ዝንቅ

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከጥቅም ውጪ የሆኑ ጎማዎች በዚህ መልኩ አረንጓዴ ቦታዎችን ማስዋቢያ ሆነዋል፡፡ አካባቢን በመበከል የሚታወቀው የተበላሸ ሲዲም ለፒኮኳ ጌጠኛ ላባ ሆኗታል፡፡  

የተገላቢጦሽ

ነጎድጓዳማ ድምፀት

የከበደ ድምነት ጭነት

የሳት ጅራፍ ጩኸት

የቀለማት ኅብረት

የጉርምርታው ክብደት

በነፋሱ ሳቢያ የዕፅዋት ስግደት

በድብደባው ብዛት

እነ ሰማይ ሰማያት ዕንባቸውን

ማንባት

እነ ጣራ ደግሞ በሰማያት ልቅሶ

ት-ጥብ-ጥብ እያሉ

እልልታን አክለው ሐሴትን አደረጉ፡፡

አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ፣ጨለማን ሰበራ፣ (1997 ዓ.ም.)

* * *

የካንሰር ታማሚዋ የመሞሸር ፍላጎት

የ28 ዓመቷ ኪው ሜይ ቺን የጡት ካንሰር በመታመሟ ጋብቻ አልቀናትም፡፡ ሆኖም ሁሌም ማግባትን ትመኛለች፡፡ የትዳር አጋር ባታገኝም የመሞሸር ምኞቷን ለማሳካት ብቻዋን የሙሽራ ልብስ ለብሳ ፎቶ ተነስታለች፡፡

ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ ቺን ታይዋን ከሚገኘው ቤቷ ሆና የሙሽራ ልብስ በመልበስ የተለያዩ ፎቶዎቿን ስትነሳ ‹‹ሁሌም የትዳር አጋር አገኝ ይሆን፣ ፎቶስ ይኖረኝ ይሆን እያልኩ አልም ነበር፡፡ ሆኖም የመጣ የለም፡፡ በመሆኑም ህልሜን ለማሳካት ብቻዬን ፎቶ መነሳት መርጫለሁ፤›› ብላለች፡፡

ኬሞቴራፒ በመውሰድ ላይ የምትገኘውን ወጣት የማግባት ፍላጎት ዘገባ የሰሙ ለወጣቷ የተለያዩ መልካም ምኞቾችን ተመኝተዋል፡፡ አብዛኞቹም ጤናዋ ተመልሶ እውነተኛውን ትዳር ትመሠርት ዘንድ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

* * *

የጃፓኗን ልዕልት ንጉሳዊ ቤተሰብነት ያሳጣ ጋብቻ

በጃፓን የንጉሳዊ ቤተሰብ የሆነችው ልዕልት ማኮ ከንጉሣዊ ቤተሰብ ውጪ ካለና በዝቅተኛ ድርጅት ውስጥ ከሚሠራ ጓደኛዋ ጋር በመጋባቷ በንጉሣዊ ቤተሰብነት የሚሰጣትን ሥፍራ አጥታለች፡፡ የ25 ዓመቷ ማኮ የ25 ዓመቱን ኪ ኮሙሮ የተዋወቀችው አብረው ሲማሩ ነበር፡፡ የጃፓን የንጉሥ ሕግ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ከመደበኛው ነዋሪ ካገቡ ከንጉሣዊ ቤተሰብ እንደሚወጡ ማስቀመጡን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡ ልዕልት ማኮ የንጉሥ አኪቶ የመጀመሪያ የልጅ ልጅ ናት፡፡

* * *

ሕገወጥ የአውራ ዶሮ ድብድብን ለማስቀረት ሰባት ሺሕ ዶሮዎች ተሰበሰቡ

በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት ባለሥልጣናት ሕገወጥ የአውራ ዶሮ ድብድብን ለማስቀረት ባደረጉት ዘመቻ ሰባት ሺሕ አውራ ዶሮዎችን መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኤንቢሲ ኒውስ በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ቁጥር ነው ያላቸውን አውራ ዶሮዎች የሰበሰበው በሕገወጥ መንገድ በሚካሄደው የዶሮዎች ድብድብ የሚሞቱና የሚጎዱ ዶሮዎችን ለመታደግ ነው፡፡

የሞቱና የተጎዱ ዶሮዎች፣ መርፌ፣ ሕገወጥ እፅ እንዲሁም ለዶሮ ተብሎ የተዘጋጀና ጥንካሬን የሚሰጥ መድኃኒት አብሮ ተይዟል፡፡ በካሊፎርኒያ ገጠራማ አካባቢ የአውራ ዶሮ ድብድብ የሚያደርጉ፣ የሚቆምሩና ለዚሁ ብለው ዶሮ የሚያረቡ አሥር ሰዎችም መታሰራቸው ተዘግቧል፡፡

* * *