ዓድዋና አዲስ አበባ ምንና ምን ናቸው?

‹‹. . . አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል . . . በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ . . . ያገሬ ሰው . . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ . . .››

ይህ ኃይለ ቃል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ምልዐተ ሕዝቡንና የየአካባቢውን ንጉሦች፣ መሳፍንቱንና መኳንንቱን በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ባስነገሩት በዚህ አዋጅ መሠረትም ከ121 ዓመታት በፊት፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል ተመቶበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን እርመኛ አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡

ሐሙስ፣ የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ  የዓድዋ ድል መታሰቢያ  በተለይ በታሪካዊው ገድላዊ ሥፍራ ዓድዋ ከተማ ከሶሎዳ ተራራ ግርጌ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሐውልትና አደባባይ  በልዩ ሥነ በዓል ተከብሯል፡፡

የዘንድሮው ክብረ በዓል ከሁለት ዐሠርታት ወዲህ ለየት ባለ መልኩ ለመከበር ታድሏል፡፡ በዐቢይ ሥነ በዓል ሊከበር ይገባ የነበረው 120ኛ ዓመቱ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ቀዝቀዝ ብሎ ማለፉ ይታወሳል፡፡

በዓሉ በባለቤትነት የያዘው በአዲሷ ሚኒስትር ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም የሚመራው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ በዓሉ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከዋዜማው ሳምንት እስከ መባቻው ድረስ እንዲከበር አድርጓል፡፡

‹‹በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም ትኩረትና ፊቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ ካስገደዱት ጥቂት ክስተቶች መካከል አንዱና ዋናው የዓድዋ ድል ነው፤›› በማለት የክተት ዓዋጅ በተሰማባት የአፄ ምኒልክ መዲና አዲስ አበባ በበዓሉ ዋዜማ የተናገሩት የታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ናቸው፡፡

በበዓሉም ዕለት ከፍተኛ ፍልሚያ በተስተናገደባቸው የዓድዋ ተራሮች መሀል ከሶሎዳ ግርጌ በተዘጋጀው መድረክ ላይ፣ በአፍሪቃና በተቀረው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ድሉን ድላቸው አድርገው መውሰዳቸውን ያስታወሱት የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት፣ ‹‹በዓድዋ ድል የተጫረው ያሸናፊነት ችቦ ተዛምቶ መላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ብርሃን ማግኘት ያስቻላቸውን ትግል እንዲያደርጉና ድልን እንዲቀዳጁ አድርጓቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

በዓድዋ አከባበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪ መገኘታቸው ለክብሩ ሞገስ እንዳሰጠው የበዓሉ ታዳሚዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በተለይ ታቦ እምቤኪ፣ ‹‹የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን ሁሉ ድል›› ብቻ በማለት አልተወሰኑም፡፡ ድል የተደረገችውም ኢጣሊያ ብቻ ሳይሆን ከድሉ 11 ዓመት በፊት በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ አፍሪካን ለመቀራመት ግብረ አበርና ስም አበር ሆነው የተገኙት አውሮጳውያን ጭምር መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ቅደመ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን የፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ በማድረግ ረገድ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያወሱት፣ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ፣ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ከግብፅ፣ ከኢጣሊያና ከሱዳን ያደረጓቸውን ፍልሚያዎች በማመልከት ነበር፡፡

መሪነት ለድል ወሳኝ መሆኑን በማውሳት፣ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ጥላ ስር በማስተባበር ላቅ ያለ ሚና የተጫወቱትን ዳግማዊ ምኒልክን ያወደሱት እምቤኪ የዓድዋ ድል በርካታ ጠቃሚ ትምህርትን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን አስተምሯል ብለዋል፡፡

አንዱ ማሳያ አገርና አህጉር አንድ በመሆን መተባበር እንደሚገባ ከማስተማር ባለፈ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔን በኅብረ አንድነት ማምጣት ይቻላል በማለትም አስምረውበታል፡፡

የዓድዋ ድል ቀደም ብለው ከወራሪ ኃይሎች ጋር በጉንደት (1867 ዓ.ም)፣ በጉርዓ (1868 ዓ.ም.)፣ በዶግዓሊ (1879 ዓ.ም.) እና በሌሎች ቦታዎች ሲገኙ የነበሩት ድሎች ማጠቃለያ እንደሆነ ያመለከቱት ደግሞ የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ዓባይ ወልዱ ናቸው፡፡ የዓድዋ ዘመቻና ድሉ በተገቢው ሁኔታ መጠናትና መጠበቅ ይገባዋል ሲሉም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

የጥበቡ ማዕድ

‹‹የዓድዋ ድል ብዝኃነትን ላከበረችው ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ሕያው አብነት›› በሚል መሪ ቃል በዓሉን ከክልል ቢሮዎች ጋር በመተባበር ያስከበረው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዳቀደው፣ ለበዓሉ ክብር  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃና ሙዚቃዊ ድራማ፣ የአደባባይ ላይ ትርኢቶች (ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ በእግር የተጓዙትን ጨምሮ)፣ ሲምፖዚየሞች በሁለቱ ከተሞች አካሂዷል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የቀረበው ሙዚቃዊ ድራማ በዓድዋ ከተማ ከዓድዋ ወጣቶች ጋር በመቀናጀትም ቀርቧል፡፡

ከሶሎዳ ተራራ ግርጌ በሚገኘው አደባባይ በተዘጋጀው ስፍራ የቀረበው ሙዚቃዊ ድራማ የዓድዋውን ዘመቻ ከክተት እስከ ስምሪት ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ድረስ የተደረገው ጉዞና የነበረውን ተጋድሎ በየምዕራፉ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ የድምፅ ማጉያ ችግር ዲስኩር ያሰሙ የነበሩት የክብር እንግዶቹ በአግባቡ ለመከታተል እንዳስቸገረ ሁሉ በጥበብ ማዕዱ ላይ ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል፡፡

የሙዚቃዊ ድራማው ድርሰት ምልዐት ይጎድለዋል ያሉ የጥበብና የታሪክ ሰዎች ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ የአፄ ምኒልክ ሕዝባቸውን ዝመት ክተት ያሉበትን ዓዋጅ በድራማው ውስጥ ያለነጋሪት እንዴት ይቀርባል? እስከነብሂሉ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› አይደል ያሉም አልታጡም፡፡

በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከዓድዋ ጋር ተያይዞ እንደሚነሳ ሁሉ፣ የዓድዋው ጊዮርጊስም በንጉሠ ነገሥቱ መቀመጫነት ይወሳል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚና የሚያሳይ በትውፊት የሚገለጸው ‹‹የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከምኒልክ ጋራ አብሮ ሲቀድስ

ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ

ጣሊያን ድል አረጉ ደም እያፈሰሱ›› እንዴት ይዘነጋል?

‹‹ከሙዚቃዊ ድራማው ድርሰት ይዘት ይልቅ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዲስኩሮች ከፍታ ይሰማባቸዋል፤›› ያሉን አቶ ፀሐዩ መንክር ናቸው፡፡

የዓድዋ ድል ማንነትን ላለመለወጥ በተደረገ ተጋድሎ የተገኘ አንደኛው ሰበዝ ሲሆን፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ፊደልና ቁጥር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ለዓድዋው መሰናዶ የታደሉት ቲሸርቶች (ካኔቴራዎች) “ADWA AN AFRICAN VICTORY” የዓድዋን አፍሪካዊ ድልነት በባዕድ ቋንቋና ፊደል ብቻ ይዘዋል፡፡ በግእዝ ፊደል በሥራ ቋንቋው በአማርኛ ማዘጋጀት፣ ‹‹121ኛ ዓመትን›› በግእዙ ቁጥር ‹‹፻፳፩ኛ ዓመት›› ብሎ አያይዞ ለማጉላትስ ለምን ሳይታሰብበት ቀረ? የብዙዎች ጥያቄ ነበር፡፡

ለዓድዋው ድል ክብር ከተዘጋጀውና ከታደለው ብሮሸር ከመጽሔት መጠን ከፍ ከሚለው በአርበኛ ሥዕል ከታጀበው ክርታስ በቀር የቀረበ ነገርም የለም፡፡

በአዲስ አበባ ከቀረቡት ጥበባዊና ታሪካዊ የዘመቻ ጉዞ አመልካች ሥራዎች በተጓዳኝ ወጣቶች ‹‹ኢትዮጵያ አገሬ የአፍሪካ መቀነት፣ የነፃነት ዓርማ የሉዓላዊነት›› የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ካናቴራ አድርገው ታይተዋል፡፡

በዓድዋ ድል የተመታው ኢጣሊያ ወይስ ፋሺስት ኢጣሊያ?

በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን በመጣ ቁጥር በየሚዲያውና በየመድረኩ አልፎ አልፎ የሚታይ ስህተት ያጋጥማል፡፡ ዓድዋ ላይ ድል የሆነው በጄኔራል ባራቴሪ የሚመራው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጎልቶ የወጣው ኢጣሊያን ያስተዳድር ከነበረው የፋሺስት ፓርቲ ስሙን የወረሰው የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን የወረረው በ1928 ዓ.ም. ነበር፡፡

ይሁን እንጂ እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ በቴሌቪዥን መስኮት ከሚቀርቡት አንዳንዶቹ (ከታሪክ ምሁራኑ ውጭ)፣ ‹‹የዓድዋ ድል በፋሺዝም ላይ የተገኘ ድል›› እያሉ በዋዜማው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ በዓድዋና በአዲስ አበባ በዓሉ ሲከበርም ዲስኩር ያሰሙት ርዕሰ መስተዳድሩና ከንቲባው ሲናገሩ እንደተደመጠው ድሉ ‹‹በፋሺስት ኢጣሊያ›› ላይ የተገኘ ሆኖ ቀርቧል፡፡

የዓድዋ ድል መቶኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በ1988 ዓ.ም. ሲከበር፣ መንግሥት በዓሉን ለመዘከር መታሰቢያዎችን ለመገንባት ቃል ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዓድዋ ሰማዕትነት ለከፈሉ ሐውልት ለማቆም የመሠረት ድንጋይ ቢጣልም፣ በተከታታይ ዓመታትም ዓድዋን የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ቢገለጽም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሌላው ገጽታ›› በሚል ከስምንት ዓመት በፊት በዓድዋ ላይ ግንባታ ለማከናወን የታሰበው ሕንፃ ዲዛይን ይፋ ቢደረግም፣ አንዱም እውን አለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል ዋዜማ በተካሄደው ሲምፖዚየም ዲስኩር ያሰሙት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ ያኔ ቃል ተገብተው የነበሩትና ድምፃቸው ያልተሰሙ ነገሮችን ከቅሬታ ጋር እንዲህ ጠቋቁመው ነበር፡፡

‹‹ዓድዋ አካባቢ ፓርክ ይሠራል ተብሎ አልተሠራም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የዓድዋ ፓርክ ይቋቋማል ተብሎ ወዲያው ተረሳ፡፡ ዓድዋ አደባባይ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ወደ ዳያስፖራ አደባባይ ተለወጠ፡፡››

ፕሮፌሰር ባሕሩ እንደሚገልጹት፣ ለዓድዋ ድል ቦታ የሚሰጡ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ብዙ ይቀራል፡፡ ዓድዋ አካባቢ ታሪኩን የሚያሳይ በግልጽ የሚታይ የአደባባይ ሙዚየም (ኦፕን ኤር ሙዚየም) እና ሐውልት የመሥራት ዕቅድ እንዳለ ብዙ ጊዜ ቢነገርም የተጀመረ ነገር የለም፡፡ በቅርቡ የፓን አፍሪካን ስተዲስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ከተጀመረው እንቅስቃሴ ውጪ ተጨባጭ ነገሮች አይታዩም፡፡ ‹‹ምን ተሠርቷል ሲባል መልስ አይኖረንም፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ታሪኩን የሚያወሳ ነገር መገንባት እንደሚያሻ በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም በክብረ በዓሉ ወቅት በአጽንኦት እንዳወሱት፣ የዓድዋ ድልን ከማክበር ባለፈ ማስታወሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎች፣ ድሉን ዘላለማዊ ለማድረግና የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሠሩበት የሚያስችሉ ሙዚየምን ጨምሮ ልዩ ልዩ ተቋማት ይገነባሉ፡፡