አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ዘንድሮ በአራት ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ የእሳት አደጋ መመዝገቡ ተገለጸ

  • ለተጨናነቁ መንደሮች የሚሆኑ ትንንሽ የአደጋ መከላከል መኪኖች ሊገቡ ነው
  • የጎዳና ጉድጓዶች ሰለባዎች ቁጥር ጨምሯል

በምሕረተሥላሴ መኮንን

በዚህ ዓመት ባሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራት 410 አደጋዎች መከሰታቸውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ ከአደጋዎቹ 291 የእሳት ቃጠሎ ሲሆኑ፣ 119ኙ በግንባታ አካባቢና ተቆፍረው ክፍት በተተዉ ጉድጓዶች የደረሱ ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡ በአደጋዎቹ የ58 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 91 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአደጋዎቹ 107.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረትም ወድሟል፡፡ የአዲስ አበባ ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የደረሱትን አደጋዎች ለመቆጣጠር በተደረገው ርብርብ ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል፡፡

እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ፣ ከአደጋዎቹ 377 በአዲስ አበባ፤ 33 ደግሞ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ተከስተዋል፡፡ አምና የእሳትና ሌሎችም ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥር 373 የነበረ ሲሆን፣ የዘንድሮው ዓመት ሳይገባደድ ከአምናው በ37 ጨምሯል፡፡ አምና በደረሰው አደጋ 58 ሰዎች ሲሞቱ 94 ሰዎች ከባድና ቀላል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ 61.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረትም ወድሟል፡፡ የአደጋው መጠን ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ እየጨመረ መሆኑን ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የደረሰው አደጋ በቁጥር፣ በውድመት መጠንና በአደጋ ዓይነት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፤›› በማለት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አሳውቀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚደርሰው የእሳት አደጋ የነበረ ሲሆን፣ አሁን አሁን በብዛት የሰዎች ሕይወት የሚቀጠፈው በግንባታ አካባቢዎች በሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም ለግንባታ ተቆፍረው ሳይደፈኑ ክፍት በተተው ጉድጓዶች ሳቢያ ነው፡፡ ከከተማዋ ድንገተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ የሰዎች እንቅስቃሴ መጨመሩ የአደጋ ተጋላጭነትን እንዳሰፋውም አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሰው በአስተሳሰብና በኢኮኖሚ ቢያድግም የአደጋ ቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ አሁንም ውስን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከአደጋዎቹ ወደ 90 በመቶው ከጥንቃቄ ጉድለት የተከሰቱ መሆናቸው ኅብረተሰቡ ስለ ቅድመ ጥንቃቄ እምብዛም ግንዛቤ እንደሌለው እንደሚያመላክትም አክለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ አደጋ ከመከሰቱ አስቀድሞ ሊወሰዱ ስለሚባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤውን ካላሳደገ በተቋሙ እንቅስቃሴ ብቻ የአደጋ መጠኑን መቀነስ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በየቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹ በቅድመ ጥንቃቄ እንዲሁም በአደጋ መቆጣጠር ረገድ የሚሠራው ሥራ በተፈለገው መጠን ለውጥ ሊያመጣ ባለመቻሉ፣ ከከተማ እስከ ወረዳ የተለያዩ ተቋሞችና ግለሰቦችን ያማከለ የሕዝብ ፎረም እንደተቋቋመም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ኅብረተሰቡ ስለ እሳትና ሌሎችም አደጋዎች ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በበጎ ፈቃደኝነት አደጋ መከላከልን የተመለከተ ሥልጠና የሚወስዱ ወጣቶችን ቁጥር የመጨመር ዕቅድም አለ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ተቋሙ ስለ ቅድመ ጥንቃቄ ለማስተማር የውይይት መድረኮች፣ ብሮሸሮችና በራሪ ወረቀት በማዘጋጀት እንዲሁም የቴሌቪዥን መርሀ ግብር ቢያስተላልፍም ኅብረተሰቡ በሚፈለገው መጠን እየተጠቀመባቸው አይደለም፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ ስለ ቅድመ ጥንቃቄ ለመማር ያለው ዝግጁነት ያነሰ ነው፡፡ ከአደጋ በኋላ እንጂ በፊት የመጠንቀቅ ነገር የለም፡፡ የጥንቃቄ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ቢነገሩም አይተገበሩም፤›› ሲሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ቅድመ ጥንቃቄ መረጃ መስጠት በመሆኑ ተቋሙ በአዲስ ቲቪና በኤፍኤሞች ከሚያስተላልፈው መልዕክት በተጨማሪ ትምህርት ሰጪ ዘጋቢ ፊልም እያሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም መጪው ክረምት እንደመሆኑ የጎርፍ፣ የመሬት ናዳና ሌሎችም ተያያዥ አደጋዎች ሥጋት ይሰፋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

አደጋን በመከላከል እንዲሁም ከደረሰ በኋላ በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ክፍተቱ ያለው ማኅበረሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከተቋሙ አቅም እንዲሁም የአገሪቱ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስንነት ጋርም ይያያዛል፡፡ በአዲስ አበባ ያረጁ መኖሪያ መንደሮች ነዋሪዎች ከሚኖሩበት የተጠጋጋ ሁኔታና ቤቶቹ ከተሠሩባቸው በፍጥነት የሚቀጣጠሉ ቁሳቁሶችም አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡

አደስ አበባ ውስጥ አደጋ እየከሰተባቸው ያሉ አካባቢዎች ለዓመታት በአደጋ ተጋላጭነታቸው የሚታወቁ ሰፈሮች ናቸው፡፡ ያረጁ ሰፈሮች የሕዝብ ቁጥራቸው ብዙ በመሆኑና ቤቶቹም የተሠሩት በፍጥነት በሚቀጣጠሉ ቁሳቁሶች በመሆኑ በተደጋጋሚ አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡ አዲስ ከተማ፣ ቂርቆስ፣ አራዳና ንፋስ ስልክ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም አደጋ የበዛባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ ከደረሱት እሳት አደጋዎች 70 የሚሆኑት የቤት ቃጠሎ ሲሆኑ፣ የተጨናነቁት አካባቢዎች በዋነኛነት አደጋው ደርሶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በከተማዋ በግንባታ አካባቢና በጉድጓድ የሚደርሱ አደጋዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑም ተያይዞ ይነሳል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አደጋ በሚከሰትበት ወቅት በሰፈሮቹ ውስጥ ለውስጥ ገብቶ አደጋውን ለመቆጣጠር የመንገዶቹ ምቹ አለመሆን እንቅፋት ይፈጥራል፡፡

‹‹አደጋ ቦታ የመድረሻችን ጊዜ ከ3 እስከ 15 ደቂቃ መሆን ቢገባውም እንዳንደርስ የሚያግዱ ብዙ ነገሮች አሉ፤›› ሲሉ አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡ የአብዛኞቹ አካባቢዎች መንገዶች ግዙፍ የአደጋ መከላከያ መኪኖችን ለማስገባት ካለማስቻላቸው ባሻገር አደጋ ሲከሰት ወደ ሰፈሮቹ የሚወስዱ አቅጣጫዎች ለተቋሙ ሠራተኞች የሚገለጹት በተለምዶ ከሚታወቁ አካባቢዎች አንጻር እንጂ መደበኛ በሆነ አገላለጽ አይደለም፡፡ አንዳንዴ የተነገራቸውን ቦታ በመፈለግ አደጋ የደረሰበት አካባቢ ዘግይተው መድረሳቸውን እንደማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ዘልማዳዊ አካሄድ ተቋሙ ዘመን አመጣሽ በሆኑ መንገዶች ለምሳሌ በጂፒኤስ ተቅሞ መንገድ በማግኘት እንዳይሠራ ቢያግድም፣ በአዲስ አበባ የተጨናነቁ መንደሮች በሚገኙ ጠባብ መንገዶች ተላልፈው አደጋ የሚከላከሉ መጠናቸው አነስተኛ የሆነ መኪኖች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሒደት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ችግር እሳት ወይም ሌሎች አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ተቋሙ የሚገኝበትን ስልክ (939) የሚያውቁ ሰዎች ውስን መሆናቸው ነው፡፡ ብዙዎች ስልክ ቁጥሩን ልብ ካለማለታቸው ባሻገር፣ የወንጀልና ሌሎችም ድንገተኛ አደጋዎች ስልክ ቁጥሮች የተለያዩ በመሆናቸው እያንዳንዱን ለማስታወስ ይቸገራሉ፡፡ እሳት አደጋን ለማግኘት ፖሊስ ጣቢያ የሚደውሉ በወንጀል ወቅት ለእሳት አደጋ የሚደውሉ ብዙዎች መሆናቸውን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ለሁሉም አደጋዎች ወደ ተመሳሳይ ቁጥር መደወል የሚቻልበት መንገድ እየተወጠነ መሆኑንም አያይዘው አሳውቀዋል፡፡

የመንገድ ምቹነት፣ የአደጋ ጊዜ ስልክ ቁጥሮች ተመሳሳይ መሆንና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ ተቋሙ ብቻውን ሳይሆን ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር ተጣምሮ መሥራት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከሌሎች ተቋሞች ጋር በጋራ ለመሥራት የተደረጉ ጥረቶች ብዙም ስኬታማ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡  

አዲስ አበባ ከሌሎች ክልል ከተሞች በበለጠ አደጋ የሚደርስባት እንደመሆኗ (በ24 ሰዓት ውስጥ ቢያንስ አንድ አደጋ በከተማዋ ይከሰታል) በከተማዋ ያሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ስምንት ቅርንጫፎች በቂ አይደሉም፡፡ ተቋሙ ቦሌ አካባቢ 50 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀ ቅርንጫፍ እያሠራ ሲሆን፣ ንፋስ ስልክ ላይም ቅርንጫፍ ለመገንባት ቦታ ተረክቧል፡፡ ቅርንጫፍ ሳይገነባ የአደጋ መከላከያ መኪናና ሠራተኞች ብቻ የሚገኙባቸው ሰብስቴሽኖች በቦሌ ኢንዱስትሪ መንደርና የካ አባዶ አካባቢ እንደሚከፈቱም ባለሙያው አመልክተወል፡፡ ተቋሙ አሁን 1,300 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ 33 የአደጋ መቆጣጠሪያ መኪኖች አሉት፡፡ ከእሳት አደጋ በተጨማሪ በግንባታ አካባቢ የሚደርሱና ሌሎችም አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ 11 መኪኖች በግዥ ላይ ናቸው፡፡