ዓደዋ በመቶ ሃያ አንደኛ ዓመቱ ሲታወስ

    በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአንድ በኩል በአውሮፓውያን የግዛት መስፋፋት፣ በአፍሪቃውያን ደግሞ የእነሱ ቅኝ ተገዥ የመሆን ምኞት ዘመንም ነበር፡፡ ይኸው ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እንደነበረም ይታወቃል፡፡ የኢንዱስትሪው አብዮት ደግሞ አውሮፓውያን ጥሬ ዕቃ እንዲፈልጉና በአነስተኛ የጉልበት ዋጋ ከፍተኛ ምርት እንዲያመርቱ፣ እንዲሁም ገበያ እንዲፈልጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ መካከለኛው ምሥራቅና ሩቅ ምሥራቅ አስፈላጊ ቅኝ ግዛቶች መሆናቸው አስተማማኝ ቢሆንም፣ አፍሪካ ግን ያኔ ጨለማው ዓለም ተብላ ትታወቅ ስለነበር እምብዛም ትኩረት አልተሰጣትም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የአፍሪካንና የተቀረውን ዓለም የንግድ ግንኙነት በአብዛኛው በባሪያ ንግድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ባሪያዎችም ከማዕከላዊ አገሮች ወደ ድንበር እየተገፋፉና እየተገፈተሩ ይመጡላቸው ስለነበር ወደ ውስጥ ዘልቀው መግባት እምብዛም አላስፈለጋቸውም፡፡ ከዚያም አውሮፓውያን የባሪያ ንግድን በሕግ ስለከለከሉ በዚህ ረገድ የነበረው ግንኙነት ደረጃ በደረጃ እየተቋረጠ ሄደ፡፡

ይሁንና ከአፍሪካውያን ባሪያዎች አንዳንድ መሠረታዊ ቁም ነገሮችን በመረዳትም ይሁን የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ወይም የቅኝ ግዛት ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግና ገበያ ለማግኘት ሲሉ ‹‹አሳሾቻቸውን›› መላክ ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ጁሴፔ ሳፔቶ የተባሉትን ኢጣሊያዊ ሚሽነሪ ወደ አሰብ የላካቸው ሩባቲኒ የተባለ የንግድ ኩባንያ ነበር፡፡ እንደ አባ ሰላማ ያሉትም ቢሆኑ የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በሚል ምክንያት ከአገራቸው ይነሱ እንጂ፣ የአፄ ምኒልክ የፖለቲካ አማካሪ የመሆን ዕድል ገጥሟቸው ነበር፡፡ ከአፄ ምኒልክ ዘመን መንግሥት በፊትም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን መድፍ የሠሩት የሃይማኖት አባቶች የተባሉት ጭምር እንደነበሩ ይታወቃሉ፡፡ ይኸው ሰርጎ የመግቢያ ዘዴ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሠርቶበታል፡፡

የስዊዝ ካናል መከፈት የቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በእጅጉ ከፍ አደረገው፡፡ የቀይ ባሕር ጠቃሚነትም በአካባቢው የሚገኙ አገሮች የባሕር ዳርቻዎችን አስፈላጊነት አጎላው፡፡ የባሕር ለባሕር ጉዞው ከኢኮኖሚ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ስለነበርም ከሰሜን ቁልቁል እስከ ደቡብ አፍሪካ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ ፈረንሣይ በባቡር ሐዲድ ለማገናኘት ትልቅ ፍላጎት አሳደረባቸው፡፡ ይኼም ሆኖ በፈረንሣይና በእንግሊዝ መካከል የጥቅም ግጭት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ ከደቡብ ወደ ሰሜን ወይም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አቋርጦ ለማለፍ ያኔ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሱዳንን መጠቀም አስፈላጊ ሆነ፡፡ ፈረንሣይ በሱዳን በኩል አቋርጣ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ለመድረስ የብሪታንያን ይሁንታ ማግኘት ነበረባት፡፡ ከዚህም ሌላ ጂቡቲ በፈረንሣይ ብትያዝም ኢትዮጵያ ነፃ አገር ስለነበረች ይህች ነፃ አገር አንድም በእንግሊዝ ካለበለዚያም እንግሊዝ በምትፈልጋት አገር ካልተያዘች ሁኔታው አመቺ አልነበረም፡፡ ይኼም በበኩሉ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳይወዱ በግድ ውስብስብ እንዲሆን አደረገው፡፡ እንዲሁም ናይልን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን መቆጣጠር ያስፈልግ ነበርና የኢትዮጵያ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ በአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሥር መዋል የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜም በወቅቱ ገናና የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ ከፈረንሣይ ይልቅ ደካማዋ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ብትይዝ ለኋለኛው ዕቅዷ አስቸጋሪ ስለማይሆን የቅኝ ግዛት ይሁንታን ለወዳጅዋ ሰጠች፡፡

 

የኢጣሊያውያን  ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ኢጣሊያ በእንግሊዝ ድጋፍ ምፅዋን መያዝ

ጁሰፔ ሳፔቶ እ.ኤ.አ. ከ1811 እስከ 1895 የኖረ ኢጣሊያናዊ የላዛሪስት ሚሽን ተከታይ ሲሆን፣ ይህም የላዛሪስት ሚሽን የተባለ ድርጅት ድሆችን በመርዳት ስም ፓሪስ እ.ኤ.አ. በ1625 ውስጥ ሴንት ቪንቸንት ፖል በተባለ የሃይማኖት አባት የተቋቋመ ነበር፡፡ ጁሰፔ ሳፔቶ የላዛሪስት ሚሽን ተከታይ የሆነው በ18 ዓመቱ ሲሆን፣ ወደ ምፅዋ ከመምጣቱ በፊትም በ1837 ወደ ሊባኖስና ግብፅ ሄዶ እንደነበር የሕይወት ታሪኩን የጻፉ ሰዎች በማስታወሻቸው ውስጥ አስፍረዋል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ ለድሆች ዕርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ይባል እንጅ ያቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት እንደነበር ይነገራል፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች ወደዚህ ሥፍራ የመጣው ከሁለት ፈረንሣውያን ወንድማማቾች ጋር እንደሆነና ከእነርሱ ጋር እ.ኤ.አ. ከ1837 እስከ 1847 ባለው ጊዜ ወደ መሀል ኢትዮጵያ በመግባት በዓደዋና በጎንደር ጉብኝት እንዳደረገ ጽፈዋል፡፡ ስለሆነም ጁሰፔ ሳፔቶም ፍራንቺስካ ጆቫኒ ከተባለ ሌላ ሚሽነሪ ጋር በምፅዋ በኩል ወደ ከረን እ.ኤ.አ. ኦገስት 23 ቀን 1851 መጣ፡፡ በእነዚህ ጸሐፊዎች መረጃ መሠረት የላዛሪስት ሚሽን ተልዕኮውን ለመፈጸም የመጣው በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጉዞው በፀና ታሞ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ በሁለተኛ ጊዜ ጉብኝቱም እንደ ሚሽነሪ ሳይሆን እንደ ጎብኚ ወደ ምፅዋ በመምጣት ደናኪል (የአፋር) ጨዋማ ሥፍራዎችን፣ ቦጎስንና ሓባብን እ.ኤ.አ. በ1851 ጎበኘ፡፡ በዚህም ጊዜ ግዕዝ፣ ትግርኛና ቢለን ቋንቋዎችን በማጥናት መዝገበ ቃላት አዘጋጀ፡፡ ከዚያም ወደ አሰብ መጣ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1858 አፄ ቴዎድሮስ በመንግሥታቸው ላይ ያመፀውን የአገው ንጉሥ ድል አድርገው በገደሉበት ጁሰፔ ሳፔቶን እስረኛ አድርገው እንደ አስተርጓሚ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሆኖም አፄ ቴዎድሮስ ከጊዜ በኋላ ነፃ አድርገው ስለለቀቁት ወደ ፓሪስ ተመለሰና በፓሪስ የቤተ መዘክር ሠራተኛ ሆነ፡፡ ስዊዝ ካናል እ.ኤ.አ. በ1869 ሲከፈትም የኢጣሊያ መንግሥት በቀይ ባህር ዳርቻ እንደ ወደብ የሚጠቀሙበትን ቦታ እንዲያስገኝ አደራ ተሰጠው፡፡ ወደ አሰብ ከመጣ በኋላም የተሰጠውን አደራ ሳያሳውቅ ከአፋር ሡልጣኖች ጋር ወዳጅ መስሎ በመቅረብ ከአሰብ የተወሰነውን መሬት በአፋር ግዛት በሚኖርበት ጊዜ ሊጠቀምበት ውል መሠረት ገዛ፡፡

ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ኃላፊነቱን ከተወጣ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ተመለሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ከሚያውቁት ሰዎች ጋር እምብዛም አይገናኝም ነበር፡፡ ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ወደ ኢጣሊያ ከተመለሰ በኋላ በአራተኛው ዓለም አቀፍ ኦሪየንታሊስቶች ጉባዔ በ1878 ተካፋይ ነበረ፡፡ በዚህ ጊዜም የተለያዩ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርቧል፡፡ ከጁሴፔ ሳፔቶ በፊት የምናገኘው የሃይማኖት ሰው ጉግልየሞ ማሳይ፣ በተለምዶ አባ ማስያስ (እ.ኤ.አ. 1809-1889) የምንለው ቄስ ሲሆን፣ ይኼም ሰው ኢጣሊያ ቦቫ በምትባል ሥፍራ የተወለደ ነው፡፡ በአገራዊ አባባል አባ ማስያስ የተባለው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ውስጥ ለ25 ዓመታት ኖሯል፡፡ አባ ማስያስ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ጉግልየሞ ስም ሲሆን፣ ከጁሴፔ ከተባለ ሌላ ፈረንሣዊ ጋር በመሆን ወደ ሮም ሄዶ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በ1846 ዓ.ም. ኦሮሞዎችን ክርስቲያን ለማድረግ በሚል ሰበብ ‹‹የኦሮሞ ቄስ›› ተብሎ እንደገና መጣ፡፡ ድሮውንም አባ ማስያስ እየተባለ የነበረው ኢጣሊያዊ አቡነ ባርቶኔሊ በሚል ስም ወደ ጎጃም ተልኮ እንደነበር እርሱን በሚመለከት የተጻፉ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ በ1849 ዓ.ም. ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሞንሲኞር ተባለ፡፡ ይኼ ሰው በ1879 ዓ.ም. ውስጥ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ በ1880 ዓ.ም. ላይ በፈረንሣይ በተካሄደው ጉባዔ በመገኘት ለኦሮሞዎች ተጨማሪ ሚሺነሪዎች እንደሚያስፈልጓቸው አበክረው የገለጹ ሲሆን፣ በ1884 ዓ.ም. የካርዲናንነት ሲመት በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአቡነ ሊዮ 33ኛ (1878-1903 ዓ.ም.) ተሰጠው፡፡ በአገሩም ውስጥ ሕይወቱ አለፈ፡፡ ይሁንና እርሱ ከሞተ ከ75 ዓመታት በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት የአባ ማስያስ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛት መመቻቸት ቅድመ ሁኔታ እንደነበር አስታውቋል፡፡ ነገር ግን አባ ማስያስ ፖለቲካዊ ሚና ይኑረው አይኑረው ያሳየው ፍንጭ አልነበረም፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም የዚህ ሰው ጥሩ ወዳጅ እንደነበሩ ሲታወቅ፣ በአማርኛና በኦሮሚኛ ያዘጋጀውን የሰዋሰው መጽሐፍ አሳትመውለታል፡፡ አባ ማስያስ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹በኢትዮጵያ ደጋማ ሥፍራዎች በሚሽን የቆየሁባቸው 35 ዓመታት›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ይኼም ስለኢትዮጵያውያን ማንነት የሚያወሳ መጽሐፍ በ1936 ዓ.ም. መታተሙ ይታወቃል፡፡ መጽሐፉ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱም ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጀርመንኛ ተተርጉሟል፡፡

እነ አባ ጁሴፔ ሳፔቶና እነ አባ ማስያስ በአንድ በኩል ሃይማኖት በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ አማካሪ፣ በዋነኛነት ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ለመንግሥታቸው መረጃ አስተላላፊ ሆነው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ተልዕኳቸውን ሲፈጽሙም ወደ አገራቸው እየተጠሩና ሹመት ሲቀበሉ፣ የኢጣሊያ መንግሥት ደግሞ ያገኘውን መረጃ በመጠቀም ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ዓላማውን ለማስፈጸም መጠቀም ጀመረ፡፡ ይኼንን በአጭሩም ቢሆን እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡ ስለዓደዋ ጦርነት በሚያወሳው ምዕራፍ እንደተጠቀሰው ሁሉ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረር የጀመረችው በነጋሪባልዲና ማዚኒ ተበታትና የነበረችው ኢጣሊያ 1861 ዓ.ም. በተዋሃደች በ17 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ኢጣሊያ ከተዋሃደች በኋላ ብዙዎች ታላቋን ኢጣሊያ የመመሥረት ሕልም ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ፍራንሲስኮ ክሪስፒ ‹‹ኢጣሊያን ትልቅ ማድረግ የሚቻለው በአፍሪካ ውስጥ ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት የተቻለ እንደሆነ ነው›› ብሎ ያምን ነበር፡፡ ስለሆነም ቀደም ሲል በተጠቀሰው ውል መሠረት ጁሰፔ ሳፔቶ የአሰብ የተወሰነ ክፍል በ1869 ዓ.ም. ሲገዛ ዓላማው ለራፌኤል ሩባቲኖ ኩባንያ የመርከብ ከሰል መሙያ የነበረ ሲሆን፣ የኢጣሊያ መንግሥት ግን በውሉ ውስጥ የነበሩትን ቀዳዳዎች ተጠቅሞ የቅኝ ገዥነት እግሩን የሚተክልበት ቦታ አደረገው፡፡

‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉም ሲኞር ጁሰፔ ሳፔቶ ሆን ብሎ በውሉ ውስጥ እርሱ ለመኖሪያነት በገዛው መሬት ላይ ሌሎች የእርሱ ሰዎች መጥተው ቢኖሩ ምንም ዓይነት ተንኮል በአፋሮች ዘንድ እንደማይደርስባቸው ቅዱስ ቁርዓን አስይዞ አስምሏቸው ስለነበር በእርሱ እግር የሩባቲኖ ኩባንያ፣ በሩባቲኖ ኩባንያ እግር የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች እስከ መጨረሻው እያታለሉና እየሸፈጡ ቦታ ያዙ፡፡ ከፊል አሰብ ለሩባቲኖ ኩባንያ በ1870 ዓ.ም. መሸጡን ተከትሎም ዘመናዊ ወደብ ተደርጎ ተሠራ፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላም ኩባንያው ከአሰብ እስከ መሀል ሐበሻ የነበረውን ንግድ ሰለማዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የጦር መርከቦች እንደሚያስፈልጉት ገለጸ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሮሊም የኢጣሊያ መንግሥት ምክር ቤት የተቀደሰ ሐሳቡን የደገፈው መሆኑን ገልጾ፣ ‹‹ቅኝ ግዛታችንን ለመጠበቅ ሁለት የጦር መርከቦች ልኬልሃለሁ›› የሚል መልዕክት አስተላለፈለት፡፡ ክሪሲፒ በሁለተኛው ደብዳቤው በአሰብ የንግድ ማዕከል መቋቋሙ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማሳደግ በኩል ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጦ፣ በንግዱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢጣሊያን የባህር ኃይል ለማደራጀትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገለጸለት፡፡ ከዚህ ደብዳቤ በግልጽ እንደምንረዳው ምንም እንኳን ጁሰፔ ሳፔቶ ለመኖሪያነት ገዝቶ ለነዳጅ መሙያነት ለራፋኤሎ ሩባቲኒ ቢያስተላልፈውም፣ አሰብን ወደ ኢጣሊያ ቅኝ ግዛትነት የመቀየር ፍላጎት የነበር መሆኑን ነው፡፡

‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ የኢጣሊያ መንግሥት በ1882 ዓ.ም. ላይ አሰብ ቅኝ ግዛቱ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲኞር ማቺኒ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በአሰብ ወደብን ከአውሮፓ ገበያ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ማዕከል አድርገው ያላንዳች ችግር እንዲጠቀሙበት ጋበዘ፡፡ በእርግጥም አሰብ ለማደግ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሄድና ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ንግድ ያስፈልገው ነበር፡፡ የአሰብ ጉዳይ በዚህ ሁኔታ መልክ ከያዘ በኋላ በምፅዋ የነበረው የግብፅ ጦር በአቅም ማነስ ምክንያት ጓዙን ጠቅልሎ ሲወጣ የፈረንሣይ ተቀናቃኝ በነበረችው በእንግሊዝ ድጋፍ ምፅዋን ተቆጣጠረች፡፡ ይኼም አፄ ዮሐንስ በሱዳን ማህዲ ታግቶ የነበረውን በጄኔራል ጎርዶን የሚመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ካስለቀቅክልኝ ድሮውንም የአንተ የግዛት አካል የነበረችውን ምፅዋን መልሼ አስረክብሃለሁ በማለት የገባችውን ቃል በማጠፍ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች መወሳቱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የእንግሊዝ ክህደት በሰፊው የተጻፈ ስለሆነ በድጋሚ እዚህ ለማቅረብ አልተፈለገም፡፡ የሆነ ሆኖ ምፅዋ በእንግሊዝ ትብብር ለኢጣሊያ ተላለፈችና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ‹‹አይዞሽ ኢትዮጵያ፣ ምፅዋ የትም አልሄደችም፣ እዚያው ድሮ ከነበረችበት ናት›› በሚል ስሜት እንደ አሰብ ሁሉ ነፃ የወደብ አገልግሎት ልታገኝ እንደምትችል እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 5 ቀን 1885 ይፋ አደረገ፡፡ ኢጣሊያ በምፅዋ ብቻ ሳትወሰን ይዞታዋን ወደ ዶጋሊ በማስፋፋቷ አፄ ዮሐንስ ሠራዊታቸውን በመላክ 500 ወታደሮቿን ደመሰሱባት፡፡ በዚህ የተበሳጨው የቀይ ባህር ጦር አዛዥ ለኢጣሊያ ማደግ አሰብንና ምፅዋን ብቻ መያዝ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሶ ወደ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ ግዛት ለመግባት የሚያስችለው ተጨማሪ የጦር ኃይልና በጀት እንዲመደብለት የኢጣሊያ መንግሥትን ጠየቀ፡፡ ምንም እንኳን ለጊዜው ኢጣሊያ የቅኝ ግዛቷን ወደ መሀል አገር ለማስፋፋት ዕቅድ እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ (1887-1896 ዓ.ም.) ለአፉ ቢገልጥም፣ በኋላ ግን የኢጣሊያን የጦር ኃይል በቀይ ባህር ማጠናከርና የንግድ እንቅስቃሴዋን ማፋጠን እንደሚገባ ያምን ነበር፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹለትም ኢጣሊያ በቀይ ባህር የንግድ መስመር ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከሐበሻ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አመነ፡፡ የውጫሌ ስምምነትን ከአፄ ምኒልክ መንግሥት ጋር የተፈራረመውም እርሱ ሲሆን፣ ስለውጫሌና ስለዓደዋ ጦርነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ራሱን የቻለ ምዕራፍ ተሰጥቶታል፡፡

ምንም እንኳን ጁስፔ ሳፔቶ አሰብን ለሃይማኖታዊና ለንግድ እንቅስቃሴው አነስተኛ ቀበሌ ቢከራይም፣ እስከ 1880 ዓ.ም. ድረስ የቅኝ ግዛት መንፈስ እንዳልነበረ ደግሞ መታወቅ አለበት፡፡ ይልቁንም ዘመኑ አፄ ዮሐንስ አራተኛ በሥልጣን ላይ የነበሩበት በመሆኑ እኚህ ንጉሠ ነገሥት በሥራቸው የነበረችውን አንዲት የአሰብ ቀበሌ ለኢጣሊያ አሳልፈው ስለመስጠታቸው ወይም ለአሰቡ ሥልጣን ይሁንታቸውን የሰጡበት የሚገልጽ መረጃ ባለመኖሩ፣ የአሰብን ሡልጣን መሬት መሸጥና መለወጥ ለአንድ በሥራቸው ላለ ሡልጣን ለአሥር ዓመታት ፈቅደዋል እንደማለት ይቆጠራል በሌላ አገላለጽ የአፋር ምድር (ኤርትራን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አካል አልነበረም እንደ ማለት ይሆናል፡፡ ይሁንና ዘመኑ አውሮፓውያን አፍሪካን የሚቀራመቱበት ዘመን ስለነበረ የኢትጵያ ግዛት መያዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ዳሩ ግን አሰብን በሸፍጥ፣ በማታለል ወይም የቀበሮ ባህታዊ የሆኑትን መነኩሴ በመጠቀም ቅኝ ግዛት አድርጋ ለመያዝ ከአሥር ዓመታት በላይ ወስዶባታል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ፀረ ኮሎኒያሊዝም እንቅስቃሴውን የጀመረው አውሮፓውያን በተለያ ምክንያቶች ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ማሳረፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ጥንት ቱርኮችን መክቶ እንደያዘ ሁሉ የእንግሊዞችም ምኞት እንዲመክን ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1882 ታላቋ ብሪታኒያ ግብፅን ከያዘች፣ እ.ኤ.አ. ጁን 26 ቀን 1885 በበርሊኑ ስምምነት አፍሪካ እንደ ቅርጫ እንድትከፋፈል ከታወጀበት፣ ይልቁንም የበርሊኑ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከወሰነችበት ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ ተጋድሎ ሲያደርግ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡ ያ ሕዝብ በአንድ በኩል አገሩንና ነፃነቱን ከጠላት እየተከላከለ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር በነበረው ምኞት ለበጎ ነገር ሁሉ ይስማማ እንደነበረም አይካድም፡፡ ለምሳሌ ማሕዲስቶች ግብፅን ትገዛ የነበረችውን የብሪታኒያ ጦር በስተሰሜን ሱዳን በኩል እንዳይወጣ ቢከለክሉ በምፅዋ በኩል እንዲያልፍ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ በሰር ዊሊያም ሔዊት የሚመራውን የብሪታኒያ የልዑካን ቡድንም በእንግድነት ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡ ሁለቱ መግሥታት ቢዋዋሉም የአፄ ዮሐንስ ጦር አዛዥ የነበሩት ራስ አሉላ ሱዳን ውስጥ የነበሩ ስድስት ክፍለ ጦሮችን በመርዳት ሲያሳልፉ  ሕዝብ ሁነኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይሁንና ብሪታኒያ በሰር ዊልያም ሔዊት አማካይነት የተዋዋለችውን የውል ቃል በማጠፍ ኢጣሊያ ምፅዋን እንድትይዝ አደፋፈረቻት፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ከጦር መሪዎቹ ጋር በመሆን ለአገሩና ለራሱ ነፃነት እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የኢጣሊያ ተስፋፊው ጦር የሌሎች የአውሮፓ አገሮች የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ ስለነበረው በገንዘብም፣ በጦር መሣሪያም እጅግ የላቀ ቢሆንም እስከ አምባላጌ ጦርነት ባለው ጊዜ ሁሉ ትውልድ ሊዘነጋው የማይችል ፍልሚያ አካሂዷል፡፡ የጉራዕ፣ የጉንደት፣ የሰሐጢ፣ የዊዓና የሌሎችም ሥፍራዎች ጦርነት ሲወሳ ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጀግንነት የተሞላበት ጀብዱ አለ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጦር ወደ ሰሜን እስከተንቀሳቀሰበት ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ቀን የትግራይ ውድ ልጆች ደማቸውን ያፈሰሱት አጥንታቸውን የከሰከሱበት ዕለት ነበር፡፡ በዓደዋ ዘመቻ ጊዜም ቢሆን ስንቅና ትጥቅ እንዲሁም አስፈላጊውን መረጃ ከማቅረብ ጀምሮ ግንባር ቀደም ተፋላሚ ሆነው ለፀረ ኮሎኒያሊዝም ድል አድራጊነት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ መሬቱም የነበረውን ዛፍ፣ እህል፣ የዱር እንስሳት መስዋዕት አድርጓል፡፡  

ወደ ዓደዋ ጉዞ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የኢጣሊያን ወረራ በመቃወም ወደ ዓደዋ ሲያመሩ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ ለመቀስቀስ ሁኔታው አስገድዷቸው ነበርና የሚከተለውን የክተት አዋጅ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም. አሳወጁ፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያስፈራራ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን!! ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታው ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››

በዚህ ጥሪም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ጦሩም አምባላጌ ደረሰ፡፡ ስለአምባላጌው ጦርነት በርክሌይ ሲገልጽ፣ ‹‹አምባላጌ በተለይም ቡታ በተባለው ቦታ ላይ በአንድ በኩል በጀግናው ራስ አሉላና በራስ መንገሻ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በራስ መኮንንና በራስ ሚካኤል የሚመራው ጦር የጠላትን ወገን እንዲሸሽ አደረጉት፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹የኢጣሊያ ጦር በጀግንነት የተዋጋ ቢሆንም ሁኔታውን የሚቋቋመው አልሆነም፡፡ ከዚህ መዓት የተረፉት ኢጣሊያኖች እንዳሉት የሐበሾች ቁጥር ከመጠን በላይ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ይሞታል፣ ነገር ግን ሌላው ወደፊት ይገፋል፡፡ የምድሩም ተኩስ አይገታቸውም፡፡ ሁኔታው ከመሬት የሚፈሉ አስመሰላቸው፡፡ ጦሩ እየተኮሰ ይገድላቸዋል፣ ነገር ግን ቁጥራቸው እየበረከተ ይሄዳል፤›› ማለታቸውን አስፍሯል፡፡ ‹‹መድፈኞች ተኩሱን እንዳቆሙ በየአቅጣጫው የራስ አሉላ ጦር ፈጥኖ እየደረሰ ጨፈጨፈው፡፡ ጄኔራል ቶዘሊም አምባለጌ ላይ ተገደለ፡፡ መቀሌም ከአርባ ቀን ጦርነት በኋላ ተያዘች፤›› በማለት በርክሌይ ስለጦርነቱ ገጽታ ጽፏል፡፡

ምንም እንኳን ኢጣሊያኖች ሽንፈት ቢደርስባቸውም ታኅሳስ 10 ቀን 1887 ዓ.ም. የኢጣሊያ ፓርላማ ባደረገው ስብሰባ ለጦርነቱ መቀጠል ከፍተኛ በጀት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ምፅዋ ወደብ የሚደርሰው መሣሪያ ወደ አዲግራት ለማድረስ 21 ሺሕ ግመል ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ አሪሞንዲ ባደረገው ጥረት ስምንት ሺሕ 200 ግመልና ሦስት ሺሕ በቅሎ ተገኝቶ እንዲጓጓዝ አደረገ፡፡ 38 ሺሕ የሚሆኑ ወታደሮች፣ 8,584 በቅሎዎችንና 100,000 በርሜሎች ከመርከብ ወርደዋል፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ስንቅ ትጥቅም ለጊዜው ፋታ የሰጣቸው ቢመስልም ጦርነቱ ቀጥሎ መቀሌ ሙሉ በሙሉ ጥር 4 ቀን 1888 ዓ.ም. ከኢጣሊያኖች ፀዳች፡፡ የአፄ ምኒልክም ጦር አቅጣጫውን ወደ አዲግራት በማድረግ ፋንታ ፊቱን ወደ ሰሜን ምዕራብ በማዞርና ጥር 22 ቀን ከሐውዜንም ጉዞውን ወደ ዓደዋ ቀጠለ፡፡

የአፄ ምኒልክ ዘመን በጨረፍታ

የአፄ ምኒልክ ዘመን የሚባለው ንጉሠ ሸዋ ከሆኑት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ የታሪክ ጸሐፊ የሆነው አርኤችኮፊ የምኒልክ ዘመንን በሦስት ከፍሎ ይመለከተዋል፡፡ አንደኛው አውሮፓውያን ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ወደ ሸዋ ገብተው የልማት ሥራ እንዲያከናውኑ ያደረጉበት ሲሆን፣ ሁለተኛውም በሰሜን በኩል የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የገነቡበት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ግዛትን አንድ ለማድረግ ያደረጉት እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡ አርኤችኮፊ እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ወቅቶች ሲያብራራ ምኒልክ በ1865 ዓ.ም. ከአፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ከወጡበት ጀምሮ ኤደን (የመን) ከሚገኙት የብሪታኒያና የፈረንሣይ ተወካዮች ጋር ግንኙነት የሚጀመርበትን መንገድ ማመቻቸት እንደ ጀመሩ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ለምኒልክ ጥያቄ እንግሊዞች ወዲያውኑ መልስ ስላልሰጧቸው ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ፈረንሣይ መለሱ፡፡ ምኒልክ አውሮፓውያኑን የጠየቋቸው የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ለሸዋ ዕድገት የሚበጀውን የልማት ሥራ ሁሉ እንዲያከናውኑላቸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ፓቲዮ የተባለ ፈረንሣዊ ተቀጥሮ የሸዋ ወጣቶችን ዘመናዊ ውትድርና ማስተማር ጀመረ፡፡ ስዊሳዊው ኢንጂነር ፒያኖም በራስ ጎበና ትዕዛዝ ሥር በነበረው ጦር ውስጥ መኮንን ሆነ፡፡ አልፍሬድ ኤልግ ዝመርማን የመንገድና የድልድይ ግንባታውን የሚያካሂድ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ እንደ ዶ/ር አልፊዮሪና፣ ዶ/ር ትንቪርስ ያሉ ኢጣሊያዊያን የሕክምና ሰዎችም በሙያቸው አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉ፡፡

በ1869 ዓ.ም. ላይም ካቶሊካዊው ሚሽነሪ ማሳያ (አባ ማስያስ የሚባሉት) ሸዋ ገቡ፡፡ የእኚህም ሰው አመጣጥ ደቡብ ወዳለውና ከ1852-1864 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ወደ አቋቋሙት ሚሽናቸው እንዲሄዱ የምኒልክን ፈቃድ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ምኒልክ ግን ማሳያ የመጡላቸውን ከአውሮፓ ኃይሎች ጋር ወዳጅነት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን ሰው ሲፈልጉ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ፣ ከ1868-1879 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለዓላማቸው መሳካት ሲሉ ሸዋ ውስጥ እንዲቀመጡ አደረጓቸው፡፡ በዚህ የሃይማኖት ሰው ምክርም አባ ሚካኤል የተባሉ ሰው በ1872 ዓ.ም. ወደ ኢጣሊያ፣ ፈረንሣይና እንግሊዝ ተላኩ፡፡ የአባ ሚካኤል መልዕክት እንደታሰበው ባይሳካም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢጣሊያ በ1879 ዓ.ም. ላይ አንድ የሳይንስና ምርምር ተልዕኮ ያለው የመልክዓ ምድር ማኅበረሰብ ላከች፡፡ ለዚህም ልዑክ ምኒልክ ‹‹ልጥ ማረፊያ›› የሚባል ሥፍራ ፈቀዱለት፡፡ በታሪክ ሰዎች እንደሚባለው ከሆነ የዚህ ቡድን ሥራ በአመዛኙ ስለላ ለማካሄድ ነበር፡፡ በኢጣሊያና በንጉሥ ምኒሊክ መካከል የነበረው ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ፣ በወቅቱ የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ማንቺኑ አንቶኖሊ የተባለ መስፍን የኢጣሊያ ተወካይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ፡፡ አንቶኖሊም ከኢጣሊያ አሰብ እንደደረሰ ከአውሳው ሡልጣን ከመሐመድ ሐንፋሪ ጋር በመነጋገር እስከ ሸዋ ያለውን መንገድ ክፍት እንዲያደርግ ተስማማ፡፡ አንኮበር ላይ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል (29) 1883 ዓ.ም. እንደደረሰም የሹመት ደብዳቤና ለምኒልክ የተላከውን ገጸ በረከት አቀረበ፡፡ ወዲያውኑም ባለ 19 አንቀጽ የወዳጅነት ስምምነት በኢጣሊያ መንግሥትና በሸዋው ንጉሥ ምኒልክ መካከል እንዲፈረም አደረገ፡፡

በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል ያለው ወዳጅነት በዚህ ሁኔታ በተጠናከረ ወቅት በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መካከል እንደዚሁ ግንኙነቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ ይልቁንም ቀይ ባሕር በሜድትራንያን በኩል ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኝ በገልፍ አድርጎ በህንድ ውቅያኖስ በኩል ደግሞ ወደ እስያ የሚወስድ በመሆኑ፣ በእንግሊዝ በኩል ጉዳዩ ለፈረንሣይ የሚተው አልነበረም፡፡ በመሆኑም የኦቶማን ቱርክ መንግሥት የቀይ ባሕርን አካባቢ ቢቆጣጠረውም እንግሊዝ ከ1849 ዓ.ም. ጀምሮ ዕውቅናን እንደማትሰጠው በይፋ አሳውቃ ነበር፡፡ በሁኔታው አስገዳጅነት ጭምር እንግሊዝ የጦር መሣሪያውን ብትልክም እንኳን መልዕክተኞቿን ማሰማራቷ አልቀረም፡፡ በ1869 ዓ.ም. ስዊዝ ካናል ሲከፈት ሜዲትራንያን ባሕርና ቀይ ባሕርን በማገናኘት እንግሊዝ ከኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ አወቀች፡፡ የእንግሊዝ ፍላጎት ሲያድግ የፈረንሣይም ማደጉ አልቀረምና በ1874 ዓ.ም. ላይ አርክኖስ የተባለው ቱጃር በአገሩና በኢትዮጵያ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚረዳ አስታወቀ፡፡ ይኸው ሰው ገበሬዎች አስተራረሳቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፣ የአውሮፓ መድኃኒት እንዲገባ፣ ወታደሮች በአውሮፓ ዓይነት እንዲሠለጥኑ፣ የአካባቢ ፀጥታ በአስተማማኝ እንዲጠበቅ ፍላጎት መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ ይኼም የአርክኖስ ፕሮጀክት ፈረንሣይ በቀይ ባሕር ላይ ለሚኖራት ሥፍራ አስተማማኝ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ ግልጽ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1879 ካውንት ፔየትሮ አንቶኖሊ የተባለው ኢጣሊያዊው መስፍን የመጀመሪያው የመንግሥት መልዕክተኛ ሆኖ ወደ አንኮበር መጣ፡፡ እ.ኤ.አ. ሜይ 21 ቀን 1879 ላይም የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ስምምነቱም የሁለቱም አገሮች ዜጎች አንዳቸው የሌላውን አገር ለመጎብኘት ቢፈልጉ ነፃ ሆነው ሊጎበኙ እንደሚችሉ፣ ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች በሸዋና በአሰብ መካከል ያለውን መንገድ ክፍት እንደሚያደርጉና ኢጣሊያ በሸዋ ውስጥ ተጨማሪ ሥፍራ እንድታገኝ የሚያወሳ ነበር፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀጽ አሥራ ሦስትን (XIII) ስንመለከተው የኢጣሊያ ባለሥልጣናት ምኒልክ ከአውሮፓውያን ጋር እንዲገናኙዋቸው ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ስለሚጠቅስ፣ እ.ኤ.አ. በ1889 በውጫሌ የተደረገው ስምምነት በተለይም አንቀጽ አሥራ ሰባትን አስቀድሞ ማየት ይጠቅማልና በትኩረት የምንመለከተው ነው፡፡

በዚህና ቀደም ሲል በቀረበው ምክንያት የአውሮፓ ሥልጣኔ በምድረ ሸዋ ብቅ ብቅ ሲል ታየ፡፡ ጥቂት ሰዎችም ከአውሮፓ ቋንቋዎች ጋር ተላመዱ፡፡ በ1886 ዓ.ም. ላይ የመልክዓ ምድሩ ማኅበረሰብ በእንጦጦ ሆስፒታል እንዲቋቋም ተስማማ፡፡ ምኒልክ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ቆይተው አፄ ዮሐንስ በመተማው ጦርነት ሲሞቱ እ.ኤ.አ. በ1889 ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘውድ ጫኑ፡፡

በርክለይ እንደገለጠው ከሆነ ምኒልክ ፍፁም ጥንቁቅ፣ ብልጥና ዕቅዳቸውን ለመፈጸም የታጠቁና የዕድላቸውን ዘለቄታ አስቀድመው ያወቁ የሚመስሉ ሰው ስለነበሩም በተለመደው ብልኃታቸው በመጠቀም፣ እንዲሁም የጊዜውን አመቺነት በመመልከት ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር ንግግር ጀመሩ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ራስ መንገሻን ለማስገበር ወደ ትግራይ ሲዘምቱ ኢጣሊም የራሷ የሆነ ዕቅድ ነድፋ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ምኒልክ የትግራይን ራስ መንገሻ ዮሐንስን ለማስገበር በጥር ወር 1882 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ሲዘምቱ የኢጣሊያው ጄኔራል ኦሬን፣ ወደ ደቡብ ዘመቻውን ቀጥሎ ችግር ሳይገጥመው ዓደዋን ያዘ፡፡ ከዚያ በኋላም የአፄ ምኒልክ ባሕርይ እየተለወጠ ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነትም እየሻከረ ሄደ፡፡ ኦንቶኖሊ ለማረጋጋት ቢጥርም እንኳ አልሆነለትም፡፡

ይህም ቁልጭ አድርጎ የሚያመለክተው ኢጣሊያ ኤርትራን አጠቃልላ ከያዘች በኋላ በዚያው ለመቆየት አልቻለችም፡፡ ይልቁንም ኢጣሊያ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ውጥረቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለባት ይሄድ ስለነበር ይኼንን የኢኮኖሚ ውጥረት ለማርገብ ከኤርትራ የእርሻ ሥፍራዎች ባሻገር ወዳሉት የኢትዮጵያ ለም መሬቶች ትኩረቷ አረፈ፡፡ ማዕከላዊው የኢጣሊያ መንግሥት ጄኔራል አርሞንዲ የራስ መንገሻን ኃይል በመደምሰስ መላው ትግራይን እንዲቆጣጠር ስላዘዘው እየገሰገሰ መቀሌንና አምባላጌን ያዘ፡፡ እስከ አሸንጌ ድረስ ከተቆጣጠረ በኋላም ኤርትራንና ትግራይን ቀላቅሎ አንድ ቅኝ ግዛት ማድረጉን እ.ኤ.አ. በ1895 አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የነበረው ግንኙነት አዲስ መልክ በመያዙም እ.ኤ.አ. ሜይ 2 ቀን 1889 በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ የወዳጅነትና የንግድ ውል ተፈረመ፡፡ ይኼም ውል የተፈረመው በአፄ ምኒልክና በአንቶኖሊ መካከል ሲሆን፣ ቦታውም ንጉሠ ነገሥቱ ሠፍረውበት በነበረው ወሎ ውስጥ ‹ውጫሌ› ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በመሆኑ የውጫሌ ስምምነት ተብሎ ይታወቃል፡፡ በኢጣሊያውያን ደግሞ ‹‹የውጫሌ ውል›› ይባላል፡፡

የውጫሌ ውል ለሁለቱም ወገኖች የሚጠቅም አንቀጾች ሲኖሩበት በዚህም ስምምነት ኢጣሊያ አስመራን ጨምሮ የኤርትራን ደጋማ ክፍሎች እንድትገዛ፣ የኢጣሊያ መንግሥትም ለምኒልክ የንጉሥ ነገሥትነት ዕውቅና እንዲሰጣት፣ እንዲሁም አፄ ምኒልክ በኢጣሊያ ግዛት በኩል የጦር መሣሪያ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና ለሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች ወዲያውኑ ወደ አለመግባባት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ዝነኛው አንቀጽ አሥራ ሰባት (XVII) ተደንቅሮ ተገኘ፡፡ ይኸው አንቀጽ ወደ አለመግባባት እንዲያመሩ ያደረጋቸውም በአማርኛና በኢጣሊያንኛ ሁለት ትርጉም ያለው ሐሳብ ይዞ በመገኘቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የውሉ የአማርኛ ትርጉም ምኒልክ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ለመገናኘት ቢፈልጉ የኢጣሊያውያን አገልግሎት ሊጠይቁ ይችላሉ ሲል፣ የኢጣሊያንኛው ደግሞ ግንኙነታቸው በኢጣሊያ በኩል ብቻ ማድረግ እንዳለባቸው ያሰምርበታል፡፡ ምንም እንኳን የውጫሌ ውል በኢጣሊያ በኩል እንደ የኢትዮጵያ የበላይ ጥቅም አስጠባቂ (ፕሮቴክቶሬት) የሚያስቆጥራት ቢሆንም፣ በወቅቱ ወደ ግጭት ለመግባት የሚያስችላት አልነበረም፡፡ ምኒልክም ከውሉ በኋላ የውጫሌ ስምምነት ይስተካከል ዘንድ የአክስታቸው ልጅ የሆኑት ራስ መኮንን ወደ ኢጣሊያ ላኩ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ያኔም ኢጣሊያ ቅኝ ገዥ ሹም የነበረው ጄኔራል አንቶኒዮ ባልዲሴራ ከመረብ ባሻገር ለሚያደርገው ወረራ ይዘጋጅ ነበር፡፡ ኢጣሊያ አስመራን እ.ኤ.አ. በኦገስት 1889 እንደያዘችም በዚሁ ዓመት ጥቅምት ወር ራስ መኮንን ከኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከክሪስፒ ጋር ተጨማሪ ስምምነት ተፈራረመው ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ኢጣሊያ የአፄ ምኒልክን ንጉሠ ነገሥትነትን በድጋሚ ከማወቋም በላይ፣ የአንድ ሚሊዮን ሊሬ ብድር እንደምትሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያም የኢጣሊያን የቀይ ባሕር ባለይዞታነትን አውቃለች፡፡ (ይህም ሆነ ራስ መኮንን ሮም በነበሩበት ጊዜ የመስፋፋት ጅምራቸውን ቀጥለውበት ነበር፡፡)

በተጠቀሰው ውል መሠረት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በበላይነት የማስተዳድር ነኝ ብላ በሙሉ አፍ ለመናገር በምትችልበት ሁኔታ ላይ ስለነበረችም፣ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 11 ቀን 1889 በበርሊኑ ስምምነት በተለይም በአንቀጽ ሰላሳ አራት (XXXIV) መሠረት ለዋና ዋናዎቹ የወቅቱ ኃያላን መንግሥታት፣ አፄ ምኒልክ በውጫሌው ውል በአንቀጽ አሥራ ሰባት ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት በኢጣሊያ በኩል እንዲከናወን የተስማሙበት መሆኑን በክሪስፒ በኩል አስታወቀች፡፡ አውሮፓውያኑም ይኼንን ማጭበርበር የተሞላበትን ልፈፋ ተቀበሉት፡፡ ከአውሮፓውያኑም በፊት ብሪታንያ ኢጣሊያ በበላይነት አስተዳድራለሁ በምትለው ግዛት እሷ በምትገዛው አገር መካከል የሚገኘውን ድንበር የሚመለከት የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈራረመች፡፡ ይሁንና ምኒልክ የውጫሌ ስምምነት ትርጉምን ያለማወላወል ተቃወሙት፡፡ ከማንኛውም ግዴታ ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ይችሉ ዘንድም ብድራቸውን መለሱ፡፡ በዚህም ጊዜ ረዥምና ዕርባና የሌለው ውይይት ማካሄድ ተጀመረ፡፡ በአንድ ወቅትም ከአንቶኖሊ ጋር ሲወያዩ፣ ‹‹ኢጣሊያ ክብሯን ከመጠበቅ ይልቅ የውጫሌን ስምምነት አንቀጽ አሥራ ሰባትን በስህተት በመተርጎም ለሌሎች ኃይሎች ማሳወቅ አልነበረባትም!›› ሲሉ ምኒልክ አስታወቁ፡፡ የምኒልክ ሁነኛ አማካሪ የነበሩትም እቴጌ ጣይቱም፣ ‹‹እኛም በበኩላችን የተባለው አንቀጽ በቋንቋችን ምን ተብሎ እንደተጻፈ ለሌሎች ኃይሎች አስታውቀናል፡፡ እኛም ደግሞ እንደ እናንተ ሁሉ የምንጠብቀው ክብር አለን፡፡ የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ሆናችሁ በሌሎች ኃይሎች እንድትወከሉ ብትመኙም በፍጹም የማይሆን ነው!›› በማለት መለሱ፡፡

የጦር መሣሪያ ጥይት ያለመታከት ሲገዙ የነበሩት ምኒልክ ከኢጣሊያ ጋር የተጀመረውን ውዝግብ በውይይት እንደማይፈቱት ሲገነዘቡ እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 12 ቀን 1893 የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን ለዓለም አስታወቁ፡፡ ፌብሪዋሪ 27 ላይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ ‹‹ኢትዮጰያ የማንንም አትፈልግ፣ እጆቿን ለእግዚአብሔር ዘርግታለች›› በማለት በኩራት አወጁ፡፡ ምኒልክም ይኼን ባሉ በዓመቱ የራሳቸውን ገንዘብ አሠሩ፡፡ ከኢጣሊያ ጋር የሚደረገው ጦርነት አይቀሬ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደሷ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከምትከተለው ሩሲያ፣ እንዲሁም በቱኒዝያና በምሥራቅ አፍሪካ፣ ከኢጣሊያ ጋር የጥቅም ግጭት ካላት ከፈረንሣይ ጋር ወዳጅነት መሠረቱ፡፡ ወዲያውኑም ከሩሲያው ዛር ከዳግማዊ ኒኮላስ የተላከውን ልዑክ በክብር ተቀበሉ፡፡ ቆይቶም በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማና በደጃዝማች ገነሜ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ላኩ፡፡ ወደ ፈረንሣይ የበለጠ በመቅረብም ፈረንሣዊው ካሲሚር ሞንዶን ቪዳይሌንት የመንግሥት አማካሪ በማድረግ፣ ሊዮን ቼፍንና ሲዊዛዊው አልፍሬድ ኢልግን ከፈረንሣይ ጂቡቲ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስከነበረችው እንጦጦ ድረስ የባቡር ሐዲድ እንዲዘረጋ የተስማሙ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡

ምኒልክ የጦር መሣሪያ በአገራቸው እንዲመረት የነበራቸው ጥረት ከፍተኛ ስለነበረም ይኼም ፍላጎታቸው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሌዮን ቺፍ፣ ብሬሞንድ፣ ታይላርድና ሳቮርድ እንዲሁም አርመናዊው ሳርኪሰ ቴርዚያን ይረዷቸው ነበር፡፡  በዚህ መካከል ከኢጣሊያውያን ጋር የታማኝነት ቃለ መሐላ ፈጽመው የነበሩት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ማንኛውንም ግንኙነታቸውን በማቋረጥ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የምኒሊክ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገቡ፡፡ እ.ኤ.አ. ጁን 9 ቀን 1894 ታማኝነታቸውን አረጋገጡላቸው፡፡ ይህም በመሆኑ በሰሜን የነበረው ሁኔታ ለምኒልክ የሚያመች ሆነ፡፡ እ.ኤ.አ በ1894 ኢጣሊያውያን በዲፕሎማሲያዊ መንገድም ሆነ በተፅዕኖ ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ የቅኝ ገዥዎች ዓላማቸው የሚሳካው በጦርነት ብቻ እንደሚሆን ተገነዘቡ፡፡

ኢጣሊያውያን እ.ኤ.አ በዲሴምበር 1894 የባህታ ሐጎስን አመፅ ካከሸፉ በኋላ መረብን ተሻግረው ዓደዋ በመግባታቸው፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስም የዚህን አፀፋ በመመለስ መረብን ተሻግረው ኢጣሊያውያን ጠንካራ ምሽግ (ይዞታ) የነበረችውን ኩዓቲትን አጠቁ፡፡ በዚህ ዓደዋን ይዞ የነበረው ኤርትራ ገዥ ጄኔራል ባራቲየሪ ኩዓቲትን ለመከላከል ጦሩን አስወጣ፡፡ በጄኔራል አሪሞንዲ ጦር በመታገዝም እጅግ ከፍተኛ ውጊያ አድርጎ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 13 ቀን 1895 ራስ መንገሻ ተሸነፉና የትግራይ ጦር ወደ ሰንዓፌ አፈገፈገ፡፡ ኢጣሊያውያንም የራስ መንገሻ ጦር ከነበረበት ከሰንአፌ ተራሮች ሥር ሳይታሰብ በመጠጋት ጃንዋሪ 15 ቀን በተደረገው የአጭር ጊዜ ጦርነት ለሁለተኛ ጊዜ አሸነፏቸው፡፡ ኢጣሊያውያን በኩዓቲትና በሰንአፌ ያገኙትን ድልም ወደ ትግራይ ለመግባት የሚያስችለው በር እንዲከፈትላቸው አደረገ፡፡ ይኼንንም አጋጣሚ በመጠቀም ዓደዋን፣ ዓዲ ግራትንና መቀሌን በተከታታይ እንዲይዙ ረዳቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ መንገሻ ሕንጣሎ አጠገብ ወደ ምትገኘው ደብረ ሐይላ ቢያፈገፍጉም የኢጣሊያ ጦር ኦክቶበር 9 በመውጋት እንደገና ድል አደረጋቸው፡፡ በዓደዋው ዘመቻ የመጀመሪያው ግጭት የተደረገው ኢጣሊያውያን ከሰሜን ወደ ደቡብ ዘልቀው በመግባት ደርሰውበት በነበረበውና የተፈጥሮ ምሽግ በሆነው በአምባላጌ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት ቀጥ ያለውን ተራራ ጦራቸውን በመምራት የወጡት ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው በኋላም ግራዝማች ታፈሰ ዓባይነህና ፊታውራሪ ታከለ ተከትለዋል፡፡ ከዚያም ሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ደርሰውላቸዋል፡፡ በጦርነቱም የኢጣሊያ ጦር ክፉኛ በመመታቱ የጦር አዛዥ ሜጀር ፒየትሮ ቶዜሊ ከሞቱት አንዱ ሆነ፡፡

ምኒልክ ኢጣሊያውያን ትግራይ ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን እንደተገነዘቡ ሕዝባቸውን ለዘመቻ እንዲንቀሳቀስ ወሰኑ፡፡ ዝናቡ በሚያቆምበት ማለትም መስከረም ወር ላይም ወደ ሰሜን የሚዘምቱ ስለሆነ የሸዋ ሰዎች እስከ ጥቅምት መጨረሻ እሳቸው እስከሚገኙበት ሥፍራ፣ ማለትም ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ከምትርቀው ወረኢሉ ድረስ እንዲመጡ አወጁ፡፡ የጎጃም፣ የደንቢያ፣ የቋራና የጎንደር ወታደሮችም ጨጨሆ ላይ፣ የሰሜን የወልቃይት ጠገዴ መቐለ ላይ እንዲገናኙ ታዘዘ፡፡ የራስ መኮንን ጦርም በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ከሐረር ተነስቶ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ የዓደዋ ጦርነት ዶ/ር ዓለሜ እሸቱ እንዳጠናቀሩት አፄ ምኒልክ የጦርነቱን ክተት አውጀው ከአዲስ አበባ የተነሱት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም. አምባላጌ ላይ፣ ታኅሳስ 1888 ዓ.ም. መቀሌ ላይ በተደረገው ዘመቻ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የፍልሚያው ሥፍራ ዓደዋ ላይ የነበረ ሲሆን፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ያዘመቱት ጦር ቁጥር ግን በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተሰላው በተለያየ ቁጥር ነው፡፡

አፄ ምኒልክ ዓደዋ ላይ ካሠለፏቸው ወታደሮች በተጨማሪ የራስ ወልደ ጊዮርጊስ ከስድስት እስከ ስምንት ሺሕ፣ የራስ ተሰማ ናደው ከአራት እስከ አምስት ሺሕ፣ የራስ ዳርጌ ሦስት ሺሕ የደጃዝማች ወልደ ፃድቅ ሦስት ሺሕ፣ የደጃዝማች ልዑል ሰገድ ሦስት ሺሕ፣ ወዘተ ግማሹ አዲስ አበባን ሲጠብቁ ሌላው ኢጣሊያውያን በአፋር በኩል ያስገቡትን ጦር ለመግጠም በመዝመቱ ዓደዋ ላይ ሳይዋጉ መቅረታቸው፣ እንዲሁም ከአፋሮች ሌላ ኢጣሊያኖች በዘይላ በኩል ሶማሌዎችን አነሳስተው ኢትዮጵያን እንዲወጉ ለማድረግ የነበራቸው ዕቅድ፣ የእንግሊዝና የፈረንሣይ መንግሥት ሳይስማሙ በመቅረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ 

በዓደዋ ጦርነት 20 ሺሕ ያህል የኢጣሊያ ጦር የተከማቸው ሳውሪያ (ኢንቲጮ) ላይ ሲሆን፣ ይኼም ከዓድዋ በስተምሥራቅ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የኢጣሊያ አሠላለፍ በአራት የተከፈለ ነበር፡፡ እርሱም፡-

ጄኔራል ዳቦርሜዳ … የቀኝ ብርጌድ 3,500 ወታደሮችና 18 መድፎች

ጄኔራል አልቤርቶኒ … የግራ ብርጌድ 8,300 ወታደሮችና 12 መድፎች

ጄኔራል አሪሞንዲ … የመሀል ብርጌድ 2,900 ጠመንጃዎችና 12 መድፎች

ጄኔራል ኤሌና … ተጠባባቂ (ሪዘርቭ) ብርጌድ 3,350 ወታደሮችና መድፎች ነበሩት፡፡

አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓደዋ ላይ የካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም. ኢጣሊያውያን ደግሞ ኢንቲጮ ላይ የካቲት 6 ቀን ከሠፈሩ በኋላ፣ የሁለቱ ወገን ሠራዊት ተፋጠው እስከ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ድረስ ቆዩ፡፡ እስከዚያ ዕለትም ሁለቱም የተፋጠጡ ወገኖች ሌላውን ሲሰልለው ሰነበቱ፡፡ በመጨረሻም ኢጣሊያውያን ‹‹ኢትዮጵያ ሠራዊት ገሚሱ ቀለብ ፍለጋ ወደ ሽሬና ወደ ተንቤን እንዲሁም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ፀለምት ተበትኗል፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አክሱም ጽዮን እሑድ የሚውለውን የጊዮርጊስ በዓል ለማስቀደስ ሄደዋል…›› የሚል መረጃ ስለደረሳቸው በዚሁ ዕለት ማለትም የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. እሑድ የጊዮርጊስ ዕለት በአጥቂነት የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ወሰኑ፡፡ የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ገብረ ሥላሴ እንደሚሉትም (ገጽ 262) ቀለብ ፍለጋ አክሱም ጽዮን ከሄዱት እሑድ ለጦርነቱ የተመለሱት ከሦስት እጅ ሁለት እጅ ነበሩ፡፡

ጆርጅ ኤፍ በርክሌይ የተባለ ጸሐፊ ‹‹የዓደዋ ዘመቻን የምኒልክ አነሳስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፉ በዳኛው ወልደ ሥላሴ ተተርጉሞ እንደምናነበው፣ አፄ ምኒልክም ሆኑ የኢጣሊያው የጦር መሪ ባራቲየሪ ቀድመው ለማጥቃት ሳይሽቀዳደም አንዱ የሌላው ጠላት ስንቅ እንዲያልቅ እየተመኘ ጦርነቱን ሳይጀመር በመቆየቱ፣ ሁለቱም  ስንቃቸውን ወደ መጨረሱ ተቃርበው ነበረ፡፡ ድል በመምታት መበቀልን የፈለገው የሮማ ሕዝብ ውሎ ባደረ ቁጥር ተስፋ እየቆረጠ በመሄዱ የባራቲየሪም ክብርና ዝና ወደቀ፡፡ የካቲት 15 ቀን 1888 ዓ.ም. በሚስጥር ባራቲየሪ ተሽሮ ጄኔራል ባልዲሴራ የጦሩ አዛዥ እንዲሆን ተሾመ፡፡

ይሁንና ይኼው የጦር መሪ የካቲት 21 ቀን 1888 ዓ.ም. በማይ ገበታ በኩል ወደ ማይ ማረት ለማፈግፈግ ወስኖ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ በዚሁ ምሽት አራቱን ጄኔራሎች ሰብስቦ ያለው ምግብ እስከ የካቲት 23 ቀን ወይም የካቲት 24 ቀን ድረስ ብቻ የሚያቆያቸው መሆኑን ካስረዳ በኋላ፣ ወደ ሰንአፌ ለመሸሽ ወይም አስፈላጊው ጥናትና ዝግጅት እንዲያደርጉ አማከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጄኔራል ዳቦር ሜዳ የጄኔራል ባራቲየሪን ንግግር ከሰማ በኋላ መሸሹ የማይደረግ ነው ብሎ ስሜቱን ገልጾ ምክንያቱን ማስረዳት ጀመረ፡፡ አንደኛ የኢጣሊያን ሕዝብ ከምናሳፍር ሦስት ሺሕ ወታደር ቢሞትብን ይመረጣል፡፡ ሁለተኛ የወታደሩ ሞራል በጣም ይወድቃል፡፡ ሦስተኛ ጠላቶቻችን ከእኛ ፈጥነው ለመጓዝ ስለሚችሉ አሁንም በመሸሽ ላይ ሳለን ደርሰው ለራሳቸው ከሚያመቻቸውና ከመረጡት ቦታ ላይ አደጋ ሊጥሉብን ይችላሉ፡፡ ይኼ ከሚሆን ወጥተን ማጥቃቱ ይሻላል ሲል አሳሰበ፡፡

ጄኔራል አልቤርቶኒም የጄኔራል ዳቦር ሜዳን ሐሳብ ደግፎ፣ ‹‹የጠላት ጦር ምግብ ለመሰብሰብ የተበታተነ ከመሆኑም በላይ ብዙውም ወደ አገሩ በመመለስ ላይ ነው፤›› በማለት የሐበሻው ጦር ሠፈር በሁለት መሪዎች የተከፈለ ከመሆኑም በላይ፣ ከ14 ሺሕ ወይም ከ15 ሺሕ ጦር በላይ እንደማይኖረው ገለጸ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሁኔታው አፄ ምኒልክም በጣም ተጨንቀዋል፡፡ የቀራቸው ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት የሚሆን ስንቅ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ከምሽጉ ወጥቶ ማጥቃት እንዲጀምር ብርቱ የሆነ ፀሎታቸው ነበር፡፡ ይኼንንም ዕድል ለማግኘት ለባሪያቲየሪ እንዲደርስ የሚያስወሩት ፕሮፓጋንዳ  ‹‹በአፄ ምኒልክ የጦር ሠፈር ችግርና ረሃብ ፀንቶ ሠራዊቱ እየሸሸ በመሄድ ላይ በመሆኑ በዙሪያው የሚገኘው ሕዝብ ተነስቷል፤›› የሚል ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ እንደተመኙትም የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም. አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ጄኔራል ባሪያቴሪ ወጥቶ ለማጥቃት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ፡፡

የባሪያቴሪ ዓላማ በሦስት አቅጣጫ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ የጠላት ጦር ሳያውቅ በተራራው ገመገም ሥር ለመመሸግና የመከላከያ ቦታ ለመያዝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የጠላት ጦር ቢያጠቃ መልካም፣ ካልሆነም የሐበሻን ጦር ፍርኃት እንዲያድርበት በዙሪያው ለሚገኘው ሕዝብ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣሊያ ጦር ተንቀሳቅሶ የእነዚህን ተራራዎች ገመገም በሚይዝበት ጊዜ የሐበሻው ጦር በርግጎ ወደኋላ ይመለሳል የሚል እምነትና ተስፋ ነበረው፡፡ ይህም ከሆነ ዓደዋን በሰላም (ያለ ችግር) ለመያዝ እንደሚችልም ገምቶ ነበር፡፡ የጦሩ አሠላለፍም፣

ሀ. በቀኝ በኩል በጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሚመራው የበላህን ተራራ አምባ፣ የበላህን ጎጥና በዙሪያው ያለውን ቦታ፣

ለ. በመካከል በጄኔራል አሪሞንዲ የሚመራው የበላህን ተራራ፣

ሐ. በግራ በኩል ‹‹በጄኔራል አልቤርቶኒ የሚመራው ኪዳነ ምሕረት ብለው የጠሯትና (ለዚች ተራራ የተሰጠው ስም በትክክል አልነበረም) ራይ የተባሉትን ተራራዎች እንዲዝ፣

መ. በጀኔራል ኤሌና የሚመራው ተጠባባቂው ጦር ረቢ አርኧየኒ በተባለው ቦታ ሆኖ እንዲጠባበቅ፣

የቀኑ ትዕዛዝም ‹‹የካቲት 22 ቀን 1888 ቁጥር 87 ዛሬ ማታ ጦሩ በሦስት አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚከተለው ሁኔታ ይቀንሳል፡፡

‹‹… የቀኙ ክፍል ጄኔራል ዳቦር ሜዳ 2ኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ የሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ሻለቃ ጦር የ2ኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ የአምስተኛ፣ የስድስተኛ፣ የሰባተኛ ከባድ መሣሪያ ጓድ፡፡ ‹‹…ግራው መስመር በጄኔራል አልቤርቶኒ (የሚመራ ሆኖ) አራት የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር የአንደኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ ከአንደኛ፣ ከሁለተኛ፣ ከሦስተኛ፣ ከአራተኛ ከባድ መሣሪያ ክፍል ጋር፡፡ ተጠባባቂ ጄኔራል ኤሌና፣ ሦስተኛ እግረኛ ብርጌድ፣ ሦስተኛ የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር ሁለት የመትረየስና የከባድ መሣሪያ ጓድና አንድ ሻምበል መሐንዲሶች፡፡ ‹‹…ጄኔራል ዳቦር ሜዳ፣ በአርሞንዲና በአልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ሲታዘዝ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ተጠባባቂው ጦር የመካከለኛውን መሥመር ተከትሎ ይንቀሰቀሳል፡፡

‹‹…የቀኙ ረድፍ በዛሃላ ጎጥ አድርጎ ጎልደም ጎጥን አልፎ ወደረቢ አርእየኒ ጎጥ ይጓዛል፡፡ የመካከለኛው ተጠባባቂ ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንድብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንደብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ደግሞ ከሶሎዳ በአዲ ቸራይራ በኩል ወደ ኪዳነ ምሕረት ይጓጓል…›› የሚል ነበር፡፡ (በዚህም ዓይነት ኢጣሊያኖች ብዛቱ 100 ሺሕ የሚሆን የጦር መሣሪያ ጦርና ጋሻ የያዘውን የሐበሻ ሠራዊት ለመግጠም 17,700 ወታደሮችና 56 መድፎች ጠምደው ተሰናድተዋል፡፡ (በዶ/ር እሸቴ ዓለሜ የተጠናቀረውን ልብ ይሏል)

በአፄ ምኒልክ ግንባር የተሠለፈው ጦር በዶ/ እሸቴ ዓለሜ ጥንቅር

አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓድዋ መጋቢት 3 ቀን 1888 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ኢጣሊያውያን ኢንቲጮ ድረስ ሄደው ለመውጋት ያልፈለጉበት ምክንያት ቦታው ለአጥቂ ጦር የማያመች መሆኑን ገብረ ሥላሴ ለሞንድ ቬዳይሌት በየካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም. ገልጸዋል፡፡ ከዚያም ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 23 ቀን ቆይተዋል፡፡

የካቲት 22 ቀን 1888 ..

…አልቤርቶኒ የታዘዘውን ትክክለኛ የጦር ሠፈር በመፈለግ ከሌሎቹ የኢጣሊያ ብርጌዶች ተነጥሎ ኪዳነ ምሕረት ኮረብታ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲደርስ፣ በሜጀር ቱሪቶ ይመራ የነበረው የብርጌዱ ግንባር ቀደም ጦር ብሎ በመድረሱ፣ በዚህ ቀን በጥበቃ ተራ ላይ ከነበረው ከራስ መንገሻ ዮሐንስ እንዲሁም ጥቂት ቆይቶም ከዋግ ሹም ጓንጉል፣ ከደጃች ገሠሠና ከበጅሮንድ ባልቻ ሠራዊት ጋር ውጊያ እንደጀመረ፣ ኮንቲሮዘኒ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ መዝግቦታል፡፡

ይኼው ኮንቲሮዚ የተባለው ጸሐፊ ዓደዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ያስቀድሱ የነበሩት አፄ ምኒልክ፣ የኢጣሊያ ወታደር በዚህ ቀን ጦር ለማድረግ መወሰኑን በተረዱ ጊዜ ሠራዊታቸውን በያለበት ቀስቅሰው ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማትያስ ጋር ሆነው ከዓደዋ ተነስተው በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አባ ገሪማ ኮረብታ ላይ ሠፍረው ነበር፡፡ የአልቤርቶኒ ብርጌድ ኪዳነ ምሕረት እንደሰፈረና ግንባር ቀደሙም ጦር አልፎ መምጣቱን እንደሰሙ በነፊታውራሪ ገበየሁ፣ በነደጃዝማች በሻህ አቡ የሚመራውን የራሳቸው ጦር ፊት ለፊት፣ የእቴጌ ጣይቱንና የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጦር በስተግራና በስተቀኝ እንዲዘምቱ አዘው ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ጦርነቱ ተጀመረ፡፡

…ከዚያ በኋላ ነጋሪት መቺው ‹‹ውጋ! ውጋ!›› እያለ እየተበረተታ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በግራና በቀኝ በሁሉም አቅጣጫ ከቦ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ አብረው በሚያዙት ላዳት (አባ ገሪማ አጠገብ) 3 ኪሎ ሜትር ከጠላት ሠፈር ርቆ ይገኝ የነበረውን የኢትዮጵያ ከባድ መሣሪያ (መድፍ) እየተደገፈ፣ በጄኔራል አልቤርቶኒ ይመራ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ደመሰሰው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ሲሆን ጄኔራል አልቤርቶኒ የተረፉ የኢጣሊያ ወታደሮችና መድፈኞች ወደኋላ እንዲሸሹ አዞ ነበር፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሠራዊት ማየል ጄኔራል አልቤርቶኒ ከብዙ መቶ ኢጣሊያውያን ጋር ተማረከ፡፡ … ጦርነቱም ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን አበቃ፡፡ ኤርትራንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ህልምም ዕውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ታላቁ የዓደዋ ድል የመላው ዓለም ጥቁሮች መመኪያ ሆነ፡፡ ይህ ታሪካዊ ድል 121 ዓመታት ቢያልፉትም፣ አሁንም አንፀባራቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሲኮራበት ይኖራል፡፡

ወደ ሰላም ማስፈን

ታላቁ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያስት ጦርነት በኢትዮጵያዊያን የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ የኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ መሐንዲስ እየተባለ ይጠራ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ከሥልጣኑ ለቀቀ፡፡ በዚያም ወቅት ኢጣሊያ በአፍሪካ ስለሚኖራት የወደፊት ዕጣ ፋንታም የሞቀ ክርክር ይደረግበት ጀመር፡፡ አንዳንዶቹ የቀኝ የፖለቲካ ሰዎች ኢጣሊያ የብቀላ ዕርምጃ ትውሰድ ብለው ሲጮሁ፣ የግራ አዝማሚያ ተከታዮች ደግሞ ከአኅጉሩ ፈጽማ መውጣት አለባት ብለው ጠየቁ፡፡ ያም ሆነ ይህ የጄኔራል ባራቲየሪ በጦር አመራር ብቃት ማነስ ምክንያት በሕግ ተጠያቂ ሆነ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የተመረጠው የሩንዲው መሥፍን አንቶኒዮ ስታራባም ክሪስፒ ያራምደው የነበረውን የመስፋፋት ፖሊሲን እንደማያራምድ በማስታወቅ ሁለቱን አገሮች የሚያስማማ መንገድ መከተል መረጠ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፓፕ) ሊዮ አሥራ ሦስተኛን በማሳመን አፄ ምኒልክ ለያዟቸው የኢጣሊያ ምርኮኞች ምሕረት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ እ.አ.አ. ሜይ 1896 እንዲጽፉ አደረገ፡፡ አፄ ምኒልክም በምሕረቱ በመስማማት ምርኮኞችን የመልቀቁ ሁኔታ ኢጣሊያ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ባላት ፍላጎት ላይ የሚወሰን መሆኑን አሳወቁ፡፡

አብዛኛው ጊዜ ‹‹የአዲስ አበባ ውል›› እየተባለ የሚታወቀውና በውሉ ርዕስ እንደሠፈረው ለዘለዓለም የሚዘልቅ የሰላም የወዳጅነት ተብሎ የሚታወቀውን ስምምነት ኦክቶበር 26 ቀን 1896 ተፈረመ፡፡ በዚህ ውል ኢጣሊያ የውጫሌ ውል እንዲሰረዝና ኢትዮጵያ ፍፁም ነፃ አገር መሆኗን አወቀች፡፡ ይሁንና አፄ ምኒልክ ያለፈው ስምምነት ያስከተለውን ውስብስብ ችግር በማስታወስ ይኼ ውል በኢጣሊያንኛ ሳይሆን በአማርኛና በፈረንሣይኛ እንዲጻፍ ወትውተው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል መግባባት የተመላበት ወዳጅነት ደረጃ በደረጃ ሲመሠረት የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞችም ተለዋውጠው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዓደዋ ጦርነት በሁለቱም አገሮች በኩል በቀላሉ የሚረሳ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከአርባ ዓመታት በኋላም ቤኒቶ ሞሶሎኒ በተባለ ፋሺስት መሪ ግፊት አዲስ ወረራ ተካሄደ፡፡

ማስታወሻ

ይኼንን ጽሑፍ ያጠናቀርኩት ቤካ ነሞ ዓደዋና ምኒልክ፣ ጆርጅ ኤፍ በርከላይ የዓደዋ ዘመቻ፣ የአፄ ምኒሊክ አነሳስ ቀኛዝማች ታደሰ ዘውዴ፣ ጣይቱ ብጡል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓደዋ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ የኤግዚቢሽን መግለጫ አይቼ መሆኑንና አቶ አህመድ ዘካሪያና ፕሮፌሰር ፓንክረስትም አንዳንድ መረጃዎችን ስለሰጡኝ በትህትና አስታውሳለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡