የሕግ ያለህ የመንግሥት ያለህ!

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የሚታየው ውጥንቅጥ ለአላፊና አግዳሚው ስጋትና ሰቀቀን የሆነው ሥርዓት አልበኝነት፣ የሕግ ያለህ የመንግሥት ያለህ ያስብላል፡፡ በየጎዳናው፣ በየአውራው መንገዱ የሚታየው ትርምስር ሥርዓት ያለው ሕዝብና መንግሥት የሚገኝበት አገር አይመስልም፡፡

በየፊናው እንዳሻው መንገድ አጣብቦ የሚሸቅጠው፣ መንገድ  አጥሮና  ዘግቶ ሕንጻ የሚገነባው፣ ስንት የተለፋበትን መንገድ ንዶና ገንድሶ የራሱን የሚያስተካክለው ስንቱ የዚህ ዘመን ሰው፣ ሰው ይታዘበኛል፣ ፈጣሪ ይቀየመኛል ማለቱን ቢተው እንኳ ምነዋ ሕግና መንግሥት ባሉበት አገር ሃይ ባይ መጥፋቱ ያሰኛል ነገረ ሥራው፡፡  በመንገድ ዳር፣ ያውም በየጊዜው እየጠበበና መጠኑና ስፋቱ እየተቀነሰ የመጣውን የእግረኞች መንገድ የሚያጣብቡ፣ ሸቀጣሸቀጥ የሚቸበችቡ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች እንደ ቀድሞው ተገቢው የመነገጃ ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲነግዱ ቢደረግና፣ ከሚያጨናንቋቸው መንገዶች ገለል እንዲሉ ቢደረግ እነሱንም እግረኞችንም ከአደጋ መታደግ በሆነ ነበር፡፡

አያድርገውና እንደ ሌሎች አገሮች ከተሞች ሕዝብ እንዲህ በሚተራመስባቸው መንገዶች ላይ አደጋ ጣዮች ሊያደርሱ የሚችሏቸውን አደጋዎችም መቀነስ ያስችል ነበር፡፡ በተለይ የሥራ  መውጫ ሠዓት ሲቃረብ እየጠበቁ፣ በዋና ዋና መንግዶች ላይ የሚዘረጉ ሸቀጦችንና የንግድ ግርግሮችን በመሸሽ፣ መተላለፊያ በማጣትም ጭምር ወደ መኪና መንገድ የሚገቡ በርካቶች መሆናቸው እየታየ ዝም መባሉ አስገራሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

እግርኛውን እንዲህ ከሚጋፉት ያልተገቡ የጎዳና ላይ ንግዶችን መቆጣጠር ካለመቻል ባሻገር በጠራራ ፀሐይ የትራፊክ መብራት ጥሰው የሚፈተለኩ ተሽከርካሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውም አስገራሚ የአዲስ አበባ ከተማ የቀን ተሌት ተግባር እየሆነ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ትራፊክ አየኝ አላየኝ ማለቱም እየቀረ የመጣ እስኪመስል ድረስ ሕግ ዋጋ ያጣበት፣ ሰዎች ሕግ አስከባሪም መሸሽ ያቆሙበት ወቅት ላይ የምንገኝ ይመስላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተስፋፉት አዳዲስ መንገዶች መካከል ሕግ የማያውቃቸው እንቅስቃሴዎች እየታዩበት የሚገኘው ከለቡ ወደ ቃሊቲ የሚወስደው አዲሱ መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በጣም ሰፊና ምቹ በመሆኑ ምክንያት ተሽከርካሪዎች ያለ ችግር በፍጥነት እንዲጓዙ አሰስችሏቸዋል፡፡ በፍጥነት መጓዛቸው ከወሰን በላይ እስካልሆነ ድረስ ተቃውሞ አይቀርብም፡፡ ይሁንና ግን በመኪኖቹ መንገድ የሚመጡትና የሚሔዱት በፈረስ ተጎታች ጋሪዎች እንዳሻቸው በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ መኪኖቹ መምጣታቸው ግን አስፈሪና አሰቃቂ ነው፡፡

እንዳሻቸው እየጋለቡ የሚመጡት መኪኖች በተለይ ከባድ መኪኖቹ ድንገት ከየመንደሩ የሚመጡባቸውን ጋሪዎች ለመታደግ፣ ከእነሱም ጋር ላለመጋጨትና አደጋ ላለማድረስ በሚደረግ ትንቅንቅ ሊደርስ የሚችለው ያልታሰበና ያልተፈለገ አሰቃቂ አደጋ ከወዲሁ ሊታብበትና መትፍሔ ሊበጅለት ይገባል እላለሁ፡፡

መንግሥት ባለበት፣ ሕግና ሥርዓት በተሠራበት አገር የሚመለከተው ሕግና ሥርዓት አስከባሪ የግዴታውን መወጣት አለመቻሉ በሕግ እንደሚያስጠይቀው ብቻም ሳይሆን ለሚደርሰው አደጋና ሰቆቃም ጭምር መጠየቅ እንደሚገባው መታወቅ አለበት፡፡ እንዲህ ያለ የምን ቸገረኝና የቸልተኝነት አዝማሚያ በርካታ ጥፋትና ጉዳት እያስከተለ መሆኑም ሊታይ ይገባዋል፡፡ በአገሪቱ ለሚታየው፣ መጠነ ሰፊ የሥነ ምግባር ዝቅጠት አንዱ መገለጫ እንዲህ ያለው ሙስና ይመስለኛል፡፡ ሙስና ገንዘብ ማጭበርበር፣ ጉቦ መቀበል ብቻ ሳይሆን እንዲህ ባለው ሁኔታ ኃላፊነትን አለመወጣትም ጭምር በመሆኑ የጥልቅ ተሃድሶ ስብሰባዎች እንዲህ ባለው ጉዳይም ላይ በጥልቅ ቢካሄዱና በጥልቅ ውጤት ቢያመጡ የሚጠላ የለም፡፡

የሆነ ሆኖ ጎዳናዎች ሥርዓት ኖሯቸው፣ እግረኛውም ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ፣ አሽከርካሪውም ለእግኛ ቅድሚያ ሰጥቶና አክብሮ፣ ነጋዴውም በተፈቀደለት ቦታ በመነገድ ያበዱ ከብቶች የሚተራመሱባት ከተማ የመሰለችውን አዲስ አበባችን እንቀይራት ዘንድ ሁሉም በህሊናው ይመራ፡፡ ሁላችንንም የሚገዛንና የሚያስማማን ሕግ ነውና፣ ለሕግ ቅድሚያ እንስጥ፡፡

                  (ሽብሬ ስማቸው፣ ከአዲስ አበባ)