አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ዓለምን ሥጋት ላይ የጣለው የሳይበር ጥቃት

ራንሰምዌር የተባለው የሳይበር ጥቃት ሰሞነኛው የዓለም ሥጋት ሆኗል፡፡ በኢንተርኔት ግንኙነት የሚኖሩ የመረጃ ልውውጦችን፣ የተቋማትና የግለሰቦችን መረጃ ማገትና ክፍያ መጠየቅ፣ መረጃዎችን ማደበላለቅና ያልሆነውን ማድረግ ለዘመነ ቴክኖሎጂ አዲስ ባይሆንም፣ ዓለም ሰሞኑን እንደገጠማት ዓይነት የሳይበር ጥቃት አላስተናገደችም፡፡ ተመራማሪዎች የሰሜን ኮሪያ እጅ አለበት ብለው በጠረጠሩት የሳይበር ጥቃት ከ150 በላይ አገሮች ሲጠቁ ከ300 ሺሕ በላይ የሚበልጡ ግለሰቦችም የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የሕግ ማስፈጸም ትብብር ኤጀንሲ (ዩሮፖል) ባለፈው እሑድ እንዳስታወቀው፣ የኮምፒዩተር ግንኙነትን በቆለፈውና ለመክፈትም 300 ዶላር በሚጠይቀው የራንሰምዌር ሳይበር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ባለፈው ዓርብ የመጀመሪያው ጥቃት ሲሰነዘር ብዙ የግንኙነት መረቦችና የግለሰብ ኮምፒዩተሮች ክፍት ስለነበሩና ጥቃቱ ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ዳግም ሲሰነዘርም ስላገኛቸው፣ ቁጥሩ የበዛ የመረጃ ግንኙነት መረብ ተጠቃሚ የችግሩ ሰለባ ሊሆን ይችላልም ብሏል፡፡

የሳይበር ጥቃቱ ከየት እንደተፈጸመ፣ መጀመሪያ የጥቃቱ ሰለባ የሆነውም ማን እንደሆነ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓርብ የተሰነዘረው የሳይበር ጥቃት መጀመሪያ የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ላይ ተፈጽሟል፡፡ በመቀጠልም ጀርመን፣ ስፔን፣ ቻይና ሩሲያና ህንድ የሚገኙ የመረጃ መረቦችን እንደጎዳ ዩሮፖል አስፍሯል፡፡

የሳይበር ጥቃቶቹ ሲፈጸሙ አንድም የአገሮችንና የንግድ ተቋማትን የመረጃ መረብ ግንኙነት ለማገት ሲሆን፣ በሌላ በኩል የመረጃ መረቡን በማገት ማስለቀቂያ ገንዘብ ለመጠየቅ ነው፡፡ የሳይበር ጥቃት ሰለባዎች ማስለቀቂያ ገንዘብ በመክፈል መልሰው የኮምፒዩተር ግንኙነታቸውን የሚያገኙበት ዕድል ቢኖርም፣ የመረጃ መረብ ጠላፊዎችን (Hackers) ላለማበረታት ሲሉ የተጠየቁትን ገንዘብ ከመክፈል ተቆጥበው ብዙ ገንዘብ በማውጣት ራሳቸውን እንደገና የሚያደራጁ አገሮች፣ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች አሉ፡፡

ሰሞኑን ለዓለም የመረጃ መረብ ደኅንነት ሠራተኞች ጭምር ፈተና የሆነውን የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ምክንያቱ አሁንም ድረስ ግልጽ አይደለም፡፡ ብዙውን ጊዜ ‹‹ራንሰምዌር›› የሳይበር ጥቃት የመረጃ መረብ ግንኙነትንና በየኮምፒዩተሩ ያሉ መረጃዎችን በማገድና ገንዘብ አስከፍሎ በመልቀቅ እንደ ገቢ ምንጭ ታስቦ ቢሆንም፣ ሰሞኑን የተጠየቀው የማስለቀቂያ ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ዘገባዎች አስፍረዋል፡፡ ዩሮፖል እንደሚለው፣ ጥቂት ኩባንያዎችና ግለሰቦች ኮምፒዩተሮቻቸውን ለማስከፈት 300 ዶላር ወይም ከዚህ በላይ ለመክፈል ወስነዋል፡፡ የሕግ አፍጻሚ አካላትም ይህንን እየመከሩ ነው፡፡

ከ300 ሺሕ በላይ ኮምፒዩተሮችን የቆለፉት የመረጃ መረብ ጠላፊዎች፣ የቆለፏቸውን ኮምፒውተሮች ለመክፈት ከየግለሰቦችም ሆነ ከተቋማት የጠየቁትን ገንዘብ ካላገኙ በዓለም የሚገኙ ኮምፒዩተሮችን ከአገልግሎት ውጪ እንደሚያደርጉ መግለጻቸው በዓለም ዙሪያ ለተሠራጩ ኩባንያዎች ሥጋት ሆኗል፡፡

ዓለም ኋላ ቀሩን ትቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተሳሰረበት፣ ትምህርቱ፣ ሕክምናው፣ ኢንጂነሪንጉ፣ የህዋ ምርምሩ፣ ትልልቅ ኢንዱስትሪው፣ ግብርናውና የደኅንነት ሥራው ሁሉ በኮምፒዩተር የኢንተርኔት ግንኙነት በመጠቀበት በአሁኑ ጊዜ የሳይበር ጥቃት እየገዘፈ መምጣቱ፣ እየተሳሰረ የመጣውን የአገሮች ግንኙነት የሚያሽመደምድ ነው ተብሏል፡፡ መረጃን የሚያዛባና ተጠቃሚውን የሚያወናብድም መሆኑ እንዲሁ፡፡

የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት በጥቃቱ ሲመታ፣ መጠነ ሰፊ የመረጃና የሕክምና ቅደም ተከል መዛባትን በእንግሊዝና በስኮትላንድ በሚገኙ ሆስፒታሎች ላይ አስከትሏል፡፡ በዚህም የጤና አገልግሎቱን ከሚሰጡ 248 ተቋማት 48 የተጠቁ ሲሆን፣ በማግሥቱ ደግሞ ከስድስቱ በስተቀር ቀሪዎቹ ወደ መደበኛ መረጃ መረብ ልውውጣቸው ተመልሰዋል፡፡

እንግሊዝ የጤና ተቋማቱን ወደ መደበኛ የኮምፒዩተር ግንኙነት ለመመለስ ለጠላፊዎቹ ገንዘብ ከፍላ ይሆናል የሚል አስተያየት የተሰነዘረ ቢሆንም፣ አገሪቱ ገንዝብ እንዳልከፈለችና ገንዘብ የሚከፍሉ ካሉም እንደምትቃወም የአገር ውስጥ ደኅንነት አምበር ሩድ ተናግረዋል፡፡

የጀርመን ብሔራዊ የባቡር አገልግሎት በቪዲዮ ቁጥጥር የሚያደርግበት ቴክኖሎጂም የሳይበር ጥቃቱ ሰለባ ሆኗል፡፡ በአውሮፓ የስፔኑ ቴሌኮም አገልግሎት ‹‹ቴሌፎኒካ››፣ የፈረንሣዩ መኪና አምራች ሬኖ፣ በስዊድን የመንግሥት ተቋማት በኮምፒዩተሮቻቸው ላይ የጠላፊዎች ጥቃት መሰንዘሩን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

ከወር በፊት የአሜሪካው ብሔራዊ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መግልጹን ተከትሎ፣ ማይክሮሶፍት ኮምፒዩተሮችን ለመታደግ የሚያስችል አፕዴት ልኮ ነበር፡፡ ሆኖም ለቁጥር የሚያታክቱ ኮምፒዩተሮች ጊዜ ያለፈባቸው ሶፍትዌር በመጠቀማቸው ወይም ማይክሮሶፍት የላከውን ‹አፕዴት› የኮምፒዩተር ሲስተማቸው መቀበል ባለመቻሉ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡

የደኅንነት አካላት ነን የሚሉትንም የተጋፋጠው ባለጋራ እ.ኤ.አ. 2016 ብቻ ኩባንያዎችና ሌሎች ተቋማት የሳይበር ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ 73 ቢሊዮን ዶላር እንዲያወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም በዓለም ያሉ የኮምፒዩተር ግንኙነት ሥርዓቶች አሁንም በተጠቃሚዎች ቸልተኝነትና ስህተት ለጥቃት እየተጋለጡ ነው፡፡ ኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች ሶፍትዌሮችን በየጊዜው ‹አፕዴት› አለማድረግ፣ በኢሜይል የሚላኩ አላስፈላጊ አባሪዎችን (Attachements) በመክፈት ኮምፒዩተሮችን ለሚያበላሹ ቫይረሶች ይጋለጣሉ፡፡

የቡልጋርድ ሳይበር ሴኪዩሪቲ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ፓል ሊፕማን፣ ‹‹የሳይበር ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ቀድመን መቆጣጠር የምንችለው ነው፤›› በማለት ድርጅቶችና ግለሰቦች ኮምፒዩተሮቻቸውን ‹አፕዴት› አለማድረጋቸውን፣ አንቲቫይረስ አለመጫናቸውንና የማያስፈልጋቸውን የኢሜይል መልዕክት መክፈታቸውን ኮንነዋል፡፡ ይህም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ምክንያት መሆኑን አክለዋል፡፡

በ150 አገሮች የሚገኙ 300 ሺሕ ኮምፒዩተሮች ባለፉት ጥቂት ቀናት በተሰነዘሩ የኮምፒውተር ጥቃቶች የተጎዱ ሲሆን፣ ቁጥሩ እያሻቀበ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ሰሞኑን ዓለምን ያናጋውና የመረጃ ደኅንነት ሠራተኞችን ያስበረገገው የሳይበር ጥቃት ‹ዋናክራይ› በተባለ ‹የማልዌር› ፕሮግራም በኢሜይል የሚመጣ ሲሆን፣ ኮምፒዩተሮችንም በአገልግሎት ላይ እያሉ የሚቆልፍና ኮምፒዩተሩ የያዘውን ሁሉንም መረጃ እንደሚያጠፋ መልዕክት የሚያስቀምጥና ይህ እንዳይሆን የሚጠይቀው ገንዘብ በሙሉ እንዲከፈል የሚያዝ ነው፡፡

በአውሮፓ፣ በእስያና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የንግድ ተቋማትንና የቤቶችን የኮምፒዩተር አጠቃቀም ሥርዓት በቆለፈው ቫይረስ የአሜሪካ ፌዴራል ሥርዓት እንዳልተጠቃ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ እስያ በጥቃቱ ክፉኛ የተመታች ሲሆን፣ ከ40 ሺሕ በላይ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት የማልዌሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ጥቃቱ ባለፈው ዓርብ ሲፈጸም የጥቃቱ ቀዳሚ ሰለባ የሆኑት የማይክሮሶፍት ዊንዶው የቀድሞ ምርቶች የሆኑና አፕዴት ያልተደረጉ ኮምፒዩተሮች ናቸው፡፡ በዕለቱም ማይክሮሶፍት ተጨማሪ የደኅንነት ማስጠበቂያ ፕሮግራሞችንና መመርያዎችን ለግለሰቦችና ለንግድ ተቋማት የለቀቀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም ቫይረሱ እንደማይስፋፋ አስታውቋል፡፡ ለዚህም የ22 ዓመቱ የእንግሊዝ ሳይበር ደኅንነት ተመራማሪ ይዞ የመጣው አዲስ መላ እንደሚያገለግል በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰፍሯል፡፡

የኢትዮጵያ የኮምፒዩተርና የመረጃ መረብ ግንኙነት ተጠቃሚነት አናሳ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶችንና ወረዳዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ተቋማትም የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ አገሪቱ እየገባችበት ያለው ይህ ቴክኖሎጂ የሳይበር ጥቃት ሰለባ እንዳይሆን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች በመረጃ መረብ የተገናኙ ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በግለሰቦች ላይ የሳይበር ጥቃት እየተፈጸመ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡