አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የሪፐብሊኩ 21ኛ ዓመት ላይ ለዴሞክራሲ የሚስማማ የመንግሥት መሠረት አለን ወይ?

በሲሳይ ገላው

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሪፐብሊክ ካቋቋመች፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሏል ከተባለ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ እነሆ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ሃያ አንደኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡ ሥጋ በለበሰ በተፈጥሮ ሰው ወይም ዜጋ ዕድሜ ቢሰላ፣ የምርጫ ሕጋችን በምዝገባው ዕለት ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነው ሰው ለመምረጥ ብቻ ሳይሆን ለመመረጥ ለዕጩነት የሚያበቃ የዕድሜ መመዘኛ ስለሚያሟላ፣ ሪፐብሊካችን 21ኛ ዓመት ሞላው ማለት ተራ ‹‹ክብረ በዓል›› አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውልና ሪፐብሊኩ ሲመሠረት (ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም.) የተወለደ ሕፃን ዛሬ ከ21 ዓመት በኋላ ለመመረጥ መብት የበቃ የሪፐብሊኩ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚችል ሰው ነው ማለት ነው፡፡

ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ሪፐብሊክ በሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያው አንቀጽ መሠረት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ደግሞ ከብዙ አማራጮች ውስጥ ለመምረጥ በማስቻልና የመንግሥት አስተዳደርንና የሕዝብ ተቀባይነትን በማቀራረብ እስከ ዛሬ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሥርዓት ነው፡፡ ከጥንታዊው ዴሞክራሲ ወዲህ በዓለም ውስጥ ህያው ሆኖ ያለ ዴሞክራሲ ደግሞ የከበርቴው ዴሞክራሲ ነው፡፡ የከበርቴውን ዴሞክራሲ ሙዚየም እከተዋለሁ ብሎ የተነሳው ‹‹ሶሻሊስት ዴሞክራሲ›› ከሽፎ ራሱ ሙዚየም ገብቷል፡፡ ዛሬ ከከበርቴ ዴሞክራሲ ውጪ የሆነ ሌላ የዴሞክራሲ ሥርዓት የለም፡፡ በከበርቴ ዴሞክራሲ ክልል ውስጥ ፓርቲዎች ዝርዝር የዓላማና የትኩረት ልዩነቶች እንዳላቸው ሁሉ፣ ከፓርላማ ወንበር ጋር በተያያዘ የፓርቲዎች ሥልጣን አቀማመርና በመሳሰሉት ላይ ልዩነት አላቸው፡፡ በዚህና ከእነዚህ ልዩነቶች ጋር በተገናኘ ምክንያት የዴሞክራሲውም አደረጃጀት የተወሰኑ ልዩነቶች ይታዩበታል፡፡

አንዳንዶች በከበርቴው ጥቅም ላይ ይበልጡን ሲጣበቡ፣ ከእነዚህ ፈንጠር ብለው በከበርቴውና በደሃው መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚሹና ከፓርቲዎች ጨዋታ ባሻገር ሰፊ አሳታፊነት ያለውን የዴሞክራሲ አወቃቀር የሚመርጡ አሉ፡፡ በከበርቴው፣ በሊበራል ዴሞክራሲ ውስጥ የምናገኛቸው ‹‹ወግ አጥባቂ››፣ ‹‹ሶሻል ዴሞክራሲ››፣ ‹‹ሶሻሊስት››፣ ወዘተ. የሚባሉ ፓርቲዎች ሁሉ የዚህ ዓይነት በአንድ የዴሞክራሲ ቤት ውስጥ ያሉ ልዩነቶች መግለጫዎች ናቸው፡፡ ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ወግ አጥባቂው ከሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጋር መንግሥት ሲመራና የሶሻሊስት ፓርቲ በሊበራል ዴሞክራሲ ውስጥ ተወዳድሮና አሸንፎ መንግሥት ላይ ሲወጣ ማየት አስገራሚ የማይሆነውም ለዚህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉም ሆነ ሥርዓቱ ምንም ዓይነት ቅጽል የሌለው፣ እንዲያውም በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት የ‹‹ነጭ ካፒታሊዝም›› ዴሞክራሲ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊብራል ዴሞክራሲ የሚለው ልዩነት በከበርቴው ዴሞክራሲ ክልል ውስጥ ያለ ቆዳዊ ልዩነት ነው፡፡ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ማስረጃ ተደርገው የሚቀርቡት እንደ የብሔሮች ጉዳይ፣ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ የመንግሥት የልማት ሚና ሁሉ የዴሞክራሲውን ዓይነት በሕገ መንግሥቱ ከታቀደውና ከታወቀው ውጪ የሚያደርጉ፣ ልንመሠርተውና ልናበለፅገው የሚገባንን ዴሞክራሲ የከበርቴው ዴሞክራሲ ከመሆን የሚያስቀረው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ብሔሮችን አውቆና አክብሮ የመያዝ ነገር ማንም ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች ሊያመልጡት የማይችሉት የኢትዮጵያ እውነታ ነው፡፡

ሃያ አንደኛ ዓመታችን መዳረሻ ላይ ሆነን የምናነሳው ጥያቄም የትኛው ዓይነት ዴሞክራሲ ይሻላል? አብዮታዊ? ወይስ ሊብራል? ልማታዊ? ወይስ የከበርቴው? የሚለው ሳይሆን እውን አገራችን ከዚህ ሥርዓት ጋር ተገናኝታለች? ዴሞክራሲን እየገነባሁ ነው ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ያለኔ የለም የሚለው፣ እኔን ምረጡ ብሎ እነሆ ሲመረጥ፣ ሲመረጥ፣ ሲመረጥ የኖረው ኢሕአዴግ ዕውን የሚለውን እያደረገ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ የሚስማማ የመንግሥት መሠረት አላት ወይ? ነው፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ህልውና የየትኛውም ፓርቲ ያልሆነ ዓምደ መንግሥት (STATE) ከማደራጀት ተነጥሎ አይታይም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ተስፋ መውጫ የሌለው ጐሬ ውስጥ የተቀረቀረው ገና ኢሕአዴግ የመናጆ ኮንፈረንስና ምክር ቤት አደራጅቶ የገዛ ራሱን ሠራዊት የሽግግር መንግሥቱ የመከላከያ ኃይል ማድረግ በቻለ ጊዜ ነው፡፡

እርግጥ ነው በነባሩ የጦርና የፀጥታ መዋቅር ላይ ኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ሆኜ ልቀመጥ ማለት አይችልም ነበር፡፡ አንደኛ መዋቅሩ ፈራርሷል፡፡ ሁለተኛም ባይፈራርስም የቂል ሥራ ይሆንበት ነበር፡፡ ይህ እውነት መሆኑ ግን ነባሩን አፍርሶ የራሱን የፀጥታ ኃይልና ሠራዊት መንግሥታዊ ማድረጉን ትክክል አያደርገውም፡፡ የሰኔው 1984 ዓ.ም. ኮንፈረንስና የተቋቋመው ምክር ቤት ሁሉንም ቡድኖች ያካተተ ሊሆን ይችል እንደነበር ሁሉ፣ የአገሪቱ የፀጥታና የመከላከያ ኃይል እንደ አዲስ መደራጀት ከአንድ ቡድን ፍላጐት የተላቀቀ አገራዊ አደራ ሆኖ ሊካሄድ ይችል ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ጠንክሮ የሚታገል አልነበረም፡፡ የኢሕአዴግም ፍላጐት አልነበረም፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግን ሠራዊት የሽግግር መንግሥት ሠራዊት አድርጐ ከመያዝ ቋሚ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ማደራጀት ሲገባም ዞሮ ዞሮ የኢሕአዴግ ሠራዊት፣ በተለይም የሕወሓት ሠራዊት ግንድ መሆኑ አልቀረም፡፡ ፀጥታንና ፖሊስን በማደራጀት በኩልም ቢሆን ኅብለሰረሰሩሞ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነበር፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ኅብለሰረሰርነት በዓመታት ሒደት ውስጥ የሚቀንስ ሆኖም አልተደራጀም፡፡ ይኸው በ21 ዓመታት የሥልጣን ዘመን ውስጥ በመሠረቱ የተቀየረ ነገር የለም፡፡ አለመቀየር ብቻ ሳይሆን ሕወሓት ተሰንጥቆ የአንደኛው ቡድን በአሸናፊነት ሲወጣ የፀጥታና የመከላከያ ኃይሉን በአመራርና ‹‹በወቅታዊ ግንዛቤ በማስጨበጥ›› ለራሱ እንደሚታመን አድርጐ የማስተካከል ሥራ ተሠራ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የተከሰተው አደጋም የፓርቲውን የዕዝና የአመለካከት ቀፍዳጅነት የሚያጠናክር ሹም ሽርን፣ ምንጠራንና አጠባን ያካተተ ተሀድሶ ተካሂዷል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል በማለት ይደነግጋል፡፡ የመከላከያም ሆነ የፖሊስ ሠራዊት ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጣ ገጽታ ያለው መሆኑና በጥቅል ቁጥር ውስጥ አውራ የሚባለው የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ቁጥርና ድርሻ ያነሳ መሆኑ ፈጽሞ የማያጠራጥር እውነት ነው፡፡ የበላይነት ለማስፈን ግን በቁጥር መብለጥ አስፈላጊ አይደለም፡፡

ለመከላከያና ለፀጥታ ኃይል የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆንና የፓርቲ ሥራ ማካሄድ የተከለከለ ይሁን እንጂ፣ አውታሩ እንዳለ በገዥው ፓርቲ አመለካከት የተጠረዘ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ የውስጡን ዝርዝር መናገር ባይቻልም፡፡ ጠቅላላ ኅብረተሰቡን በአንድ ፓርቲ (የኢሕአዴግ) አመለካከት ለመጠረዝ የሚለፋ ቡድን ዋናው የሥልጣን መሣሪያ ላይ የበለጠ ትኩረት ከማድረግ እንደማይመለስ ግልጽ ነው፡፡ ከሎጂካዊ ወይም አመክኖአዊ ግምት ያለፉ ነፀብራቆችንም ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ‹‹ሥርዓቱን/ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅ ኃላፊነት››፣ ‹‹የአገሪቱን ሰላም ከውጭ ጠላት፣ ከፀረ ሰላሞችና ከአሸባሪዎች መጠበቅ›› ለዚህም በየጊዜው የአሪቱን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማስገንዘብ የኢሕአዴጋዊ አጠባ ግልጽ መንገዶች ናቸው፡፡

በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በየዜናው መዋቀሩንና መኖሩን የምንሰማለት የአንድ ወይም የሌላው ተቋም ‹‹የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክቶሬት›› ራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ ኢንዶክትሪኔሽን ማለት እምነትን ቀኖናን (ዶክትሪን) ወይም አይዲዮሎጂን በሥርዓትና በሥልት ማስተማር ብቻ አይደለም፡፡ ነፃ እሳቤን፣ ሌላ ዝንባሌን ከመከላከልና ከመከልከል ግብ አንፃር ማስተማር ማለት ነው፡፡ በየምርጫ ዙሩ በሠራዊቱ ውስጥ የድምፅ መስጠት ውጤት የኢሕአዴግ አመለካከት ምን ያህል ገዥ እንደሆነ መፈተሻም ነው፡፡ ከፀረ ሰላምና ከሥርዓት ቀልባሽ የሚቆጠር ወይም እንዲቆጠር የሚፈለግ ተቃዋሚ በወታደሩ ዘንድ የረባ ድምፅ ቢያገኝ በዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የተከተለው ተሃድሶ የዚህ ውጤት ነው፡፡ ሕወሓት በአንጃ በተከፈለበት ጊዜ አሸናፊው ወገን እንኳንስ በመከላከያና በፀጥታው አውታር ይቅርና የተቃራኒ አንጃ ዝንባሌ ባሳዩ ጭፍራ ፓርቲዎች ጭምር የማፅዳት ሥራ አከናውኗል፡፡

ደደቢት የስፖርት ማኅበር ነው፡፡ የስፖርት ክበብ ነው፡፡ ደደቢት ቡድንና ‹‹ባለ ሰላማዊው ዓርማ፣ የደደቢት ድል ዜማ፣ ካጽናፍ አጽናፍ ተሰማ›› የሚለው ዝነኛ ዝማሬው የሕወሓት ተጋድሎ ተምሳሌት ነው፡፡ የዚህ ቡድን ድል በድል እየሆነ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘትና የዝማሬው መገናኘት በተዘዋዋሪ የሕወሓት ተጋድሎን ሞገስና ዝና የማቀዳጀትም ምልክት ነው፡፡ ይህን የመሰለ አብነት ያለው የደደቢት የእግር ኳስ ቡድን በመከላከያ ሰዎች የሚመራና በዋነኛነት ከሠራዊቱ በሚገኝ የገንዘብ ምንጭ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ምንም ዓይነት ክፋትና ጥፋት የለበትም፡፡ ማሳየት የፈለግሁት፣ እደግመዋለሁ ይህን የመሰለ አብነት ያለው የእግር ኳስ ቡድን በመከላከያ ሰዎች የሚመራና በዋነኛነት ከሠራዊቱ በሚገኝ የገንዘብ ምንጭ የሚንቀሳቀስ መሆኑ፣ ስለዚህም መከላከያ ሠራዊቱ የቱን ያህል ኢሕአዴጋዊ እንደሆነ የሚያሳይ ቀላል ምሳሌ መሆኑን ነው፡፡

ተቃዋሚ በጠራው ስብሰባ ላይ የወታደር/የፖሊስ አባል እንደ ተሰብሳቢ መገኘት ከዓላማና ከራስ ጋር የመጣላት ያህል መሆኑ በተቃራኒው በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ ላይ መገኘት ግን በመንግሥት ስብሰባ ላይ ከመገኘት እጅግም ተለይቶ አለመታየቱና አለማስደንገጡ፣ እንዲያውም የድርጅት ልደት ዓይነት ክብረ በዓላዊ ሁኔታና አጋጣሚ ላይ መለዮን ገጭ አድርጐ መሳተፍ ከነውር አለመቆጠሩ፣ ለኢሕአዴግና ለመንግሥት ተግባር መታመን የቱን ያህል እንደተሳከረ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ያለውን ግንኙነትና ዝምድና የሚባርክበትና የሚመራበት አንድ የታወቀ መፈክር አለው፡፡ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር የሚል፡፡ ይህ ግን ለኢሕአዴግም ይሠራል፡፡ የሕግ የበላይነት ዋናው ትርጉምም ይኸው ነው፡፡ ከሕግ በላይ ሆኖ ለሕግ የበላይነት መታገል አይቻልምና፡፡ ኢሕአዴግ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር የምርጫ ሥነ ምግባር ድርድር ሲያደርግና ከእሱ ጋር በተያያዘው መግባቢያ ላይ መከላከያንና ታጣቂ ኃይሎችን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን ከማስቀመጥ በላይ አልፎ ሄዶ፣ ከየትኛውም ቡድን ገለልተኛ ናቸው የሚል ስምምነት ላይ ሊደርስ ያልቻለው፣ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ በነበሩ የ2002 እና የ2007 ዓ.ም. ምርጫዎች ከተቃዋሚዎች ጋር ባደረጋቸውም ክርክሮችም ውስጥ ስለመከላከያ የአገር ሉዓላዊነትና ሰላምን የማስከበር አኩሪ ዝና ከማውሳት አልፎ ስለገለልተኛነቱ መከላከል ያልቻለው፣ ወይም ዴሞክራሲያችን የተቋቋመው ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ነው ማለት የማይችለው ሀቁ በአፍ ስለማይጋረድ ነው፡፡

የመከላከያ ወይም የፖሊስ አባል ወይም ዳኛ ሆኖ የፓርቲ አባል ያለመሆን ደንብ ኢሕአዴግን በተመለከተ የሌለ ያህል ነው፡፡ የፓርቲ ካርድ ወይም የአባልነት መታወቂያ ኖረም አልኖረም ዋናው ጉዳይ ለገዥው ቡድን መታመን መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎችን ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረ ገጽ የሚገኘው የክቡር አቶ አባዱላ ካሪኩለም ቪቴ ይህንን አሳምሮ ያሳያል፡፡ ከኢሕአዴግ አመራር አባልነት፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በጄኔራልነት (ማዕረግ)፣ ከፍተኛ ሹም እንደገና ጄኔራልነቱን ለቅቆ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87 እንደተደነገገው የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ስለሆነ ለመከላከያ ሚኒስትርነት ያደረጉት ጉዞ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ዘንድ የፓርቲ ካርድ በቀላሉ ሊነሳና ሊጣል የሚችል መሆኑንና ዋናው ጉዳይ ያለው ካርድ ላይ ሳይሆን ፖለቲካዊ ታማኝነት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከመከላከያና ከፀጥታውም ውጪ ያሉት መንግሥታዊ አውታራት በጠቅላላ በኢሕአዴግና በአጋር ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች የተጥለቀለቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በድርጅታዊ ሰንሰለት በመንግሥታዊ ስብሰባና በሚዲያ የሚናኝ የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››ን (የኢሕአዴግን ገዥነት) መተኪያ የለሽ የሚያደርግ ተቃዋሚዎችን ቀልባሽ፣ ሕገ መንግሥት አፍራሽ፣ የሰላምና የሕዝብ ፀር አድርጎ የሚያቀርብ አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ አብሮ ተዘርግቷል፡፡ ይህም ሥራ የማግኘትና በሥራ የመቆየት፣ የዕድገትና የሹመት እንዲሁም ሌሎች ጥቅሞችንና ዕድሎችን ከፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት ጋር ያጣበቀና ሁሉንም (ነባሩም፣ አዲስ መጡንም፣ ገና በትምህርትና በሥልጠና ላይ ያለውን) በሚሊዮኖች ያጥለቀለቀ ክንዋኔ ነው፡፡ ሒደቱ ብልጥ ለብልጥ የሚባባሉበት ዓይነት ነው፡፡ ተመልማይ አባልነቱን ለጥቅሙ መሣሪያ ለማድረግ እንደሚሻ ሁሉ፣ መልማዩም ድርጅት ኢሕአዴጋዊነትን በተግባር አሳይ ይላል፡፡ በዚህም ተመልማይ ቢወድም ቢጠላም የፖለቲካ ሎሌነት ሥራው የሚያጋጭና የሚያስተዛዝብ ተግባር ውስጥ እየነከረው በዚያው እንዲቀልጥ ያደርገዋል፡፡

በሌላ አነጋገር ኢሕአዴግ ከነጭፍሮቹ በየአምስት ዓመት ምርጫ መንግሥትነት ‹‹የሚሾም›› ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት (State) ሆኖም ተደራጅቷል፡፡ የአገሪቱ መከላከያ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግንም ከመውደቅ የሚጠብቅ ኢሕአዴጋዊ ሠራዊት ነው፡፡ የደኅንነት አውታሩም የአገሪቱን ደኅንነት እንደሚጠብቅ ሁሉ ለኢሕአዴግም ደኅንነት ጠባቂ ነው፡፡ እንዲያውም አገር የመጠበቅ፣ ሉዓላዊነት የማስከበርና ለአገር ደኅንነት ዘብ የመቆም የተቋማቱ ቅኝት የተቃኘው ከፓርቲው ጥበቃ ማዕዘን አኳያ ነው፡፡

ዴሞክራሲ ገንብተናል፣ ፍትሕ አስፍነናል የምንለው እነዚህንና እነሱን በመሳሰሉ እውነታ ላይ ሆነን ነው፡፡ በዚህ እውነታ ላይ እንኳንስ ፍትሕና ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትንና የሕግ ማስከበር፣ በሕግ የመተዳደር ተራ ሕይወት እንኳን መኖር አይቻልም፡፡ የማይቻልባቸውን ምክንያቶች በአጭሩ እንዘርዝር፡፡

  1. አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ገዢ ቡድን መንግሥታዊውን የጉልበት ኃይል (ወታደራዊና የፀጥታ አውታሩን) ታማኝ መሣሪያው አድርጎ ካነፀ በማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ተራ ሰው ላይ በማንኛውም ቡድን (ሸሪክም ሆነ ተቃዋሚ) ላይና በየትኛውም አካባቢ መንግሥት ላይ አዛዥና ናዛዥ የመሆን ጉልበት ይሰጠዋል፡፡ ይህ ባለጉልበትነቱ በማንኛውም ወገን ላይ ፍርኃት ያሳድራል፡፡ ፍርኃቱ ደግሞ ከሕግ የበላይነት፣ ከነፃ ዳኝነትና ከዴሞክራሲ ጋር ይጣላል፡፡
  2. ለተገኘው ድል ሁሉ መሠረት እኔ ነኝ፣ ሕዝባዊና ልማታዊ እኔ ብቻ ነኝ፣ መካከለኛ መደብ እስኪበዛ የኔ በሥልጣን መቆየት የግድ ነው፣ የእኔ መውረድ የአገሪቱ መበጥበጥና የዱሮውን ሥርዓት መመለስ ነው፣ ከተቃዋሚዎች ጋር የጋራ መግባባት መፍጠርና አብሮ መሥራት የማይቻል ነው፣ የሚለው በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ መቆየትን ለኢሕአዴግ ብቻ ተገቢና የግል ንብረት የሚያደርግ፣ ይህን ሥልጣን የሚከጅሉ ተቃዋሚዎችን በጠላት ዒላማ ውስጥ የሚያስገባ ርዕዮተ ዓለምና ፖለቲካ ለመንግሥት ጡንቻ መዘርጋት ሌላው ፀር ነው፡፡
  3. ፀርነቱ በቃላት የሚዥጎደጎድ ብቻ አይደለም፡፡ በተግባርም የሚሠራ በአጠቃላይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲዎችንና መንግሥታዊ ቢሮክራሲውን (እስከ መጨረሻው የከተማና የገጠር ቀበሌ መዋቅር ድረስ) እንዲሁም ቅጣይ የሲቪክ ማኅበራትን (የወጣት፣ የሴት፣ የመምህራን፣ ወዘተ) ሥጋና ደም አድርጎ የተዘረጋ፣ ተማሪውን፣ ገበሬውን፣ ሴቱን፣ የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ሥራ አጡን፣ ነጋዴውን ሁሉ የተበተበ አሠራር ነው፡፡ ትብትቡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚዎች እንደ ልብ ሕዝብ ዘንድ እንዳይደርሱ፣ ድምፃቸው እንዳይሰማና ማስፈራሪያ እንዲሆኑ በግልጽና በስውር ይሠራል፡፡

መንግሥታዊ የሥራ፣ የዕድገት፣ የምግብ ለሥራ፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ መብቶችን ሁሉ በመደለያነትና በመቅጫነት መጠቀም የሐሰት መረጃ በማቀናበር ወይም ማሳበቢያ የሚሆን ጥፋት ፈልጎ፣ ወደ ጥፋት መርቶና አጥምዶ መወንጀል፣ ማሰር፣ በሕግ ሽፋን ሊጠመድ ያልቻለውን ወይም የዚያ ዓይነት ልፋት የማያስፈልገውን በርግጎ እንደጠፋ የማድረጉ ሥራ ሁሉ የሚከናወነው በዚህ የአመለካከትና የመዋቅር መረብ ውስጥ ነው፡፡

ሕግ ሆኖ የወጣ ሥነ ምግባር አለ መባሉም ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው መሣሪያ ተቀናቃኝን ጠላት የሚያደርገው የመንግሥት፣ የቢሮክራሲው የጠቅላላው የሥርዓቱና የሕጉ አፈጻጸም ጭምር ድጋፍ ያለው አመለካከት ነው፡፡

ይህን የመሰለ አፋኝ አመለካከት ድርጅታዊ ሥራና የፍርኃት ጥላ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተዘርግቶ እያለ ገለልተኛ ፖሊስ፣ ዳኝነትና የምርጫ አስፈጻሚነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ከቅዥት አያልፍም፡፡ አፋኝ ሁኔታው የሚገፈፍበትን ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በመፈለግና ለዚያ በመታገል ፋንታ የፓርቲ አባል በመሆንና ባለመሆን ላይ ገለልተኝነትን ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ ተሳስቶ ከማሳሳት በቀር የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ገዢው ፓርቲ በምርጫ አስፈጻሚዎች፣ በፍርድ ቤት፣ በሠራዊቱ፣ በፖሊስ ውስጥ አንድም የፓርቲ አባል የለም፣ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል ካለ ወዲያውኑ የእርምት ዕርምጃ ይወሰዳል ቢል፣ ከዚህም አልፎ ‹‹በሕግ የበላይነት፣ በዳኝነት ነፃነት፣ በፍርድ ቤትና በፖሊስ ሥራ፣ በምርጫ አስፈጻሚነት ላይ ያሉ ችግሮች ባመዛኙ የአመለካከት ናቸው›› እየተባለ እንከን የሌለው ሥልጠና ቢሰጥ ከመልክ ሥራ በቀር የሚቀየር ነገር የለም፡፡ ሥልጠና ሰጪውም ተሰጪው ይህንን ያውቁታል፡፡ እውነት የሚመስለው አዲስ ገብ ቢኖር ትንሽ ቆይቶ ከቅዠቱ ይወጣል፡፡

ዳኞች በሙያዊ ጥፋትና የሥነ ምግባር ጉድለት በዳኞች አስተዳደር የሚወገዱ ካልሆነ በቀር በማንም ሊባረሩ አለመቻላቸው የዳኝነት ነፃነትን የሚያረጋግጥ ነው የሚባለውም ወግ ተበድሮ ማጭበርበር ነው፡፡ ይህ የሚሠራው አንድ ፓርቲ የመንግሥት ዓምድ ባልሆነበት በምርጫ ወጪና ወራጅ በሆነበት ሥርዓት ነው፡፡ እንደኛ ባለ ሥርዓት ግን ለዳኝነት የመመረጥ፣ በዳኝነት የመቆየት ጥበብ ምን እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የወይዘሪት ብርቱካን ዓይነት ‹‹ወፈፌ›› ዳኛ ወይም እንደ ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ያለ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቴን እጠቀማለሁ የሚል ‹‹ምስኪን›› ካጋጠመውም የፈለገውን ከማድረግ የሚከለክለው ነገር የለም፡፡

እንጀራ ገመድን ተመርኩዞ እየተስፋፋ ያለው ኢሕአዴጋዊ የፖለቲካ ሎሌነት እንኳንስ መንግሥታዊ አውታሩ ውስጥ ተቃዋሚ የሚባሉትን ሁሉ በስርገት ተብትቦ የሚያምስ፣ በተለይም ምርጫ መዳረሻና ዋዜማ ላይ መከፋፈልና ማስፈንገጥን ፖለቲካዊ ርባና ለማሳጣት የሚጠቀም ሆኗል፡፡

በዕለት ተዕለት የዘወትር ፖለቲካ ውስጥ መንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ‹‹የሚያስደምጠንን›› ዜና ‹‹የሚያደርሰንን›› ወቅታዊ ሪፖርት የሚከታተል ማንኛውም ተራ ሰው የመንግሥት ነገር የሚያስገርመው ደግሞ ደጋግሞ ነው፡፡ በፕሮፓጋንዳና በቅርፅ ሽፋኑ ሰብዓዊ መብቶችንና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብር፣ በምርጫም ሕጋዊነቱን የሚያገኝ መንግሥት ነው፡፡ በመንግሥት መገናኛ ፕሮፓጋንዳው፣ በሴሚናርና በኮንፈረንስ ስለፍትሕ፣ ስለእኩልነት፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ስለሰብዓዊ መብትና ስለነፃ ዳኝነት ሲንበለበልለት ይሰማል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና ኢትዮጵያ መመረጧን የመንግሥቱ የሥራ አፈጻጸም ማስረጃ አድርጎ ለሕዝብ የሚያቀርበው መንግሥት አባል የሆነበትን ግዳጅ ሪፖርት ሲያቀርብ አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ 47 አባላት ያሉት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ በዓመት አሥር ሳምንት የሚሰበሰብበትና ውሳኔዎች የሚያሳልፍበት ታላቅ ግዳጅ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ውስጥ ተሳትፎዋ እንዴት ነው? ተሳትፎዋ ፍዝ ነው? ንቁ? አገር ቤት ውስጥ ወሬው የማይሰማው ሪፖርትና ሪኮርዳችን እንደሚያሳየው ግን አቋማችን በድምፅ ተዓቅቦ ውስጥ የሚሸሽግ መሆኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በዘጠኝ ጉዳዮች፣ እ.ኤ.አ. በ2015 በስምንት ጉዳዮች፣ እ.ኤ.አ. በ2016 በሦስት ጉዳዮች ድምፅ ተዓቅቦ ሰጥተናል፡፡ በአንፃሩ ‹‹ይሁን›› ብለን ድምፅ የሰጠንባቸው ጉዳዮች ቁጥር እንደቅደም ተከተላቸው አምስት፣ አራትና ሦስት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

አባል የሆነበት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ሥርዓት ውስጥ ታላቅ ቦታና ዕውቅና ያላቸው ዓለም አቀፋዊ፣ አካባቢያዊ፣ ብሔራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኢትዮጵያ አገር ቤት ዜና ውስጥ ግን ኩስ የነካው እንጨት፣ ቤተ ክርስቲያን የገባ ውሻ ናቸው፡፡

እንዲያም ሆኖ መንግሥት እንኳን የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ የምዕራብ ረጂዎችንም ማታለል እያቃተው ቢመጣም ሕግን ተከትሎ የሚሠራ ለምምሰል መሞከሩ አልቀረም፡፡ ነገር ግን በሕጋዊና በፊት ለፊት የማይሆነው በጓሮ በር ሲፈጸም ሕጋዊነትንና የጓሮ ሕገወጥነትን አዘማምደው ሲሠሩ ይታያል የስዬ አብረሃ ጉዳይ ሕግ እንደፈለጉ በማውጣት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመሻር ከፓርላማ እንዲነሳ ሕዝብ ‹‹የጠየቀበትን›› የፊርማ ዝርዝር ለማቅረብ፣ መንግሥት የተጠቀመበትን ሕጋዊና ሕገወጥ አሠራሮችን የማጣቀስ ብሉይ ማስረጃ ነው፡፡

ግድያን በሕክምና ሆነ በፖሊስ ማስረጃ ተፈጥሮአዊ ወይም ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የሌለው ማድረግ እንደማይከብድ፣ ጠመንጃ ያልያዘ ተቃውሞን በጥይት እየመቱ ሳይጠየቁ መቅረትን ባህል አድርጎ ያሰፈነ ‹‹የአጣሪ ኮሚቴ›› ወግ ታይቷል፡፡

በአሁኑም ወቅት ‹‹የፌዴራል ፖሊስ ረዘም ላለ ጊዜ ያደረገውን ክትትል መሠረት በማድረግ በጎንደር ከተማ ውስጥ ሰርገው የገቡትን ተጠርጣሪዎች እንደተለመደው በሕዝብ ላይ ጉዳት በማያደርስ መንገድ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለፍርድ ለማቅረብ ያደረገው ጥረት … ያልታሰበ እክል አጋጥሞታል…›› የሚል መግለጫ መውጣቱን ተከትሎ፣ ፖሊስን መቃወምና አለመታዘዝ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎች እንዴት እንደሚያዙ የሚያስተምሩ ዜናዎች በማድመጥ ላይ ነን፡፡ በመንግሥት ተቆልፎ የተያዘውና ከላይ ወደታች የሚታዘዘውን ሐሳብን የማሠራጫ ሥርዓት ብቻ ሕጋዊ አድርጎ ሌላውን ከሞላ ጎደል ዘግቶ አካባቢውን ጋዜጠኞች በነፃ የማይደርሱበት፣ መሄድም የማይፈልጉበት አድርጎ እውነቱን ለሕዝብ አስረዳለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣውና አሁንም የቀበጠ በጀት ለተመደበለት የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ወሬና ልፈፋ ጆሮዬን አልሰጥም የሚል ተጠራጣሪ ሲበዛ ጠርጣሪ ሕዝብ ፈጥሯል፡፡

ሹክሹክታን ከአፍ ወደ አፍ የሚያሠራጭ ‹‹ጋዜጣ››ን ከመኃይም እስከ ምሁር፣ ከተራ ሥራ አጥ እስከ ማዕከላዊ መንግሥት አባላት ድረስ የሚገለገሉበት ሰፊ ተጠቃሚ ያለው የዜና ማሠራጫ ያደረገውም ይኼው የመንግሥት አሠራር ነው፡፡

ፌዴራሊዝማችን የድሬዳዋን፣ የአዲስ አበባን፣ የወልቃይታንና የጠገዴን ጉዳይ መፍታት አቅቶት የለየለት ጦርነት ባይከፍትም ጥይት መጮኹና ባሩድ መሽተቱ የጤናማ ሥርዓት ምልክት አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ አጣሁ ብላ ሰበብ የፈጠረችበት ደቡብ ሐዋሳ ላይ ኤርፖርት ቢሠራ ኦሮሚያ ደግሞ አስቸገረኝ አለ የሚባልበት ሰበብ ሁሉ በብልኃትና በሥርዓት ካልተፈታ የጤናማና የተሳካ ፌዴራሊዝም ምልክት አይደለም፡፡

ኢህአዴግ በምርጫ ከሥልጣን ወርዶ ታማኝ ተቃዋሚ ሆኖ፣ እንደገና በምርጫ አሸንፎ፣ እንደገና ወርዶ ገዥውን ፓርቲ ጥንብ እርኩሱን እያወጣ ሲቃወም የማንሰማበት፣ በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል እንዲህ ያለ የሥልጣን ቅብብሎሽ የሌለበትና ይህን የማይፈቅድ፣ ለኢሕአዴግ ብቻ በዕውቅ የተሠራ ሌላውን አፈናጥሮ የሚጥል ሥርዓት ማንንም አያኮራም፣ ለማንም መመኪያ አይደለም፣ የማንም መታፈሪያ አይሆንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡