አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ዝምታም ልክ አለው!

ሰላም! ሰላም! በገና ማግሥት ማንጠግቦሽ ያለልማዷ ሬት ሬት የሚል ቡና አፍልታ ትግተናለች። ባሻዬ ከእነ ልጃቸው ደግሞም እኔ ተሰባስበናል። “በረካውን ይደግማሉ?” ተባሉ ባሻዬ። ባሻዬ ሲመልሱ፣ “የባህሪውን ተካፋይ አንዴ ቀምሸዋለሁ። እንግዲህ በሦስት የማስረው ምን ብዬ ነው?” ብለው በቅኔ ሲመልሱ ማንጠግቦሽ ሳቋን ለቀቀችው። በሳቋ መሀል ጀበናው ገና በደንብ እንዳልተሟሸ አስረድታ ይቅርታ ጠየቀች። ባሻዬ የሦስትን አንድነት በቡና አሳበው ወደ ሥላሴ ትምህርት ሊገቡ ሲሉ ልጃቸው ተራውን መሀል ገብቶ በአንድነትና በልዩነት አሳቦ ወሬውን ፖለቲካዊ አደረገው። የዘንድሮ ሰው ፈር ሲሰጡት አትሉም? ለነገሩ ሦስቱም የየራሳቸው ዘመን ሰዎች ናቸው። ብቻ የበላነውን ነውና የምንተፋው እንዳማረልን እያጠጋጋን መተንፈስ ተፈጥሮ መሆኑን ልብ በሉልኝ። ይኼን በምን አነሳኸው ብትሉኝ መቼም ጉድ አንድ ሰሞን ነው፣ የሰሞኑን ጉዴን ላጫውታችሁ። አላፊ አግዳሚው ሕፃን አዋቂው ሁሉ በዚሁ የአንድነትና የልዩነት ግብር ተወጥሮ ሲያደርቀኝ ሰነበተ።

ሰው ሁሉ ‘ኅብረት ኅብረት’ ይለኛል። እኔ ምኑም ሊገባኝ አልቻለም። ‘‘የምን ኅብረት ነው እሱ?” ብዬ ስጠይቅ፣ “ዓደዋ ላይ ድል ያደረገው ኅብረት፣ ቀን ቆጥሮ ጊዜ አስልቶ ማይጨውን የተበቀለው ዓይነት ኅብረት…” ይሉኛል። “እኔ የምለው ግን ሰው መጀመሪያ ከገዛ ራሱ ጋር ኅብረት ሳይፈጥር እንዴት ብሎ ነው ከሰው ኅብረት የሚኖረው?” ይህን ስል ሁሉም ዳር ዳሩን ይዞራል። ለምን አትሉም? ራሱን ማየት የሚፈልገው ሰው በአቅምም በቁጥርም ቀንሷላ። አንድ ወዳጄ ምን ቢለኝ ሸጋ ነው? “የዘመኑ ሰው በገንዘብ ዙሪያ ካልሆነ ስለራሱ ማሰብ ራስን ማየት የሚባል ነገር አቅቷል፤” አለኝና ሲቀጥል፣ “በዚህ ጉዳይ ፀሐይ ሳትቀር ትንጨረጨራለች፤” አለኝ። እኔ ደግሞ ፀሐይ ሲል ሰው መስላኝ “ፀሐይ? ፀሐይ?” ማለት። ለካ በፀሐይ ዙሪያ ከሚዞሩ ፕላኔቶች ይልቅ በገንዘብ ዙሪያ የሚሽከረከሩት ፀሐይን አብግነዋት ኖሯል ስላቁ። ወይ ሰውና ፀሐይ!

ካነሳነው አይቀር አንድ ቤት መግዛት የፈለገ ዳያስፖራ ደንበኛ አጋጥሞኝ ነበር። ያው የዘንድሮ ሻጭና የገዢ ታሪክ ለእናንተ ምኑም አይነገርም። ብቻ ራሱን ሰርቆ በሰው ላትርፍ የሚለው በዝቶ ናላዬን ሲያዞረው ይውላል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከዳያስፖራው ደንበኛዬ ጋር ስንጫወት ድንገት ውሎ አድሮ አትርፎ ለመሸጥ ካሰበ በማለት፣ “ተመልሰህ ትሄዳለህ?” ብዬ ጠየቅኩት። “ፎር ጉድ ነኝ፤” አለኝ። ሰዋሰውን እርሱት። ይኼ እንግሊዝኛና መቶ ብር ዘንድሮ የሚገባበት አጥቷል። “ኧረ?” ስለው ቅስሜ እየተሰበረ፣ “ከዚህ በኋላ ምን ተብሎ ይኬዳል? አገሬን መለወጥ አለብኝ፣ የመጣሁት ወገኔን ለመቀየር ነው፤” ብሎ ብዙ አወራኝ። እንግዲህ ካወራው የማስታውሰውን ነግሬያችኋለሁ። ቀሪውን ለመስማት ትዝ ያለኝን ታዋቂ ታሪክ መርሳት ነበረብኝ።

አንዴ የባሻዬ ልጅ፣ “ዘመኑ የመረጃ ስለሆነ የታሪክና የእውቀት ወሬ ስትጀምር ‘ታዋቂ’ ብለህ አትጀምር፤” ያለኝ እዚህ በቀይ ብዕር አስምሩበት። ቀይ ብዕር ያላችሁን ብቻ ይመለከታል። እና ወሬ ሳላበዛ ታሪኳን ባጭሩ ላስታውሳችሁ። ሰውዬው መጀመሪያ ዓለምን ለመቀየር አስበው ተነሱ። አልሆን ሲላቸው ወደ አገር ወረዱ። ከዚያ እናንተም እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ወደ ታች መውረድ ነው። የዴሞክራሲ ጥማት ገደለን እያሉ ሐተታ የማዳመጥ ብቃት ያነሳቸው ስላሉ ብዬ ነው ‘ስኪፕ’ ያደረግኩት። መጨረሻ ላይ ሰውዬው የአልጋ ቁራኛ ሲሆኑ ነገሩ መሆን የነበረበት የተገላቢጦሽ ነበር። መጀመሪያ ራስን መለወጥ። ከዚያ ሁሉ ይከተላል። ባሻዬ ይኼን ታሪክ ደጋግሜ ሳጫውታቸው፣ “የለም መጀመሪያ ጽድቁንና ሰማዩን መፈለግ ነው። ከዚያ ነው ሁሉ የሚከተለው፤” እያሉ ወሽመጤን ይቆርጡታል። የወሽመጤ ርዝመቱ አይገርምም ግን?

ህልምና ወሽመጥ ባይረዝም ኖሮ እንጃ የአዳም ዘር መቀጠሉን። ብቻ እንደማየውና እንደምሰማው ከሆነ በህልም ፍቅር ጭልጥ ብሎ በእንቅልፍ የቀረው በዝቷል። የጤና ያድርግልህ እንዳትሉት እንቅልፉ እንጂ ህልሙ የጤና የሆነ ቸግሯል። አንድ ደቀ መዝሙር ነው አሉ። መምህሩ ከሚሰጡት ጥበብና ትምህርት ይልቅ በስማቸው ይመካ ነበር። እናም ተኝቶ በህልሙ መምህሩ በመላዕክት ታጅበው በአክሊልና በክብር ደምቀው አየር ላይ እየተንሳፈፉ ሲያስተምሩት ያያል። ጠዋት ተነስቶ ተጣድፎ ሄዶ ህልሙን ሲነግራቸው፣ “እስኪ ድገመውና ና…” አሉት። ቀኑን ተኛ። ማታውን አልነቃም። ህልሙ አልተደገመም። አዝኖ ወደ መምህሩ ሲጓዝ መምህሩ ፍትኃት እየተረገላቸው ደረሰ። በዚያች 24 ሰዓት በህልም ሲፈልጋቸው በገሃድ ካጣቸው መምህሩ የቀረበት ትምህርት አያስቆጭም? ብለን እንዳንቆጭ ደግሞ የእኛው እንቅልፍ ቁጭት አያሳልምምም? ወደ ጉዳዬ ስመለስ ከታች መጀመር ያለበት ለምን ከላይ ይቀርባል?

ምን ማለት መሰላችሁ? ተምሮ ተመርቆ ቀበሌ ወርዶ መልካም አስተዳደር ማስፈን ያለበት ብርቱ ንቁ ወጣት በሃያ ስድስት ዓመቴ ፕሮፌሰር ተብዬ በቴለቪዥንና በሬዲዮ ካላሰለቸኋችሁ ባዩ፣ ‘እኔና ትውልዴ ይህቺን አገር ካልተረከብን ቁልቁለቱ ይቀጥላል’ የሚላችሁ ዓይነቱን ማለቴ ነው። ይኼን ምን ትሉታላችሁ መሰላችሁ? ‘ልረከብ ማለትህ ብቻ በቂ ነው’ ነዋ። ልንጠቅ ቢልስ ኖሮ? ሆሆ! ‘ለሰበበኛ ምን መረቅ አታብዛበት’ ማለት እኮ ይኼንን ነው። አቤት ግን ይኼኔ ይኼ ተረት በእንግሊዝኛ ቢሆን ኖሮ እኮ ቃሉ አይገደፍም ነበር። እንደወረደ መናገርና ማሰብ ስንፈራ ይኼው ከዘመን ዘመን የሚዋረድብንን የአስተሳሰብ ህፀፅ ሳናውቀው ሳንገድፈው አረጀን። ማምሻም ዕድሜ ነው ግድ የለም።

ብቻ ቅድም ቴሌቪዢንና ራዲዮ ስል ባሻዬ ትዝ ብለውኛል። በቀደም እኔም ድለላዬን በጊዜ አጠናቅቄ በስንት ዘመኔ መክሰስ ልበላ ወደ ቤቴ አዘገምኩ። ጎበዝ ግን መክሰስ መብላት ማቆማችንን ልብ ብላችሁታል? ምን ነበረበበት በስሪ ዲ፣ በሰቭንዲ ቴክኖሎጂን በማስገባት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብለን ስንኩራራ ዓለም ከሚስቅብን፣ በቀን ሦስቴ የሚያበላ ጎተራ ባይኖራቸውም በቀን አራቴ የመብላት መርሐ ግብር አላቸው ብሎ ማስተዛዘኛ ቢፍቅልን? የምር! አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል የማልረግጠው የለም። ላጫውታችሁ የፈለግኩት ምን መሰላችሁ? መክሰስ ልበላ ከቤቴ ስደርስ መብራት ጠፋ። የዘመኑ ሰው ፍቅርና መብራት ተመልሶ እስኪበራ ከመጠበቅ መቼስ ለህዳሴው ግድብ በሰላም መጠናቀቅ መፀለይ፣ ፍቅር ላጡት ምሕረት መለመን ነጥብ ያሰጣል። ወዲያው እጥፍ ብዬ (ፍሬቻ ያላበራሁት መብራት ስለሌለ ነው እንዳለው አሽከርካሪ) ባሻዬ ዘንድ ሄድኩ። ስደርስ በረንዳቸው ላይ በጃኖ ተጀቡነው ሬዲዮናቸውን እየጎረጎሩ ደረስኩ። ሳያቸው አንዱንም አያዳምጡም። ጣቢያ ማሽከርከሪያዋን ወደ ቀኝ ወደ ግራ ይጫወቱባታል።

“ባሻዬ ለምን አንዱን አይተውትም? እናዳምጠው እንጂ…” እያልኩ ዱካ  አውጥቼ አጠገባቸው ስቀመጥ፣ “የሚደመጥ ሲኖር እኮ ነው?” አሉኝ። “ተው እንጂ ባሻዬ የሚደመጥ አይጠፋም። ዋናው ጆሮ ነው፤” አልኳቸው። ‘‘እንዳሻህ…’’ ብለው አንዱ ጣቢያ ላይ ለቀቁት። ባለጣቢያው አዘጋጁ ነው። ‘ይኼን ፕሮግራም ስፖንሰር ያደረጉላችሁ’ ብሎ ሰባት ደቂቃ ስፖንሰሮቹን በግጥምና በዜማ አሞካሸ። ምን ያበደ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ይሆን እያልኩ መቁነጥነጥ ስጀምር ወዲያው እጥፍ ብሎ ‘የስፖንሰሮቻችንን ማስታወቂያ ሰምተን እንመለሳለን’ ብሎ ጠፋ። ያው እሱ ያስተዋወቀን ስፖንሰሮች አንድ በአንድ በበጀታቸው ያሰሯቸውን ማስታወቂያዎች አስደመጡን። አሥራ ምናምን ደቂቃዎች ላይመጡ ሄዱ። ፕሮግራሙ ሲመለስ ባልደረባውን አስተዋውቆ ‘ዛሬ  የሚያቀርብልን ስኬታማ ሰዎች ምን ያህል ምቀኛ እንደሚበዛባቸው ያረጋገጠ ጥናት ይሆናል’ አለን። ባሻዬ ይኼን ጊዜ ትዕግሥታቸው አልቆ፣ “እናንተን ከምሰማ ባትሪ ብቆጥብ ይሻለኛል፤” ብለው ዘጉት። ኋላ ወደኔ ዞረው፣ “አጅሬ በገዛ ሬዲዮንህ የማድመጥ መብት አለህ። በሰው ጆሮ አስታኮ መስማት ግን ዕድሜ ለፀሐዩ መንግሥታችን ድሮ ቀረ፤” ሲሉኝ ከት ብዬ ሳቅኩ። በሰው አፍ ለፍላፊው፣ በሰው ወርቅ ደማቂው፣ በሰው ጆሮ አድማጩ በዝቶ ቢያቅራቸው ነዋ። ወይ ባሻዬ!

እንሰነባበት መሰለኝ። ዕድሜም ነው መሰለኝ እንጃልኝ፡፡ መስከረም ከጠባ አንስቶ ዝምታ ምቾቴ ሆኗል። ለወትሮው ስከራከር፣ ስተች፣ ሳጥላላ፣ ሳደንቅ፣ ስወድ… የሚያውቁኝ ሁሉ ‘አንበርብር ፈዘዘ’ እያሉኝ ነው። አድማጭ በሌለበት ማውራት ጩኸት ሆኖብኝ ብቻ እንዳይመስላችሁ። እርግጠኛ መሆን፣ ከእኔ እምነትና አስተሳሰብ ውጪ ሌላው ላሳር ብሎ ድምዳሜ ፍርኃት እየለቀቀብኝ ስለቸገረኝ ነው። ዕድሜም መሰለኝ ያልኳችሁ ይኼንን ነው። ልኩን የማያውቅ ካልሆነ ዕድሜ በበኩሉ በዘመን በዘመን ልክን ከማስመር ቦዝኖ አያውቅም ባይ ነኝ። የምሬን ነው። ሲኩል በልክ፣ ሲድር በልክ፣ ሲሰጥ በልክ፣ ሲነሳ ለልክ እንደሆነ እኔ የዕድሜ አንዱ ምስክር ነኝ። ዕድሜም ሰውም መክሮት ልኩን የሚያልፍ ሲገጥማችሁ ዝምታ፣ የትኛውም ሚዲያ ያላስተዋወቀው ምቹ ፍራሽ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ከባሻዬ ልጅ ጋር ትናንትና አንድ ሁለት እያልን ስንጨዋወት ይኼን ስሜቴን ነግሬው፣ መቼም እሱ አያመጣው የለም ሰምቶኝ ሰምቶኝ፣ “ዝምታም ልክ አለው፤” ሲለኝ ደነገጥኩ። ጥበብ አብስትራክት በሆነበት ጊዜ ጥበብ ነው ብዬ መናገር ቢከብደኝም ‘ሚዛን ጠብቆ ተጫዋች ያድርጋችሁ’ መመረቁ ጥበብ መሰለኝ። አሜን ነው?! መልካም ሰንበት!