውጭ አገር ደወለላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • እንዴት ነህ ባክህ?
 • ሰላም ነኝ ጋሼ፡፡
 • አንተ በቃ ሸፍተህ ቀረህ አይደል?
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው ጋሼ?
 • ወደ ኢትዮጵያ እገባለሁ ስትል አልነበር እንዴ?
 • እኔማ ፎር ጉድ እመጣለሁ ብዬ ነበር፡፡
 • እና ምን ተገኘ?
 • አሁንማ ነገሮች እንኳን አልመጣሁ እያስባሉኝ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ወይ ጉድ ብዬ ነበራ የምመለሰው፡፡
 • እኮ ለምን?
 • እኔ እኮ ባለፈው ኢንዱስትሪ ለመገንባት ሁላ አስቤ ነበር፡፡
 • እና ምን ተገኘ?
 • እንዴ ጋሼ? ያ ሁላ ፋብሪካ ሲቃጠል ሳይ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፡፡
 • እንኳን ተቃጠለ ብለህ ነው ያመሰገንከው?
 • ኧረ እንኳን እኔ አልከፈትኩ ብዬ ነው እንጂ፡፡
 • አሁን እኮ አገሪቷ ተረጋግታለች፡፡
 • ተረጋግታለች ስትለኝ?
 • ይኸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ ሁሉ ነገር በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
 • ጋሼ ምንም የሚስብ ነገር ግን አላየሁም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው የባንክ ሼሬን በግድ ልታሸጡኝ አይደል እንዴ?
 • ለምንድን ነው የምትሸጠው?
 • ኢትዮጵያዊ አይደለህም ተብዬ ነዋ፡፡
 • ኢትዮጵያዊ አይደለህም እንዴ አንተ?
 • በልቤማ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
 • በምንድን ነው ኢትዮጵያዊ ያልሆንከው ታዲያ?
 • በወረቀት፡፡
 • ፓስፖርት ቀየርክ እንዴ?
 • ሰሞኑን ፕሮሰሴ አልቆ ፓስፖርት ሰጡኝ፡፡
 • እንኳን ደስ አለህ፡፡
 • ፓስፖርት ሳገኝ ግን ሼሬን ልቀማ ነው፡፡
 • ለምንድን ነው የምትቀማው?
 • መንግሥት ሊሸጠው ነው፡፡
 • እና ምን ይሻላል?
 • ጋሼ እሱን ላማክርህ ነው የደወልኩት፡፡
 • ምን ማድረግ ይቻላል?
 • ለእኔማ የእኛው ቤተሰብ ቢወስደው ነው የሚሻለው፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • በውርስ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ብሔራዊ ባንክ ደወሉ]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • የባንክ ሼር እንዲሸጥ አዛችኋል እንዴ?
 • የምን የባንክ ሼር?
 • የዳያስፖራዎችን ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የውጭ አገር ዜግነት ያለው ሰው እኮ የባንክ ሼር መግዛት አይችልም፡፡
 • ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም?
 • ወንጀል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እና ልትሸጡባቸው ነው?
 • ሊወረስ የሚገባው ሼር ነበር ስልዎት?
 • ማን ነው የሚወርሰው?
 • መንግሥት ነዋ፡፡
 • እንዲያውም ሐሳብ መጣልኝ፡፡
 • ምን ዓይነት?
 • ሚኒስትር እንደመሆኔ መጠን…
 • እ…
 • ለዘመዴ መሆን እችላለሁ፡፡
 • ምን?
 • ወራሽ!

[አገር ውስጥ ያለ የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • አንተ እንዴት ነህ?
 • አለሁ ጋሼ፣ አንተ ግን ጠፍተሃል፡፡
 • ምን ይኼ ሹመት ከዘመድ ጋር አቆራረጠኝ፡፡
 • ሹመትማ ያቀራርባል እንጂ አያቆራርጥም፡፡
 • እንዴት?
 • ስትሾም ያው ዘመዶችህን መጥቀምህ ስለማይቀር ትቀራረባለሃ፡፡
 • ብለህ ነው?
 • እንዴታ ጋሼ?
 • ምን እያደረክ ነው?
 • ይኸው ጋሼ ሥራ ፍለጋ እየተንከራተትኩ ነው፡፡
 • እንዴ ባለፈው ክረምት አይደል እንዴ የተመረቅከው?
 • ሥራዬን አቁሜ ትምህርቴን የቀጠልኩት የተሻለ ሥራ አገኛለሁ ብዬ ነበር፡፡
 • ምንድን ነበር የተማርከው?
 • ኢንጂነሪንግ፡፡
 • ታዲያ በኢንጂነሪንግ ነው ሥራ ያጣኸው?
 • ጋሼ በፊት በልምድ ስሠራ ብዙ ገንዘብ አገኝ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • ይኸው ራሴን ላሻሽል ብዬ ዲግሪ ብይዝም ሥራ ከየት ላምጣ?
 • ምን ትቀልዳለህ? ኢንጂነር ሆነህ ሥራ የለህም?
 • ይኸው መንግሥት የ70/30 ፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ ጉድ ሆንና፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው 70 በመቶ የሳይንስ ተማሪ ይሁን ሲባል፣ ሥራውም በዚያን ያህል ይበዛል ብዬ አስቤ ነበር፡፡
 • ለሳይንስ ተማሪ ሥራ የለም እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር 70 በመቶው ደላላ፣ 30 በመቶው ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • አንድ የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ ከ500 ሰው በላይ ነው የሚያመለክተው፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • እና ጋሼ እንድትረዳኝ ፈልጌ ነው፡፡
 • እኔ ምን ልርዳህ? ሕንፃዬ ገና አልተጀመረም፡፡
 • እስኪጀመር አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • አሁን የወጣቶች ፈንድ የሚባለው ሊጀመር ነው፡፡
 • የ10 ቢሊዮን ብር ፈንዱን ነው የምትለኝ?
 • አዎን ጋሼ፣ ከእሱ ፈንድ ተጠቃሚ ብሆንስ?
 • እየቀለድክ ነው?
 • ኧረ የምሬን ነው፡፡
 • ዕድሜህ እኮ ሃምሳዎቹ ውስጥ መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
 • ቢሆንም ጋሼ ወጣትነቴን የጨረስኩት ለዚህ ሥርዓት ስታገል ነው፡፡
 • እና ምን እያልከኝ ነው?
 • ልጦር ይገባኛል፡፡
 • በምን?
 • በወጣቶች ፈንድ!

[አንድ የተቃዋሚ መሪ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ነኝ፡፡
 • እንዴት ነህ ባክህ?
 • እናንተ እያላችሁ ምን ደኅንነት አለ?
 • አትማረር እንጂ?
 • ለምን አልማረር?
 • ሁሉን ነገር ለመቅረፍ ቆርጠን ተነስተናል፡፡
 • እኛ ደግሞ በእናንተ ተስፋ ከቆረጥን ሰነባበትን፡፡
 • ለምን?
 • ሁሌም ሊፕ ሰርቪስ ነው የምትሰጡት፡፡
 • ኧረ እኛ የፐብሊክ ሰርቪስ ነው ያለን፡፡
 • እኔ የምልዎት ሁሌ ወሬ ብቻ ነው የምታውቁት፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው ሙስናው ተባብሷል፡፡
 • እ…
 • የሰብዓዊ መብት ረገጣውም እንደቀጠለ ነው፡፡
 • ምን ሆናችሁ?
 • አባሎቻችን እስካሁን ዘብጥያ እንደወረዱ ነው፡፡
 • ዘብጥያ ያወረድናቸው እኮ በእናንተው ጥያቄ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ከሥልጣን አልወርድ ሲሏችሁ እኮ ነው ዘብጥያ ያወረድንላችሁ፡፡
 • እናንተም ዘብጥያ ካልወረዳችሁ ሥልጣን አትለቁም ማለት ነው?
 • የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች አሉ፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መጀመሪያ ውስጣችሁን ፈትሹ፡፡
 • እናንተ እያላችሁ ራሳችንን መፈተሽ አንችልም፡፡
 • ለምን?
 • የፖለቲካ ምኅዳሩን አጥብባችሁታላ፡፡
 • ምኅዳሩንማ ልናሰፋው ነው፡፡
 • በምንድን ነው የምታሰፉት?
 • በድርድር ነዋ፡፡
 • የፖለቲካ ምኅዳሩ በድርድር አይሰፋም፡፡
 • ታዲያ በምንድን ነው የሚሰፋው?
 • በሥልጣን መጋራት!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንዱ የተቃዋሚ መሪ ደውሎልኝ ነበር፡፡
 • ምን አለዎት ታዲያ?
 • ሥልጣን አጋሩን፡፡
 • ምን?
 • አይገርምህም?
 • አይደለም ሥልጣን ሐሳባችንን አናጋራቸውም፡፡
 • እንዴት?
 • እኛ መጨነቅ ያለብን ለሌሎች ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማን ነው መጨነቅ ያለብን?
 • በመጀመሪያ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለተጠመቁ፡፡
 • እ…
 • ሲቀጥል ለልማታዊ አጋሮቻችን፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • ቆይ ላስረዳዎት፡፡
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቁት ማለት መጽሐፍ ቅዱስን አምነውና የሕይወት መርሐቸው አድርገው በክርስትና እንደተጠመቁት ማለት ነው፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • በቃ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጠምቀው፣ አዲስ ራዕይን እንደ ሕይወት መርሐቸው የተቀበሉትን ማለቴ ነው፡፡
 • እና እነዚህ ሰዎች በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በኩል ሲያልፉ ያማትባሉ ማለት ነው?
 • በቃ ሐሳቡን በደንብ አግኝተውታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ልማታዊ አጋሮቻችን ያልካቸውስ?
 • እነሱ ማለት በክርስትናው ታማኝ ምዕመናን እንደሚባሉት ማለት ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • እነዚህ አሥራቶቻቸውን በሚገባ የሚከፍሉ ማለት ናቸው፡፡
 • አሃ በቃ እነዚህም ግብራቸውን በአግባቡ እየከፈሉ መንግሥትን የሚረዱትን ማለት ነው?
 • በሚገባ ገብቶዎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እኮ ሥልጣን አጋሩን ሲለኝ ደንግጬ ነው፡፡
 • እነሱማ ቢችሉ የባንክ አካውንቶቻችሁንም እንጋራ ማለታቸው አይቀርም፡፡
 • እኔም እኮ እሱ ነበር ያስፈራኝ፡፡
 • አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • ተቃዋሚ ቢንጫጫ…
 • እ…
 • በአንድ ሙቀጫ!